የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት እየተሳተፈ ለሚገኘው የሳዑዲ-ኤምሬቶች ጥምር ኃይል የምታደርገውን እገዛ እንድታቋርጥ ኮንግረሱ ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ውድቅ አድርገውታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ኮንግረሱ ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ እንደማይቀበሉት ባስታወቁበት መግለጫቸው ‹‹ ይህ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አስፈላጊ ያልሆነና የእኔን ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ለማዳከም ያለመ ና ዛሬም ሆነ ወደፊት ያለውን የአሜሪካውያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነው›› ብለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤቱ 247 ለ 175፣ ሴኔቱ ደግሞ 54 ለ 46 ያሳለፈው ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ አሜሪካ አስከፊ በሆነው በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ለማስቆም ያስችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ ውሳኔን የመሻር መብታቸውን (Veto Power) ተጠቅመው የሻሩት ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በርካታ አሜሪካውያን ፖለቲከኞችን እንዳሳዘነ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ በተለይ የኮንግረሱ አባላት እጅግ መናደዳቸውንና ማዘናቸውን የአልጀዚራ ዘጋቢዋ ሮዚላንድ ጆርዳን ከዋሽንግተን ዲሲ ባሰራጨችው ዘገባ አመልክታለች፡፡ ‹‹በርካታ የኮንግረሱ አባላት ‹የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር መቋጫ ያላገኘው የየመን ጦርነትና የየመናውያን ስቃይ ፍፃሜ እንዲያገኝ የማድረግ ፍላጎት የለውም› የሚል ሃሳብ እንዳላቸውም ዘጋቢዋ ገልፀለች፡፡
በተወካዮች ምክር ቤት አባልና ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡን ካመነጩት መካከል አንዱ የሆኑት የዴሞክራቲክ ፓርቲው ሮ ካና ‹‹የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጦርነቶች መቋጫ እንዲያገኙ ለማድረግ ቃል ገብቶ ወደ ሥልጣን ከመጣ ፕሬዚዳንት የማይጠበቅና የየመንን ጦርነት ለማስቆም የነበረውን እድል ያበላሸ እርምጃ ነው›› ብለዋል፡፡
በየመን የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ
የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የፕሬዚዳንቱን ውሳኔ አድንቃለች፡፡ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዋር ጋራሽ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ውሳኔው ወቅቱን የጠበቀና ተገቢ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሳዑዲ-ኤምሬቶች ጥምር ኃይልን የመደገፍ አስተሳሰብ አወንታዊ የሆነ እርምጃ ነው›› ብለዋል፡፡
እ.አ.አ በ2015 የየመን የቀድሞ ፕሬዚዳንት አሊ አብዱላህ ሳሌህ ታማኞች ከሐውቲ ታጣቂዎች ጋር አብረው በፕሬዚዳንት አብዱ ራቡ መንሱር አል- ሃዲ ኃይሎች ላይ ጥቃት ጀመሩ፡፡ እ.አ.አ በታህሳሥ ወር 2017 የተገደሉት የቀድሞው የየመን ፕሬዚዳንት የአሊ አብዱላህ ሳሌህ ደጋፊዎችና የሐውቲ ታጣቂዎችም በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የየመንን ሰፊ ግዛት በቁጥጥራቸው ስር አደረጉ፡፡ የአድራቡህ መንሱር ሃዲ መንግሥትም መቀመጫውን ከሰነዓ ወደ ኤደን አዛወረ፡፡ ቀጥሎም የሐውቲ ታጣቂዎች የመንሱር ሃዲን መንግሥት ለመገልበጥ እቅድ አውጥተው በመንቀሳቀስ ወደ ኤደን ሲጠጉ መንሱር ሃዲ ሀገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላም በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው የተለያዩ ሀገራት ጥምር ጦር የመንሱር ሃዲን መንግሥት ወደ መንበሩ ለመመለስ በሐውቲ ታጣቂዎችና በሳሌህ ታማኞች ላይ የአየር ጥቃት መፈፀም ጀመረ፡ ፡ ሳዑዲ መራሹ የአየር ጥቃትም በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት እየጨመረ ሲመጣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጥምር ጦሩን ጥቃት ክፉኛ አወገዘው፡፡
በሳዑዲ አረቢያ የሚመራው ጥምር ጦር በሐውቲ ታጣቂዎች ይዞታዎችና ንብረቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም የሀገሪቱን ዋና ከተማ ሰነዓን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ፍልሚያ በር ማስከፈት እንዳልቻለ ይገለፃል፡፡ በየመን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጀርባ የመካከለኛው ምስራቅን ፖለቲካ በበላይነት ለመቆጣጠር የሚሽቀዳደሙት የሳዑዲ አረቢያና የኢራን
እንዲሁም ወሳኝ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውን ይህን ቀጣና በእጅ አዙር ለመቆጣጠር ምንጊዜም ቢሆን የማይተኙት የምዕራባውያን ሀገራት እጅ እንዳለበት ተደጋግሞ ይገለፃል።
በእርግጥ ሳዑዲ አረቢያ ሀገር ጥለው የተሰደዱትን የመንሱር አል-ሃዲን ታማኞች ደግፋ በጦርነቱ መሳተፏና ሐውቲዎች የሺኣ እስልምና ተከታይ ናቸው መባሉ ሺአዋ ኢራንና ሳዑዲ አረቢያ በየመኑ ጦርነት እጃቸውን ስለማስገባታቸው እንደዋነኛ ማሳያ ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡
ኢራን የቀድሞውን ፕሬዚዳንት አብደላህ ሳሌህን ታማኞችና የሐውቲ ታጣቂዎችን እንደምትረዳ ተደጋግሞ ቢነገርም ሀገሪቱ ግን ይህን መረጃ በተደጋጋሚ ስታጣጥለውና ‹‹የሳዑዲ አረቢያና አጋሮቿ ውንጀላ ነው›› በማለት ስትደመጥ ተስተውላለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፣ ከፍተኛ ጂኦ-ፖለቲካዊ ፋይዳ ያለውን የመካከለኛው ምስራቅ ቀጣናን ለመቆጣጠር ለአፍታ ያህል የማይዘናጉት ምዕራባውያን በበኩላቸው በሳዑዲ አረቢያ ለሚመራው ጥምር ጦር የሎጂስቲክና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በተለይ አሜሪካ ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ኢራንን ለማንበርከክ ያላት ፍላጎት በየመን በየዕለቱ የሚቀጠፈውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ችላ እንዲባል አድርጎታል፡፡
በየመን ለበርካታ ዓመታት ስር ሰደው የቆዩ ችግሮች የሀገሪቱን ቀውስ ከድጡ ወደ ማጡ አድርገውታል፡፡ በየመን ሰፊ ይዞታ እንዳለው የሚነገርለት ዓለም አቀፉ አሸባሪ ቡድን አልቃይዳ የየመናውያንን ሰቆቃ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ካደረገው ቆይቷል፡፡ ራሱን እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድንም በአካባቢው ያለውን ይዞታውን ለማስፋት እንደመሸጋገሪያና መቆያ ከሚጠቀምባቸው የአካባቢው ሀገራት መካከል የመን አንዷ ናት፡፡ የንፁሃንን አንገት መቅላት የየዕለት ተግባሩ የሆነው ይህ አረመኔ ቡድን የአየር ጥቃት ለሚያሰቃያቸው የመናውያን ሌላ የሕልውና አደጋ ሆኖባቸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም፣ ሀገሪቱ በእነዚህ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች፣ በሐውቲዎች እና በመንሱር አል-ሃዲ ታማኞች ቁጥጥር ስር ተከፋፍላ ትገኛለች።
የሀገሪቱ ዋና ከተማ ሰነዓ በሐውቲዎች ቁጥጥር ስር ትገኛለች፡፡
ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በየመን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመሩ ወዲህ ከ15ሺ የሚበልጡ ሰዎች እንደተገደሉና (ከነዚህም መካከል ከ60 በመቶ የሚበልጡት ሰላማዊ ዜጎች እንደሆኑ)ና ከዚህ የሚበልጡ ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ አካላት በየጊዜው ይፋ የሚደረገው የሟቾቹና የቁስለኞቹ ቁጥር የተለያየ ነው፡፡
በተለይ ከፍተኛ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላትንና እ.አ.አ በ2014 በሐውቲ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የወደቀችውን የሁዴይዳ ወደብን ለመያዝ የሚደረገው የተፋፋመ ውጊያ 600 ሺ ከሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ከ120ሺ የሚበልጡትን ለስደት እንደዳረገ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ይፋ ያደረጉት መረጃ ያሳያል፡፡
የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወታደሮች ከሆደይዳ ወደብ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ፡፡ በልዕለ ኃያላኗ አሜሪካ የትጥቅ ድጋፍ የሚደረግለት የሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጥምር ኃይል በየመን ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረ ወዲህ ከ16ሺ በላይ የአየር ጥቃቶችን ፈፅሟል፡፡
በእርስ በእርስ ጦርነት በምትታመሰውና ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መካከል በድህነት የሚወዳደራት የለም በምትባለው የመን እየተካሄደ የሚገኘው የእርስ በእርስ ጦርነት ያስከተለው ረሀብና በሽታ የሀገሪቱን ዜጎች ስቃይና መከራ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎባቸዋል፡፡
በርካታ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና የፖለቲካ ተንታኞች በበኩላቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በየመን ያለውን አስከፊ ቀውስ ችላ ብሎታል በማለት ተደጋጋሚ ወቀሳቸውን አሰምተዋል፡፡ ለዚህም ነው የመገናኛ ብዙኃኑና የፖለቲካ ተንታኞቹ የየመኑን ፖለቲካዊ ቀውስ ‹‹የተረሳው/ የተዘነጋው ጦርነት (The Forgotten War)›› የሚል ስያሜ የሰጡት፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11/2011
በአንተነህ ቸሬ