*‹‹በፈፀሙት የሥነ-ምግባር ጉድለት የተወሰደ እርምጃ ነው›› የመንግሥት አካላት
ጉዳዩ
በአዲስ አበባ ከተማ በወርሃ ጥቅምት 2015 ዓ.ም በተለያዩ ትምህርት ቤቶች መጠነኛ ግጭቶች ተከስተው እንደነበር አይዘነጋም። መረጃዎች እንደሚያሳዩትም፤ የግጭቱ ቅጽበታዊ መንሰኤ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መዝሙር በትምህር ቤቶች ይዘመር አይዘመር እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀል አይሰቀል የሚል እሰጣ እገባ ነበር። መሰል ችግሮች ከተፈጠሩባቸው ትምህር ቤቶች መካከል ደግሞ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ዕድገት ጮራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ነው። ታዲያ ይህ ችግር በተከሰተበት ወቅት የተለያዩ ጥፋቶች የደረሱ ሲሆን ተጠርጣሪዎችም ተይዘው የዕርምት እርምጃ ስለመወሰዳቸው የከተማ አስዳደሩ አስታውቋል።
ታዲያ በወቅቱ በዚህ ግጭት ውስጥ ተሳትፈው የነበሩ ታዳጊዎች የቃላት ተግሳጽና የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸው ይታወሳል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም ልጆች በይቅርታ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ከወላጆችና እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መግባባት ላይ ስለመደረሱም በመገናኛ ብዙኃን ጭምር መናገራቸው ይታወሳል። ይሁንና ‹‹በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው ዕድገት ጮራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የከንቲባዋን የይቅርታ ቃል ለመፈፀም ዝግጁ አልሆነም፤ ልጆቻችንም ከትምህርት ገበታ ያለአግባብ አሰናብቶብናል›› ሲሉ ወላጆች ለዝግጅት ክፍላችን አቤቱታ አቅርበዋል። የዝግጅት ክፍላችን ደግሞ በየደረጃው የሚመለከታቸውን የሥራ ኃላፊዎች እና ተቋማትን በማነጋገር እንሆ ለአንባቢያን ብሏል።
ወላጆች ምን ይላሉ?
ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከመጡት መካከል የራሚ ሚፍታ ወላጅ እናት አንዷ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በሌሎች ክፍለ ከተሞችም ከተማሪዎች ጋር የተያያዙ ተመሣሣይ ችግሮች ተከስተዋል። በወቅቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት መድረክ ውይይት ተደርጎና በይቅርታ መንፈስ ወደ ትምህርተ ገበታቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። በዚህም ተማሪዎች ወደ ዕውቀት ገበታቸው መምህራንም ወደ ማስተማር ሥራቸው ተመልሰዋል። ይሁንና ግን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የዕድገት ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሆነው ከዚህ የተለየ ነው።
ተማሪዎቹን ወደ ትምህር ቤቱ ከመመለስ ይልቅ የማባረር ተግባር ተፈፀመ። በወቅቱ በጥፋቱ ላይ በቀጥታ የተገኙትን ሳይሆን በቦታው የሌሉትን ተማሪዎችም ጭምር ከትምህርት ገበታ ወደ ማሰናበት የተሄደበት አጋጣሚ አለ። በተጨማሪ በጥፋተኝነት ተጠርጥረው በፖሊሲ ጣቢያ በህግ ቁጥጥር ሥር ባሉበት ቀን እንኳን መስታወት ሰብራችኋል በሚል የውሸት ክስ እና ሥም ማጥፋት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ የማሰናበት ሥራ መሠራቱንና ይህም ከፍተኛ በደል መሆኑን ያስገነዝባሉ።
ሌላኛው ቅሬታ አቅራቢ ወላጅ ደግሞ የተማሪ ሚኪያስ አብርሃም ወላጅ አባት ናቸው። እራሳቸው እንደሚሉት፤ ልጃቸው የተከሰሰበት እና ከትምህርት ገበታ እንዲሰናበት የተደረገበት ሂደት ፈጽሞ የማይገናኝ መሆኑን ይናገራሉ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ መስታወቶች ተሰባብረዋል፤ ግጭትም ተከስቷል በተባለበት ቀን ልጃቸው ከትምህርት ቤቱ ውጭ ነበር። ታዲያ ክሱ ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ዓይነት በመሆኑ እና ፍርድ ቤቱም ጉዳዩን መርምሮ ስለደረሰበት ጥፋተኛ አልሆነም። ይህም በመሆኑ ወደ ትምህርት ገበታው መመለስ ነበረበት። ይሁንና ግን ትምህር ቤቱ ተማሪ ሚኪያስ ወደ ትምህር ቤቱ እንዲገባ አልፈቀደም፤ ይህ ደግሞ ከሞራልም ሆነ ከህግ አኳያ አግባብ አይደለም ባይ ናቸው።
የሆነው ሆኖ ጥፋት እንኳን ቢገኝበት የከተማዋ ከንቲባ ‹‹በይቅርታ አልፈናቸዋል፤ ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሱ›› ብለው ከወሰኑ በኋላ፤ ትምህር ቤቱ ብቻውን ይህን መሰል ውሳኔ መወሰኑ አሳዛኝ እና ለህግ ተገዥ አለመሆናቸውን ያሳያል። እነዚህ ታዳጊዎች በአሁኑ የዕድሜ ክልል ጥፋት ሊያጠፉ የሚችሉ ቢሆንም በተግሳጽ ወደ ትምህር ገበታቸው መመለስ አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን አልባሌ ቦታ የሚውሉ እና እንደ አገርም ማህበራዊ ቀውስ ሊያደርሱ በሚችሉ ድርጊቶች ውስጥ የመሳተፍ ዕድል ሊያጋጥማቸው ይችላል። ይህን ትምህርት ቤቱ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት። የወላጆችን ሞራልና ፍላጎት ማወቅ ሲገባው ይህንን ድርጊት የፈፀመበት ምክንያት ግልፅ አይደለም ሲሉ ምሬታቸውን ይገልፃሉ።
ሌሎች ወላጆች በበኩላቸው፤ ችግራቸውን በአግባቡ ለማሳወቅና እውነታውን ለመረዳት መቸገራቸውን ይናገራሉ። ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ በሚያደርጉት ጥረት ትምህርት ቤቱ ፈቃደኛ አለመሆኑን ያስገነዝባሉ። ወደ ትምህርት ቤቱ ገብተን ለመነጋገር ስንሞከርም ‹‹መግባት አይቻልም›› በሚል በጥበቃ ከበር ላይ እየመለሷቸው መሆኑንም ተናግረዋል። ወደ ክፍለ ከተማ ሲሄዱ መጀመሪያ ከትምህርት ቤቱ ጋር ተነጋገሩ የሚሏቸው መሆኑን በመጠቆም፤ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ሲሄዱ ደግሞ ‹‹ይህ እዚህ የሚደርስ ጉዳይ አይደለም፤ በቀላሉ እዚያው የሚፈታ ነው›› ብለው እንደመለሷቸው ያስረዳሉ።
በመሃል መፍትሄ ማጣታቸውን በምሬት የሚናገሩት ወላጆች፤ ልጆቻቸው ፍትህ ማጣታቸውን፤ በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ ልጆቻቸውም መብት ተነፍገው፤ ከትምህርት ገበታቸው ተናጥፈው ጩኸታቸውን የሚሰማ አካል እንዳላገኙ ይገልፃሉ።
የተጠርጣሪዎች እና የፖሊስ ክርክር በፍርድ ቤት
በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ ችሎት በቀን 03 ታህሳስ 2015 ዓ.ም በመለያ ቁጥር 00805 በሰፈረው መረጃ መሰረት፤ መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ካቀረባቸው መረጃዎች መካከል፤ ‹‹ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ አሻራ ሪከርድ ለመቀበል፤ ያልተያዙ አባሪዎችን ለመያዝ የ14 ቀን ቀጠሮ ጠይቋል። ከዚህም በተጨማሪ የዋስትና መብታቸው መከበር የለበትም፤ በጉዳዩ ቀጥታ ግንኙነት ስላላቸውና ስለተጠረጠሩም ጭምር ፍርድ ቤቱን ዋስትናም እንዳይፈቅድ ጠይቆ ነበር›› ይላል።
ተጠርጣሪዎች በበኩላቸው፤ ‹‹ድርጊቱ ተፈጽሟል በተባለው ቦታ አልተያዝንም። ዓርብ እለት ረብሻ ተነስቶ ተማሪ ሁሉ ተለቆ እያለ ድንጋይ ውርወራ ተጀምሮ እኛ የተያዝነው አይስክሬም ቤት ተደብቀን እያለን ነው። ዓርብ ይዘው አቆይተውን ዛሬ አቀረቡን። ሌሎቹ ከመካከላችን ሦስቱ ልጆች ጠዋት ሁለት ሠዓት ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ እያለ የተያዙ ናቸው። ስልክም መደወል አትችሉም፤ ከቤተሰብም ጋርም መገናኘትም አትችሉም በማለት እስከ ዛሬ አቆዩን›› ሲሉ ተማሪዎቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
በመጨረሻም በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ ችሎት በቀን 03 ታህሳስ 2015 ዓ.ም በመለያ ቁጥር 00805 በሰፈረው መረጃ መሰረትም የተጠርጣሪዎቹንና የፖሊስን መረጃ ግራ ቀኝ ካገናዘበ በኋላ ፖሊስ ለተጨማሪ ምርምራ የጠየቀው ተጨማሪ 14 ቀናት አግባብ ሆኖ ስላላገኘው፤ ተጠርጣሪዎቹ በብር 1ሺ500 ዋስ ሲያቀርቡ ወይንም ገንዘቡን በሞዴል 85 ሲያስይዙ ከእስር ይፈቱ ተብሎ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ዋስትና ሊያሟሉ ካልቻሉ በፖሊስ ጣቢያ (መምሪያ) በእስር ቆይተው ፖሊስ በተፋጠነ ሁኔታ በምርመራ መዝገቡን አጠናቆ እንዲልክ ታዟል ይላል።
በምርመራ ውጤቱም የወንጀል ሁኔታ በግልጽ ተለይቶ ያልተቀመጠ በመሆኑና ድርጊቱም የዋስትና መብት የማያስከለክል በመሆኑ የጊዜ ቀጠሮ አቤቱታውም ውድቅ ስለመደረጉ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለሚ ኩራ ምድብ ችሎት በቀን 03 ታህሳስ 2015 ዓ.ም በመለያ ቁጥር 00805 የተቀመጠው መረጃ ያትታል።
ትምህርት ቤቱ
የዕድገት ጮራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሹመት በበኩላቸው፤ በተማሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ብዙ ጊዜ ሂደቶችንና ድምር ውጤቶችን የተመለከተና ያገናዘበ እንጂ በግብታዊነት የተወሰደ እርምጃ አለመሆኑን ይጠቁማሉ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች መምህራንም ሆነ ተማሪዎች ስጋት ላይ ወድቀዋል። ይህም በመሆኑ መምህራን በቂ እውቀት ለማስጨበጥ ተማሪዎችም በተረጋጋ መንፈስ ለመማር እክል ገጥሟቸዋል። ይህም በመሆኑ ትምህር ቤቱ ለመማር ማስተማር ሂደት ይጠቅማሉ ያላቸውን ሠላማዊ አማራጮችን ሲጠቀም እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹በትምህር ቤቱ ውስጥ የሚመጡ ተማሪዎች ከወላጆቻቸው በአደራ መልክ የተቀበልናቸው ልጆቻችን ናቸው። ነገ ደግሞ የኢትዮጵያ ተረካቢ ናቸው።›› የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፤ የሥነ ምግባር ጥሰት ሲፈጽሙ ግን መስተካከል ስላለባቸው በየደረጃው የሚጠበቀውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ይናገራሉ። ይህም በመሆኑ በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በመጀመሪያዎቹ ወራት በትምህር ቤቱ የተከሰተውን ችግር ለማስተካከል ሲባል እርምጃ ተወስዷል ይላሉ።
የተወሰደው እርምጃው በርዕሰ መምህሩ ወይም ደግሞ በተወሰኑ መምህራንና አካላት ፍላጎት ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የሥነ- ምግባር ኮሚቴዎች፤ ወላጅ እና መምህራን ህብረት እና የበላይ አመራሮች ጭምር የሚያውቁት ጉዳይ ነው ይላሉ። እርምጃውም ተማሪዎቹ የሚስተዋልባቸውን የሥነ ምግባር ጉድለት እንዲያሻሽሉ ከማሰብ የመነጨ እንጂ በመሰረታዊነት ሕይወታቸውን ለማጨለም የታሰበ አለመሆኑን ያስረዳሉ። እንዲያውም የተወሰደው አርምጃ እና ተማሪዎቹ ያጠፉት ጥፋት የሚመጣጠን አይደለም ይላሉ።
አንዳንዶቹ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸውና ለመጨረሻ ጊዜ ፈርመው የነበሩ ናቸው፤ ወላጆቻቸውም ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሌሎቹ ደግሞ በተግሳፅ በምክርም ጭምር ከጥፋታቸው ሊታቀቡ ያልቻሉ ናቸው። ይሁንና የተወሰደው እርምጃ አስተማሪ እንዲሆን በማሰብ እንጂ እስከመጨረሻው እንዲጎዱ በማሠብ አይደለም። የተወሰደው እርምጃም የትምህርት ሥርዓቱ በሚፈቅደው መመሪያ መሰረት የተወሰነ ነው። ይህም ሆኖ በሚቀጥለው ዓመት ባህሪያቸውን አስተካክለው ሲመጡ በደስታ የሚቀበሏቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ወረዳው
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 አስተዳደር ትምህርት ፅህፈት ቤት ጉዳዩን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ፤ ምንም እንኳን ትምህር ቤቱ መገኛው በወረዳው ውስጥ ቢሆንም የማስተዳደር ጉዳይ ግን ለወረዳው የተሰጠ አይደለም። በከተማው አሰራር መሠረትም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው የክፍለ ከተማውን የትምህርት ፅህፈት ቤት ነው። ምናልባትም ጉዳዩ ከዚህ የዘለለ ከሆነም ከክፍለ ከተማው በላይ ያሉ አመራሮችን እንጂ ወረዳውን የሚመለከት አይደለም ብለዋል። ከትምህርት ቤቱ ጋር ሊኖር የሚችለው ግንኙነትም የጋራ የስብሰባ መድረኮች ሲኖሩ አሊያም ደግሞ በመንግስት አቅጣጫ በትብብር የሚሠሯቸው ተግባራት ሲኖሩ ብቻ ነው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ክፍለ ከተማው
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሣይ ከኔ በትምህርት ቤቱ እና በትምህርት ገበታ ላይ በነበሩ ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ክስተት በቀላሉ የሚታይ አለመሆኑንና ይህም በጥልቀት በመመርመር እርምጃ የተወሰደ መሆኑን ከግንዛቤ እንዲገባ ያሳስባሉ።
ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ቤቱ ተደጋጋሚ ችግሮች ይፈጠሩ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ሲሣይ፤ በአዲስ አበባ ከተማ በትምህር ቤቶች ለሚከሰቱ አብዛኞቹ ችግሮችም መነሻው ይኸው ትምህርት ቤት እየሆነ መምጣቱን ይገልፃሉ። ታዲያ ይህም በመሆኑ ችግሮች እየተወሳሰቡና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ እየተስተጓጎለ፤ ወላጆችም ሆኑ መምህራን ስጋት እየገባቸው ስለመሆኑ ያስረዳሉ።
ይህን መነሻ በማድረግም ‹‹የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መዝሙር በትምህርት ቤቶች ይዘመር አይዘመር እና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰንደቅ ዓላማ ይሰቀል አይሰቀል›› ከሚለው ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ወከባ እና ችግር ነበር። ቀደም ሲል ደግሞ በሃይማኖት ሰበብ በትምህርት ቤቱ ችግር ነበር። በወቅቱ በተፈጠረው ችግርም ለአራት ቀናት ትምህርት ቤቱን ለመዝጋት መገደዳቸውንና ወላጆችና ተማሪዎች ስጋት ላይ ወድቀው እንደነበርም ያስታውሳሉ። በትምህር ቤቱ በተፈጠረው ችግርም 40ሺ የሚገመት ንብረት ወድሟል። መስታወቶች ተሰባብረዋል፤ በሮችና መስኮቶች ተጎድተዋል ብለዋል።
ታዲያ ችግሩ ከተከሠተ እና ነገሮችን ማረጋጋት ከተጀመረ ወዲህ የፀጥታ አካላት፣ አመራሮች እና መምህራንን በመያዝ የልየታ ሥራ ሲከናወን ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ 254 ተማሪዎች በጉዳዩ ላይ ሲሳተፉ ነበር የሚል መረጃ ተገኝቷል። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 52ቱ ደግሞ በህግም ጭምር ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርገዋል። ከ52 ተማሪዎች መካከልም በጥልቀት በተካሄደው ዝርዝር ውይይት የእነዚህ 52 ተማሪዎች የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊዎችና እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ብሎም ወላጆችና መምህራንም በተሳተፉበት መድረክ የክስ ሂደቱ እንደማይቀጥልና ክሱ ተቋርጦ በይቅርታ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ የተደረገበት ሂደት ነበር።
ይሁንና በዚህ ደረጃም ችግሮችን ማለፍ ከተቻለ በኋላም በትምህርት ቤቱ መረጋጋትን ማምጣት አልተቻለም። ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱንም መቀጠል አልተቻልም፤ ችግሩም እየተባባሰ ቀጥሏል። በዚህ ጊዜ 52 ተማሪዎች መካከል አሁንም ችግሮችን እየፈጠሩ ያሉት እና የትምህርት ሥርዓቱን እያወኩ ያሉት እነማን ናቸው የሚለውን የመለየት ሥራ በጥናት መጀመሩን ያስታውሳሉ- አቶ ሲሣይ። በዚህም የችግሩን ምንጭና ጠንሳሾች ለመለየት በተደረገው ጥረት ውጤት እየተገኘ መጣ ይላሉ። ከ52 ተማሪዎች መካከልም አሁንም ከጥፋታቸው ያልተመለሱ ስለመኖራቸውና ይህም የመማር ማስተማር ሂደቱን በቀጣይም ለማወክ የተዘጋጁ ታዳጊዎች መኖራቸው ተደርሶበታል።
የታሰሩት 52 ተማሪዎች በሙሉ ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰው ነበር። ይሁንና ግን ጥቂቶቹ ግቢ ውስጥ ሆነው መምህራን እረፍት በሚሆኑበት ሰዓት መስታወት መስበር ጀመሩ። ጩኸትና የመሳሰሉትን አዋኪ ድርጊቶችንም ፈፀሙ። በዚህን ጊዜ በትምህርት ቤቱ ያሉት 4000 ተማሪዎች ለከፋ ስጋት ተጋለጡ። ይህ በመሆኑ አሁንም የድርጊቱ አባባሾችን የመለየት ሥራ መጀመሩን ያስታውሳሉ። ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ባይጠቀስም ‹‹መረጃዎችን በመስጠት እና በመጠቆም ተማሪዎችና መምህራንም ተሳትፈዋል›› ብለዋል።
መምህራን ላይ ያረፈው ቅጣት
ተጠያቂነቱ ያረፈው ደግሞ ተማሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን መምህራንን ጭምር ያካተተ ነው። ሁለት ምክትል ርዕሳነ መምህራን ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር ራቅ ያለ ቦታ ተመድበዋል። ዋና ርዕሰ መምህር ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ተደርጓል። ስድስት መምህራንም በከባድ ማስጠንቀቂያ ጭምር በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ተመድበዋል። ተማሪዎች ላይም በተለያየ ደረጃ እርምጃ ተወስዷል። በዚህም በ18 ተማሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል። እነዚህ ተማሪዎች የተቀጡት ለአንድ ዓመት ከትምህርት ገበታ እንዲሰናበቱ በማድረግ ነው። ይሁንና ግን ባጠፉት ጥፋት ልክ ይታይ ቢባል ከዚህ በላይ ቅጣት ሊያርፍባቸው ይችላል። ነገር ግን ወላጆች ለልጆቻቸው ትኩረት አልተሰጠም ማለታቸው እንደ ወላጅ ትክክል ቢሆንም በህግ ዓይን ግን ተቀባይነት የለውም ሲሉ አቶ ሲሳይ ተናግረዋል።
ወላጆች ት/ቤት እንዳይገቡ ለምን ተከለከሉ?
እነዚህ ተማሪዎች መጀመሪያውኑ ጉዳያቸው በማኔጅመንት እየታየ ስለሆነ ወደ ግቢ እንዳትገቡ ከሚል መረጃ ጋር ሥማቸው ውጭ ተለጥፏል። ካሉ በኋላ፤ እነዚህ ስማቸው የተለዩ ተማሪዎች ወላጆች በአካል እርሳቸው ቢሮ ድረስ መጥተው ያነጋገሯቸው መሆኑንም የክፍለ ከተማው ትምህር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሲሳይ ይገልፃሉ።
እንደኃላፊው ገለፃ፤ ይሁንና ጥቂት ወላጆች ወደ ግቢው እንዳይገቡ የተደረገው በቂ ምክንያት አለው። አንዳንድ ወላጆች በየቀኑ ወደ ትምህር ቤቱ እየሔዱ ግጭት ውስጥ የመግባት ዝንባሌ አሳይተዋል። ይህ ደግሞ ትምህርት ሥርዓቱ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው። በተጨማሪ አጠቃላይ ሂደቱን ወደተባባሰ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን በማወቅ እርምጃው ተወስዷል። ይህ እርምጃ የተወሰደውም ለብዙሃኑ ሲባል የተወሰደ መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ወላጆች ወደ ትምህር ቤቱ እየገቡ ሃይለ-ቃል በተናገሩ ቁጥር ስሜታዊ የመሆን አዝማሚያዎች ስለታየባቸው እንዳይገቡ ተደርጓል። ይሁንና አሁንም ቢሆንም በግልጽ መረጃ አላገኘሁም የሚል አካል ካለ ወደ ክፍለ ከተማው ትምህርት ጽህፈት ቤት በመምጣት መነጋገርና መፍትሄ ማምጣት ይቻላል።
የተማሪዎቹ ዕጣ ፋንታ
በአሁኑ ወቅት ከትምህርት ገበታ የተሰናበቱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የመመለስ ዕድል እንደሌላቸው የክፍለ ከተማው እና ትምህር ቤቱ ውሳኔ ያሳያል። አሁን የተወሰደው እርምጃ ተማሪዎቹ በቀጣይ እራሳቸውን አስተካክለው እንዲመጡ ዕድል የሚሰጥና በቀጣይ ሕይወታቸውም መማሪያ እንዲሆናቸው የታሰበ ነው ተብሏል። ከዚህ በዘለለ ግን በአሁኑ ወቅት ወደ ትምህርት ገበታ ይመለሱ ቢባል እንኳን ረጅም የትምህርት ወቅቶችን በትምህርት ገበታ ላይ ባለመገኘታቸው ተማሪዎቹ በቂ እውቀት አይቀስሙም። ይህም በውጤታቸው ሆነ መቅሰም የሚገባቸውን ትክክለኛ እውቀት ሳይዙ ወደ ሌላ ክፍል እንዲሻገሩ ይሆናል። ይህም አሁን መንግስት የጀመረው የትምህርት ጥራትን ከማስጠበቅ አኳያ እክል ይፈጥራል የሚል ስጋት አላቸው።
በተጨማሪም እነዚህ ታዳጊዎች ከጥፋታቸው በደንብ የተማሩበት ጊዜ ባለመሆኑ ድጋሚ ወደ ትምህርት ገበታ ቢመለሱ የትምህርት ቤቱን ሠላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱን የሚያውኩ ይሆናል። ይህ ደግሞ ለትምህር ቤቱ ማሕበረሰብ ብቻ ሳይሆን አጋጣሚውን መጠቀም ለሚፈልጉ አካላት ሁሉ በር የሚከፍት ነው። በመሆኑም በእነዚህ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በ2015 ዓ.ም ከትምህር ገበታ ለአንድ ዓመት ብቻ የተሰናበቱ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቱ ተመልሰው ከጓደኞቻቸው ጋር ትምህርታቸውን የሚቀጥሉበት ዕድል አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
እነዚህ ታዳጊዎች ከስህተታቸው ከተማሩና በወላጆቻቸው እና በትምህር ቤቱ አስፈላጊውን ምክር ከተለገሱ በኋላ በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን በትምህርት ገበታቸው ላይ የመገኘት መብት አላቸው። እንደ ክፍለ ከተማም ሆነ ከተማ አስተዳደር የተያዘው እቅድ አሁናዊ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ላይ ያተኮረ ሥራ በመስራት ላይ ነው ተብሏል። ለአብነትም በ2016 የትምህርት ዘመን የዕድገት ጮራ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ለማዘመን በ41 ሚሊዮን ብር መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ ከወዲሁ የተጀመረ ሲሆን፤ ይህንን የሚያግዝ ባለሃብትም አግኝተናል ብለዋል። በመሆኑም የትምህርት ተቋማት በበለጠ የሚዘምኑበትና ችግሮች የሚቀረፉበት እንጂ ችግር መፍጠሪያ አይሆኑም ሲሉም አሳስበዋል።
እንደ ክፍለ ከተማም ሆነ ከተማ አስተዳደር የተያዘው እቅድ አሁናዊ ችግሮችን መፍታት ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ላይ ያተኮረ ሥራ በመስራት ላይ ነው
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም