ከሩጫ ውድድሮች ሁሉ ረጅሙን ርቀት የሚሸፍነው ማራቶን እጅግ ፈታኝ መሆኑ ይታወቃል። በዚህ ርቀት ጠንካራ ተፎካካሪና አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት አይደለም በተደጋጋሚ ለመሳተፍ እጅግ ከፍተኛ ብቃትና ጽናትን ይጠይቃል። ይህንን የሚያሳኩትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ይህንን ልዩ ችሎታ ከተካኑት አትሌቶች መካከልም በማራቶን ለ25ኛ ጊዜ ለመወዳደር የተዘጋጀችው ኢትዮጵያዊቷ አትሌት አሸቴ በከሪ ተጠቃሽ ናት። ላለፉት 12 ዓመታት አትሌቷ በመላው ዓለም በተካሄዱ ዕውቅ የማራቶን ውድድሮች ላይ በመሳተፍ እጅግ ከፍተኛ ልምድ አካብታለች።
አትሌት አሸቴ በክሪ አሁን ደግሞ በሳምንቱ መጨረሻ በሚካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ለሶስተኛ ጊዜ ለመሳተፍ ዝግጅቷን አጠናቃለች። ቫሌንሺያ፣ ሮተርዳም፣ በርሊን፣ ለንደንና ሌሎች ታላላቅ ማራቶኖች ላይ በመሮጥ ስኬታማ የሆነችው ይህች ኢትዮጵያዊት አትሌት፤ የቶኪዮ ማራቶን ለውድድር ከምትመርጣቸው ውድድሮች መካከል ቀዳሚው እንደሆነ ትናገራለች። በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ የፕላቲኒየም ደረጃ ከተሰጣቸውና ቀዳሚ ከሆኑት ስድስቱ የማራቶን ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቶኪዮ ማራቶን አዘጋጆች በዚህ ውድድር እንዲሳተፉ ግብዣ ካደረጉላቸው አትሌቶች መካከልም በሴቶች ዘርፍ አትሌት አሸቴ ቀዳሚ ናት። ይኸውም ካላት ልምድ ባሻገር በርቀቱ ባስመዘገበችው ፈጣን ሰዓት (2:17:58) ጭምር ነው። አትሌቷ ይህ በርቀቱ ካስመዘገበቻቸው ሰዓቶች ፈጣኑ ሲሆን፤ ያለፈው ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀችበትም ነው።
ይህም ዘንድሮ የውድድሩ አሸናፊ ሊያደርጋት እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ዋናው ዕቅዷ ግን አዲስ ሰዓት ማስመዝገብ መሆኑን አሰልጣኟ ማስረሻ አስራት ገልጿል። የ34 አመቷ አትሌት እአአ 2021 ላይ በለንደን ማራቶን ሶስተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የገባችበት ሰዓት 2:18:18 ነበር፤ ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ ይህንኑ ሰአት በአንድ ደቂቃ ለማሻሻል ችላለች። ይህም ዘንድሮም ሰዓቷን ለማሻሻል የምትችልበት አቋም ላይ መገኘቷ ዕቅዷን እንድታሳካ ይረዳታል በሚል ይጠበቃል። የግሎባል ኮሚዩኒኬሽን አትሌቷ ለዚህ ስኬቷ እንድትበቃ ምክንያት የሆናትም ማራቶንን በዓመት ሁለት ጊዜ ብቻ መሮጧ ሲሆን፤ ለማገገምና ለልምምድ ሰፊ ጊዜ ያላት መሆኑንም ገልጻለች። ለዚህ ውድድርም ‹‹በስነልቦና ረገድ በቂ ዝግጅት አድርጌያለሁ፤ በመሆኑም ካለፈው ይልቅ አሁን ጠንካራ ነኝ። ውድድሩን በደንብ አውቀዋለሁ፤ በመሆኑም ፈጣን ሰዓት ለማስመዝገብ ነው ያቀድኩት። እንደሚሳካልኝም ተስፋ አደርጋለሁ›› ስትል ተናግራለች።
በርቀቱ ባስመዘገበችው ሰዓት የአሸቴ ከፍተኛ ተፎካካሪ ልትሆን ትችላለች ተብላ የምትጠበቀው አትሌት ኬንያዊቷ ሮዝሜሪ ዋንጂሩ ናት። ያለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን ተሳትፎዋ ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ይህች አትሌት፤ ከኢትዮጵያዊቷ አትሌት በአንድ ደቂቃ የዘገየ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ናት። በዚህ ውድድር አሸቴ ብቸኛዋ ተሳታፊ ኢትዮጵያዊት አይደለችም። 2:18:03 የሆነ ፈጣን ሰዓት ያላት አትሌት ትዕግስት አባያቸው በውድድሩ ውጤታማ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት መካከል ትገኝበታለች። ያለፈው ዓመት በበርሊን ማራቶን ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ይህች አትሌት ከተሳታፊ አትሌቶች መካከል ሶስተኛዋ ፈጣን አትሌትም ናት።
ሌላኛዋ ያለፈው ዓመት የበርሊን ማራቶን ተሳታፊ ወርቅነሽ ኢዴሳ በዚህ ውድድር ተፎካካሪ ከሆኑ አትሌቶች መካከል አንዷ መሆኗ ተረጋግጧል። አትሌቷ በበርሊን አራተኛ ደረጃን ስትይዝ የገባችበት 2:18:51 የሆነ ሰዓትም የግሏ ፈጣን ሲሆን፤ ከተወዳዳሪዎች ደግሞ አምስተኛውን ደረጃ ይዟል። በቅርቡ የማራቶን ተሳታፊ የሆነችው አትሌት ጸሃይ ገመቹም በቶኪዮ ማራቶን ተሳትፏቸውን ካረጋገጡ አትሌቶች መካከል ትገኝበታለች። የአትሌቷ ፈጣን ሰዓትም አምስተርዳም ማራቶንን ያጠናቀቀችበት 2:18:59 ነው።
በወንዶች መካከል በሚካሄደው ውድድርም በተመሳሳይ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ማግኘት ችለዋል። በውድድሩ ከሚሳተፉ አትሌቶች መካከል ባለው ፈጣን ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ የተቀመጠው ሲሳይ ለማ ነው። እአአ በ2019 የበርሊን ማራቶን 2:03:36 የሆነ ሰዓት ያስመዘገበው ሲሳይ፤ ከኬንያዊያን አትሌቶች እና የሀገሩ ልጆች ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥመውም ይጠበቃል። አትሌት ዴሶ ገልሜሳ፣ መሃመድ ኢሳ እና ታዱ አባተ ደግሞ በውድድሩ ተካፋይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው።
እአአ ከ2012 አንስቶ ከዓለም ጥቂት ቀዳሚ የማራቶን ውድድሮች መካተት የቻለው የቶኪዮ ማራቶን በመጪው እሁድ የካቲት 26/2015 ይካሄዳል። በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ በማራቶን ሀገራቸውን መወከል የሚፈልጉ አትሌቶች እንደ መስፈርት ከሚያዝላቸው ተሳትፎ መካከል አንዱ በሆነው በዚህ ውድድር በርካታ አትሌቶች ተሳታፊ ይሆናሉ። በቦታው በተለያዩ ርቀቶች በሚካሄዱ ሩጫዎችም ከ30ሺ የሚልቁ ሯጮች ይሳተፋሉ።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015