የግድያው ሚስጥር ፍቅር ወይስ ጥላቻ?

የፆታዊ ፍቅር አተያይ አንዱ ከሌላው የሚለያይ ቢሆንም፤ አንዳንድ ሰዎች ግን ፍቅርን ቃላትም ሆነ ጽሑፍ አይገልጸውም ሲሉ ረቂቅነቱን ለማሳየት ይሞክራሉ። በውስጥ ስሜት የሚገለጽ ነው ይላሉ። አንዳንዱ ፍቅሩን በውስጡ ይዞ ለሚወደውም ሰው ሳይነግር፣ የቅርቤ ናቸው ለሚላቸው ሰዎች እንኳን ስሜቱን ሳያካፍል ለብቻው ይብሰከሰካል። በፍቅር የተነሳ የሚያለቅሱ፣ የሚያዝኑ፣ እስከ መታመም ደረጃ ይደርሳሉ። ሕመማቸውም ፀንቶባቸው የአእምሮ ታማሚ የሚሆኑም ይኖራሉ።

ፍቅር ከባድ የሆነ ስሜት ያለው፤ በስቃይ፤ በስብራት፤ በደስታና ሀዘን ይገለጻል። በሰዎች ዘንድ ጠንካራና ጀግና ነው ተብሎ የሚነገርለትን ሰው እንኳን የማንበርከክ አቅም አለው። ፍቅር በብዙዎች ላይ ኃያልነቱን የሚያሳይ እንደሆነ ቢታወቅም፤ ስሜታቸውን ግልጽ አድርገው ላፈቀሩት ሰው ፍቅራቸውን በመግለጽ እፎይታ ለማግኘት የሚሞክሩም አይጠፉም።

በፍቅር ውስጥ ስቃዩንም የሚያጣጥሙት አሉ። ከብዙ ስቃይ በኋላ የሚገኘው ፍቅር ጣዕም አለው የሚሉ አይጠፉም። በተቃራኒውም ፍቅርን በማጣጣል አሳንሰው ለማየት የሚሞክሩም አሉ። የተለያዩ ሰዎች ለፍቅር የተለያየ ትርጉም እና ድምዳሜ የሚሰጡት ለዚህም ነው። እዚህ ላይ ፍቅር መስጠት እንጂ መቀበል እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል። ሆኖ መገኘት እንጂ በማስመሰል ለራስ ትልቅ ግምት በመስጠት የሚገለጽ መሆንም የለበትም።

ፍቅር አንዱ ለሌላው ማሰብን እንጂ ሞትና ስቃይ መመኘት፣ ለመግደል መነሳሳት መሆን የለበትም። ፍቅር ደስታን በሚሰጥ ዓለም ውስጥ ተያይዞ መስመጥ እንጂ መለያየትን አይወክልም። አንዱ ለሌላው ደስታ መጨነቅ ማበሳጨት አይደለም። በታላቁ መጽሐፍ ላይ እንደተገለፀው፤ ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም። አይመካም፤ አይታበይም። የማይገባውን… በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ነሐስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጽናጽል ሆኜአለሁ በሚልም በመጽሐፉ ሰፍሯል። በዚህ መልኩ የተሞካሸው ፍቅር ለምን ባልተገባ መንገድ ይገለፃል? የሚል ጥያቄ ይፈጥራል።

በፍቅር ሰበብ አንዱ በሌላው ላይ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ የአካልና የሞት ጉዳት ሲያስከትል ይስተዋላል። ስለፍቅር ጉዳይ ለጽሑፌ መነሻ የሆነኝ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ መዘገብ ላይ የሰፈረው መረጃ ነው።

ለዛሬ ያቀረብንላችሁ ተናጋሪ ዶሴ ‹‹ከእኔ ጋር በፍቅር ጓደኝነት ለመቀጠል ፈቃደኛ አልሆንሽም›› በሚል አስገድዶ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት በመፈጸም ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረግ በአንዲት ሴት ላይ ተደራራቢ በደል ስለፈፀመ ግለሰብ ታሪክ ነው። ታሪኩ እንደሚከተለው ነው።

አስጨናቂው የፍቅር ጥያቄ

ቁመቱ አጠር፣ ደልደል ያለ ሰውነት ያለው ወጣት ነው። ተክለ ሰውነቱና ገጽታው በአጠቃላይ ዓይነ ግቡ የሚባል ዓይነት ሰው ነው። ፍቅረኛ ቢሆን የሚጠላ ዓይነት ወንድ አይደለም። ከታሪኩ መረዳት እንደሚቻለው የፍቅር ትርጉም የሚገባው ሰው አይደለም። ፍቅርም ይዞት አያውቅም። ከእለታት አንድ ቀን በጠዋት ወደ ሥራ ጣደፍ ጣደፍ እያለ በመሄድ ላይ ሳለ ነበር የቀይ ዳማ ለግላጋ ወጣት ከፊት ለፊቱ የተመለከተው።

እንዳያት ልቡ ደነገጠ። ወጣቷ ታምራለች፤ የሆነ ተአምራዊ ውበት ያላት ሴት ሆና ታየችው። ዓይኑን ከሷ ላይ መንቀል ተሰኖት አፉን እንደከፈተ አጠገቡ ስትደርስ በዓይኑ ተቀብሏት አፉን ሳይዘጋ በዓይኑ ሸኛት። ልክ ከዓይኑ ስትሰወር ከገባበት የቁም ቅዠት ባነነ። ያቺ ለአፍታ አይቷት ያፈዘዘችውን ወጣት ሙሉ ቀን ሲያስባት ከአእምሮው ውስጥም ሳትወጣ ቀኑን ዋለ።

ከሥራ ሲመለስ፤ ጠዋት ላይ ወጣትዋን ያያት ቦታ ቆሞ እስከ ምሽት ጠበቃት። ተስፋ ቢያደርግም አላገኛትም። በነገታው ጠዋት ሥራ አልነበረውም። በልቡ ውስጥ የቀረችውን ወጣት ለማግኘት ብሎ በተለመደው ቦታ ሄደ። እንደ ሞኝ በመንገዱ ላይ ቆሞ አመሸ። በዚህ ሁኔታ ሳምንቱን ሙሉ፤ ድንገት ያደነዘዘችውን ወብ ፊት ያላትን ልጅ ሊያገኛት ቀርቶ ሊያያት አልቻለም።

ከቀናት ጥበቃ በኋላ ተስፋ ቆርጦ ራሱን አረጋግቶ ሥራውን መሥራት በጀመረ በሳምንቱ ልጅቷን ድጋሚ በድንገት አያት። ዓይኑን ማመን ያቃተው ወጣት ያን ዕድል አላሳለፈም። ተከትሏት መኖሪያዋ ድረስ በመሄድ የት እንደምትኖር አረጋገጠ። በልቡ የተመኛትን ለቀናት ዓይኑ ላይ ተስላ ሌላ ምንም ነገር እንዳይመለከት የከለለችውን ወጣት መኖሪያ በማወቁ ግዳይ እንደጣለ ጀግና ዓይነት ስሜት ተሰማው። ልቡም በኩራት ተሞላ። ደስ አለው።

መኖሪያ ቤቷን ካወቀ በኋላ መመላለሱን ተያያዘው። ፍቅረኛዬ ካልሆንሽ ብሎ መውጫ መግቢያ አሳጣት። የፍቅር ጥያቄ አይሉት፣ ውትወታ ትንፋሽ አሳጣት። ተወዳጇ በበኩሏ ከአፍቃሪ ነኝ ባዩ ለመገላገል መንገድ ቀየረች። መውጫ መግቢያ ሰዓቷንም እየለዋወጠች አማራጮችን በሙሉ ብትሞክርም ወጣቱ ከቤቷ ደጃፍ ዞር ሊል አልቻለም። ማስጨነቁን ቀጠለ።

በቀላሉ በራሷ ልትወጣው አልቻለችም። ነገሩ ጠንከር ብሎ ግራ ሲገባት ለወላጆቿ ተናግራ ቢገስፁትም ቢያስፈራሩትም አሻፈርኝ አለ። “ወደድሽም ጠላሽም የኔ ነሽ ” በማለት መዛትና ማስፈራራቱን ቀጠለ።

ወጣትዋ የፍቅር ጥያቄውን ባለመቀበሏ የደረሰባት አሰቃቂ ድርጊት

የአሥራ ሰባት ዓመቷ ራህመት መሐመድ ተምራ ከፍተኛ ቦታ የመድረስ ህልም ያላት ልጅ ነበረች። በትምህርቷ በጣም ጎበዝ፣ በወላጆቿና በመምህራኖቿ የተወደደች ነበረች። የአሥራ አንደኛ ክፍል ተማሪ ስትሆን፣ ከትምህርቷ ውጭ ያለውን ሰዓት ቤተሰቧን በማገዝ በመልካም ሥነ ምግባር የምትመራ ጠንቃቃ ተማሪ ናት።

ይህች ሁሉን አሟልቶ የሰጣት ይህ ቀረሽ የማትባል ወጣት ከእለታት በአንዱ ቀን አብዱ ኪያር ዩሱፍ የተባለ ወጣት ዓይን ውስጥ ገባች። ራህመት የፍቅር ግንኙነት ሃሳብ ያልነበራት ሙሉ ትኩረቷ ትምህርቷ ላይ ብቻ የሆነች ሴት ነበረች። እያንዳንዷን ሰዓት ወጤታማ የሚያደርጋትን ተግባር በማከናወን ታሳልፍ ነበር። እንኳን የፍቅር ጓደኛ ስለወንድ ማሰብ አትፈልግም ነበር።

የእርሷ ፍላጎት ምንም ይሁን ምን አፍቃሪዋ አፈቀርኩሽ ያላትን ልጅ ማግኘት የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኖበት በኃይል ሊያገኛት ያቅድ ጀመር። ጠልፎ ለማስቀመጥና የልቡን ለመሙላት የወሰነው ይህ አፍቃሪ ራህመት ለብቻዋ የምትወጣበትን አሳቻ ሰዓት ለማወቅ አድፍጦ ሲጠባበቅ ቆየ። ያለወትሮው አፍቃሪ ነኝ ባዩ ሰው ከዓይኗ የተሰወረባት ራህመት “እፎይ ተገላገልኩ” በሚል ስሜት ዘና አለች።

ተመላልሶ ሲያቅተው የተዋት እንጂ ክፉ ነገር ያሰበባት አልመሰላትም ነበር። እንደሚወዳትና አብሯት መሆን እንደሚፈለግ ሲነግራት፤ በምንም ሁኔታ የእርሱ መሆን እንደማትችል አስረግጣ ስትነግረው የቆረጠለት መስሏት ነበር። እንቢታው ከሚያርቀው ይልቅ እልህ ውስጥ የከተተው አፍቃሪ አድፍጦ ሲጠባበቅ ከቆየ በኋላ ከእለታት በአንዱ ቀን የጣለው ወጥመድ የሚፈልገውን ያዘለት።

ጭጋጋማ ቀን ነበር። በነጩ ችፍ ችፍ እያለ የዋለው ዝናብ እኩለ ቀን አካባቢ እንደመቆም ብሏል። ጳጉሜን 01 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡30 ሰዓት አካባቢ ነበር። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ ቀርሳ ቢላ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ጥጉን ይዞ ሲጠብቃት ቆየ። ዝናቡ ጋብ ሲል ራህመት ዣንጥላዋን ይዛ ከቤቷ ወጣች። ሳታስበው ከኋላዋ መጥቶ ያዛት። ባላሰበችውና የሰው እንቅስቃሴ በሌለበት ጭር ባለው መንገድ ላይ ያዛት። ራህመት ለመጮህ ስትሞከር በጠንካራ እጆቹ አፏን አፈነው።

ራህመት ከእኔ የፍቅር ጓደኝነት ጥያቄን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነችም በሚል ምክንያት መንገድ ላይ ጠብቆ አንገቷን አንቆ በመያዝ በአካባቢው ወደሚገኝ ካባ እየጎተተ ወሰዳት። ራህመት ላለመሄድ ስትታገለው በለበሰችው ልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ አንገትዋን አንቆ መሬት ላይ በመጣል በወደቀችበት የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ሊፈጽምባት ሲል ጩኸት ታሰማ ጀመር። በድጋሚ በልብስ ማሰሪያው ጨርቅ አንገቷን አጥብቆ በመያዝና እራስዋን እንዳትከላከል በማድረግ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ፈጸመባት። በድጋሚ አንገቷን በወገብ ማሰሪያ ጨርቅ በማነቅ ሕይወቷ እንዲያልፍ አደረገ።

በወቅቱ በርቀት ጉዳዩን የተመለከቱት የዓይን አማኞች በፍጥነት ሄደው ፖሊስ ለመጥራት ቢሞከሩም የወጣት ራህመትን ሕይወት ሊያተርፉ አልቻሉም። ፖሊስ በቦታው ሲደርስ ተጠርጣሪው አስከሬኑን ለመደበቅ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ ተያዘ።

የፖሊስ ምርመራ

ፖሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማድረግ ጀመረ። ተጠርጣሪው የእምነት ክህደት ቃሉን ተቀብሎ፤ የፎረንስክ ምርመራውን አያይዞ የዓይን አማኞችን ቃል ተቀብሎ መረጃውን በተገቢው መልኩ አደራጀ።

ተጠርጣሪው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕግ አንቀጽ 620(2)(ሀ) እና (3) መሠረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት እንዲቀጣ ሲል ማስረጃውን አቀረበ።

የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

የፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጉዳዩን ተመልክቶ ፍርድ ቤት አቀረበ። የአቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር እንደሚያመለክተው ኪያር ዩሱፍ የተባለ ተከሳሽ በጳጉሜን 01 ቀን 2015 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 6፡30 ሰዓት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ሰፈራ ቀርሳ ቢላ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ የ17 ዓመት የሆነችውን የግል ተበዳይ ከእኔ ጋር በፍቅር ጓደኝነት ለመቀጠል ፈቃደኛ አልሆነችም በሚል ምክንያት መንገድ ላይ ጠብቆ አንገቷን አንቆ በመያዝ በአካባቢው ወደሚገኝ ካባ በሚወስዳት ጊዜ ላለመሄድ ስትታገለው በለበሰችው ልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ አንገትዋን አንቋታል።

መሬት ላይ በመጣል በወደቀችበት የግብረ-ሥጋ ግንኙነት ሊፈጽምባት ሲል የግል ተበዳይ ጩኸት ስታሰማ በድጋሚ በልብስ ማሰሪያው ጨርቅ አንገቷን አጥብቆ በመያዝና እራስዋን እንዳትከላከል በማድረግ የግብረ-ሥጋ ግንኙነት የፈጸመባት እና አንገቷን በእጅ እና በልብስ የወገብ ማሰሪያ ጨርቅ በማነቅ ሕይወቷ እንዲያልፍ በማድረጉ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምርመራ ተጣርቶበት በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት በወ/ሕግ አንቀጽ 620(2)(ሀ) እና (3) መሠረት በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 11ኛ ወንጀል ችሎት ክስ ቀርቦበት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን ተሰጥቶ ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት በ25 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 26 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You