ለረጅም ዓመታት በውትድርና ዓለም ውስጥ ነው የቆዩት፡፡ በጤና እክል ከወታደር ቤት ከተገለሉ በኋላ በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ ነፃ ፕሬስ ሲጀመር በዋናነት ካቋቋሙት ሰዎች አንዱ ነኝ የሚሉት የ65 ዓመት አዛውንት በተለያዩ የግል ጋዜጦች ላይ ለ11 ዓመት እንደሰሩ ይናገራሉ፡፡ አዛውንቱ ከ20 በላይ መፃህፍትን ተርጉመዋል፤ በስማቸው ባይወጣም። ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ግን በገጠማቸው ድንገተኛ ችግር ጐዳና ላይ ወደቁ። በአሁን ወቅትም በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የዛሬ የ‹‹ሕይወት እንዲህ ናት›› እንግዳችን ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ፤ መልካም ንባብ!
ልጅነት እና የትምህርት ህይወት
የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከተማ ነው፡፡ ለውትድርና ልዩ ፍቅር እንዳላቸው የሚናገሩት ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ከወላጅ አባታቸው ትርፌ ከወላጅ እናታቸው አሰለፈች ረታ በ1946 ዓ.ም ተወለዱ፡፡ ውልደታቸውና ኑሮአቸው በጀመሩበት በደብረ ብርሃን ከተማ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም አስኳላ ገብተው ከቀለም ትምህርት ጋር ትውውቅ አደረጉ፡፡
አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ደብረብርሃን ነው የተማሩት፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከወሰዱ በኋላ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሚያስገባ ነጥብ ቢያመጡም መግባት አልፈለጉም፡፡ይልቅ ለውትድርና ትልቅ ፍቅር ያላቸው ኮሎኔል ጉዞአቸውን ወደ ሀረር ወታደሮች ማሰልጠኛ አካዳሚ አደረጉ፡፡ አካዳሚው ከውትድርና ሳይንስ ውጭ የቀለም ትምህርትም ይሰጥበት ነበር፡፡ ታዲያ ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ በሀረር የወታደሮች ማሰልጠኛ ሶስት አመት ተምረው “በአካውንቲንግ” ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ሀረርጌ ተመደቡ፡፡ እስከ 1969 .ዓ.ም ሀረርጌ ነው የቆዩት፡፡
ህይወት በአውደ ውጊያ ላይ
አገር ሰላም ብለው ሀረርጌ በቆዩበት ወቅት ነው የሶማሊያ ጦርነት አገሪቱ ላይ ጦርነት የከፈተው፡፡ታዲያ ቀድሞውንም በአግር ድርድር የለም የሚሉት ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ የሶማሊያ ውጊያ ላይ ዘመቱ፣ ተዋግተውም ከጨረሱ በኋላ የሻለቃነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ወደ ሰሜን ዘመቱ፡፡ ሰሜን ረዘም ላሉ ዓመታት ከቆዩ በኋላ በውጊያ ወቅት ዘጠኝ ቦታ በጥይት በመመታታቸው ከጦር ሰራዊቱ ሊወጡ ችለዋል፡፡ ዘጠኙ ጥይት የመታቸውን ቦታ ሲናገሩ “ አብዛኛው እግሬ ላይ ነው የመታኝ፡፡ ክንዴም ላይ ተመትቻለሁ። ጀርባዬ ላይ የጥይት ፍንጣሪ አለ፡፡ዋናዎቹና አብዛኞቹ እግሬ ላይ ያሉት ናቸው። እስካሁን ሁለት ጥይት በውስጤ ሳይወጣ አብሮኝ እየኖረ ነው፡፡” በዚህም ምክንያት ላይመለሱ ከውትድርናው ዓለም በ1981 ዓ.ም ወጡ። “የወጣሁበት ምክንያትም እነዚህ በውስጤ ያሉት ጥይቶች በጤናዬ ላይ ባስከተሉት ችግር የተነሳ ነው፡፡”
አሁን ላይ ለመናገር እቸገራለሁ፡፡ እስኪ ወደ ጦር ሜዳ ውሎዎ አውደ ውጊያው እንዲሁም የጦር ህይወት እንዴት ይመስል ነብር… “መቼም ዘጠኝ ጊዜ ተመትቶ መትረፍና ታሪኩንም ለማውጋት መብቃት እድለኝነት ነው… ስለ ጦር ሜዳ ውሎ ካነሳን ከ1969 ዓ.ም እጀምራለሁ፡፡ ሐረርጌ ከአንበሳው ክፍለ ጦር ጋር ነው የነበርኩት፡፡ ከዚያ ከሶማሊያ ጋር ነው የተዋጋነው፡፡ በጣም ከባድ ውጊያ ነበር፡፡ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ ሰራዊት አልነበረንም፤ ሚሊሺያው ገብቶ መሰልጠን ነበረበት፡፡ እንደገና መድፈኛም ከኩባ መምጣት ነበረበት። አውሮፕላኖችም መለወጥ ነበረባቸው፡፡ በወቅቱ ይህ ሁሉ ችግር ነበር፡፡”
ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ እንደሰለጠነች የሚያስታውሱት ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን፣ ሱዳን የምትፈልገው የእኛን ደካማ ጐን ነበር ይላሉ፡፡ የነበረውን ነባራዊ ሁኔ በምልሰት ሲያወሱ “ወቅቱ ሀይለስላሴ ወርደው መንግስቱ ሲመጣ ስለነበር፣ ግርግር ነው፡፡ ሶማሌያም ይህን ክፍተት አይታ ነው የመጣችው። በአንድ ጊዜም ሐረርጌንና ጅጅጋን አስለቅቃናለች፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ኖሮም ሱማሊያ ድባቅ ተመትታ ነው በኢትዮጵያ አሸናፊነት የተጠናቀቀው፡ ፡” በዚያ ሁሉ አለመቀናጀት እና ግርግር እንዴት ድሉ ሊመጣ እንደቻለ ሲያስረዱ፤ ሚሊሻውን በማሰልጠን እና በመሳሰሉት… ብቻ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሀይሉን በማሰባሰብ ማጠናከራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሶማሊያ በመልሶ ማጥቃት ሽንፈትን ተከናንባ ልትሄድ ችላለች፡፡ ስለ ሰሜኑ ውጊያ አንዳንድ ጉዳዮችን ያጫወቱን ሲሆን… “ወደ ሰሜኑ ስንዞር ውጊያው አንድ አይደለም። ይሄ “ኮንቬንሽናል” ነው፡፡ ያኛው (የሶማሊያው) የሰርጐ ገብ ውጊያ ነው፡፡ እንግዲህ በሰሜኑ በኩል ትዋጋለህ፣ ታሸንፋለህ ትሄዳለህ፡፡ ” ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ይናገራሉ ከሁመራ ጀምረው ነው ኤርትራ ግዛት እየገቡና እየተዋጉ የሄዱት፡፡ በመጨረሻ ከረንን ሁሉ ይዘው ከዚያ ናቅፋ በር ላይ ነው እንደተመቱ የሚናገሩት፡፡ ውጊያው በዛን ጊዜ ከባድ እንደነበርም ያወሳሉ ፡፡ ከባድ ከሚያደርጉት ውስጥ አንዱ ረጅም ርቀት በእግር መሄድ አለ፤ ሌሎችም ፈተናዎች ነበሩ፡፡ ስለውጊያው አሁን ባለኝ የማስታወስ አቅም ልነግርህ የምችለው ይህንን ነው፡፡ነገር ግን የነገርኩህ በጣም ጥቂቱን ነው፡፡
በጋዜጠኝነትና በትርጉም ሥራ
ከሚሊታሪ ቤት ከወጡ በኋላ ለሁለት ዓመት አንድ ድርጅት ውስጥ ሰርተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነፃው ፕሬስን ካቋቋሙት ውስጥ አንዱ እኔ ነኝ የሚሉት ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ፤አሁን ከሚያስታውሷቸው እንኳን አዲስ አድማስና ሪፖርተር ጋዜጦች ይገኙበታል፡፡ ሌሎችም ነበሩ፡፡ በዘመናቸው ዝነኛ የነበሩ አሁን ገበያው ላይ የሌሉ የህትመት ውጤቶች ላይም ከፍተኛ ኃላፊ ደረጃ ላይ ሆነውም ሰርተዋል፡፡
በአጠቃላይ በጋዜጠኝነት ለ11ዓመታት እንደሰሩም ይናገራሉ፡፡ ለመጨረሻ ጊዜም “በኢትኦጵ” ላይ ነው ይሰሩ የነበረው፡፡ በ1997ቱ ምርጫ በነበረው የተለያዩ ችግሮች ሌተናል ኮሎኔል ካሳሁን ትርፌ ባልጠቀሷቸው ማለቴ ነው ኢትኦጵም አባይ ጋዜጣ ታገዱ፡፡ እሳቸውም ከጋዜጠኝነቱ ወጡ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ወደ ትርጉም ስራ የገቡት፡፡
ከ20 በላይ መፃህፍትን ተርጉመዋል፤ የወጡት በሌላ ሰው ስም ነው፡፡ ይህ የሆነው በስምምነት ነው ይላሉ። የተረጎሟቸው መጽሐፍት በስማቸው ያልወጣበትን ምክንያቱን ሲያስረዱ ይህንንም ለማንም ላይናገሩ ምለው እንደተገዘቱ ይናገራሉ፡፡ አሁንም ምህላቸውን እንደማያፈርሱም ገልጸውልኛል፡፡ለምን በሌላ ሰው ስም ወጣ የሚለውን ጥያቄ እንተወውና የተረጎሟቸውን መጽሐፍ አርስትን ይንገሩኝ… በፈገግታ ከተመለከቱኝ በኋላ “የመጽሐፉን ስም ከጠቀስኩ መሀላዬን አፈረስኩ ማለት ነው፡፡ ይህንን ደግሞ አላደርግም፡፡ እሱን አልነግርህም አትድከም፡፡ ዋናው እውነታው መታወቁ ነው።”
አሁን አንድ “የዲቴክቲቭ” መጽሐፍ ተርጉመው ያጠናቀቁ ሲሆን ፤እሱ በስማቸው እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡ “ዳንኪረኞች” በሚል የተረጎሙት እና ከውጭ የመጡ ጎብኚዎች የትርጉም ክህሎት እንዳላቸው እና መተርጎም እንደሚችሉ ገልጸው በላኩላቸው መሰረት ነው ይህ መጽሀፍ አግኝተው የተረጎሙት፡፡
ፈታኝ ጊዜ
የማንኛውም ሰው ጥያቄ ሊሆን የሚችለው ወደ የአዕምሮ ህሙማን መርጃ እንዴት እንደመጡ ነው፤ ማዕከሉ ደግሞ የሚቀበለው ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማንን ነው ፡፡እሳቸው ደግሞ ትዳርና ቤት ነበራቸው፡፡ እንዴት ወደዚህ ማዕከል ሊገቡ እንደቻሉ ስንጠይቃቸው … ልክ ነው፤ “ትዳርና ቤት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን 2004 ዓ.ም ላይ ባለቤቴ በስኳር ህመም ተሰቃይታ ሞተች፡፡ ባለቤቴ፤ ከእንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት በአካውንቲንግ ተመርቃ፣ ሥራ ስፈልግላት ነው ያረፈችው፡፡ በዚህ ምክንያት ጭንቅላቴ ተረበሸ፡፡ ባለቤቴ ለእኔ ሚስቴ ብቻ ሳትሆን ጓደኛዬም መካሪዬም ነበረች፡፡ ለእኔ ሁሉ ነገር ነበረች፡፡ አንዳንዴ ሁለመናዬን ስታጣ ይጨልምብሃል፤ በዚህ ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ራሴን አላውቅም ነበር፡፡”
መቄዶኒያ በምን ሁኔታ እንዳገኛቸው ሲናገሩ በምን ሁኔታና የት ነው እንደሆነ ሲናገሩ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ላስቲክ ቤት ውስጥ ወድቀው እንደቆዩ ነበር፡፡ከዚያም ወደ መቄዶኒያ በአንዲት ተማሪ ጠቋሚነት አንስቶ እንዳመጣቸው ይናገራሉ፡፡ ስለድርጅቱ ቆይታቸው ሲናገሩ “እዚህ ከመጣሁ በኋላ ለማገገም ሁለት ወር እንኳን አልወሰደብኝም። የድርጅቱ መስራች አቶ ቢኒያም “መጽሐፍ እንደምትተረጉም እናውቃለን፣ አሁን ጥሩ መጽሐፍ ፈልገህ ተርጉም፤ ድርጅቱ ያሳትምልሃል” አለኝ፡፡ ከዚህ በኋላ አዕምሮዬን ለማስተካከል አማኑኤልም አልሄድኩም፤ ምን አለፋህ ይሄ የቢኒያም ቃል ብቻ ለወጠኝ፡፡ በውስጤ እንዲህ የሚል ሃሳብ መጣ፡፡ ማንም ሰው በህይወቱ ሊወድቅ ይችላል፤ መጥፎው ነገር ግን ወድቆ መቅረቱ ነው አልኩኝ፡፡” ይህ ሃሳብ ሞራላቸውን ከፍ እንዳደረገውና አሁን መጽሐፍ ተርጉመው ጨርሰዋል፡፡ ኮሎኔሉ በተጨማሪ መጽሐፍ መተርጐም ብቻ ሳይሆን በድርጅቱ ፋይናንስ ክፍል ውስጥ ኃላፊነት ተሰጥቷቸው አገልግለዋል፡፡ ኮሎኔል “እውነት ነው፤ ኃላፊነቱን ወስጄ በጥሩ ጤንነትና መንፈስ ድርጅቱን አግልግያለው። ለድርጅቱ የሚገቡትን እርዳታዎች በደረሰኝ እረከባለሁ፡፡ አሁን ግን ስለደከመኝ ለተሻለ ሰው አስረክቤያለሁ፡፡”
ከትዳራቸው ልጆች አላፈሩም ይህም ዋናው የአዕምሮዋቸው መናወጥ እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ለዚህ ነው ይላሉ ኮሎኔሉ “ባለቤቴ ስትሞት ጐዳና የወጣሁት ልጆች ስለሌሉኝ ነው፡፡ ልጆች ቢኖሩ አጽናንተው ደግፈው ያኖሩኝ ነበር፡፡ በህይወቴ ውስጥ ከባለቤቴ ሌላ ማንም አልነበረኝም፡፡”
ባለቤታቸው ስትሞት ቤታቸውን እንዳማረበት ትተውት እንደወጡ የሚናገሩት፡፡ አሁን ጥለውት በወጡት ቤት የባለቤታቸው ዘመዶች እንደሚኖሩበት እንደሰሙ አጫውተውኛል። ኮሎኔል አሁን ወደ ቤታቸው መመለስ አይፈልጉም፤ ምክንያቱንም ሲያስረዱ “እሱን እያሰብኩ መጨነቅም አልፈልግም፡፡ አሁን በሰላማዊ ቦታና በጥሩ መንፈስ ነው ያለሁት። የባለቤትዎ ዘመዶች አይጠይቁዎትም? አንድ ሌላ ቦታ የነበረች እህቷ ብቻ በኢቢኤስ ላይ አይታኝ መጥታ ጠይቃኛለች፡፡ ስለ ሌሎቹ ምንም ለማለት ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ እስካሁን መጥተው አልጠየቁኝም፤ እኔም አልጠብቅም፡፡”
አሁን እየተረጐሙ ያሉት መጽሐፍ ርዕሱ “ዳንኪረኞቹ” የሚል ሲሆን ቀደም ብለው እንደተረጎሟቸው መጽሐፎች የወንጀል ክትትል ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ነው፡፡
ቀደም ሲል ሲጋራ እንደሚያጨሱ፣ መጠጥ እንደሚጠጡም ይታወቃል፡፡ አንዳንዶች ህይወትዎ ያልተለወጠው በሱስዎት ምክንያት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። አሁንስ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? “ይህን ሀቅ ማንሳቱ ለሌሎችም ትምህርት ይሆናል። በነገርህ ላይ በዛን ወቅት እጠጣ የነበረው በአጠቃላይ ህይወቴ እበሳጭ ስለነበር ነው፡፡ ብዙ አልጠጣም ግን በውስጤ ብስጭት ስለነበር በትንሹ እሰክራለሁ፡፡ ሲጋራ ለ37 ዓመታት አጭሻለሁ። አሁን መጠጡም ሲጋራውም ተረት ሆኗል፤ አልጠጣም አላጨስም፡፡ በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” ወዝዎት ግጥም ብሎ ወጣት ሆነዋል፡፡ ይታወቅዎታል? አሁንም ይናገራሉ ኮሎኔሉ “እንዴታ! አሁን ጤነኛና ደስተኛ ነኝ፡፡ ወፍሬ አታየኝም እንዴ! እኔ አሁን ተረጂ ሳልሆን በድርጅቱ ውስጥ ሰራተኛ ነኝ፡፡ ቀደም ብዬ እንደነገርኩህ ለድርጅቱ በአይነትም ሆነ በጥሬ ገንዘብ ሲመጣ ደረሰኝ ቆርጬ እቀበላለሁ፡፡ ጐብኚዎች ሲመጡ ስለ ድርጅቱ መረጃ እሰጣለሁ፤ እንደ ህዝብ ግንኙነትም ያደርገኛል ማለት ነው፡፡” ወደ ሚዲያው ተመልሰው የመፃፍ ሃሳብ የለዎትም? እሱን አላወቅሁም፡፡ “በትርጉሙ እቀጥላለሁ። ጋዜጦች ላይ ለመፃፍ ግን ወደፊት አመቺ ሁኔታዎች ይኖሩ እንደሆነ አላውቅም፡፡”
አሁን እድሜዎት ስንት ነው? 65 ዓመቴ ነው። እኔ ገና ጐረምሳ ነኝ እያልኩ ነው። ጐረምሳ ስልህ… ስራ ለመስራት ብዙ አቅም እንዳለኝ ይሰማኛል፡፡ አሁን ወደ ከተማ ይወጣሉ? በደንብ ነዋ! አሁን እግሬም ጤናዬም ደህና ነው፤ እየወጣሁ እመለሳለሁ። በአጠቃላይ ደህና ነኝ፡፡ እዛው መርካቶ ላስቲክ ቤት ውስጥ ወድቆ መቅረትም ይኖር ነበር። እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ከዚያ ወጥቼ አዕምሮዬ ወደ ቀድሞ ጤናው ተመልሶ፤ ለዚህ መብቃቴ ተዓምር ነው፡፡ አሁን እንዲህ በጤና መኖር ከጀመርኩ አንድ ዓመት ከሁለት ወሬ ነው። በውትድርና ህይወትዎ በወቅቱ ከነበሩ ባለስልጣናት ጋር ምን አይነት ቅርርብ ነበረዎት? መልካም ቅርርብ ነበረኝ፡፡ በተለይ ከእነማን ጋር ይቀራረቡ ነበር? ጀነራል አበበ ገብረየስ ለምሳሌ በጣም ይቀርቡኝ ነበር፤ የማዕከላዊ አዛዥ ነበሩ፡፡ አሁን አሜሪካ ይኖራሉ፡፡
በነገራችን ላይ በውትድርና ህይወቴ የመረጃም ሰው ነበርኩ፡፡ ሀረር ሶስተኛ ክፍለጦር እያለሁ ሴኩዩሪቲ ኦፊሰር ነበርኩኝ፣ በዚህ ምክንያት ከሁሉም ጋር በስምምነት ነው የምኖረው። አንተ የመረጃ ሰው ሆነህ ፀባይ ካላሳመርክ የመረጃ ድርቅ ይመታሃል ማለት ነው፡፡ አሁን ለጋዜጠኞች የሚሰጠው “ኮርስ” በዛን ወቅት ለመረጃ ኦፊሰር የሚሰጠው አይነት ነው፡፡ ጋዜጠኛ ሆነህ መረጃ የምትፈልገው ለህዝቡ ለማቀበል ነው፡፡ በሚሊታሪ የመረጃ ኦፊሰር ሆነህ መረጃ የምትሰበስበው ግን ለጦር ሰራዊቱ ለማቀበል ነው፡፡ ጋዜጠኝነትና በወቅቱ እኔ የምሰራው የመረጃ ስራ የስፋትና የጥልቀት ካልሆነ ልዩነት የለውም። ነገር ግን ጋዜጠኛ ሆነህ አንድ በእውነታውና በዘገባው መካከል ልዩነት ያለው ነገር ብታቀርብ እንደምንም ሊድበሰበስ ይችል ይሆናል፡፡ የመረጃ ኦፊሰር ሆነህ ለጦሩ የምታቀርበው መረጃ ከተለያየ መዘዝ ያመጣል፡፡ እንዴት? ለምሳሌ በወታደር ቤት ጠላት አንድ ሺህ ሆኖ ሳለ፣ አንተ አምስት መቶ ነው ብትል አገርህን ገደል ከተትክ ማለት ነው፡፡ አንተም ዋጋ ትከፍልበታለህ፤ ስለዚህ ጉዳዩ ሃይለኛ ነው፡፡ ረጅም ጊዜ ከወረቀት ጋር እንደማሳለፍዎ አይንዎት እንዴት ነው? አይኔ ጥሩ ነው፡፡ ሀኪም ያዘዘልኝ መነጽር አለ፤ ስሰራ እሱን እጠቀማለሁ፡፡ እርግጥ መነፅር ሳላደርግ ለማንበብ እቸገራለሁ፡፡ በሌላ ጉዳይ ግን አይኔ ደህና ነው፡፡ በመጨረሻ የምታመሰግኗቸው ሰዎች ካሉ እድሉን ልስጥዎት… እኔም በጣም አመሰግናለሁ፤ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የዚህን ድርጅት መስራች አቶ ቢኒያምን እና በጐ ፈቃደኛ ሆነው እኛን የሚያገለግሉትን ሁሉ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡ በአንድ ወቅት የአገር ባለውለታ የነበርን ሰዎች ነን መንገድ ላይ ወድቀን የነበርነው፡፡ አሁን ከየቦታው ተሰብስበን ቀሪ ዘመናችንን በደስታና በጤና እንድናሳልፍ ሆነናል፤ ደስተኞች ነን፡፡እናንተም ወጣቶች ከሚያለያያችሁ ብዙ ጉዳዮች ይልቅ የሚያቀራርቧችሁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ስለዚህ መገፋፋቱን ትታችሁ ለአግር አንድነት ሰላም እና ብልጽግና እንድትሰሩ እንድትኖሩም እመክራለው፡፡እኛም ቀሪ ህይወትዎ እንደተመኙት ያሰቡትን አሳክተው ተደስተው የሚኖሩበት እንዲሆን ተመኘን፡፡ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
አብርሃም ተወልደ