አዲስ አበባ፤- የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት በፓስፖርት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ የብልሹ አሠራር ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል ተጠያቂነት ያለው አሠራር በመዘርጋት ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ አለመሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታወቀ። በቀጣይ የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በአካል ተገኝተው ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስቧል ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአገልግሎቱን የ2015 እና 2016 በጀት ዓመት የፓስፖርት አሰጣጥ ውጤታማነት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ትናንት ባደመጠበት ወቅት የኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር)፣ የኦዲት ሪፖርቱ አገልግሎቱ በፓስፖርት አሰጣጥ ዙሪያ የሚታዩ የብልሹ አሠራር ችግሮችን ለመከላከል የሚያስችል ተጠያቂነት ያለበት አሠራር በመዘርጋት ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ አለመሆኑን ያመላከተ ነው ሲሉ ገልጸዋል ።
ተቋሙ ከሚከታተሉት አካላትም ሆነ ከሕዝቡ በርካታ ቅሬታዎች የሚነሱበት መሆኑን ያመለከቱት የኮሚቴው ሰብሳቢ፣ አሁንም በርካታ አገልግሎት ፈላጊዎች እየተንገላቱ ነው ። እኔ ራሴ በአካል ተገኝቼ የችግሩ ተካፋይ በመሆን ያለውን ነገር አይቼዋለሁ ብለዋል።
ከአሠራር ውጭ በኃላፊዎች ውሳኔ ፓስፖርት የሚወስዱ ዜጎችም መኖራቸው መረጋገጡን ያመለከቱት ሰብሳቢዋ፤ አገልግሎቱ ከምክር ቤቱም ሆነ ከዋና ኦዲተር ለሚሰጡት ምክረ ሀሳቦችና ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ ግልጽነት የጎደለውና ያልተሟላ እንደሆነ አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ ችግሩን ለመፍታት ጊዜ ሳይሰጥ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶቹን ማብቃትና የቅርብ ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል ፣ ዜጎች ቅሬታ የሚያቀርቡበት መንገድም የተለያዩ ቋንቋዎችን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሸሜቦ በበኩላቸው፣ ዛሬም ድረስ አገልግሎት ለማግኘት የሚመጡ በርካታ ዜጎች በፀሐይ ሲንገላቱ እንደሚውሉ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ወቅትም ከፍተኛ ማመናጨቅና ሌሎች ያልተገቡ ተግባራት በአገልግሎቱ ሠራተኞች ሲፈጸሙ ይስተዋላል ብለዋል።
የአገልግሎቱ ሠራተኞች ማንነታቸውን የሚገልጽ ባጅ የማያንጠለጥሉ በመሆናቸው ችግር የገጠመው አካል ቅሬታ ለማቅረብ ሆነ ለመጠቆም የሚያስችለው ዕድል የለውም ያሉት ኃላፊው፤ ባጠቃላይም ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት ግልጽና ሕዝብ የሚያውቀው አሠራር ሊዘረጋ እንደሚገባ አመልክተዋል። የሠራተኞችን ሥነምግባር ለመቆጣጠርም በፍትሕ ሚኒስቴር የፀደቀ የሥነ ምግባር ደንብ ሊያዘጋጅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።
የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢቂላ መዝገቡ ለተሰነዘሩት አስተያየቶች በሰጡት ምላሽ፣ ችግሮቹ አሉ፣ አብዛኛዎቹ እኛ ወደ ኃላፊነት ከመምጣታችን በፊት ጀምሮ የነበሩ ናቸው ። በ2015 ዓ.ም ሦስት መቶ ሀምሳ ሺህ ክፍያ ከፍሎ የሚጠብቅ ዜጎች ነበሩ። በወቅቱ የፓስፖርት እጥረት በማጋጠሙ ሳይዳረስ ቀርቷል ነው ያሉት።
ችግሩን ለመፍታት መመሪያ በማዘጋጀት በጊዜያዊነት ለሕክምና፣ ለትምህርትና ለሌሎች አስቸኳይ ለሆኑ ጉዳዮች ፓስፖርት የሚፈልጉ ዜጎች በኃላፊዎች ፊርማ ፓስፖርት እንዲያገኙ ሲደረግ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግን ሙሉ መረጃውን ላሟላ የፓስፖርት ጠያቂ በሁለት ወር ለእድሳት በአንድ ወር ውስጥ ተደራሽ እያደረግን እንገኛለን ብለዋል።
ወረፋና መንገላታትን በተመለከተ ከግቢ ውጪ ላይ የሚታዩት ፓስፖርት ወሳጆች ሳይሆኑ እነሱን ተከትለው የሚመጡ ቤተሰቦች ናቸው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ቅሬታ ለማቅረብና ሌሎች አገልግሎቶችን ለማግኘት በአሁኑ ወቅት ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር እየተሠራ ያለው ሲስተም የተለያዩ ቋንቋዎችን ማስተናገድ የሚያስችል በመሆኑ ችግሩን ለዘለቄታው መፍታት እንደሚያስችል ጠቁመዋል።
ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱን በተመለከተም፣ እስካሁን እንደዋና መሥሪያ ቤት እራሳቸውን የሚያንቀሳቅሱበት ሁኔታ ነበር። በዚህም በርካታ ችግሮች ነበሩ። አሁን ግን በየሳምንቱ ግምገማ እያደረግን ነው። አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግም አስራ አራት ቅርንጫፎች በዚህ ዓመት እንከፍታለን ብለዋል ።
በወቅቱም የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር በአካል አለመገኘታቸው ተገቢ አለመሆኑን የኮሚቴው ሰብሳቢ የሺመቤት (ዶ/ር) አመልክተው፣ በቀጣይ በአካል ተገኝተው ከኮሚቴው አባላት ለሚነሱ ጥቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ አሳስበዋል ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም