
በቁመትም በመልክም ለሚያያቸው ሰው ይመሳሰላሉ:: አንዳንዶች ወንድማማቾች ናችሁ ወይ? ብለው ይጠይቋቸዋል:: እነርሱ ግን በአንድ አካባቢ ተወልደው ያደጉ አብሮአደግ ባልንጀሮች እንጂ ስጋ ዝምድና እንኳን የላቸውም:: አዲስ አበባ መጥተው መኖር ከጀመሩ አምስት ዓመት ያህል ያስቆጠሩ ሲሆን ከዚህች ከተማ ጋር ሲተዋወቁም አብረው ጓዛቸውን ሸክፈው ከትውልድ ሀገራቸው የብዙዎች መገኛ ወደሆነችው አዲስ አበባ መጥዋል::
ወደ ዋና ከተማዋ ሲመጡ ግርግሩን፤ ሁካታውን እና ጥድፊያው እኩል ተመልክተውታል:: በዚህ ውስጥ የእነርሱ ስፍራ የት እንደሚሆን በምን መልኩ ተላምደውት እንደሚኖሩ ባያውቁም ነገር ግን ከሰው ጋር በቀላሉ ለመግባባት ያላቸውን ክህሎት ተጠቅመው ሕይወታቸውን የተሻለ ለማድረግ ወስነው የግርግሩ ዓለም አካል ሆነዋል::
ሀዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ ሁለቱም ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ የመጀመርያ ጊዜያቸው ነው:: የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ የተሻለ ሥራ እናገኛለን ብለው ወደ ከተማ መጥተው ሕይወትን መጋፈጥ እና ሕልማቸውን በቶሎ ለማሳካት ወስነዋል:: ለመጀመርያ ጊዜም የተማሩበትን የተመራመሩበትን ሳይሆን ኑሯቸውን ለመግፋት ያግዘናል ያሉትን ሥራ ለመሥራት ወስነዋል::
በመሆኑም በኮንስትራክሽን ሥራ ላይ ተሰማርተው በጋራ በተከራዩት ቤት ውስጥ እርስ በርሳቸው እየተጋገዙ ሕይወታቸውን ለመቀጠል ወሰኑ :: ሥራውንም ጀመሩ:: በሂደትም በሚያገኙዋት ገንዘብ ወጣቱ ብርሀኑ መንጃ ፍቃድ በመማር በሥራ አጋጣሚ ከሚያውቃቸው ሰዎች የታክሲ መኪና ተቀብሎ ከአብሮ አደጉ ጋር የታክሲ ሥራን ተቀለቀሉ:: ሥራቸውን በጥሩ በማስኬድ እና የሚጠበቅባቸው ክፍያ ለተሽከርካሪው ባለቤት በመክፈል ሕይወታቸውን መምራት ቀጠሉ ::
ሆኖም ከዕለታት በአንዱ ቀን ችግር አጋጠማቸው:: ብርሀኑ በሚያሽከረክርበት ሰዓት ከሌላ መኪና ጋር በተፈጠረ ግጭት መኪናዋ ከሥራ ውጪ ሆና ለጥገና ወደ ጋራጅ ገባች::
ታዲያ ብርሀኑ እንደገና ያለምንም ሥራ ሲቀመጥ ከቤቱ ውጪ ከሚያውቃቸው ጓደኞቹ ጋር አብሮ ማሳለፍን ምርጫው አድርጓል:: በዚህ አጋጣሚ በታክሲ ተራ ከተዋወቃቸው እና የተለያዩ ሥራዎችን ከሚሰሩ ወጣቶች ጋር እየዋለ ሥራ ለመሥራት ቢሞክርም ከመልካም ሰው የተጠጋ ግን አይመስልም:: ይልቁንስ በላባቸው ከመሥራት ይልቅ የሰውን የሚመኙ መንታፊዎች ጋር ወዳጅነት መስርቷል::
ውሀ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው እንደሚለው ብርሀኑም ሆነ አብሮ አደጉ ሀዱሽ በዚህ ተልካሻ ተግባር ውስጥ ተዘፍቀው ራሳቸውን አገኙት:: ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለስ ከማሰብ ይልቅ ፍጹም ከነበራቸው ማንነት ወድቀው ከጸጥታ አካላት ጋር የድብብቆሽ ሕይወትን ጀመሩ ::
የሰውን መመኘት
ብርሃኑ እና ጓደኞቹ ካለባቸው የሥርቆት ባህሪ በተጨማሪም የተለያዩ ሱሶች ውስጥ ወደቁ:: እነዚህን አጓጉል ባህርያት ለማስታገስ ደግሞ የማይፈነቅሉት ድንጋይ አልነበረም:: ታዲያ ከእለታት በአንድ ቀን እነዚህ ሁለት ጓደኛማቾቸ ሀዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል የተሽከርካሪ ሥርቆት ወንጀል ለመፈጸም በጋራ አቀዱ::
ሐምሌ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረደ 9 ልዩ ቦታው አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አካባቢ ከሌሊቱ 8፡00 ሠዓት ገደማ የግል ተበዳይ ወጣት መልሳቸው ሀበሻ አሻግሬ የተባለን በወቅቱ ሲያሽከረክር የነበረውን ኮድ 3A 75963 አ/አ የሆነ ቪትስ ተሽከርካሪ የዋጋ ግምቱ 1ሚሊዮን 4 መቶ ሺ የሚያወጣ መንገድ ላይ ካስቆሙት በኋላ ወደ ገርጂ ሮባ ዳቦ እንዲወስዳቸው ይነጋገራሉ።
ሹፌሩም በመስማማቱ ወደ መኪናው ውስጥ ይገባሉ:: መኪናው ውስጥ ከገቡ በኋላ የግል ተበዳይን ከኋላ አንቀው በመያዝና ከተናገርክ እንገልሀለን በማለት እጅና እግሩን አስረው 2 የሞባይል ስልኮች የዋጋ ግምታቸው 35 ሺ ብር የሆነ ከወሰዱበት በኋላ ጨለማ ቦታ ላይ በመገፍተር ተሽከርካሪውን ይዘው ከአከባቢው ተሰወሩ። በመቀጠልም ተሽከርካሪውን ለሌላ ግለሰብ አሳልፈው ይሸጣሉ:: በዚህ ወቅት ጉዳዩ ፖሊስ ጆሮ ይደርሳል:: ፖሊስም ወንጀለኞችን በቁጥጥሩ ሥር አውሎ ንብረቱን ለባለቤቱ ለመመለስ እልህ አስጨራሽ ጥረት ማድረጉን ቀጠለ::
ሌላ እድል
ሁለቱ ወጣቶች በሰው ሕይወት እና የላብ ውጤት ለመክበር መንገድ መቀየሱን ተያይዘውታል:: ለአንድ ወር ያክል ጊዜ ድምጻቸውን አጥፍተው ቆይተዋል:: ይህ ነው የሚባል ልዩ ሰፈር መኖርያ አድረሻ ስለሌላቸውም ወንጀለኞችን አድኖ ለመያዝ ፖሊስ ተቸግሯል::
ሆኖም እነዚህ ወንጀለኞች ድምጻቸውን አጥፍተው በሌላ ሥራ መስክ ለመሰማራት እያማተሩ ነው:: የሜትር ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት በከተማዋ በብዛት እየተለመደ የመጣ ሲሆን ወደዚህ የሥራ ዘርፍ የሚገቡ አሽከርካሪዎች የመብዛታቸውን ያክል ይህንን ሥራ በኩባንያ ደረጃ በሥራቸው አሽከርካሪዎችን ይዘው በስፋት እየሠሩበት ይገኛሉ::
በዚህ የክረምት ወቅት ሰዎች ከሥራቸው እና ከእለት ሕይወታቸው ከክረምቱ አየር ፤ ዝናብ እና ብርድ ጋር እየተገዳደሩ ቀናቸውን አሳልፈው ወደቤታቸወ መግባትን ይመኛሉ:: በተቃራኒው ደግሞ በተዋከበ ቀን ውስጥ ሆነው ሕይወታቸውን የሚመሩትን በመምረጥ፤ በሀሳብ የተዋጡትን በመለየት ፣ ወደ ሥራቸው አልያም ወደቀጠሮ ቦታቸው ለመድረስ የሚቸኩሉትን ትኩረት በማድረግ ለሥርቆት የተዘጋጁ በርካታ ሌቦችም ክረምትን ምርጫቸው ያደርጉታል ::
ሐዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ ይህንን የክረምት ገጸ በረከት ለመጠቀም ቋምጠዋል:: ነሀሴ ሁለት ቀን 2015 ዓ/ም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረደ 4 ልዩ ቦታው ለም ሆቴል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተመሳሳይ የውንብድና ወንጀል ለመፈጸም አቅደዋል::
በረከት ሙሉጌታ እለቱን ሲሰራ ውሎ ማምሻውን ወደ ሚኖርበት ቤት አቅጣጫ መጓዝ የሚፈልግ ደንበኛ ይኖር ዘንድ የመጨረሻዋን ደንበኛው ባደረሰበት 22 አከባቢ መጠባበቅ ጀመረ:: ሰዓቱ ወደ እኩለሊት እየተጠጋ ሲሆን በሜትር ታክሲ አገልግሎት ለተሰማሩ አሽከርካሪዎች በተፈጠረላቸው ሲስተም አማካኝነት የሚያገኗቸውን ደንበኞች ተቀብለው የተዘረጋው ሲስተም በተጓዘው የኪሎሜትር ርቀት ታሪፉን አስልቶ ያስቀምጣል:: ይህም የአሽከርካሪውንም የተጓዡንም ማንነት በመመዝገብ ደህንነትን የሚረጋግጥ ይሆናል::
ታዲያ ግን ይህ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተለመደ በመምጣቱ ሰዎች አቅራቢያቸው ያገኙትን በተለምዶው አጠራር የቤት መኪና ወደ ጉዳያቸው በፍጥነት እንዲያደርሳቸው ይዋዋላሉ:: ከዚያም በሕጉ መሰረት ክፍያቸውን መዳረሻቸው ላይ ክፍያ ይፈጽማሉ::
በረከት የመጨረሻዬ ይሁን ያለውን ሥራ እየተጠባበቀ ሳለ ፤ እነዚህን ሁለት ወጣቶች ከአንድ መዝናኛ ስፍራ ወጥተው ወደ እርሱ ሲመጡ ተመለከታቸው:: እሱም በዚያ ምሽት እዚያ ቦታ የመገኙቱ ምክንያት ሥራ ነውና የትራንስፖርት አገልግሎት ፈልገው ስለመሆናቸው አልተጠራጠረም:: ከ22 ወደ ለም ሆቴል ለመሄድ መፈለጋቸውን ገልጸውና ተስማምተው ተሳፈሩ::
አንደኛው ተሳፋሪ ከሹፌሩ ጎን ሌላኛው ከኋላ በመቀመጥ ጉዟቸውን ጀመሩ:: ስፍራው እንደደረሱም ወደ ውስጥ በሚያስገባ ቅያስ እንዲያደርሳቸው ጠየቁት:: በረከት ምንም እንኳን ሰዓቱ እምብዛም ሰው የማይንቀሳቀስበት ቢሆንም አካባቢው አንዳንድ የንግድ ሱቆች የሚገኙበት በመሆኑ ፤ ብዙም ሳያንገራግር የሚፈልጉበት ቦታ ለማድረስ የሚመሩትን አቅጣጫ መከተል ጀመረ::
ባላሰበበት ሁኔታ ግን ከኋላ በኩል አንቀው በመያዝ እና በማስፈራራት ለሥራ የሚጠቀምበትን ሁለት ተንቀሳቃሽ ስልክ ፣ በመኪናው ውስጥ የነበረውን የግል ኮምፒውተር ከነጠቁት በኋላ ፤ በዚህም ሳይበቃ የቦታውን ሰዋራነት በመጠቀም እና በያዙት ስለት በማስፈራራት ከገዛ መኪናው ላይ ገፍትረው ከጣሉት በኋላ መኪናውን ይዘው ከአካባቢው ተሰወሩ::
የወንጀል ማጣራት
ጥቆማው የደረሰው የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስም ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋልና ንብረቱን ለባለቤቱ ለማስመለስ እንቅስቃሴ ጀመረ። ሁለቱም ተከሳሾች የሰረቁትን ተሽከርካሪ ይዘው ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ወደ ትግራይ ክልል በመውሰድ የተሽከርካሪውን ሻንሲ እና የሞተር ቁጥርን በመቀየር እንዲሁም ትክክለኛውን የሠሌዳ ቁጥር ኮድ 3B51731 አ/አ የሚለውን ወደ ኮድ 203493 ትግ በመቀየር ፊሊሞን ኃይሌ ለተባለ ግለሰብ በአንድ ሚሊዮን ብር በመሸጥ ደብዛውን ለማጥፋት ሞከሩ:: ሆኖም ከሕግ አይን የሚሰረቀው ተግባር የለምና የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ከትግራይ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት እና ተከታታይ ክትትሎችን በማድረግ ተሽከርካሪውን ለባለቤቱ አስመልሷል::
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ፖሊስ ባደረገው ማጣራት ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት የግል ተበዳይ ወጣት መልሳቸው ሀበሻ አሻግሬ ከተባለ ግለሰብ በወቅቱ ሲያሽከረክር የነበረውን ኮድ 3A 76395 አ/አበባ የሆነ ቪትስ ተሽከርካሪ የዋጋ ግምቱ አንድ ሚሊዮን 400 ሺህ ብር የሚያወጣ መኪና መስረቃቸው ይደረስበታል:: ከመኪና ስርቆት ባሻገርም የግል ተበዳይን ከኋላ አንቀው በመያዝና ከተናገርክ እንገልሀለን በማለት እጅና እግሩን አስረው 2 የሞባይል ስልኮች የዋጋ ግምታቸው 35 ሺ ብር የሆነ ከወሰዱበት በኋላ ጨለማ ቦታ ላይ በመገፍተር ተሽከርካሪውን ይዘው ተሰውረዋል። ዐቃቤ ሕግ በመዝገቡ ላይ ተጨማሪ የወንጀል ሪከርድ ያለባቸው እና በቁጥር ስር ሳይው ሌላ ወንጀል ሲፈጽሙ በመገኘታቸው በተከሳሾች ላይ ክስ እንዲመሠረትባቸው ተደርጓል።
በተጨማሪም ተከሳሾቹ ሐዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ በቀን አንድ ነሀሴ በረከት ሙሉጌታ የተባለን የግል ተበዳይ በወቅቱ ኮድ 3B 51731 አ/አ የሆነ ቪትስ ተሽከርካሪ የዋጋ ግምቱ 1 ሚሊዮን 200ሺ ብር የሚያወጣ እያሽከረከረ እያለ ተከሳሾቹ የራይድ አገልግሎት ፈላጊ በመምሰል ግለሰቡን አስቁመው ከ 22 ወደ ለም ሆቴል አድርሰን በማለት ከተሳፈሩ በኋላ ሐዱሽ አባዲ የተባለው ገቢና በመቀመጥ ሌላኛው ብርሀኑ ኃይሌ የተባለው 2ኛ ተከሳሽ ከኋላ ወንበር ላይ በመቀመጥ ለም ሆቴል አካባቢ ሲደርሱ አሽከርካሪውን ወደ መንደር ውስጥ እንዲያስገባቸው ይነግሩታል።
የግል ተበዳይም ወደ ተባለው ቅያስ መንገድ እየገባ ሳለ ከኋላ ወንበር ላይ የተቀመጠው ተከሳሽ የግል ተበዳይን አንቆ በመያዝ ቢላ በማውጣትና ከተናገርክ አርድሀለሁ ብሎ በማስፈራራትና በመደብደብ በወቅቱ ይዞት የነበረውን ከ4ሺ ብር በላይ እና ሳምሰንግ ሞባይል የዋጋ ግምት 10ሺ የሚያወጣ፤ እንዲሁም ላፕቶፕ የዋጋ ግምቱ 18 ሺ ብር የሆነ ከወሰዱበት በኋላ ከመኪናው ላይ ገፍትረው በመጣል ተሽከርካሪውን ይዘው ተሰውረዋል።
የተከሳሾቹን የወንጀል መዝገብ ሲከታተል የቆየው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ጥር 9 ቀን 2017 ዓ/ም በዋለው ችሎት ተከሳሾች ሐዱሽ አባዲ እና ብርሀኑ ኃይሌ ግለሰቡ ላይ ባደረሱበት አካላዊ ጉዳትና በወሰዱት ንብረት በከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ እያንዳንዳቸው በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ያስተላለፈ ሲሆን በ2ኛ መዝገብ ጥር 13 ቀን 2017 ዓ/ም በተመሳሳይ እያንዳንዳቸውን በ11 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል። ተከሳሾቹ በሁለቱም የክስ መዝገብ በድምሩ 22 ዓመት ጽኑ እስራት እንደተወሰነባቸውም የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም