ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርን ከስልጣን ያስወገደው የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ስልጣኑን ለህዝብ እንዲያስረክብ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች እየበረቱበት መሆኑን አልጀዚራ ገለጸ። ግለሰቦች፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሙያ ማህበራት ወታደራዊ ኃይሉ ስልጣኑን ለህዝብ ያስረክብ በሚል አሁንም ተቃውሟቸውን እየገለጹ ሲሆን የአፍሪካ ህብረትና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራትም ይህንኑ ሀሳብ በመደገፍ ግፊት እያደረጉ ይገኛሉ።
በነዳጅ፣ በዳቦና በሸቀጣ ሸቀጥ የዋጋ ንረት ምክንያት በካርቱም የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ባለፉት ተከታታይ ወራት በመላ ሀገሪቱ እየተጠናከረ መጥቶ ለፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ከስልጣን መወገድ ምክንያት ሆኗል። ይሁንና በህዝብ ተቃውሞ በተንገጫገጨው የአልበሽር ወንበር ላይ በስተመጨረሻ መጥቶ ቁጭ ያለው ወታደራዊ ኃይል ትናንት ሥርዓቱን ለማስቀጠል ከአልበሽር ጎን በመቆም ሲገድል የነበረና ዛሬም ያንኑ ለማስቀጠል የሚፈልግ ነው በሚል ውስጣዊና ውጫዊ ተቃውሞ ገጥሞታል።
የሱዳን የሙያ ማህበር /ኤስ ፒ ኤ/ አባል ጣሐ ኦስማን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት የሱዳን ህዝብ የአልበሽርን አገዛዝ በመቃወም ለወራት ተቃውሞ አድርጓል። ብዙ መስዋዕትነት ከፍሎም ሀገሪቱን ወደ ሌላ ምዕራፍ ለማሸጋገር ጫፍ ላይ ሲደርስ ወታደሩ መፈንቅለ መንግሥት አድርጎ ስልጣኑን ይዟል። በመሆኑም ሲደረግ የነበረው ህዝባዊ ተቋውሞ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ተቀልብሶ ህዝቡ የታገለለት ዓላማ ግቡን እንዳይመታ ተደርጓል። የትግሉ ቁልፍ ዓለማ ሲቪል የመንግሥት ስርዓት ማስፈን በመሆኑ ይህን ለማድረግ ትግላችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
የአፍሪካ ህብረት በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ለያዙት ወታደራዊ ኃይሎች ባስተላለፈው ጠንከር ያለ መልዕክት በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ስልጣናቸውን ለህዝብ እንዲያስረክቡ አሳስቧል። ይህ ካልሆን ግን ከሱዳን ጋር የሚኖረው ማንኛውም አይነት ግንኙነት እንደሚቋረጥና ሀገሪቱንም ከአባልነት እንደሚያግዳት አሳስቧል።
የህብረቱ የሰላምና ጸጥታ መማክርት እንደገለጸው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ ህዝብ ከታገለለት ዓላማ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ሱዳን በአጭር ጊዜ ውስጥ ግልጽ፣ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ መዘጋጀት እንዳለባትም ገልጧል። ይሁንና አሁን ስልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ኃይል የቀጠናውን ሰላም ከሚያደፈርሱ እንቅስቃሴዎች እንዲታቀብና ለህዝቡ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ አስጠንቅቋል።
የጀርመን ቻስለር አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው የሱዳን ወታደራዊ ኃይል የተቆጣጠረውን የሀገሪቱ ላዕላዊ ስልጣን ከእጁ ለማውጣት በህዝባዊ አስተዳደር እንዲተካ ከሚታገሉ ተቃዋሚዎች ጎን እንደሚቆሙ አሳውቀዋል። ሜርክል በተባበሩት መንግሥታት የስደተኛ ኤጀንሲ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር በሱዳን እና ሊቢያ የሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዜጎችን ለስደት እና ለእንግልት ሊዳርጋቸው እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።
የሱዳን ወታደራዊ ኃይል የፈጸመውን ህገ ወጥ ድርጊት በግንባር ቀደምትነት እየተቃወመ ያለው የሙያ ማህበር አመራሩ / ኤስ ፒ ኤ/ ደጋፊዎቹ በካርቱም ከፍተኛ የጦር አመራር ቢሮዎች አካባቢ እየተገኙ ተቃውሟቸውን እንዲገፉበት እያበረታታ ይገኛል። ተቃዋሚዎች አንድ ላይ በመሰባሰብ በወታደራዊ ተቋማት መግቢያና መውጫ ባሉ ጎዳናዎች በመቀመጥና መንገድ በመዝጋት ባለፈው ሳምንት ሲያደርጉ ከነበረው ተቃውሞ ጠንከር ያለ ጫና እንዲፈጥሩና እንዳይበታተኑም እያሳሰበ ነው። ህብረተሰቡም በማህበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሞውን በተጠናከረ መልክ ለማስቀጠል በሚያስችሉ ስልቶች ላይ እየተነጋገረ ነው።
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠሩት ፕሬዚዳንት ኦመር ሐሰን አልበሽር ከሶስት አስርት ዓመታት የስልጣን ቆይታ በኋላ እርሳቸውም በመፈንቅለ መንግሥት ከስልጣን ቢወርዱም ሱዳን አሁንም ከወታደራዊ አገዛዝ ሥርዓት አልተላቀቀችም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 10/2011
ኢያሱ መሰለ