ጌታቸው አለምጸሀይ ክፍሉ በሚሠራበት የሥራ ተቋም ውስጥ የፋይናንስና ልማት ክፍል ውስጥ የሂሳብ ባለሙያ ሆኖ ያገለግላል። በዚህ የሥራ ዘርፍ ከ10 ዓመት በላይ የሆነው ጌታቸው በአጠቃላይ 20 ዓመታትን በሥራ አሳልፏል። የሥራ ቦታው ከእርሱ ረጅም ቀኑን ክፍል የሚያሳልፍበት እንደመሆኑም በሥራ ገበታው ካሉ ሠራተኞች ጋር ከሥራ ባልደረባነት ባሻገር መግባባትን እና ጓደኝነት እንዲሁም ቤተሰባዊነት የሚገነባበት ነው።
ጌታቸውም በዚህ የሥራ ቦታው ይህንን ወዳጅነት ገንብቷል። የሂሳብ ሙያ ጥንቃቄ እና ታማኝነትን የሚፈልግ ሲሆን ሴቶች ከእነዚህ ባህሪያት ጋር በተለይም በጥንቃቄ ሥራዎችን የሚያከናውኑ በመሆናቸው በፋይናንስና ልማት ክፍል ውስጥ በአብዛኛው ሴት ሠራተኞች ይበዛሉ። ወይዘሮ መዓዛ በዚህ የሥራ ክፍል ውስጥ የፋይናንስ ባለሙያ ናት።
በሥራ ቦታ በሚፈጠር የእርስ በርስ መቀራረብ ሰዎች ከትውውቅ ባሻገር ጓደኝነትን አልፎም ቤተሰባዊነትን ወደ መመስረት ይሸጋገራሉ። ወይዘሮ መዓዛም ከባለቤቷ ጋር የተዋወቀችው በምትሠራበት ሕንጻ ውስጥ በተደጋጋሚ ሲተያዩ ቆይተው በአጋጣሚ በተፈጠረ ትውውቅ ነው።
ወይዘሮ መዓዛ በጸባይዋ ከብዙዎች ጋር በቀላሉ ለመግባባት የምትችልና ደርባባ የምትባል ውበት ያላት እንስት ናት። ጌታቸው አሁን የሚሠራበትን ክፍል ሲቀላቀል በቅድሚያ ከተዋወቃቸውና የሥራ ከባቢውን እንዲለምደው በጥሩ አቀባበል ካስተናገዱት መሀከል አንዷ ናት። ጌታቸው በሥራ ረጅም ዓመትን ያሳለፈና በእድሜው ጎልማሳ የሚባለውን የእድሜ ክልል የተሻገረ ነው።
ትዳር ለመመስረት ከአንድም ሁለት ጊዜ መጣሩን በተለያየ ጊዜ ከመዓዛ ጋር አውርቷል። በሥራ ቦታው ቀድማ አይኑ ውስጥ የገባችው ሴት መዓዛ ብትሆንም ባለትዳር መሆኗ ሀሳቡን እንዲተወው እና እንደሥራ ባልደረባ ብቻ እንዲመለከታት አድርጎታል።
ጌታቸው በባህሪው ግልፍተኛና ቶሎ ተናዳጅ ነው:: ወደ ሥራ ቦታው ከሚመጡ ደንበኞች ጋርም ይሁን በሥራው በሚያጋጥመው ተግዳሮት በቀን ውስጥ ሳይናደድ ሳይጮህ አይውልም። ከሥራ ባልደረቦቹም ሆነ ከቅርብ አለቃው ጋር ሳይጨቃጨቅ የሚያሳልፈው ጊዜ ጥቂት ነው። በዚህ ባህሪው ምክንያት ብዙዎች የማይቀርቡትና ለወዳጅነት የማይመርጡት ሰው ነው። ስለዚህ ብዙውን ጊዜ በሥራ ሰዓት ፋታ ለመውሰድ የሚኖረውን የሻይ ቡና ጊዜውን ከወይዘሮ መዓዛ ጋር ያሳልፋል። በአንጻሩ መዓዛ በባህሪዋ ታጋሽ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር በቀላሉ የምትግባባ በመሆኗ ብዙ ሰዎች ለወዳጅነት ይመርጧታል።
ታዲያ ጌታቸው ወዳጅነታቸው በያዘው መስምር ብቻ የሚቀጥል መሆኑ አይዋጥለትም። አልፎ አልፎ ይህንን መስመር በማለፍ የተለየ ስሜት ሲያሳይ የተመለከተችው መዓዛ፣ መስመር የሳተ ግንኙነት እንዳይፈጥር የቻለችውን ያህል ትጠነቀቃለች። ባስ ሲልም ባለትዳር እንደሆነችና ልክ እንዳልሆነ ልትነግረው ትሞክራለች።
ማለቂያ የሌለው ጉትጎታ
መዓዛ፣ ጌታቸው ለትዳር ያለውን ጉጉት በመመልከት ሌሎች እንስቶችን ልታግባባው ትሞክራለች። ነገር ግን የምታስተዋውቃቸው ሴቶች ባሕሪውን ለመረዳትም ሆነ ለመልመድ በመቸገራቸው ከወራት የዘለለ ጊዜን አብረውት አይጓዙም።
የሥራ ቦታ ሰዎች ከሥራቸው በዘለለ የማኅበራዊ ሕይወታቸው አንዱ አካል በመሆኑ የግል ሕይወታቸውን በሥራ ቦታ ካፈሯቸው የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር ይወያያሉ። እድል ከቀናቸው እና ጥሩ ወዳጅም ካገኙ ሚስጥራቸውን የሚያካፍሉት ይሆናል። ወይዘሮ መዓዛ በትዳሯ ላይ በገጠማት ችግር ምክንያት በሥራ ገበታዋ ላይ እንደከዚህ ቀደሙ በትኩረት ለመሥራት እየተቸገረች ነበር። ይህንን ያስተዋለው ጌታቸው ምን እንደሆነች ቢጠይቃት ልትነግረው ባትፈልግም ከሌሎች የሥራ ክፍሎች መስማቱ ግን አልቀረም። ታዲያ ይህንን አጋጣሚ እንደ መልካም አጋጣሚ በመመልከት በተደጋጋሚ ሀሳቧን እንድትቀይርና ትዳሯን ትታ እርሱን የፍቅር ጥያቄ እንድትቀበል ለማድረግ ይሞክራል።
ወይዘሮ መዓዛ ይህ ጉዳይ ያለቀለትና እሷም ደግሞ ባለትዳር መሆኗን በተደጋጋሚ ብትነግረውም ጌታቸው በሕይወቷ የተፈጠረውን ክፍተት ተገን አድርጎ መውጪያ መግቢያ አሳጣት። መዓዛ በይሆናል ተስፋ ጥረት ማድረጉን በመቀጠሉ አንዳንዴም ደግሞ ጤናማ ያልሆነ ምልልስ በማድረጋቸው ለመጨረሻ ጊዜ ለትዳሯ ታማኝ መሆኗን በመናገር ጓደኝነታቸውንም ለማቋረጥ መወሰኗን ነገረችው ።
ሰዎች ከራሳቸው አልፈው ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖራቸው ማኅበራዊ ሕይወት ሊያዳብሩት የሚገባ የተግባቦት ክህሎት አለ። ጌታቸው ግን ይህንን ክህሎት ያዳበረ አይመስልም። እንዲያውም በተግባቡት ሰዎች ላይ የበላይነትን የመውሰድና እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የማለት ባሕሪ አለው። ይህን ባሕሪውን መላይ ለመትገበር ጥረት ቢያደርግም ስላልተሳካለት የመናቅ ስሜት ተሰምቶታል። የሥራ ቦታውም እንደ ከዚህ ቀደሙ ምቹ እና መልካም ቀንን የሚያሳልፍበት አልሆነለትም። ምክንያቱም በራሱ የባህሪ ግትርነት እና ግልፍተኝነት ከመዓዛ ጋር የነበረውን ወዳጅነት አቋርጧል።
በመሆኑም ለተወሰኑ ቀናት የዓመት እረፍት ወስዶ ከሥራ ቦታው ገለል ማለትን መርጧል። ይህ ሁኔታ ለወይዘሮ መዓዛ ጥቂት ጊዜም ቢሆን እረፍት ሰጥቷት ነበር፤ ያላሰበችውና ያልገመተችው አደጋ ሕይወቷን እስኪነጥቃት ድረስ፡፡
ወይዘሮ መዓዛ እንደወትሮው ማልዳ ነበር ወደ ሥራዋ የገባችው። እንደተለመደውም ሥራዋን ከመጀመሯ በፊት በምትሠራበት ሕንጻ የታችኛው ወለል ላይ በሚገኘው ካፌ ከሥራ ባልደረባዋ ጋር ቡናዋን ጠጥታ ወደ ሥራ ክፍሏ ተመለሰች። መዓዛን ጨምሮ ሶስት ሰዎች የምትሠራበትን ቢሮ ይጋራሉ። የሥራ ባልደረቦቿ ለተጨማሪ ሥራ ከቢሮ በመውጣታቸው መዓዛ ብቻዋን ሥራዋን ጀምራለች።
ታዲያ በዚህ ሰዓት በእረፍት ላይ የነበረው የሥራ ባልደረባዋ ጌታቸው ወደ ቢሮው አቅጣጫ ሲመጣ ተመለከተችው። የሚሠሩበት ተቋም አንድ ሲሆን የሥራ ክፍላቸው ፊት ለፊት በመሆኑ የእሷን ቢሮ አልፎ ወደ ቢሮው ሲገባ አስተውላዋለች። ጉዳዩ ምን እንደሆነ ያልጠረጠረችው መዓዛ ካለችበት ቢሮ ወደሌላኛው የሥራ ክፍል በእጇ የተወሰኑ ፋይሎችን ይዛ ወጣች። በሕንጻው መተላለፊያ ላይም ከጌታቸው ጋር ተገናኙ።
የተመለደውን ሰላምታ ሰጥታ ለማለፍ ብትሞክርም ጌታቸው ቆይታውን እንዲያረዝምለት በማሰብ በእሷና በትዳር አጋሯ መካከል የተፈጠረው ችግር ስለመፈታቱ ይጠይቃታል። መዓዛም ችግሩ ስለመፈታቱ ምላሽ ሰጥታ ወደ ሥራዋ ስትመለስ እጇን ይዞ አብራው እንድትሆን ለመጨረሻ ጊዜ ይጠይቃታል። በዚህ ጊዜ መዓዛ በሀይል እጇን አስለቅቃ ምላሽ ሳትሰጥ ወደቢሮዋ በምታመራበት ወቅት በድንገት በእጁ ላይ ቢላ ስለተመለከተች ራሷን ለማዳን እየጮኸች መሮጥ ጀመረች።
እሱም እየተከተለ በያዘው ቢላ በተደጋጋሚ በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት አደረሰባት። በርካታ ሰዎች ሲዘዋወሩ በሚውሉበት ሕንጻ ውስጥም ከፍተኛ ሁካታ ተፈጠረ። በወቅቱ በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ርብርብ አማካኝነትም እብሪተኛው ጌታቸው በቁጥጥር ስር ሲውል ወይዘሮ መዓዛ በሰዎችና በጸጥታ ኃይሎች እርዳታ ወደ ሕክምና ተቋም ተወሰደች። በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿ ላይ ጉዳት የደረሰባት መዓዛ ከፍተኛ የደም መፍሰስ ስላጋጠማት እርዳታ ብታገኝም ሕይወቷን ግን ማትረፍ አልተቻለም።
ዝርዝር ወንጀል
ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋለው ጌታቸው አለምጸሀይ ክፍሉ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 የሚገኘው ሳባ ሕንጻ ስድስተኛ ፎቅ የሥራ ባልደረባውን ወይዘሮ መዓዛ ካሳን የፍቅር ጥያቄ አቅርቦላት ባለትዳር ነኝ በማለቷ የግድ አብረን እንሁን እያለ ሲያስቸግራት ቆይቶ ፈቃደኛ ባለመሆኗ በሥራ ገበታዋ ላይ እያለች ጨካኝነቱን እና ነውረኛነቱን በሚያሳይ መልኩ እያባረረ በቢላዋ በቀኝ እና በግራ የሆዷ ክፍል በመውጋት ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስባት አድርጓል። በእለቱም ሕክምና ሲደረግላት ቆይታ ጉዳቷ በመባባሱ ከሁለት ወር በኋላ መጋቢት 15 ቀን 2011 ዓ.ም ሕይወቷ ያለፈ በመሆኑ በከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ተከሷል።
ከሕግ በላይ
ፖሊስ በሚያደርገው ማጣራት ሟች ሕይወቷ ከማለፉ በፊት ለፖሊስ የሰጠችውን ቃል እንደ ሰነድ ማስረጃ አድርጎ የወሰደ ሲሆን፤ የመጀመርያ እርዳታ ያገኘችበትን የአለርት ሆስፒታል ማስረጃዎችን በመያዝና ተከሳሽ ጌታቸው አለምጸሐይ ክፍሉን በቁጥጥር ስር በማዋል ተጨማሪ የተለያዩ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ እንዲሁም የተከሳሽን ቃል በመቀበል መረጃዎቹን ሲያደራጅ ቆይቷል። ተከሳሽ ከፈጸመው አሰቃቂ ወንጀል በኋላ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ታስሮ የነበረ ሲሆን፣ በተደጋጋሚ አሞኛል በማለት የሕክምና ክትትል ያደርግ ነበር። ፖሊስ ተጨማሪ ማጣራቶችን እያደረገ በሚገንኝበት ወቅትም የካቲት 19 ቀን 2011 ዓ.ም አሞኛል በማለት በአንድ አጃቢ ለሕክምና ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ባመራበት ከእስር ሊያመልጥ ችሏል።
ፖሊስ ተከሳሽን ለመያዝ የተለያዩ ጥረቶች ያደረገ ሲሆን ከእስር ማምለጡ ከታወቀ በኋላ የምርመራ ክፍሉ በደረሰው አምቦ ከተማ፣ አዳማ እንዲሁም በአዲስ አበባ ቡራዩ አካባቢ ይገኛል በሚል በቁጥጥር ስር ለማዋል የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል። ወንጀል ፈጽሞ ከሕግ ማምለጥ የማይቻል በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ የክስ ሒደቱን በመቀጠል እና መረጃዎችን በማጠናከር
ወንጀለኛውን ለመያዝ የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል።
ማስረጃዎች
ዓቃቤ ሕግ ክሱን ያስረዱልኛል ያላቸውን ወንጀሉ በተፈጸመበት እለት በቦታው የነበሩና ከሟች ወይዘሮ መዓዛ ጋር ቅርበት ያላቸውን ሰባት የሰው ምስክሮች ቃል ተቀብሎ ከተከሳሽ መዝገብ ጋር በማያያዝ ለፍርድቤት አቅርቧል። በተጨማሪም በወቅቱ የደረሰውን ጉዳት የሚያሳይ የአለርት ማዕከል ማስረጃ፣ ሕይወቷ ካለፈ በኋላ በምርመራ ክፍሉ የቀረበ የአስክሬን ምርመራ እንዲሁም በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ የቀረበ የአስክሬን ምርመራ ውጤት የሰነድ ማስረጃ አያይዟል። አቃቤ ሕግ ወንጀሉ በተፈጸመበት እለት ወንጀሉ ሲፈጸም የሚያሳይ ገላጭ የተንቀሳቃሽ ምስል በማስረጃነት አያይዞ አቅርቧል።
ተከሳሽ ሆን ብሎ በሰው ልጆች ላይ አደገኛ ጉዳት በሚያስከትል መሳሪያ (ቢላ) ደጋግሞ በመውጋት ለገላጋይ በማስቸገር ሟች የሥራ ግዴታዋን እየተወጣች የምትገኝ መሆኗን ከግምት ውስጥ በማስገባት ዓቃቤ ሕግ ከፍተኛውን የቅጣት ጣሪያ እንዲቀጣ ጠይቋል። በዚህም ተከሳሽን ያርማል ሌሎችንም ያስተምራል ያለውን ውሳኔ አስተላልፏል።
በመሆኑም በፌደራል ዓቃቢ ሕግ እና በተከሳሽ ጌታቸው አለምጸሀይ ክፍሉ መካከል በፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ ችሎት የነበረው ክርክር በቀን 3/12/2014 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ተከሳሽ በሌለበት በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ፣ ከሕዝባዊ መብቶቹ ለዘወትር እንዲሻር ውሳኔ በመስጠት ፖሊስ ተከሳሽ ጌታቸው አለምጸሀይ ክፍሉን በመያዝ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህም ማንኛውም ግለሰብ ወንጀል ፈጽሞ ተበዳይም ፍትህ ሳያገኝ በዳይም ቅጣቱን ሳይቀበል አይቀርምና ወንጀለኛው ወንጀሉን ፈጽሞ ከእስር ቤት በማምለጥ ተከሳሽ ከሰባት ዓመት በኋላ እንዲሁም በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ በፍርድቤት ውሳኔ ከተሰጠ ከሶስት ዓመት በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከተሸሸገበት በመያዝ በሕግ ጥላ ስር ሆኖ የእስራት ቅጣቱን እንዲፈጽም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲላክ አድርጓል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2017 ዓ.ም