ብዙ ሰዎች እርር ድብን ብለን እናውቅ ይሆናል። በቅናት! ዛሬ እኔ እና እናንተ ስለ ቅናት ልናወጋ፣ በቅናት ያረርንባቸውን ጊዜያቶች በድጋሚ እንድናጤን የሚያደርገንን ታሪክ ከፍትህ ሚኒስቴር ድረገፅ አግኝቻለሁ። መቼም ቀንቼ አላውቅም አትሉኝም። ቅናት መጠኑ ይብዛም ይነስም የሁላችንንም ልብ ያንኳኳል። ቅናት እና እሳት ቤት አይዘሉም። እርግጥ ነው፤ ቅናት ውስጣችን አስደሳች ስሜት የሚፈጥር አለመሆኑን እናውቃለን። ለመሆኑ ቅናት ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ትንሽ ስለቅናት ግንዛቤ ይሰጠናል ብዬ አሰብኩ።
ቅናት ማለት በተቃራኒ ፆታ ግንኙነት ውስጥ እያለን በተለያዩ ምክንያቶች በውስጣችን ሊፈጠር የሚችል፣ የምንወደውን ሰው ከማጣት ጋር የተያያዘ የስጋት እና ሽብር ስሜት ነው። ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ይሄ የሽብር ስሜት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ይችላል። በተጨማሪም ቅናት ያለንን ግንኙነት ሊጠቅምም ሊጎዳም እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልፃሉ። ቅናት አሉታዊም አወንታዊም ሊሆን ይችላል።
ቅናትን አሉታዊ የምንልበት ዋናው ምክንያት በዓለም ላይ ከተፈፀሙ የትዳር ጓደኛ ግድያ መንስኤዎች መካከል ቅናት ፊታውራሪ ሆኖ በመምራት ላይ ስለሚገኝ ነው። ይሄ ደግሞ ቅናት ልክ የማይኖረው ከሆነ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ያሳያል።
የቅናት ስሜት በሚፈጠርበት ወቅት ስሜታችንን ለመግለፅ ቃላትን ሳይሆን ጉልበትን መጠቀም ስንጀምር፤ በግልፅነት ከመወያየት ይልቅ ቅናት እንዲያድርብን አደረግን የምንለው ሰው ላይ ለዱላ ስንጋበዝ፤ የትዳር አጋርህ/ሽ፣ ጓደኛህ/ሽ ካንተ/ካንቺ ጋር በሌለ/ች ሰዓት ጊዜህን/ሽ ‹‹ምን እያደረገ/ች ይሆን?›› በማለት ቀኑን ሙሉ የምንብሰለሰል ከሆነ፤ አልፎ ተርፎም ቀኑን ብቻ ሳይሆን ሌሊትም ኮርኒስ እየቆጠርን ነገር የምንበላ ከሆነ ችግር አለ ማለት ነው።
የቅናት ስሜት ከፍቅር የመነጨ ሳይሆን እምነት ከማጣት የመጣ ሲሆን፤ የትዳር አጋርህ/ሽ ውሎውን/ ዋን ለመናገር ወይም አንተ/አንቺ በሌለህበት/ሽበት ሰዓት የተፈጠሩ ነገሮችን ለመናገር የምትሳቀቅ/ቂ ከሆነ፤ በዚህ በመዘዘኛ ቅናት ምክንያት ለምግብ ያለን ፍላጎት ከቀነሰ፤ ጭንቀት ውስጥ ከገባን፤ የልብ ምታችን በተደጋጋሚ የሚጨምር ከሆነ፣ ከልክ በላይ የሚያልበን እንዲሁም ቶሎ የሚደክመን ከሆነ፤ በመጨረሻም ቅናት ከፍቅረኛችሁ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ላይ ክፍተት እየፈጠረ ከመጣ ችግር አለ ማለት ነው።
ከላይ ባነሳነው መነሻ መሰረት የፍቅር ጓደኛዬ ጋር የተለየ ግንኙነት አለህ ብሎ የሰው ነፍስን የቀጠፈውን አስር አለቃ ታሪክም በአሉታዊ ቅናት የተጋለበ ነው አያስብል ይሆን? ነገሩ እንዲህ ነው……
ህግን የጣሰው ህግ አስከባሪ
አስር አለቃ እስራኤል ክፍሌ ሰው አክባሪ ትሁት ነው። በስራው ታታሪ ከአፉ ክፉ ቃል የሚወጣ የማይመስል አይነት ሰው ነው። በዝምታና በእርጋታ ሲመላለስ ለተመለከተው አይደለም ሰው ሰንዝሮ ሊመታ ለመገላመጥ እንኳን አቅም ያለው አይመስለም ነበር።
በአንድ አጋጣሚ ከአንዲት ቆንጆ ጋር ይተዋወቃሉ። ምን ተናግሮ ጓደኛው እንዳደረጋት የብዙ ሰዎች ጥያቄ ነው። በቃ ዝም ነው። የእሷ ቁንጅናን የተመለከተ በሙሉ የሱ የፍቅር ጓደኛ ስለመሆኗ ይጠራጠራል። ይህ ቀረሽ የማትባል ቆንጆ ናት።
የፍቅር ጓደኛው ከልቧ ብታፈቅረውም እሷን የማጣት ስጋት ልቡን የሚያስጨንቀው አፍቃሪ በውሃ ቀጠነ ይጣላታል። ያ ትሁት ሰው በፍቅረኛው ሲመጡበት ፍጹም አውሬ ይሆናል። ይሄን ማንነቱን የተረዱ የእሷ ጓደኞች ቀስ በቀስ ይሸሿት ጀመር።
በምንም ሁኔታ እውነተኛ ፍቅሯን ልታሳየው እንደምትችል ግራ የሚገባት ፍቅረኛው ዘወትር ጭቅጭቁ እየሰለቻት ይመጣል። ብትመክረው ብታስመክረው አላቆም ያለው ቅናት ከፍቅር ይልቅ ፍርሃትን እየጫረባት ሲሄድ ያላትን ግንኙነት ለማቆም ትወስናለች።
ውሳኔዋን ሳታሳውቀው በሰበብ አስባቡ ሸሽት ማለት ትጀምራለች። የእሷ እለት በእለት ከሱ በሰበብ አስባቡ መራቅ፤ ይበልጥ በቁጣ ያነደደው አስር አለቃ መግቢያ መውጫዋን ይከታተል ጀመር። በአጋጣሚ አንድ አብሮ አደግ ጓደኛዋ ከተወለደችበት አካባቢ ይመጣና እሷና ወንድሞቿ የሚኖሩበት ቤት ያርፋል።
ያ ልጅም ስራ ስላልነበረው ስትወጣ ይሸኛታል፤ ስትመጣ ደግሞ ይቀበላት ጀመር። ያንን የተመለከተው ፍቅረኛ ከእኔ የሸሸችው ከአዲስ ሰው ጋር ሆና ነው በማለት ልጁን የሚያጠፋበትን አጋጣሚ ይጠባበቅ ጀመር።
ወጣቱ
ወጣት ኤርሚያስ አይቼው ለእናት ለአባቱ ብቸኛ ልጅ ነው። ይህ የብቻ ልጅ በብዙ እንክብካቤ ያደገ ከመሆኑም በላይ በትምህርቱ ከፍ ያለ ውጤት እንዲያመጣ ባላቸው አቅም ያላቸውን በሙሉ ሲያደርጉለት ኖረዋል። የአይን ማረፊያ ልጃቸውም በትምህርቱ ጎበዝ በመሆን ልፋታቸው በከንቱ እንዳይቀር የበኩሉን ጥረት አድርጓል።
በትምህርቱ ውጤታማ የሆነው ልጅ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በከፍተኛ ውጤት ተመርቋል። በትምህርቱ ውጤታማ ቢሆንም ስራ ሊያገኝ ባለመቻሉ አዲስ አበባ የሚኖሩ የጎረቤት ልጆች ጋር ተጠግቶ ስራ ለመፈለግ በማሰብ ከተወለደባት ቀዬ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል።
ሰንቅ አስቋጥሮ ፤ የእናቱን መቀነት አስፈትቶ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ወጣት በፈለገው ፍጥነት ስራ አለማግኘቱ ተስፋ አስቆርጦታል። ስለዚህም የአስር አለቃው ፍቅረኛ ከጎኑ ባለመለየት ልታፅናናው ትሞክራለች።
ለአንድ አመት ስራ ፈልጎ አለማግኘቱ ያሳሰበው ወጣት እዚህ ስራ ከምፈታ ቢያንስ ወላጆቼን በስራ ላግዛቸው በማለት ገበሬ ቤተሰቦቹን በስራ ሊረዳ ለጉዞ የሚሆኑትን እቃዎች ለመግዛት አዲስ አበባ ጨርቆስ ቤተክርስቲያን አካባቢ ያለው ገበያ ጋር ከአብሮ አደጉ የአስር አለቃው ፍቅረኛ ጋር ገበያ ይወጣል።
ያኔ ቀድሞም ያልወደደው አስር አለቃ ጭራሽ ከፍቅረኛው ጋር ገበያ ሲመለከተው ወደ ቤቱ ተመልሶ የሽንኩርት ቢላዋ ይዞ ይመጣል። ሀገር ሰላም ብሎ ከጓደኞቹ ባገኘው ሳንቲም ለእናት ለአባቱ ስጦታ የሚሆን ጨርቅ ገዝቶ በፌስታል የያዘው ወጣት ከኋላው በቢላዋ ይወጋዋል። ወጣቱም ምን እንደሆነ ባላወቀው ምክንያት መሬት ላይ ተዝለፍልፎ ይወድቃል።
ፍቅርና ቅናት መካከል የወደቀች ነፍስ
ቆንጆ ወጣት ናት። መልከ ቀና፤ መልክ ብቻ ሳይሆን ፀባይ ከውበት የታደለች የሚሏት አይነት ናት። 10 አለቃ እስራኤልን እንዳየችው ነበር የወደደችው። መስፈርቷ ፍቅርና ፍቅር ብቻ በመሆኑ የተነሳ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነበር፤ የፍቅር ጥያቄውን የተቀበለችው። ኑሮን በመማርና በመስራት ለማሸነፍ የምትታትረው ይች ወጣት አመለ ቀና ፍቅረኛ በማግኘቷ ደስታዋ ወሰን አልነበረውም።
በፍቅር ወራትን ከቆዩ በኋላ የፍቅረኛዋ ባህሪ እየተቀየረ መጣ። የት ወጣሽ የት ገባሽ ከማን ጋር ነሽ በሚል አላስገባ አላስወጣ ይላት ጀመር። ጠዋት ማታ ጭቅጭቅ ብቻ የሆነባት ወጣት የተመኘችውን አይነት ፍቅር ለወራትም በሰላም የሄደውን ግንኙነት ለማቆየት የቻለችውን ሁሉ ታደርግ ጀመር።
ፍቅሯን ያሳይልኛል ያለችውን ነገር በሙሉ የምትሞክረው ይች ወጣት፤ ፍቅረኛዋ ይህን የቅናት አመሉን በልክ ከማድረግ ይልቅ እየባሰበት ከአይኑ ሰር በጠፋች ቁጥር ንጭንጭና ቁጣ እያስከተለ ፍቅሯን ወደ ሲኦልነት ይቀይረው ጀመር።
አሁን ደግሞ ይባስ ብሎ ከሷ ጋር ያያቸውን ሰዎች እገላለሁ በማለት ሲጋበዝ ቆይቶ በዚህች የተረገመች ቀን በእንግድነት እርሷ ጋር ለማረፍ የመጣውን አብሮ አደግ የቀየዋን ልጅ በቢላ በመውጋት መሬት ላይ ጣለው። ያን ጊዜ ጭራሽ ይሆናል ብላ የላሰበችው ነገር ሲፈጠር በጩኸት አካባቢውን አናጋችው። በአካባቢው የነበሩትም የፀጥታ አካላት አስር አለቃውን ከነቢላዋው ይዘው ወደ ህግ ወሰዱት።
የፖሊስ መርመራ
10 አለቃ እስራኤል ክፍሌ ከሴት ጓደኛዬ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ኤርሚያስ አይቸውን ከጀርባው መውጋቱን የተመለከተው ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ ጥላ ስር ያቆየዋል። ተጎጂውንም ሆስፒታል በማድረስ ምርመራውን ያጠናከረ ሲሆን፤ ተጎጂው ከሁለት ሳምንታት በኋላ ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል። በዚህም የተነሳ ፖሊስ የሰውና የሰነድ ማስረጃን በማቅረብ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርትበት ያደርጋል።
የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 10 አለቃ እስራኤል ክፍሌ የተባለው ተከሳሽ ግንቦት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ጨርቆስ ቤተ-ክርስቲያን ፊት ለፊት ሟች ኤርሚያስ አይቸውን ከሴት ጓደኛዬ ጋር ግንኙነት አለህ በሚል ተነስቶ የነበረውን ጸብ ምክንያት አድርጎ ቂም በመያዝ በሽንኩርት መክተፊያ ቢላዋ ጀርባውን ወግቶታል። ኤርሚያስ አይቸውም በመወጋቱ ምክንያት ሰኔ 14 ቀን 2012 ዓ.ም ሕይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶበታል።
ተከሳሹ የተከሰሰበት ክስ በችሎት ተነቦለት ድርጊቱን አልፈፀምኩም ያለ ሲሆን፤ አቃቤ ህግም ተከሳሹ ክዶ የተከራከረ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሚያስረዱ የህግ ምስክሮች ስላሉ ይሰሙልኝ በማለት 5 የሰው ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቷል። የዐቃቤ ህግ ምስክሮችና ማስረጃዎችም በተከሳሹ ላይ በክሱ መሰረት ያስረዱ በመሆኑ የመከላከያ ማስረጃ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤቱ ቀጠሮ ቢሰጠውም የመከላከያ ማስረጃ አቅርቦ ማሰማት ባለመቻሉ የመከላከል መብቱ ታልፎ ተከሳሹ ይከላከል በተባለበት ድንጋጌ ስር በጥፋተኝነት ተፈርዶበታል።
ውሳኔ
ጉዳዩን የተመለከተውም የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎትም ታኅሣሥ 24 ቀን 2015 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት በተከሳሹ ላይ በደረጃ 1 እርከን 38 ስር መነሻ ቅጣት በመያዝ፣ ተከሳሹ የወንጀል ሪከርድ የሌለበትና ሀገሩን በወታደርነት በማገልገሉ 2 የቅጣት ማቅለያዎች ተይዘውለት በእርከን 36 ስር በማሳረፍ ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በተከሳሹ ላይ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 2015 ዓ.ም