አዲስ አበባ፡– በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በ23 ቀበሌዎች በተመረጡ አካባቢዎች ከሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአሲዳማ አፈር ሕክምና መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በክልሉ አሲዳማ አፈርን በማከም ሥራ በ11 ወረዳዎች በሚገኙ 23 ቀበሌዎች፤ በተመረጡ የሙከራ ቦታዎች 2 ሺህ 004 ሄክታር መሬት ላይ የአሲዳማ አፈር የማከም ሥራ ተሠርቷል፡፡
ከክልሉ የመሬት አቀማመጥና ዝናባማ አካባቢ መሆኑን ተከትሎ የአፈር መሸርሸር ስለሚያጋጥም ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች አንጻር የተጎዱ አካባቢዎች ይዞታ ከፍ ይላል ያሉት አቶ ማስረሻ፣ የክልሉ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ከሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር በላይ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሆነው በአዝርዕትና በቋሚ እህሎች እየለማ ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ኃላፊው እንደገለጹት፤ በክልሉ ከሚለማው አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሄክታር መሬት 863 ሄክታር የሚሆነው በአሲዳማ የተጠቃ ነው፡፡ አሲዳማ አፈር በሚዘሩ አዝርዕቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ እንደመሆኑ በክልሉ ይህን ችግር ለመቀነስ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን መርሐ ግብር ተቀርጾ ወደ ሥራ ተገብቷል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት የሙከራ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየታቸውን በመግለጽ፤ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ኖራን ከተፈጥሮ ማዳበሪያ እና ከሌሎች ነገሮች ጋር በመደባለቅ ከማከም ጋር ተያይዞ ከ238 በላይ ሠርቶ ማሳያዎች በማድረግ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡
አንድ ሄክታር መሬት ለማከም ከ30 እስከ 50 ኩንታል ኖራ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ማስረሻ፤ በክልሉ ኖራ የማግኘት ችግር መኖሩን ተከትሎ ከሌሎች አካባቢዎች በማምጣት የማከም ሥራው እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው እንደተናገሩት፤ የፌደራል መንግሥት ለክልሉ ከመደበው አንድ መቶ ሺህ 500 ኩንታል ኖራ፤ 26 ሺህ ኩንታል የሚሆነውን በማስገባት እስካሁን ከታከመው መሬት አንድ ሺህ 500 ሄክታር መሬት የሚሆነው በዘንድሮ በጀት ዓመት የታከመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሲዳማ አፈርን በማከም አርሶ አደሩ በመኸር እርሻ የተሻለ የስንዴ ምርት ማግኘቱን አመልክተው፤ በቀጣይም የማከም ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው ኖራ ለማፈላለግ በተሠራው ሥራ በሁለት አካባቢዎች የእምነበረድ እና ሌላ ለኖራ የሚሆን ማዕድን መገኘቱን ገልጸው፤ በቀጣይ ኖራ የሚፈጭ ማሽን የመትከል እቅድ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በአካባቢው ኖራ አለመኖሩ እና ለአንድ ሄክታር መሬት በርካታ ኩንታል ኖራ የሚያስፈልግ መሆኑን እንደተግዳሮት ያነሱት ኃላፊው፤ ከሌሎች ቦታዎች በማምጣት ከ800 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማከም አስቸጋሪ ነው፡፡ የተጎዱ መሬቶችን ከማከም ጎን ለጎን ከአሲዳማ መሬት ጋር የሚስማሙ አዝርቶችን የመዝራት እና የቡና ተክልን ማስፋፋት እንደአማራጭ ተይዟል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ የኖራን ጥቅም ተረድቶ ቢሮው የሚያቀርበውን ኖራ በወቅቱ እንዲጠቀም ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም