በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 በተለምዶ መላጣ ጋራ ተብሎ የሚጠራ ቦታ ላይ ነው። ቦታው የአዲስ አበባን ሰሜናዊ ክፍል ካቀፈው ከየካ ሰንሰለታማ ተራራ መካከል የካ ሚካኤል ቤተክርቲያንን ከፍ ብሎ ይገኛል። እናም የየካ ተራራ ግርጌ ልጆች ከየአቅጣጫው ተሰባስበው አረፍ ከሚሉባቸው ቦታዎች አንዱ ነው።
በተለይ ክረምት አካባቢ ልጆች አጋምና ቀጋን ለቅመው በመላጣ ጋራ ላይ አረፍ ብለው ይቋደሳሉ። ዙሪያውን በአረንጓዴ ዛፎች የተከበበው ይህ ጋራ ለወትሮው ሰላማዊ፤ ነፋሻማና አእምሮን ማሳረፊያ ቦታ ነበር። ህፃናት በሰላም ቦርቀው ያደጉበት፤ አውሬ እንዳይመጣ እንጂ ሰው ይተናኮላቸዋል የማይባልበት አካባቢ ነበር።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንኳን ልጆች ጫካውን አቋርጠው መላጣ ጋራ ላይ ሊደርሱ ይቅርና የአካባቢው ነዋሪዎች ጫካውን ለማቋረጠ ሶሰት አራት መሆን ግድ የሚላቸው ጊዜ ላይ ደርሰዋል። ለብቻ ጫካውን ማቋረጥ ማለት በገዛ ፍቃድ ራስን አሳልፎ ለዘራፊና ለነፍሰ ገዳይ እንደመስጠት እየተቆጠረ የአካባቢው ነዋሪዎች በስጋት ለመኖር ተገድደዋል።
ጫካው ጥቅጥቅ ከማለቱ የተነሳ የፀጥታ ሀይሎችም በህብረት ካልሆነ የማይደፍሩት አካባቢ ከሆነ ሰነባብቷል። የተፈራውም አልቀረም በአንድ ክፉ ቀን ሁለት ግለሰቦች ላይ ድንገተኛ ጥቃት እንደተሰነዘረባቸው ተሰማ።
በማህበር የተደራጁት ዘራፊዎች
መሰለ ጋሻውና አለባቸው እሸቱ ይባላሉ። በወጣትነት እድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ናቸው። በማህበር ተደራጀተው የብረት ስራ ቢጀምሩም ስራው ከድካሙ እኩል ክፍያ የማይገኝበት በየጊዜው ሞቅና ቀዝቀዝ እያለ የፈለጉበት የእድገት ደረጃ አለመድረሳቸው ዘወትር ያስቆጫቸው ነበር። ብዙ ጊዜ ስደት ለመሄድ ሞክረው አልተሳካላቸውም። የሚሰሩትንም ስራ ሳይወዱ ስለሚሰሩ ውጤታማ አላደረጋቸውም። ስለዚህ ምንም ይሁን ምን ብቻ ገንዘብ የሚገኝበት አማራጭ ላይ አተኮሩ፡፡ ይሁነን ብለው መንገድ መርጠው ህልማቸው ጋር ለመድረስ ዝግጅት ጀመሩ።
በርከት ብለው ስለ አሰቡት ጉዳይ መነጋገር ቢቀጥሉም ብዙዎቹ ጓደኞቻቸው በሀሳቡ ባለመስመማታቸው ከሁለቱ ተነጥለዋል። ሁለቱ ወጣቶች በበኩላቸው ወጣትነት ሀይልና ጥበብ የሰጣቸው ሲሆን፤ ፈርጣማነታቸው ተጨምሮበት ለበጎ ነገር ከመጠቀም ይልቅ በአቋራጭ ገንዘብ የሚያገኙበትን አማራጭ ማፈላለጋቸውን ቀጥለዋል። ከስራቸው ጎን ለጎን ጡንቻቸውን ለማፈርጠም ስፖርት መስራትን፤ የተሻለ ተፈሪነት ለማግኘትም ድምፅ የሌለው መሳሪያና ሽጉጥን መታጠቅ ጀመሩ።
ቀለል ያለ እንደ ሞባይል ነጥቆ መሮጥን አይነት ዘረፋዎችን ድፍረት እስኪያገኙ ድረስ የጀመሩት ወጣቶች፤ ጨለማን ተገን አድርገው ጫካው አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን በማፈን ያላቸውን ተረክበው ሊታገሏቸው የሞከሩትን ደግሞ ጉዳት እያደረሱ ለወራት በዝርፊያቸው ቀጠሉ።
እጃቸው ላይ ያለው ገንዘብ ጠርቀምቀም ሲል የተሻለ ቤት ተከራዩ፡፡ የተሻለ ኑሮ መኖር የጀመሩት ወጣቶቹ፤ ከእለት እለት ፍላጎታቸው እየጨመረ በየእለቱ ያገኙትን ከመዝረፍ ወደ ኋላ አይሉም ነበር።
ይህን ተጠናክሮ የቀጠለ የዘረፋ ወንጀል እንዲያስቆምላቸው የህግ አካላትን የተማፀኑት ነዋሪዎችን ጥቆማ ተከትሎ ዘረፋው ተካሂዶበታል የተባለ አካባቢ በተደራጁ የፀጥታ ኃይሎች ተሞላ። በጥንቃቄ ክትትላቸውን የጀመሩት የፀጥታ ኃይሎች በአሁኑ በለስ የቀናቸው ይመስላል።
ልማደኞች ተደብቀው ከዋሉበት ጎሬ ወጥተው አመሻሹ ላይ የተለመደ ቦታቸውን መሽገው ተዘራፊዎችን ይጠባበቃሉ። ጉዳዩን እየፈተሸ ያለው የወንጀል ክትትል ቡድንም በበኩሉ እነዚህን አካባቢውን በዘረፋ ያሸበሩ ልማደኛ ሌቦችን ለመያዝ አድፍጧል።
ድንገት ከዋናው መንገድ ወደ ጫካው አቅጣጫ ሁለት ግለሰቦች በዝግታ እያወሩ ይመጣሉ። የእነዚህን ሰዎች አመጣጥ በአይነ ቁረኛ የሚከታተሉት ዘራፊዎች ምቹ ቦታ ጠብቀው ለመዝረፍ በእጃቸው የያዙትን ሽጉጥና ጩቤ ለማስፈራሪያነት ለመጠቀም አመቻችተው ይይዛሉ።
ሀገር ሰላም ብለው ይሄዱ የነበሩ መንገደኞች ድንገት ከፊትና ከኋላቸው መሳሪያ የያዙ ፈርጣማ ወጣቶች ሲከቧቸው ክው ብለው ይቀራሉ። ወጣቶቹም በፍጥነት ትእዛዝ መስጠት ጀመሩ።
ያላሰቡት የገጠማቸው ግለሰቦች
ተስፋሁን ገብረስላሴ እና ወራሽ ጴጥሮስ ለፍቶ አዳሪ ጎረቤታሞች ናቸው። ያገኙትን ገንዘብ ቆጥበው አነስተኛ ጎጆ መላጣ ጋራ አካባቢ ቀልሰው እየኖሩ ነበር። ታታሪ የግንባታ ባለሙያ የሆኑት ግለሰቦች ቀኑን ሙሉ ሲደክሙ ውለው ወደ ሰፈራቸው ሲያዘግሙ የነበሩት ያገኟትን በኪሳቸው ከተው ለልጆቻቸው ዳቦ ቢጤ በፌስታል አንጠልጥለው ነበር።
ሁልጊዜ በምስጋና የሚኖሩት ጎረቤታሞች ባላቸው ልክ እየኖሩ ያገኙትን ቆጥበው ጥሪት ለማፍራት በቀተዋል። ሶስት ጉልቻ ጥደው ጎጆ መስርተዋል። ልጆቻቸው ገና ህፃናት ቢሆኑም ነጋቸው ያማረ ይሆን ዘንድ ታታሪ አባቶቻቸው ሌት ከቀን ለፍተው ያገኙትን ይዘው ወደ ቤታቸው ይገባሉ።
በስራ ምክንያት ካልሆነ ማምሸትም ሆነ መጠጥ መቀማመስ የማይወዱት ግለሰቦች በእለቱ ከሚሰሩበት ህንፃ የወጡት የያዙትን ስራ ለመጨረስ ጓጉተው ሲታትሩ ቆይተው ለአይን ያዝ ሲያደርግ ነበር። ሳይመሽ ወደ ቤታቸው ለመድረስ ልባቸው ቢሰቀልም ቀኑን ሙሉ ሲለፋ የዋለ ጉልበት ዳገቱን መቋቋም አቅቶት እየለገመ ፍጥነታቸውን ቀንሶባቸዋል።
በዝግታም ቢሆን መንገዱን አጋምሰው ቤታቸው ለመድረስ የሚያቋርጡትን ጫካ ሲጀምሩ ያላሰቡት ዱብዳ ገጠማቸው። በድንገት ከፊትና ከኋላቸው የቆሙትን ወጠምሻ ወጣቶች ሲመለከቱ በድንጋጤ ክው ብለወ ቀሩ። እንኳን ደንግጠውበት በድካም የተሳሰረው ጉልበታቸው ወዴትም አቅጣጫ አላላውስ አላቸው።
የሞት ሞታቸውን በጩኸት እርዳታ ለመጠየቅ ቢሞክሩም ጉሮሮዋቸውን አልፎ የሚሰማ ድምፅ አልወጣ አላቸው። ስለዚህ በዝምታ ወጣቶቹ የሚሏቸውን ማድረግ ጀመሩ።
የመስከረም 29ኙ ዘረፋ
ቀኑ መስከረም 29 ቀን 2014 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ነበር። በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 መላጣ ጋራ ጫካ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተስፋሁን ገብረ ስላሴን እና ወራሽ ጴጥሮስን ሽጉጥ በማውጣት “እንዳትንቀሳቀሱ” የሚል ቀጭን ትእዛዝ ከፊትና ከኋላቸው ከቆሙት ወጣቶች አንደበት ተሰማ። በመቀጠል “እንዳንጎዳችሁ ከፈለጋችሁ የያዛችሁትን በሙሉ ያለምንም ማቅማማት መሬት ላይ አስቀምጡ” ብለው በያዙት ጩቤ እያስፈራሩ ተናገሩ። በድካምና በድንጋጤ የዛሉት ግለሰቦች ለልጆቻቸው የገዙትና ዳቦ መሬት ላይ ቁጭ አድርገው በሚንቀጠቀጥ እጃቸው ከኪሳቸው ውስጥ ከተው ያገኙትን ነገር በሙሉ በደመ ነፍስ መሬት ላይ ይጥሉ ጀመር።
መሬት ላይ ከወደቀው ንብረት መካከል አንደኛው ዘራፊ ወጣት የሞባይል ስልኮቻቸውን እና ጥሬ ገንዘብ በድምሩ 7 ሺ 900 ብር የሚገመት ንብረት በመሰብሰብ “ፊታችሁን ሳታዞሩ ቀጥሉ” በማለት አዘዟቸው። ሰዎቹም ቁልፎቻቸውንና መታወቂያዎቻቸውን ሰብስበው ወደፊት መሄድ ጀመሩ። ያን ጊዜ ተደብቀው የወንጀለኞቹን ተግባር ሲከታተሉ የነበሩ የፀጥታ አካላት በፍጥነት ከበባ በማድረግ ወንጀል አድራጊዎቹን በቁጥጥር ስር አውለዋቸዋል።
ወንጀለኞቹ ከዘረፉት ገንዘብ በተጨማሪ መሰለ ጋሻው ቤት በተደረገ ብርበራ ኢኮልፒ ሽጉጥ ከመሰል 3 ጥይቶችና 1 ካዝና ጋር የተገኘ በመሆኑ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ ማስቀመጥ ወንጀል በተጨማሪ ክስ ቀርቦበታል፡፡ ለጊዜው በኤግዚቢትነት ተይዞ የነበረው የግል ተበዳዮች ንብረት ተመልሶላቸው ወንጀለኞቹ ክስ ተመሰርቶባቸዋል።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ በዘረፋ ተግባር ተሰማርተው አካባቢውን እያሸበሩ ያሉ ዘራፊዎች መኖራቸውን ከሰማበት ቀን አንስቶ አካባቢ እየቀያየረ ወንጀለኞቹን ሲከታተል ቆይቷል። በእለቱም የግል ተበዳዮች ላይ የደረሰውን በሙሉ ከመመልከቱም ባሻገር በእጃቸው ላይና ቤታቸውን በመበርበር የተለያዩ ማስረጃዎችን ለማግኘት ችሏል።
በሰውና በሰነድ ማስረጃ የተጠናከረው የምርመራ ውጤትን ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በማቀረብ ክስ እንዲመሰረትባቸው ያደርጋል።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ መሰለ ጋሻው፣ 2ኛ አለባቸው እሸቱ በተባሉ ተከሳሾች ላይ የእያንዳንዳቸው የተሳትፎ ደረጃ ተጠቅሶ በዐቃቤ ሕግ ሶስት ክሶች የተመሰረተባቸው ሲሆን፤ በክሱ ዝርዝር እንደተገለጸው ተከሳሾች መስከረም 29 ቀን 2014 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 መላጣ ጋራ ጫካ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የግል ተበዳይ ተስፋሁን ገ/ስላሴን እና ወራሽ ጴጥሮስ ላይ ሽጉጥ በማውጣት እንዳትንቀሳቀሱ ብለው በያዙት ጩቤ እያስፈራሩ የሞባይል ስልኮቻቸውን እና ጥሬ ገንዘብ በድምሩ 7 ሺ 900 ብር የሚገመት ንብረት ወስደውባቸዋል፡፡
በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን 1ኛ ተከሳሽ በሆነው መሰለ ጋሻው ቤት በተደረገ ብርበራ ኢኮልፒ ሽጉጥ ከመሰል 3 ጥይቶችና 1 ካዝና ጋር የተገኘ በመሆኑ የፀና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያ ማስቀመጥ ወንጀል በተጨማሪ ክስ ቀርቦበታል፡፡
ክርክሩን በመራው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች፤ የተከሰሱበት ክስ በችሎት ተነቦላቸው ድርጊቱን አልፈፀምንም ያሉ በመሆኑ ዐቃቤ ህግ ማስረጃ በማቅረብ በበቂ ሁኔታ ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን ወንጀል ስለመፈጸማቸው ሲያስረዳ ተከሳሾች በበኩላቸው 3 የመከላከያ ምስክር አቅርበው ቢያሰሙም የዐቃቤ ህግን ምስክሮችንና ማስረጃዎችን ያላስተባበሉ በመሆኑ ተከሳሾች ይከላከሉ በተባሉበት ድንጋጌ ስር የጥፋተኝነት ፍርድ ተላልፎባቸዋል፡፡
ውሳኔ
ፍርድ ቤቱም ጥር 23 ቀን 2015 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቅጣት ማቅለያዎችን በመያዝ ተከሳሾችን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን እያንዳንዳቸው በ12 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ሲወስን 1ኛ ተከሳሽ በተጨማሪ በ5 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2015