መቼም የጦርነት ደግ የሰላም ክፉ የለውም ይባላል። ጦርነት ካለ ሰው በሰላም መኖሩ አክትሞ በጭንቀትና በሀዘን እንዲኖር ይፈረድበታል። በጦርነት ከሚመጡት ሰብዓዊ ቀውሶች አንሰቶ ሰው እድሜ ዘመኑን ያፈራውን ሀብት ንብረት እንዲያጣ ይሆናል። ይባስ ብሎ ስደቱ መፈናቀሉ ሲታከልበት ባለ ሙሉ አካሉ ሰው ወደ ተረጂነት ሲቀየር አእምሮው ይዛባል። የሚያደርገው እና የሚያስበው ሁሉ ጥፋት ብቻ ይሆናል። ስለጦርነት ማንሳታችን ለዛሬ ከፍትህ ሚኒስቴር ያገኘነውን በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ ከቀየው ተፈናቅሎ ወደ ወንጀል የገባውን ሰው ታሪክ ልንገልፅላችሁ ስለወደድን ነው ። ታሪኩ እንዲህ ነው…..
ብሶተኛው አዳነ
አቶ አዳነ ሰማው ተወለዶ ያደገው ሰሜን ወሎ አካባቢ ነው። እርሱ የተወለደባት ቆቦ አካባቢ የሚገኝ የገጠር ቀበሌ በምርታማነቷ የታወቀች ምርት በገፍ የሚታፈስባት ነበረች። መሬቱ የሰጡትን ተቀብሎ ያለስስት ጎተራ ሙሉ የሚያሳቅፋቸው የአካባቢው ገበሬዎች በምርት ጊዜ ወለም ዘለምን የማያውቁ ታታሪዎች ነበሩ። ከታታሪዎቹ ገበሬዎች አንዱ የሆነው አቶ አዳነ ጎተራው ማጀቱ ሙሉ ከራሱ አልፎ ለሰው የሚተርፍ የጠገበ ገበሬ ነው።
በሀገሩ ወግ ተድሮ የሙሽራነት ጊዜውን በወጉ ሳያጣጠም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተቀሰቀሰ። ሙሽራይቱን ሚስቱን ሳይጠግብ ለአመት ይሆነኛል ብሎ ጎተራ የሞላውን እህል ሳይሸጥ ሁሉም በጅምር እንዳለ ጦርነቱ ወደ እነሱ ቀበሌ መስፋፋት ጀመረ። ሚስቱን ከእናት ከአባቱ ጋር ቀደም ብለው እንዲወጡ አድርጎ ቤቱ የቀረው ቆፍጣና ገበሬ እጅግ በጣም ያዝን ጀመር።
ከልጅነቱ ጀምሮ ቦርቆ ያደገባት ውቧ ቀዬው ሰው አልባ ሆና፤ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ በአካባቢው ያሉ የቤት እንስሳትን ሲሰበስቡ ብሎም ሀገራቸውን ከጥፋት ሲጠብቁ ሰነበቱ። ይባስ ብሎ የመንግስት ጦርም ሆነ የሌለኛው ወገን ጦር በቅርብ ርቀት መመሸጋቸውን ሰማ። ያኔ ከመሞት መሰንበት ብሎ ቤቱን መለስ አድርጎ በመውጣት ወደ ዋና መዲናይቱ አዲስ አበባ ገባ። የስልክ አገልግሎት ስላልነበረ ቤተሰቦቹም የት እንደደረሱ ማወቅ አልቻለም። እንደ ምንም አዲስ አበባ የገባው ገበሬ በያዛት ሳንቲም ቤት ተከራይቶ የአቅሙን ስራ ለመስራት ቢሞክርም ሊሆንለት አልቻለም።
ከተማዋ ከአቅሟ በላይ ስራ አጥ ሰዎችን በመሸከሟ ለአዲስ መጤዎቹ ጭርሱኑ ቦታ አልነበራትም። ትናንት ተንደላቆ ይኖር የነበረው፤ ከራሱ አልፎ ለሰዎች የሚተርፈው፤ ከእጁ አጥቶ ነጥቶ የማያውቀው ገበሬ እጀጉን ተከፋ፤ ንዴቱ አቅሉን አስቶት ከሳሩም ከቅጠሉም ጋር መጣላት ጀመረ።
የሰላም ሰፈሩ ሰላም አደፍራሽ
ይሳቅ ያዕቆብ እና መልካሙ በንቲ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ሰላም ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪዎች ናቸው። ጥብቅ ጓደኛሞች ነበሩ። ከስራ መልስ ተጠራረተው ሻይ ቡና ማለትን ለምደዋል። ሰዎቹ ጨዋታ የማያልቀባቸው ሁሌ ፊታቸው በፈገግታ ተሞልቱ የሚታዩ ደስተኞች ነበሩ።
ይሳቅን ያለ መልካሙ መልካሙን ያለ ይሳቅ ሰፈር ውስጥ መመልከት ያልተለመደ ነበር። አይለያዩም ሁልጊዜ አብረው ናቸው። ወዳጅነታቸው የሚያስቀናው እነዚህ ጓደኛሞች አንዳንድ ጊዜ የእግር ጉዞ በማድረግ መንገድ ላይ ቆም እያሉ ያወሩ ነበር። አንዳንዴ ደግሞ መጠጥ ቤት ውስጥ እየተጎነጩም ያመሻሹ ነበር። ብቻ ምንም ይሁን ምን ሳይገናኙ ማደር እስከማየችሉ ድረስ በየእለቱ አብረው ይውላሉ፤ ያመሻሉ።
አንድ ቀን እንደልማዳቸው ከሰፈራቸው ወጣ ያለ አካባቢ ድረሰ በእግራቸው ሄደው እየተመለሱ ነበር። ወሬያቸው ሞቅ ሲለ መንገድ ላይ ቆም እያሉ አውርተው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ። አሁንም ቆም ደግሞ ሄድ እያሉ የሚያወሩት ጓደኛሞች ትኩረታቸው በሙሉ ጨዋታቸው ላይ ስለነበር ሌላውን ነገር እያስተዋሉ አልነበረም።
ጨዋታቸው ሞቅ ስላለ የሰዓቱንም መሄድ ልብ አላሉም ነበር። በዝግታ እየተጓዙ ሞቅ ባለ አንደበት ያወራሉ። ያኔ ከየት መጣ ያላለቱን የቁጣ ድምፅ ይሰማሉ። ቀና ብለው ሲያዩ የሁለቱም ቤት አቅራቢያ ደርሰዋል። ያለምንም ስጋት “ አቤት….” አሉ። “ተንቀሳቀስ መንገድ ዘግተህ መቆም አትችልም….” የሚል የቁጣ ድምፅ ከወደ ጨለማው አቅጣጫ መጣ።
የሞቀውን ጨዋታ ወደ ለቅሶ የቀየረው ገጠመኝ
ጥቅምት 03 ቀን 2014 ዓ.ም ነበር። ቀዝቀዝ ያለው የጥቅምት ንፋስ ፊትን በለሆሳስ እየገረፈ ያልፋል። ንፋሱ ቀዝቀዝ ቢልም ብርዱ ግን አጥንት ሰንጣቂ አይነት ነበር። ቀደም ብለው ጃኬቶቻቸውን ደራርበው፤ እጃቸውን ጃኬታቸው ኪስ ከተው ለሀገር ጉዞ የወጡት ጓደኛሞች ሞቅ ባለ ጨዋታቸው ብርዱን ረስተው የእግር ጉዞ ያደርጋሉ። ከምሽቱ 2፡30 አካባቢ ሲሆን ከሄዱበት እየተመለሱ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ክልል ልዩ ቦታው ሰላም ሰፈር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ደርሰዋል። ወሬያቸውን ስላልጨረሱ ቆም ብለው ጨዋታቸውን ቀጥለዋል።
ድንገት ‹‹ተበተኑ እናንተ መንገድ ዘግታቹህ ትቆማላቹሁ፤ እዚያ ሰው እያለቀ ነው። እኛም የመጣነው ጠላት ከመኖሪያ ቄያችን አባሮን ነው።›› የሚል ድምፅ ይሰማሉ። ድምፁ ወደመጣበት አቅጣጫ ፊታቸውን ሲያዞሩ አንድ በንዴት የተሞላ ሰው ሽጉጥ ደግኖ ወደ እነሱ አቅጣጫ ሲመጣ ተመለከቱ።
ሰውየው አለባበሱ የባላገር ሰው ይመስላል። “ከሌላ ሰው ጋር ተመሳሰለንበት ይሆን?” ከሚል ጥርጣሬ ባለፈ አደጋ ያደረስብናል የሚል ግምት አልነበራቸውም። ሁለቱም ሰውየው እንዲረጋጋ ለማድረግ ቢሞክሩም ሰውየው ንግግራቸው እያናደደው ጭራሽ መጮህና መሳደብ ጀመረ። ነገሩ ያላማራቸው ጓደኛሞች ከቦታው ለመሄድ ፊታቸውን ሲያዞሩ ይዞት በነበረው ሽጉጥ ሁለቱንም አንድ አንድ ጊዜ ተኩሶ አንደኛውን ጀርባው ላይ ሌላኛውን ደግሞ የግራ ትክሻው ላይ በመምታት ይጥላቸዋል። በደረሰባቸው ምት የተነሳ ከሁለቱም ከፍተኛ ደም መፍሰስ ይጀምራል።
በሰላም ስራ ውለው ልማዳቸውን አደርሰው፤ በሰላም ወደ ቤታቸው ሊገቡ የነበሩት ጓደኛሞች ባልታሰበው ዱብዳ ቆሰሉ። የተኩስ ድምፅ የሰሙት የአካባቢው ነዋሪዎችና የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ሲደርሱ ሁለቱ ታጣቂዎች መሬት ወድቀው አጥቂው ደግሞ ዙሪያቸውን እየዞረ ዘራፍ ሲል ይደርሳሉ። ማህበረሰቡ ተባብሮ ወንጀለኛውን በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ተጎጂዎቹን ወደ ሆስፒታል አደረሷቸው።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ፤ ምርመራውን ጀመረ። የግል ተበዳዮች በጊዜ ሆስፒታል በመድረሳቸው ብዙ ደም ቢፈሳቸውም ሕይወታቸው አልጠፋም። ከህመማቸው እንዳገገሙም ፖሊስ ቃላቸውን ሊቀበላቸው ወደ ሆስፒታል ጎራ አለ።
የግል ተበዳዮችም ያልታሰበውን ገጠመኝ ለፖሊስ አብራርተው ካስረዱ በኋላ ፖሊስ የወንጀል ፈፃሚው ለዚህ ጥፋት መገፋፋት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? በማለት የተለያዩ ምርመራዎችን ሲያደረግ ቆየ። ከዛም ወንጀለኛው ቤት ንብረቱን በማጣቱ የተነሳ ከደረሰበት ብሶት የተነሳ በሰዎች ሁሉ ላይ ያሳደረው ጥላቻ መሆኑን ለመረዳት ተቻለ።
ምንም እንኳን በመከፋት ውስጥ ቢቆይም ሰውን ማጥፋት ወንጀል በመሆኑና፤ ፍቃድ የሌለው መሳሪያ ይዞ በመገኘቱ ፖሊስ ለዐቃቤ ህግ ክስ እንዲመሰረትበት ማስረጃዎቹን አጠናቅሮ አቀረበ።
የፍርድ ቤት ክርክር
በፍትህ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ቦሌ ምድብ ጽ/ቤት የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀፅ 27/1/ እና 540 ስር የተመለከተውን በመተላለፉ ተከሳሽ ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ክርክሩን መርቶ የቅጣት ውሳኔውን አስተላለፈ። ጥቅምት 03 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡ 30 ሰዓት ሲሆን፤ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ክልል ልዩ ቦታው ሰላም ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የግል ተበዳይ ይሳቅ ያዕቆብ እና መልካሙ በንቲ የተባሉትን ግለሰቦች ‹‹ተበተኑ እናንተ መንገድ ዘግታቹህ ትቆማላቹሁ፤ እዚያ ሰው እያለቀ ነው። እኛም የመጣነው ጠላት ከመኖሪያ ቄያችን አባሮን ነው።›› በማለት ይዞት በነበረው ሽጉጥ ሁለቱንም የግል ተበዳዮች አንድ አንድ ጊዜ ተኩሶ አንደኛውን ጀርባው ላይ ሌላኛውን ደግሞ የግራ ትክሻው ላይ በመምታት በሁለቱም ተበዳዮች ላይ ከፍተኛ ደም መፍሰስ እንዲያገጥማቸው ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ተራ የሰው ግድያ ሙከራ ወንጀል ተከሰሰ።
ተከሳሽ በችሎት ቀርቦ ክሱ ደርሶትና ተነቦለት የእምነት ክህደት ቃሉን ሲጠየቅ “እኔ ድርጊቱን አልፈፀምኩም ጥፋተኛም አይደለሁም ” ሲል ቃሉን ሰጥቷል።
ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሳሽን ጥፋተኝነት ለፍርድ ቤቱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ዝርዝር ሶስት የምስክሮች ቃል፣ የሰነድ፣ ኤግዚቢት እና ገላጭ ማስረጃዎችን በማቅረብ በበቂ ሁኔታ ለችሎቱ በማስረዳቱ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም፤ የዐቃቤ ህግን ክስ እና ማስረጃ ማስተባበል ባለመቻሉ የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ፍርድ ቤት ዐቃቤ በበቂ ሁኔታ ተከሳሽ ወንጀሉን መፈጸሙን ያረጋገጠ በመሆኑ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል።
ውሳኔ
በክርክሩ መሰረት ተከሳሽ ከዚህ በፊት የጥፋተኝነት ሪከርድ የሌለበት፤ ወንጀሉ በሙከራ ደረጃ የቀረ በመሆኑ የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለት በ10 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። ነገር ግን ውሳኔው ወንጀለኛው ዋስትና ተፈቀዶለት በሌለበት የተሰጠ ውሳኔ ነበር፡፡
የግድያ ወንጀልን በተመለከተ በጊዜ ቀጠሮም ሆነ በመደበኛ ክስ መዝገብ ማንኛውም ተጠርጣሪ ወይም ተከሳሽ ክስ እንደሚቀርብበት ወይም በተከሰሰበት ክስ ጥፋተኛ እንደሚባል አውቆ መሰወሩ መደበኛ ክርክር ማድረግን የማይከለክል ሲሆን፤ መብቱን ጠብቆ አለመከራከር መብት ከማሳጣቱም በላይ ዘወትር የፍርሃት እና የስጋት ኑሮን እንዲመሩ ያደርጋል፡፡ ከፍትህ በድብብቆሽ እንደማይኖር አውቆ ወንጀለኛው እጁን እንዲሰጥ ጥሪ ቀርቦለታል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም