ባለፉት አራት ዓመታት ኢትዮጵያ እንደ አገር ስር ነቀል የሚባል ለውጥ ውስጥ ገብታለች፡፡ አገሪቱ ከሴራና ከመገፋፋት ፖለቲካ ወጥታ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ካደረገችው ጥረት ባሻገር በኢኮኖሚ ዘርፉም በራሷ መንገድ ተጉዛ በርካታ መሻሻሎች ተመዝግበዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በነበሩ ዓመታት ኢትዮጵያ ስትከተለው የነበረው የኢኮኖሚ ሥርዓት የውጭ ብድርና ዕርዳታን መሠረት ያደረገ ስለነበረ አገሪቱን ከፍተኛ ለሆነ የብድር ዕዳ ጫና ዳርጓታል፡፡ ከገንዘብ ሚኒስቴር በተገኘው መረጃ መሠረትም በለውጡ ማግስት የኢትዮጵያ የውስጥና የውጭ ብድር ጫና 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር ወይም 52 ነጥብ 57 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ ነበር፡፡ ይህ የብድር መጠን ደግሞ አገሪቱ ተጨማሪ ብድሮችን ከአበዳሪ አገራትና ተቋማት እንዳታገኝ ከማድረጉም ባሻገር የተገኘውን ሀብት ሁሉ ለዕዳ ክፍያ እንዲውል አስገድዷል፡፡
በርካታ የልማትና የሥራ ዕድል ጥያቄ ባለባት አገር ውስጥ ለትውልድ የሚተላለፍን ዕዳ እያከማቹ መሄድ በቀጣይ አገሪቱ የማትወጣው አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚከታት መንግሥት በመረዳቱ በአፋጣኝ በዓይነቱ አዲስ የሆነ አገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመተግበር እንደአገር ከተገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ኢትዮጵያን ለማውጣት ተችሏል፡፡
አገር በቀል የኢኮኖሚው ማሻሻያው አገር በቀል ዕሳቤን በመያዝ ዜጎች ያላቸውን ሀብት እንዲያለሙ፤ ኢትዮጵያ ስትወስድ የነበረውን ከፍተኛ ብድር እንድታቆም የሚያስገድድና የውጭ ባለሀብቶችን በስፋት እንዲገቡ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ማሻሻያውም በመቆም ሂደት ላይ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት እንደገና እንዲያንሰራራ ከማድረጉም ባሻገር በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁን የኢኮኖሚ አቅም መፍጠር ያስቻለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በውስጣዊ ችግሮችና ውጫዊ ጫናዎች ከፍተኛ ፈተና ገጥሟት የነበረ ቢሆንም ኢኮኖሚው ዕድገት ከማስመዝገብ ወደ ኋላ አላለም፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ አጣብቂኝ ውስጥ በገባበት ወቅት እንኳን ኢትዮጵያ 6 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ ኢኮኖሚዋን መታደግ ችላለች፡፡ ባለፉት ሁለት አመታት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የነበረው ጦርነት በርካታ ቁሳዊና ሰብአዊ ጉዳት ቢያስከትልም ቀደም ሲል ለፈተና የማይበገር ኢኮኖሚ በመገንባቱ እንደ አገር የከፋ ጉዳት ሳያስከትል ችግሩን ማለፍ ተችሏል፡፡
ይኼው ዕድገት ቀጥሎም በተያዘው በጀት አመት ግማሽ አመትም ኢኮኖሚው በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁሞ የ8 ነጥብ 2 በመቶ እድገት አስመዝግቧል። ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች የሚገኘው የአገር ውስጥ ገቢም ከፍተኛ አፈጻጸም ካስመዘገቡት መካከል ይጠቀሳል። በስድስት ወራት ከታክስና ታክስ ካልሆኑ ምንጮች 222 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ28 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል።
በወጪ ንግድ አፈጻጸም ከዘርፉ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ አፈጻጸሙ ከእቅዱ ጋር ሲነጻጸር 77 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በዓለም ገበያ ያለው የምርቶች ዋጋ ተገማች አለመሆን፤ የሕገ-ወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ መስፋፋት፤ በንግድ ሰንሰለቱ ያሉ ማነቆዎችና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች የወጪ ንግድ ዘርፍ ፈተናዎች ቢሆኑም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳብ ተችሏል። ይህም በተለይ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ሚና አበርክቷል።
ኢኮኖሚው በፈጠረው ምቹ ሁኔታም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በአገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል።
እንደ አጠቃላይ መተግበር የጀመረው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢኮኖሚውን ከውድቀት ከመታደጉም ባሻገር አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የነበረውን ኢኮኖሚ በማነቃቃት የቀጥታ ኢንቨስትመንትን ስበት ጨምሯል፤ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ብዛትና በዓይነት በማበራከት ከውጭ የሚገኘውን ገቢ አሳድጓል፤ የሥራ ዕድልንም አበራክቷል፡፡ ይሄ ደግሞ በዓለም አቀፍ ተቋማትም ጭምር የተመሰከረና በችግር ውስጥም ሆኖ የማይበገር ኢኮኖሚንም መፍጠሩን የሚያረጋግጥ ነው!
አዲስ ዘመን ጥር 25 ቀን 2015