
ለዘመናት በቆየውና በምንታወቅበት አብሮ በመኖር ሂደት ውስጥ ያለው የሌለውን ማገዝ የተለመደ ተግባር ነው። አንዱ እርስ በእርስ የመወዳጀት ምክንያት ብቻም ሳይሆን ሰዎች እርስ በእርሳቸው ቤተሰባዊነትን ፈጥረው ረጅም ጊዜ በመልካም ጉርብትና እንዲኖሩ የሚያስችላቸው ነው። በመሆኑም አንዱ የሌለውን በቅርቡ ካለው ጎረቤቱ ተውሶ ወደቤቱ የሚመጡ እንግዶቹን በጥሩ ሁኔታ አስተናግዶ ይሸኛል ። ታዲያ ይህ መረዳዳት እና አብሮነት በኀዘንም ሆነ በደስታ ጊዜ የሚገለጥ ነው።
ሆኖ ይህንን መረዳዳት ባልተገባ መንገድ የሚጠቀሙበት በርካታ ናቸው። መረዳዳት የሚለው እሳቤ እና ራስን አጋልጦ እና እጅ አጠረኝ ብሎ እጅን ለመመጽወት መዘርጋት እጅግ የተለያዩ ሃሳቦች ናቸው ። ባለንበት በዚህ ወቅት በምንጓዝበት መንገድ ሁሉ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሰዎች ህጻናት በየመንገዱ ይለምናሉ። አንድ ብር ስጡኝ ፣ ዳቦ መግዣ ፣ የቤት ክራይ ቸግሮኝ ነው እና በደረሰባቸው የተለያዩ ህመሞች ምክንያት መድሃኒት ለመግዛት አቅም ያጠራቸውና በዚህም መደበኛ ሕይወታቸውን ለመምራት የተቸገሩ ፣ ቤተሰቦቻቸውን ማስተዳደር ያልቻሉ ሰዎች ወደ አደባባይ ወጥተው ርዳታ ይጠይቃሉ ወይንም በተለመደው ቃል ይለምናሉ።
ሰዎች ካልቸገራቸው በቀር የሰው ፊተ ለማየት መድፈር በቀላሉ የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም በሚል በየመንገዱ ለእነዚህ ዜጎች እጃቸውን የሚዘረጉ ብዙ ናቸው። በዛሬው ተናጋሪው ዶሴ ገጻችን ያልሆነውን እንደሆነ በማድረግ አንዳንዶች ከመሥራት ይልቅ ለራሳቸው ሌላ ስያሜ በመስጠት በሀሰት በልመና እንደሚሰማሩ መረጃዎች ያሳያሉ ። በመሆኑም ትኩረቱን በዚህ ላይ ያደረገ እና ብዙዎችን ያስተምራል ብለን ያሰብነውን ታሪክ እነሆ።
እማዋይሽ ተከስተ ትባላለች በአዲስ አበባ ከተማ መኖር ከጀመረች ረጅም ዓመታትን አስቆጥራለች። ወይዘሮ እማዋይሽ ከቤተሰቦቿ ተለይታ ወደ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ኑሮዋን ለመምራት የተለያዩ ጥቃቅን ሥራዎችን እየሠራች ቆይታለች። በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ በአንድ ወቅት በሥራ አጋጣሚ ከተዋወቀችው አቶ ታሪኩ ከተማ ጋር የትዳር ሕይወትን ለመመሥረት በመወሰን አብረው በትዳር ለሰባት ዓመት ያክል ጊዜ ቆይተዋል።
በእነዚህ ሰባት ዓመታት ውስጥ አንድ ወንድ ልጅንም አፍርተዋል። ነገር ግን የእማዋይሽ ባለቤት አቶ ታሪኩ በሚሠራበት የኮንስትራክሽን ሥራ ላይ በደረሰበት ድንገተኛ አደጋ ሕይወቱ አልፏል። ይህ ሲሆን ልጃቸው ትምህርት ቤት ለመግባት እየተዘጋጀ ነበር። ወይዘሮ እማዋይሽም ይህ ነው የሚባል ቋሚ ሥራ ያልነበራቸውና በባለቤታቸው ገቢ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ባለቤታቸውን ካጡ በኋላ ልጃቸውን እና የእሳቸውን ሕይወት ለማትረፍ ሥራ ለመሥራት ወሰኑ ። ታዲያ ለወይዘሮ እማዋይሽ በቶሎ ለመጀመር ምቹ የነበረውን ሥራ የክረምት ወቅትን አስታኮ በሠፈራቸው መውጫ በሚገኘው መንገድ ላይ በቆሎ እየጠበሱ መሸጥ ነው። በመሆኑም በብዛት የበቆሎ እሸት ከሚሸጡ ሰዎች የተወሰኑትን በመረከብ መሸት ሲል ልጃቸውን ይዘው ሥራቸውን ያከናውናሉ፡፡
መጠኑ ይነስም ይብዛ ንግድ ነው እና እስከሚለምድ ድረስ በጥቂቱም ቢሆን አታግሏቸው ነበር። እሳቸውም ከሌሎች ሻጮች ትምህርት እየወሰዱ የእለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እና ኑሯቸውን ለመምራት የተለያዩ አትክልቶችን እያመጡ በጎን መሸጣቸውን ቀጥለዋል። ነገር ግን ወይዘሮ እማዋይሽ በቂ የሚባል ገበያን እያገኙ ባለመሆናቸው ኑሯቸውን ሊደጉም ቀርቶ የሚኖሩበት የቤት ኪራይ ለመሸፈን ተቸግረዋል። ታዲያ ወይዘሮ እማዋይሽ የያዙትን የበቆሎ እሸት በሚሸጡበት ወቅት የያዙትን እስከሚጨርሱ አልያም የመሸበት ገበያን ብለው ወደቤታቸው የሚገቡት ከሌሎቹ ሻጮች አምሽተው ይገቡ ነበር።
ወይዘሮ እማዋይሽ ውጪ በሚያመሹበት በዚህ ወቅት ልጆች ያዘሉ እናቶች በየመንገድ ጥርጊያው እና የትራፊክ መብራት ይዟቸው የሚቆሙ መኪኖች አጠገብ በመሄድ ሲለምኑ ይመለከታሉ። አንዳንዴም ምንም ሳይሸጡ ወደቤታቸው በሚገቡበት ወቅት ልጃቸውን ይመለከቱ እና እንደሌሎች በመንገድ ላይ እንደሚመለከቷቸው ልጅ ያዘሉ እናቶች ወጥተው መጠየቅ በሃሳባቸው ውልብ ይላል ፤ መለስ ብለው ደግሞ ይኖሩበት የነበረውን ሕይወትና ሰው ምን ይለኛል ብለው በማሰብ ሃሳባቸውን ትተው ሲነጋ ወደሥራ ለመሄድ ያቅዳሉ።
ይህም ሆኖ የሚኖሩበትን የቤት ኪራይ ለመክፈል ግን ከወር ወር ተችግረዋል። ወይዘሮ እማዋይሽ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሳሉ የቤተሰባቸው አባል የሆኑ ወይዘሮ ጤናዬ የተባሉ የአክስታቸው ልጅ የህክምና ቀጠሯቸው በመድረሱ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ይመጡና ወይዘሮ እማዋይሽ ቤት ያርፋሉ ። ወይዘሮ ጤናዬ ሲመጡም የ10 ዓመት ልጃቸውን ይዘው ነበር የመጡት ፤ ታዲያ በቀጠሯቸው መሠረት ወደ ህክምናቸውን ካደረጉ በኋላ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጡ በመቀጠራቸው ልጃቸውን ወይዘሮ እማዋይሽ ጋር ትተውት ወደ መጡበት ይመለሳሉ። እማዋይሽ ምንም ቢሆን ዘመድ ነኝ ብለው ተቀበሉት እንጂ ይዘው ለመቆየት የሚያስችል ገቢ አልነበራቸውም ፤ እንዲቆይ የፈቀዱበት ምክንያት ግን የወይዘሮ ጤናዬ ልጅ ከተወለደ ጊዜ ጀምሮ ምክንያቱ ያልታወቀ ህመም ያለበት በመሆኑ እማዋይሽ በሚኖሩበት ሥፍራ ከሚገኝ ጸበል እየተመላለሰ እንዲጠመቅ ከእናቱ ጋር ተማክረው በመስማማታቸው ነበር ። የወይዘሮ ጤና ልጅ አካላዊ ጤና ያለው ቢሆንም አልፎ አልፎ የሚጥለው በመሆኑ ወይዘሮ እማዋይሽ ጠዋት ጠዋት ይዘውት ወደ ጸበል መመላለስ ጀመሩ።
ከአቅም በታች
ወይዘሮ እማዋይሽ ጠዋት ጠዋት ወደ ቤተክርስቲያን መሄድን የዘወትር ተግባራቸው አድርገውታል። በአደራ የተሰጣቸውን ልጅ ተቀብለው ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው። ከእለታት በአንድ ቀን ታዲያ ወደ ጸበሉ ስፍራ ከመድረሳቸው በፊት የአደራ ልጃቸው ይጥለውና መሬት ላይ ይወድቃል። በሁኔታው የተደናገጡት ወይዘሮ እማዋይሽ ሲጮሁ ሌሎች ሰዎችም በቦታው ተሰባሰቡ ፤ በሚወድቅበት ወቅት ይህ ነው የሚባል ምልክት ያላሳየው ህጻን አማኑኤል ሲወድቅ እጁ ላይ እና እግሩ ላይ መጋጋጥ እና መድማት ደርሶበታል ። ታዲያ በቦታው የተሰበሰበው ሰውም በኪሱ ያለውን ጥቂት ገንዘብ በማዋጣት በትራንስፖርት ወደቤት እንዲመለሱ አልያም ወደ ሀኪም እንዲሄዱ ነገሯቸው።
ወይዘሮ እመዋይሽም ይህንኑ ሃሳብ በመቀበል የአደራ ልጃቸውን ይዘው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ነገር ግን በዚህ ውስጥ በዚች ቅጽበት ብቻ ያገኟት ገንዘብ እሳቸው በአንድ ቀን ውስጥ ለመሥራት እንኳ የማያስቡት በመሆኑ ተደንቀዋል።
ታዲያ ወይዘሮ እማዋይሽ በድንገት ይህንን ሃሳብ በቀን ውስጥ ሲያሰላስሉበት ዋሉ ። ቀኑ ወደ ማምሸት ሲያመራም በአደራ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ረስተው ህጻን አማኑኤልን ፊቱን በነጠላ በመሸፈን እና ደግፈው በመያዝ ከሰፈራቸው ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ ሄደው በአንድ ጥግ ላይ ቁጭ አሉ። በዚህ ስፍራ ህጻናት ፣ ልጅ የያዙ እናቶች ተሰብስበዋል ። ወይዘሮ እማዋይሽም ከእነርሱ ጋር ተመሳስለው ቁጭ አሉ ። በዚያን እለት እስሚመሽበት ሰዓት ድረስ ከቆዩ በኋላ በምጽዋት ያገኙትን ገንዘብ ይዘው ወደ ቤታቸው አቀኑ። ይህ ሲሆን የገዛ ልጃቸውን ግን ከጎረቤት በአደራ አስቀምጠው ነበር የሚሄዱት።
የአንድ ቀን ልማድ እና ድርጊት እንዲሁ አልመጣም እና ወይዘሮ እማዋይሽ በቀጣዩ ቀንም እንዲሁ ህጻን አማኑኤልን እንደ ታመመ ሰው በነጠላቸው ሸፍነውና ደግፈው በሌላ ስፍራ ለመለመን ተገኙ። ከአላፊ አግዳሚው የሚቀበሉትንም ገንዘብ በጎናቸው እየሸጎጡ ከቆዩ በኋላ ረፈድፈድ ሲል ወደቤታቸው አቀኑ ።
ወይዘሮ እማዋይሽ ድርጊት በብዙ ሰዎች ዓይን ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው መሆኑን ግን አልተመለከቱም። ምክንያቱም ለመለመን ከመዘጋጀታቸው በፊት ልጄ ብለው የያዙትን ህጻን አማኑኤል ሲያመናጭቁትና አንዳንዴም ሲጎትቱት ይስተዋላሉ። ታዲያ ይህ ድርጊታቸው ልጃቸው ነው ወይ የሚል ጥርጣሬን የአካባቢው ሰዎች እርስ በእርስ የሚነጋገሩበት ነው።
እጅ ከፍንጅ
በሌላኛው ቀን ወይዘሮ እማዋይሽ ከተሳፈሩበት ባስ ወርደው ልጃቸውን በአንድ እጃቸው ይዘው እየጎተቱ ብዙ ቁጥር ያላቸው ተመጽዋቾች ወደሚሰባሰቡበት ቦታ ለመቀላቀል ጥድፍ ጥድፍ በማለት ሥፍራው ላይ ደረሱ። ጥቂት ደቂቃ እንደቆዩም አንድ ሰው መጥቶ ቀርቦ ያነጋግራቸዋል። ወይዘሮ እማዋይሽ እጃቸውን ወደሚያናገራቸው ሰው ዘርግተው ለመመለስ ጠጋ አሉ ፤ በድንት ግን ሌሎች ሰዎችም ቀስ በቀስ በመሰባሰብ የማን ልጅ ነው ብለው ይጠይቋቸዋል። ታዲያ በዚህ መሀል ግርግሩን የተመለከቱ የአካባቢው ደንብ አስከባሪዎች ወደ ሥፍራው በመጠጋት ያለውን ሁኔታ ለማጣራት በመሞከር መረጃውን ከነዋሪዎች ያገኛሉ። ወይዘሮ እማዋይሽንም ለማጣራት እንደሚፈልጓቸው በመግለጽ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው ። ታዲያ የያዙት የ10 ዓመት ህጻን የታመመ አለመሆኑን አረጋገጡ።
በሰው መነገድ
መረጃው የደረሰው ፖሊስ ጉዳዩን ለማጣራት ተጨማሪ መረጃዎችን ማሰባሰቡን ቀጠለ። በመሆኑም ጤነኛ የሆነን ታዳጊ ህመምተኛ አስመስላ በማጭበርበር ስትለምን ነበረች በሚል ክስ መስርቶ የማጣራት ሥራውን ጀመረ።
በከተማዋ በተለያዩ ጊዜያት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ሙሉ ጤነኛ ሆነው ሳለ ህመምተኛ በመምሰልና በማስመሰል ህብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ የነበሩ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው በመያዝ እና ተገቢውን ቅጣት በማሳለፍ ልምድ ያለው ሲሆን ይህንንም ጉዳይ ህዳር 10 ቀን 2017 ዓ/ም በጉለሌ ክ/ከተማ ወረዳ 8 አካባቢ ተከሳሽ እማዋይ የተባለች ግለሰብ ልጄ ነው መናገር አይችልም በማለት ስትለምንበት በቦታው በነበሩ የደንብ ማስከበር ባለሙያዎች ተይዛ ለፖሊስ ተላልፋ ተሰጥታለች።
ጉዳዩ የደረሰው የጉለሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያም ተጠርጣሪዋን ተረክቦ ተገቢውን ምርመራ የማጣራት ተግባር ሲከውን ቆይቷል። ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ ላይ የግል ተበዳይ የ10 ዓመት ታዳጊና የተከሳሽ ዘመድ ቢሆንም ከአክስታቸው ልጅ በአደራ መልክ ከትውልድ አካባቢው ወደ አዲስ አበባ መጥቶ እንደተቀመጠ መለመኛ ማድረጓንም ያትታል፡፡
ፖሊስ የተከሳሿን የምርመራ መዝገብ በተገቢው የሰውና የሰነድ ማስረጃ በማደራጀት ለዐቃቤ ሕግ በማቅረብ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሿን ያርማል እንዲሁም ሌሎችንም ከመሰል ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያስተምራል ሲል በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ወር ቀላል እስራት እንድትቀጣ በማለት ውሳኔ አሳልፏል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 25 ቀን 2017 ዓ.ም