አጠቃቀሙን ካወቅንበትና ኃላፊነት በሚሰማው አካል እጅ ከገባ ዓለም እንዴት ውላ እንዳደረችና አገር መንደሩ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መረጃ የሚሰጠን ጠቃሚ ነገር ነው። ፍቅርና ሰላምን በመስበክም ወዳጅነትን ያጠናክራል። ህዝቦችን ለልማት በማነሳሳትና አገር በመለወጥም ወደር የለውም። የዜጎችን ብሶት ለሚመለከተው አካል በማድረስ ለብዙዎች ችግር ፈዋሽ መድኃኒትም ነው። የዘረፋና የስርቆት ድብቅ ገመናዎችን በአደባባይ በማዋል ቅሌቶችን ለህዝብ ዓይንና ጆሮ አድርሶ ብዙዎችን ከስልጣን አውርዷል፤ በህግ ፊት ቀርበው የተጠየቁም አያሌ ናቸው።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ኃላፊነት በማይሰማቸውና የተሰጠ ነጻነት ገደብ የለሽ አድርገው በሚቆጥሩ እጅ ሲወድቅ ደግሞ የሚያደርሰው አደጋ ምነው ባልተፈጠረ የሚያስብል ነው። ጥላቻ ተሰብኮበት ምንም የማያውቁ ሰብዓዊ ፍጡራን ላይ አስከፊ አደጋ እንዲደርስባቸው እንዳደረገም ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው። ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው ደግሞ የርዋንዳ ጉዳይ ነው። በርዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ሰለባ ለሆኑ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ዋነኛ መንስዔው ሚዲያ እንደነበር ታሪክ ዘግቦት አልፏል። ጦሰኛ ሚዲያዎች በርዋንዳ በረጩት መርዛማ የጥፋት ፕሮፖጋንዳ ምንም የማያውቁና የፖለቲካ ተሳትፎ እንኳን ያልነበራቸው ህጻናትና አዛውንቶች እንኳን ሳይቀሩ የጥፋቱ ሰለባ ሆነዋል።
በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በተለይም ከለውጡ በፊት ከሚዲያ ነጻነት ጋር ተያይዞ የአገራችን ስም በበጎ አይነሳም ነበር። ብዙ ጋዜጠኞችን በማሰር፣ ድረ ገጾችን በመዝጋትና የተቃውሞ ድምጽ የሚሰማባቸውን መገናኛ ብዙሃን በማፈንም ተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባት እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው። ይህ ደግሞ በአገር ውስጥ ለዜጎች ቅሬታ ዋነኛ ምንጭ ሲሆን በውጭ ደግሞ የአገራችንን ገጽታ ጥላሸት ያለበሰ ተግባር ነበር።
ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መታፈን፣ ኢፍትሃዊነትና ሌሎችም ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቅሬታዎች ህዝብን ለቁጣ ቀስቅሰው የአገሪቱ ዕጣ ፋንታ በሚያሰጋ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎም አገራችንን በሁሉም መልክ በመለወጥ ላይ ያለ የለውጥ አመራር ሊፈጠር ችሏል። የለውጥ አመራሩ የፖለቲካ ምህዳርን በማስፋት፣ ፍትሃዊነትን በማስፈን ወዘተ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ያልተገመቱ ለውጦችን ያስመዘገበ ሲሆን ከሁሉ ይልቅ በቀደምትነት ሊጠቀስ የሚገባው ግን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽን መብት ሙሉ ለሙሉ ለማረጋገጥ የተወሰደው እርምጃ ነው።
በእስር ቤት የነበሩ ጋዜጠኞችና ብሎገሮች ሙሉ ለሙሉ መለቀቃቸው፣ በፍርሃት ምክንያት መቀመጫቸውን በውጭ አገር አድርገው የነበሩ መገናኛ ብዙሃን አገር ቤት ገብተው በነጻነት እንዲሰሩ መደረጉ፣ ጋዜጠኞች ያለምንም ስጋት ሃሳባቸውን በነጻነት ማንሸራሸር መቻላቸው፣ አሳሪና መብት ተጋፊ የተባሉ ህጎችን ለመቀየር ተጨባጭ እንቅስቃሴ መጀመሩ፣ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን ከአዝማሪነት ወጥተው ሥራቸውን በነጻነት የሚያከናውኑበት አውድ መፈጠሩ የለውጥ አመራሩ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ያለምንም መሸራረፍ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው።
ስለሆነም ዛሬ ከሚዲያ ነጻነት አንጻር የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ዓይነት ምክንያት ማንሳት አይቻልም። ዛሬ የሚጠበቀው ነጻ ተደርጎ የተሰጠውን የሚዲያ አውድ ለአገርና ለህዝብ እንዴት እንጠቀም የሚለው ነው። በአግባቡ ከተጠቀሙበት አገርንና ህዝብን ለመጥቀም በማንአለብኝነት ከተገለገሉበት ደግሞ የጥፋት መንስዔ ለመሆን ኳሷ በመገናኛ ብዙሃን እጅ ትገኛለች።
በአገራችን እውን ከሆነው የፕሬስ ነጻነት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ዓይነት አመለካከቶች የሚገለጹባቸው የህትመትም ሆኑ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን እንደ አሸን እየፈሉ ነው። ይህ ደግሞ የሃሳብ ገበያን ይፈጥራልና ይበል የሚያሰኝ ነው። ዛሬ ዛሬ ጋዜጠኛው ያለምንም መሸማቀቅና ፍራቻ በነጻነት ይጽፋል፤ አንባቢም እከሌ አየኝ አላየኝ ሳይል የመረጠውን በአደባባይ ሲያነብ ይስተዋላል። ይህ ደግሞ የህዝቦች የዓመታት ጥያቄ ምላሽና የዴሞክራሲ መገለጫ ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው።
ይሁንና ከፕሬስ ነጻነቱ ጋር ተያይዞም አገርንና ህዝብን ስጋት ላይ የሚጥሉ አንዳንድ ድርጊቶችም ይስተዋላሉ። መረጃዎችን ሳያጣሩ መልቀቅ፣ የአሉባልታ መድረክ መሆን፣ ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩና ልዩነትን የሚያሰፉ መረጃዎችን ማሰራጨትና መገናኛ ብዙሃንን ኃላፊነት በማይሰማውና የሚያመጣውን ጉዳት ሳያገናዝቡ መጠቀም ወዘተ በአሁኑ ወቅት የሚታዩ የዘርፉ ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች በእንጭጩ ካልተቀጩ ደግሞ የፕሬስ ነጻነቱን የሚያቀጭጩ ከመሆናቸውም በላይ ጦሳቸው ለአገርና ለህዝብ የሚተርፍም ይሆናል
ስለሆነም የግሉም ሆነ የህዝብ መገናኛ ብዙሃን አሁን የሰፈነውን የፕሬስ ነጻነት በጥንቃቄና ኃላፊነትን በተላበሰ መልኩ በመጠቀም ለአገርና ለህዝብ የሚተርፉ ሰናይ ተግባራትን ሊያከናውኑ ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011