ዜና ትንታኔ
የቱሪዝም ሚኒስቴር በ2001 ዓ.ም የወጣውን ፖሊሲ ለማሻሻል በሂደት ላይ መሆኑን ይፋ አድርጓል። ረቂቅ ማሻሻያው ለባለድርሻ አካላት ቀርቦ የግብዓት ማሰባሰብ ሂደትን አልፏል። ማሻሻያው በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ፀድቆ ተግባር ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
የዝግጅት ክፍላችንም ቀደም ሲል የነበረው ፖሊሲ ክፍተቶች እና አዲስ የሚሻሻለው ረቂቅ ፖሊሲ የያዛቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው ሲል ባለሙያዎችን አነጋግሯል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የፖሊሲ አናሊስት የዚህዓለም ሲሳይ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በሥራ ላይ የሚገኘው ፖሊሲ ‹‹የፖሊሲ አቅጣጫ›› ክፍተቶች ነበሩበት። ‹‹ቱሪዝምን ተወዳዳሪ እናደርጋለን፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጠራል›› ተብሎ ሲታሰብ ፖሊሲው አሁን ካለው ሀገራዊ ለውጥ ጋር አብሮ መሄድ አለበት። በመሆኑም ከኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች፣ ከልማት ስትራቴጂዎች ጋር መጣጣም ስላለበት እንዲሁም የዘርፉን ተለዋዋጭ ባሕሪይ ታሳቢ በማድረግ መሻሻሉ አስፈላጊ ሆኗል።
‹‹የቱሪዝም ሚኒስቴር በአዋጅ ራሱን ችሎ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤትነት ተቋቁሟል›› የሚሉት የፖሊሲ አናሊስቱ፤ ዘመኑ በሚጠይቀው የአገልግሎት ጥራት፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂና የቱሪዝምን አጠቃላይ መዋቅር ከማስፋትና ከማደራጀት አንፃር የፖሊሲው መሻሻል በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ፖሊሲ ግን ይህንን ፍላጎት የሚያስተናግድ አይደለም ነው ያሉት።
በቱሪዝም ዘርፍ ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ ፍትሕ ማስፈን ያስፈልጋል የሚሉት የዚህዓለም (ዶ/ር)፤ የተቀናጀ የቱሪዝም አጠቃቀምን ሊያረጋግጥ በሚያስችል መልኩ ፖሊሲው መከለስ አለበት ይላሉ። አሁንም ድረስ እንደ ክፍተት የሚነሱ የሆቴሎች ደረጃ አሰጣጥ ሥርዓት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ጉድለት፣ በዘርፉ የሚታየውን የሙያ ሥልጠና እጥረት እንዲሁም የተቀናጀ የቱሪዝም መሠረተ ልማት ለማስፋፋት የሚያስችል ማሕቀፍ በነባሩ የፖሊሲ አፈፃፀም ላይ አልነበረም። አሁን ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ፖሊሲ እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚያስችል የፖሊሲ አቅጣጫዎች የሚያስቀምጥ በመሆኑ ወቅታዊውን ሁኔታ ያገናዘበ ነው ይላሉ።
የዚህዓለም ሲሳይ (ዶ/ር) ለፖሊሲም መከለስ ሌላ ገፊ ምክንያት ያሉት ደግሞ በቅርቡ የተከሰቱ ዓለም አቀፍ ክስተቶች ሌላው ምክንያት መሆናቸውን ያነሳሉ፤ ከዚህ ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝ፣ የአየር ንብረት መዛባት፣ የኢኮኖሚ መዋዠቅ እና የጂኦ ፖለቲካል ለውጦችን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያ መልማት የሚችሉ የተለያዩ የቱሪዝም ሀብቶች ባለቤት መሆኗን የሚናገሩት የዚህ ዓለም (ዶ/ር)፤ ከእነዚህ መካከል በመንግሥት፣ በኅብረተሰብና በግል ባለሀብቶች እንዲሁም በጋራ በቅንጅት መልማት የሚችሉትን በፖሊሲው ለማመላከት መሞከሩን ይጠቅሳሉ። ይህም ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጣቸው የዘርፉ ሀብቶች ተገቢውን የመልማት ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል ሲሉ ነው የገለጹት።
አቶ ይታሰብ ሥዩም የቱሪዝም ማሠልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የቱሪዝም ፖሊሲው በዚህ ወቅት መከለስ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። ምክንያታቸውን ሲገልፁ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱና በዓለም አቀፍ ደረጃ (በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ) ከፍተኛ ለውጦች ተከስተዋል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የኮሮና ወረርሽኝ ሲሆን በቱሪዝም ኢንዱስትሪው ላይ የፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የሚያስችል አቅጣጫ አሁን ሥራ ላይ ባለው ፖሊሲ በሚፈለገው ልክ አልተቀመጠም። በመሆኑም ክስተቱ ካስከተለው ጉዳት በፍጥነት ማገገም አልተቻለም። የሚሻሻለው አዲሱ ፖሊሲ ይህንንና መሰል አቅጣጫ የሚያስቀምጥ መሆኑን ያነሳሉ።
‹‹የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የአደረጃጀት ቅርፅ መቀየሩ ለፖሊሲው መሻሻል አስፈላጊነት ሌላው ምክንያት ነው›› የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ ቀደም የቱሪዝም ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ጋር የሚለጠፍና እራሱን ችሎ ያልተቋቋመ መሆኑን ይናገራሉ። ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ግን ራሱን ችሎ መደራጀቱን ገልጸው፤ ፖሊሲው መሻሻሉና አዳዲስ እይታዎች ማካተቱ ተገቢ መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ ይታሰብ ሌላው የሚያነሱት ምክንያት ቱሪዝም የኢኮኖሚ ምሰሶ ከሆኑ ዋና ዋና ዘርፎች እንደ አንዱ ተቆጥሮ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ማግኘቱን ነው። ቀደም ሲል ቱሪዝም በማኅበራዊ ዘርፍ ላይ የሚካተት ሲሆን አሁን ግን ከግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ሀገሪቱ መሸጋገሯና ቱሪዝም የዚህ አንዱ አካል መሆኑን ይገልፃሉ። ይህ አጋጣሚ የፖሊሲውን መከለስና ዳግም መሻሻል አስገዳጅ ያደርገዋል የሚል እምነትም አላቸው።
ቴክኖሎጂ ዘርፉ ላይ ቀደም ሲል የነበረው ተፅዕኖ እና አሁን ያለው ከፍተኛ ልዩነት አለው የሚሉት አቶ ይታሰብ፤ በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ (የሆስፒታሊቲ) ዘርፉ ተጋላጭነት ከፍተኛ መሆኑን ያነሳሉ። ጎብኚዎች ማረፊያ ቦታ ሲይዙ፣ የጉዞ እቅድ ሲነድፉና ቴክኖሎጂን መጠቀማቸው፤ የክፍያ ሥርዓቱ በተመሳሳይ ከዘርፉ ጋር መያያዙ፤ ለጉብኝት ቨርቹዋል ሪያሊቲ እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ መዋላቸው አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዩ መሆኑን ያነሳሉ። በዚህ ምክንያት ፖሊሲው ይህንን ታሳቢ አድርጎ ዳግም መከለሱ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማሉ።
‹‹የጎብኚዎች ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል›› የሚሉት አቶ ይታሰብ፤ በተለይ የደኅንነት፣ የአመጋገብ እንዲሁም ሁሉን አቀፍ ምቾትና ጥራትን የማግኘት ቅድመ ሁኔታ እንደሚታይ ያስረዳሉ። በመሆኑም በፖሊሲው ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል አቅም እንድትገነባና ለዘርፉ ትኩረት እንድትሰጥ የሚያስችል አቅጣጫ እንዲኖራት ይረዳል ይላሉ።
በተጨማሪ በቱሪዝም ፕሮሞሽን እንዲሁም የሠለጠነ የሰው ኃይል ዙሪያም አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት የፖሊሲው መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የቱሪዝም ዘርፍ በኢትዮጵያ በመካከለኛ ግዜ ዕቅድ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ እንዲሁም ለኢንቨስትመንትና ለውጪ ንግድ አስተዋፅዖ እንዲያደርግ ከመጠበቁም በላይ የሥራ እድል በስፋት እንዲፈጥር ይጠበቃል።
ሁለቱም የዘርፉ ባለሙያዎች ለቱሪዝም ፈርጀ ብዙ ዕድገት የፖሊሲው በዚህ ወቅት መሻሻል አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2017 ዓ.ም