አዲስአበባ፦ የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ትንሿ ኢትዮጵያ በምትንፀባረቅበት አዲስ አበባ ከተማ መከበሩ የህዝቦችን በአንድነትና በመከባበር የመኖር እሴት አጉልቶ ለማሳየት ፋይዳው የጎላ እንደሚሆን ተጠቆመ።
የዘንድሮው ከብረበዓል መርሃ ግብር አካል የሆነው አገር አቀፍ ባዛርና ኤግዚቢሽን ትናንት በተከፈተበት ወቅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ መሃመድ ረሺድ እንደገለፁት፤ አዲስ አበባ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መናኸሪያ ብቻም ሳትሆን ከመላ ዓለም የተወጣጡ ዜጎች የሚኖሩባት ከተማ ናት ።
የከተማዋ ህዝብ በአንድነትና በእኩልነት ልዩነቱን አክብሮ በመቻቻል የሚኖር ነው ያሉት አቶ መሀመድ፤ የዘንድሮው የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልም ይህን እሴቱን ይበልጥ አጉልቶ ለማሳየትና ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ በበኩላቸው፤የዘንድሮው በዓልም ትንሿ ኢትዮጵያ በምትንፀባረቅበት በርካታ ብሄር ብሄረሰቦችና ሃይማኖቶች በአንድነትና በእኩልነት ተዋህደው በሚገለፁባት አዲስ አበባ መከበሩ የከተማዋን መሰል እሴቶች ይበልጥ ለማስተዋወቅ ከፍተኛ አቅም ይኖረዋል ብለዋል።
የዘንድሮው በዓል የከተማዋንና የህዝብ እሴቶች ከማስተዋወቅ ባሻገር ቀጣይነቱንም ለማጎልበት የሚኖረው አስተዋፆኦ ከፍተኛ መሆኑን ያመላከቱት ዶክተር ሰለሞን፤ የከተማው ነዋሪ በሰላም የታጀበ የአብሮነትና የመከባበር እሴቱን በማጠናከር እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓሉ መርሃ ግብር አንዱ አካል በሆነው አገር አቀፍ ባዛር ከዘጠኙ ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ከ130 በላይ ኢንተርፕራይዞች ተካፍለዋል።አዲስ አበባ ከተማ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ስታስተናግድ ዘንድሮ ሁለተኛዋ ሲሆን፤ለ13ተኛ ጊዜ የሚከበረው በዓልም «በብዝሃነት የደመቀ ኢትዮጵያዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል ከህዳር 24 እስከ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ይከበራል።
ታምራት ተስፋዬ