በጉልበት የሀብት ማማን መመኘት

ተክቶ በአዲስ አበባ መኖር ከጀመረ ወደ ስድስት ዓመት ያክል አስቆጥሯል። የመጣውም ትምህርቱን ለመማር ሲሆን፤ በዚህ አጋጣሚም ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በማረሚያ ቤት ውስጥ የመሥራት ዕድል ነበረው።

አቶ ተክቶ ፀጋዬ ወርቁ ትውልድና እድገቱ በአማራ ክልል ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ምክንያት የ10ኛ ክፍል ትምህርቱን ለመቀጠል ነበር። በ2009 ዓ.ም ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በፌዴራል ማረሚያ ቤት ተመዝግቦ በመሠልጠን በቃሊቲ ማረሚያ ቤት የእስረኞች ጥበቃ በመሆን አገልግሏል።

አቶ ተክቶ ታዲያ ከዚህ ሥራው በሕጋዊ መንገድ የለቀቀ ሲሆን ሌላ ሥራ ዘርፍ ላይ በመሰማራት ሕይወቱን ለመምራት በመወሰን ነበር ሥራውን የለቀቀው። ታዲያ ሥራውን ከለቀቀ በኋላ በሚኖርበት የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አካባቢ ያሉ ጓደኞችን በማፍራት የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ሞክሯል። የድለላ ሥራ የተለያዩ የሚከራዩ ቤቶችን የማገናኘት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። ይህም ሥራው በሰፈሩ ውስጥ ባለው ወረዳ ሠራተኛ የሆኑ፣ የታክሲ ሹፌሮች እና ረዳቶች እንዲሁም ሌሎች ወጣቶች ጋር በቀላሉ ለመተዋወቅ እና ለመግባባት ዕድል ፈጥሮለታል።

በተጨማሪም የድለላ ሥራውን ተጠቅሞ ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ የተለያዩ መኪና ሽያጮችን እንዲሁም ጥቁር ገበያ ተብሎ በሚጠራው የውጭ ምንዛሪ ሥራን ከሌሎች በተለያየ ሥራ ላይ ከሚገኙ ጓደኞቹ ጋር ይሠራል። ነገር ግን ይህ ሥራ የሚሠራው በድብቅ ነው።

ከመደበኛ የሥራ ሂደት ውስጥ ባገኘው ሰዓት የሚሠራው እና የትም ቦታ ሆኖ ሊሠራ የሚችለው ባለመሆኑ አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው በሰፈሩ ውስጥ ካለ አንድ የሻይ ቡና መሸጫ ቦታ ነው። አብዛኛዎቹ ሰዎች ስልኩ እንኳን አልሠራ ቢላቸው ነገር ግን እዚች ቡና ቦታ ቢመጡ አያጡትም።

ወይዘሮ ሐና ተክቶን የምታውቀው ከባለቤቷ ጋር ሰፋ ያለ ቤት ፈልገው ይኖሩበት የነበረውን ቤት ለመቀየር በፈለጉበት ወቅት ነበር። ተክቶ በሚኖርበት አካባቢ ለወላጆቻቸው ቤት ቅርብ በመሆኑ በተክቶ አማካኝነት ቤቱን ሊያገኙ ችለዋል። በዚህም ከደላላ የሚታጣ ነገር የለምና ከተክቶ ጋር ትውውቃቸው በዚህ መልኩ ጀምሯል።

ወይዘሮ ሐና እና ባለቤቷ አቶ ቴዎድሮስ ጠንከር የተለያየ የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ አቶ ቴዎድሮስ በጋራጅ ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያ ሲሆን የተለያዩ ደንበኞቻቸው መኪናቸውን ከማደስ ባለፈ አዳዲስ መኪና የሚገዙ ሰዎች አስቀድመው የሚገዙትን መኪና እንዲፈትሹለት በመጀመሪያ የሚመርጡት ሰው ነው።

ታዲያ በዚህ አጋጣሚ ባለቤቱ ወይዘሮ ሐና እና ባለቤቷ ቴዎድሮስ መኪና ለመግዛት እቅድ ነበራቸው። ለዚህም ቴዎድሮስ እንደ ባለሙያነቱ በዙሪያው የተለያዩ አማራጮችን አይቶ መግዛት የሚችል ነው። ሐና እና ባለቤቷ መኪና ለመግዛት ሲያስቡ በዙሪያዋ ከምታውቃቸው ሰዎች አንዱ የሆነው ተክቶ ጋር መረጃው ደርሷል።

ታዲያ በንቃት ሥራውን የሚሠራው ደላላ እንደመሆኑ አሉኝ የሚላቸውን ግንኙነቶች ተጠቅሞ የተለያዩ የመኪና ዓይነቶችን ለማሳየት ይጥራል። ሐና በአብዛኛው በፍጥነት ለምትፈልጋቸው ጉዳዮች የቤት ሠራተኛ

እንዲፈልግላት አልያም ሌሎች ጉዳዮችን ስትፈልግ ተክቶ በፍጥነት ስለሚሠራላት አብዛኛውን ጊዜ እርሱን ታምነዋለች። በመሆኑም አንድ የሚሸጥ እና ብዙም ያላገለገለ መኪና ስለመኖሩ መረጃውን ከነገራት በኋላ በፍጥነት እንድትወስን በተደጋጋሚ መኪናውን እንድታየው ቀጠሮ እንዲይዙ ይጠይቃት ነበር።

በዚህም ከባለቤቷ ቴዎድሮስ ጋር በመሆን መኪናውን ለማየት ቀጠሮ ያዙ። ለዚህም መኪናውን አይተው ቢስማሙ ቅድመ ክፍያ እንደሚከፍሉ በማስማማት 200 ሺህ ብር ጥሬ በመያዝ በሜትር ታክሲ ወደ ቀጠሮው ስፍራ ሄዱ ።

ቴዎድሮስ ጠንክር መኪና የመገጣጠም እና ሰዎች መኪና ከመግዛታቸው በፊት የመፈተሽ ልምድ ያለው በመሆኑ መኪናውን ለመግዛት በማሰብ አስቀድማ ለማየት በማሰብ መኪናው ይገኝበታል ወደተባለው ስፍራ ይዛው እንደሄደች ይናገራል።

የተገናኙበት ቦታ እንደደረሱ በድለላ ሥራ የተሰማራው ተክቶ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ሆነው በተባለው ስፍራ ተገኝተዋል። በዚያ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተቋም ውስጥም አንድ ፒክ አፕ መኪና በጊቢው ውስጥ ትገኛለች። ታዲያ አዲስ መኪና ገዢዎቹ ሐና እና ባለሙያው ቴዎድሮስ መኪናው ለማየት እና አስፈላጊውን ፍተሻ ለማድረግ በሚጠብቁበት ጊዜ ያልተጠበቀ ነገር ሆነ።

በቦታው በነበሩ ተክቶ እና ሌሎች አባሪዎቹ እንዲሁም የፖሊስ ልብስ የለበሰ፣ መሣሪያ የያዘ ሰው በደረሰባቸው ማስፈራሪያ ተሳፍረው ከመጡበት መኪና እንዲወርዱ በማስገደድ እና ሌላ መኪና ውስጥ በግድ እንዲገቡ በማድረግ ከአካባቢው ይዘዋቸው ተሰወሩ።

በዚህም የግል ንብረት ለማፍራት መኪና ለመግዛት እቅድ የነበራቸው ባለትዳሮቹ መኪናውንም ሳይገዙ ይዘው የነበሩትን ገንዘብ እንዲሁም የእጅ ስልካቸውን በመስረቅ ወደማይታወቅ ቦታ ወስደው ከመኪናው ገፍትረው እንዲወርዱ ካደረጉ በኋላ ከእነአባሪዎቻቸው ሊሰወሩ ችለዋል።

በዚህም አቶ ቴዎድሮስ ጠንክር ወደ ፀጥታ አካል በመሄድ እና ጥቆማ በመስጠት በሥራ በማሳበብ እና በማታለል እንዲሁም በማስፈራራት ከባድ ውንብድና በመፈጸም አጭበርባሪዎች እንዲያዙ እና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ አድርጓል።

የወንጀሉ ዝርዝር

በሰኔ አራት ቀን 2014 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ልዩ ስሙ አዲስ አበባ መሬት ማኔጅመንት ተብሎ በሚጠራው ቦታ ዶላር እንመነዝራለን በማለት ሦስት ሺህ ዶላር ለመመንዘር በመስማማት ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ተቀጣጥረው ከግል ተበዳይ ጋር 200 ሺህ ብር እንዲያመጡ በመስማማት ከተገናኙ በኋላ አንደኛ ተከሳሽ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መለያ የሆነውን ካኪ የደንብ ልብስ በመልበስና፤ መሣሪያ በመያዝ የግል ተበዳይን ባለቤቷን እና አብረዋት በቦታው የመጡ ሰዎችን በማስፈራራት እና ብሎም መሣሪያ በመደቀን ከመጡበት የራይድ መኪና እንዲወርዱ በማድረግ መሣሪያን ተጠቅመው በማስፈራራት የግል ተበዳይ ይዘውት የነበረውን ጥሬ 200 ሺህ ብር እንዲሁም የእጅ ስልክ በመውሰድ እና አስፈራርተው መኪና ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ራቅ ወዳለ ቦታ ወሰዷቸው። ከዚያም የያዙትን ስልክ እና ገንዘብ ከተቀበሏቸው በኋላ መንገድ ላይ ጥለዋቸው ከሌሎች አባሪዎቻቸው ጋር ተሰውረዋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ሄኖክ ደጀኔ ከጥር አንድ 2010 ዓ.ም ጀምሮ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አስተዳደር የሆነውን ኮድ 04 መኪና በሹፌር የሙያ ዘርፍ እንዲሠራ የተሰጠው ቅጥርም የፈጸመ ሲሆን ማዝዳ ፒክአፕ መኪና ከተቋሙ ተረክበው ይሠሩ እንደነበር አረጋግጠዋል።

ተከሳሽ ተክቶ እና በአባሪያቸውም ይህንን ወንጀል የፈጸሙት ይህንን የሚሠሩበትን ሠራተኞችን ለማጓጓዝ በኃላፊነት የተሰጣቸውን ተሽከርካሪ ከኃላፊነታቸው ውጪ ለከባድ የውንብድና ወንጀል የተጠቀሙት፤ የተቋሙ ሠራተኞች መሆናቸው ተረጋግጧል።

ዓቃቤ ሕግም ክስ ከመሠረተ በኋላ የተለያዩ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና ማስረጃዎችን ሲያጠናክር ቆይቷል። በዚህም የሰነድ፣ የሰው ማስረጃዎችን በማጠናከር በመዝገቡ ጋር አያይዞ ለፍርድ ቤት አቅርቧል።

ማስረጃዎች

ዓቃቤ ሕግ መረጃው ከደረሰው በኋላ ባደረገው ማጣራት እና ክትትል ተከሳሾችን በቁጥጥር ስር በማዋል የራሱን ተከታታይ ማጣራት ማድረጉን የቀጠለ ሲሆን ከሳሽ አቶ ቴዎድሮስ ጠንክር ወንጀለኞችን ሲለዩ የሚያሳይ ፎቶግራፍ፣ ገንዘብ የተላለፈባቸው የባንክ ደረሰኝ ማስረጃዎች፣ ተከሳሽ አቶ ደስአለኝ ዳምጠው እንዲሁ በተከሰሰበት የዘረፋ ወንጀ ፣ የወንጀል ፍሬ ነገር የሆነውን መሳሪያ በዘረፋ ወንጀል ወቅት ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ወንጀሉን ሲፈጽሙ መጠቀማቸው እንደ ማስረጃ ቀርበዋል ለፍርድ ቤት ቀርቧል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 540 መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ወንጀል ችሎት በፈፀመው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ምስክር አቅርቦ ያሰማ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበበትን ክስ መከላከል ባለመቻሉ ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ በአንደኛ ተከሳሽ አቶ ተክቶ ላይ 21 ዓመት ከስድስት ወር ጽኑ እስራት እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ደስአለኝ ዳምጠው በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ውሳኔውን አሳልፏል።

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You