የግንቦት ግርግር

በ1953 ዓ.ም በቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ላይ የተደረገው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ‹‹የታኅሳስ ግርግር›› በመባል ይታወቃል:: እንዲህ የተባለበት ምክንያት ሙከራው የተደረገው በታኅሳስ ወር መጀመሪያ ሳምንት ስለነበር እና በሙከራው ግርግር ተፈጥሮ ስለነበር ነው::

ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ የንጉሡን ሥርዓት ገርስሦ ሥልጣን የያዘው ደርግ በግንቦት ወር የመጀመሪያ ሳምንት 1981 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደረገበት:: ከታኅሳስ ግርግር 28 ዓመታት በኋላ የግንቦት ግርግር ተደረገ ማለት ነው:: በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን ይህን እና ሌሎች የዚህ ሳምንት የግንቦት ክስተቶችን እናስታውሳለን::

ከ67 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 5 ቀን 1949 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ እና የእቴጌ መነን አስፋው ልጅ የሆኑት ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ አረፉ::

ከ76 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 1940 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 1948) እስራኤል ሉዓላዊ (ነፃ) አገር ሆና ተመሰረተች::

ከ40 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 6 ቀን 1976 ዓ.ም (በአውሮፓውያኑ 1984) የፌስቡክ ኩባንያ (Facebook, Inc.) መስራች ማርክ ዙከርበርግ ተወለደ::

ከ156 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን 1860 ዓ.ም የንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ባለቤት የነበሩት እቴጌ ጥሩወርቅ ውቤ ኃይለማርያም አረፉ::

ከ8 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም አንጋፋው የአትሌቲክስ አሠልጣኝና የኢትዮጵያ ባለውለታ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ አረፉ::

ከ115 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጼ ምኒልክ፣ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል የዙፋናቸው ወራሽ መሆኑን በአዋጅ አሳወቁ::

አሁን ደግሞ የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ምርጫን እና የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ዘርዘር አድርገን እንያቸው::

ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም

ከ19 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ኢትዮጵያ ምርጫ አካሄደች:: ይህ ምርጫ በኢህአዴግ መንግሥት ትመራ ለነበረው ኢትዮጵያ ታሪካዊ ምርጫ ተባለ:: በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው ምርጫም ሆነ:: ስለምርጫ ሲወራ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የፖለቲካ ጉዳይ ሲነሳም ምርጫ 97 ይነሳል::

ይህ ቀን ታሪካዊ የሆነበት ምክንያት፤ ከዚያ በፊትም ሆነ ከዚያ በኋላም ከተደረጉ የኢህአዴግ ምርጫዎች የተሻለ አሳታፊ ስለነበር ነው:: አሳታፊ ሆኖ ጀምሮ በኋላ ወደ ደም አፋሳሽነት በመቀየሩ ነው::

ይቺ ታሪካዊ ቀን በኋላ ደግሞ ‹‹ግንቦት ሰባት›› የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ እንዲፈጠር አደረገች:: በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ግንቦት ሰባት ታሪካዊ ስም ለመሆን በቅታለች::

ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ከ14 ዓመታት በኋላ የ1997ቱ ምርጫ መሠረታዊ የአስተዳደር ለውጥ እንዲያመጣ የተገደደበት የመጀመሪያው ጊዜ ነው። በምርጫ 97 ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል::

የ1997ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከመካሔዱ በፊት የፖለቲካ ምኅዳሩ የሰፋበት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በከፍተኛ ሁኔታ የተጠናከሩበት፣ ሃሳብን በነጻነት መግለጽ እምብዛም የማይገደብበት፣ የፖለቲካ እስረኞች እስር ቤቶቹን ያላጨናነቁበት ጊዜ ነበር። ይህ ሁሉ ግን በምርጫው ውጤት አጥቢያ ገዢው ፓርቲና ዋና ዋናዎቹ ተቃዋሚዎች፣ በተለይም ቅንጅት ሲወዛገቡ በአንድ ጊዜ ወደ ተቃራኒው ሁኔታ ተለወጧል። ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ቢያንስ ለስምንት እና ዘጠኝ ዓመታት ያህል የአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ አልተካሔደም። የዋነኛዎቹ ተቀናቃኞች የቅንጅት ለአንድነት እና ለፍትሕ አመራሮች፣ የሲቪል ማኅበራት አባላት እና ጋዜጠኞች በገፍ እና በግፍ ታሰሩ:: የፖለቲካ ድርጅቶች ተዳከሙ፣ በርካታ ብዙኀን መገናኛዎች ተዘጉ፣ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ሕግጋት ወጡ።

ከምርጫ 97 በኋላ የተከተለው ፖለቲካዊ አፈና ‹‹ኢሕአዴግ ዴሞክራሲን ለመገንባት የሚፈልገው ራሱ ምርጫ የሚያሸንፍ መሆኑን እስካረጋገጠ ድረስ ብቻ ነው›› በሚል እንዲተች አደረገው።

የምርጫውን ዕለት ክስተቶች በዕለቱ አዲስ አበባ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ያስታውሱታል:: አንዳንዶችም ራሱን የቻለ መጽሐፍ ጽፈውበታል:: ከእነዚህም አንዱ የኢህአፓ መሥራችና ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ›› በሚሉት መጽሐፎቹ የሚታወቀው ክፍሉ ታደሰ ነው:: ክፍሉ ታደሰ ‹‹ግንቦት 7›› በሚለው መጽሐፉ በዕለቱ በአዲስ አበባ የተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ያስተዋለውንና የታዘበውን ለታሪክ ጽፎ አስቀምጧል::

ክፍሉ ታደሰ ‹‹ግንቦት 7›› በተሰኘው መጽሐፉ፤ ምዕራፍ 5 ‹‹ግንቦት 7 ታሪካዊ ቀን›› በሚል ርዕስ እንዲህ ጽፎታል::

‹‹ግንቦት 7/1997 ዓ.ም 524 የምክር ቤት ወንበሮች ለውድድር ቀረቡ:: 23 የሚሆኑት በነሐሴ ወር በሶማሌ ክልል ለሚደረገው ምርጫ ወደ ጎን ተተው::

ግንቦት 7 በተካሄደው ምርጫ ተሳትፌያለሁ:: ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው፤ ያየሁትን፣ የሰማሁትን፣ የተሳተፍኩበትን ነው የማቀርበው:: እኔ የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ታሪኩን በሦስተኛ ሰው አድርጌ ላቀርበው አስቤ ራቀብኝ:: የእኔ መስሎ አልሰማህ አለኝ፤ እናም በቀጥታ ላቀርበው ወሰንኩኝ›› በማለት ደራሲው ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ውስጥ የነበረውን ሁነት በቀጥታ በመሳተፍ ያየነውን ነግሮናል::

ማለዳ 12፡00 ተነስቶ መገናኛ ሲደርስ ረጅም ሰልፍ አጋጠመው:: ሰልፉ እየተጠማዘዘ ቢያንስ ከ300 ሜትር በላይ እንደሚሆን ይገምታል:: ደራሲው የዕለቱን እንቅስቃሴ ማየት ፈልጎ ስለነበር ብዙ የምርጫ ጣቢያዎችን እየተዘዋወረ ተመለከተ:: ሁሉም ረጃጅም ሰልፎች ያሉባቸው ናቸው::

ደራሲው ከዚያ በፊት የነበሩ ምርጫዎችንም ያስተዋለ መሆኑን አስታውሶ፣ የዚያን ዕለት የነበረው ተሳትፎ ግን በኢትዮጵያ ከተደረጉ ምርጫዎች ሁሉ የተለየ እንደነበር ይገልጻል:: መጽሐፉ ከ2013ቱ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ በፊት የተጻፈ ስለሆነ በዘመነ ብልጽግና የተደረገውን ምርጫ አያካትትም::

የግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም ምርጫ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ተስፋ ጥሎበት የነበረ ለመሆኑ፤ የምርጫው እንቅስቃሴ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ተሳትፎ አስተውሏል:: የምርጫው ዕለትም እንደሌላ ጊዜ ‹‹ውጣ›› እየተባለ ሳይሆን፤ ሕዝቡ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ ወጣ::

በዚህ ዕለት ሕዝቡ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሄደው በመንግሥት ካድሬዎች ቅስቀሳ ሳይሆን በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ቅስቀሳ ነው:: የምርጫ ካርድ ያላወጡ ዜጎች ተፀፀቱ::

ምርጫው በዕለቱ ፍጹም ሰላማዊ እንደነበር ደራሲው ይገልጻል:: ምንም አይነት አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ስላልነበረ ፖሊሶች ደክሟቸው ቁጭ ይላሉ:: ሕዝቡም አዛውንትና አካል ጉዳተኞችን እያስቀደመ ፍጹም ሰላማማዊ በሆነ መንገድ ሲመርጥ ዋለ::

በዕለቱ ከወለደች ገና 15 ቀን የሆናት አራስ፣ ታመው ከአልጋ ላይ የመጡ፣ በሰው ድጋፍ የመጡ… መራጮች እንደነበሩ ደራሲው አስተውሏል::

የደራሲውን ሁለት ገጠመኞች ጠቅሰን የግንቦት ሰባትን ትውስታ እንጨርስ::

አንደኛዋ መራጭ ሴትዮ የዋህ ነገር ናቸው መሰለኝ የውስጣቸውን መደበቅ አልቻሉም:: እናም ወደ ምርጫ ጣቢያው እየገቡ በወቅቱ ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበረውን ፓርቲ ስም ጠርተው ‹‹የት ጋ ነው እገሌን መምረጫው?›› ብለው በቦታው የነበረውን ሰው ሁሉ ፈገግ አሰኝተውታል:: ምንም እንኳን የውስጣቸውን ሁሉም ቢሰማውም ለደንቡ ሲባል ‹‹እንደሱ አይደለም ማዘር፤ እዚህ ጋ ይግቡና የፈለጉትን ይምረጡ›› ብለዋቸዋል::

ሁለተኛው የደራሲው ገጠመኝ በወቅቱ የነበረውን የአንድ ወገን የበላይነት ምሬት የሚገልጽ ይመስላል:: አንደኛዋ ሴትዮ ለመምረጥ ተሰልፈው አንዲት ሴት ስለምርጫው ቴክኒካዊ ማብራሪያ ስትሰጥ ይሰማሉ:: ማብራሪያ ሰጭዋ የትግርኛ ቋንቋ ጫና ያለባት ናት:: ደራሲው እንደሚለው ከኋላዋ ያሉት አንዲት ሴትዮ እየደጋገሙ ‹‹ይቺ ሰላቢ›› እያሉ እግረ መንገድም የአገዛዙን አስከፊነት ይኮንናሉ:: ደራሲው ማብራሪያ ሰጭዋ እና መራጯ የግል መቀያየም ይኑራቸው አይኖርቸው አያውቅም::

ምርጫ 97 ብዙ ነገሮችን ያሳየ ምርጫ ነው:: በዕለቱ አዲስ አበባ የነበረውን ሁነት ያስተዋሉ ሁሉ የተለያየ ገጠመኝ አላቸው:: ይህ ታሪካዊ ቀን እነሆ በበጎም በመጥፎም እየታወሰ ይኖራል::

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም

ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሄዱ:: በዕለቱም መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የመጨረሻው የአድማ ስብሳባ ቦታ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ጊቢ ነበር::

ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ (የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም)፣ ሜጀር ጀኔራል ኃይሉ ገብረሚካኤል (የምድር ጦር ዋና አዛዥ)፣ ሜጀር ጀኔራል አምሃ ደስታ (የአየር ኃይል ዋና አዛዥ)፣ ሪር አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ (የባሕር ኃይል ዋና አዛዥ)፣ ሜጀር ጀኔራል ወርቁ ዘውዴ (የፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ)፣ ሜጀር ጀኔራል አብዱላሂ ዑመር (የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ)፣ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ (የኢንዱስትሪ ሚኒስትር)፣ ሜጀር ጀኔራል አበራ አበበ (የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ)፣ ብርጋዴር ጀኔራል ተስፋዬ ትርፌ (በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ዘመቻ መኮንን)፣ ብርጋዴር ጀኔራል ደሳለኝ አበበ (የጦር ኃይሎች አካዳሚ ዋና አዛዥ)፣ ኮሞዶር ኃይሌ ወልደማርያም (በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የእቅድና ፕሮግራም መምሪያ ኃላፊ) እና ሌሎች የጦሩ አባላት ከመከላከያ ሚኒስትሩ ቢሮ አጠገብ ባለው አነስተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ተሰበሰቡ::

በስብሰባው ላይ የተገኙት ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የጦሩ ባለሥልጣናት ይሁኑ እንጂ ከየጦር ክፍሎቹ የተመለመሉት አዛዦችም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመፈፀም በተለያዩ አካባቢዎች ተዘጋጅተው ነበር:: ለአብነት ያህልም፤ የ603ኛ ኮር መምሪያ ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል አውዴ ገብረየስ (ጎንደር)፣ የአየር ኃይል ምክትል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ሰለሞን በጋሻው (ደብረ ዘይት)፣ የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጀኔራል ደምሴ ቡልቶ (አስመራ) እና ሌሎች የጦሩ አባላት ተጠቃሽ ናቸው::

እዚህ ላይ አንድ መታወስ ያለበት አስቂኝ ድርጊት አለ:: የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሽና የአድመኞቹ ሰብሳቢ ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ወደ ስብሰባው የመጡት ዘግይተው ነበር:: ወደ አዳራሹ ሲገቡ የሰብሳቢነቱን ቦታ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ንጉሤ ይዘውታል:: ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን መልቀቅ ሲገባቸው ዝም አሉ:: ይባስ ብለውም ሜጀር ጀኔራል መርዕድ ቦታውን የመልቀቅ አዝማሚያ ሳያሳዩ ስብሰባውን መምራት ቀጠሉ:: መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የተሰበሰቡት የጦር አዛዦች እዚያው በዚያው ሌላ መፈንቅለ መንግሥት አደረጉ:: ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በሁኔታው ተበሳጭተው ስብሰባውን ጥለው ወጥተው እጃቸውን ኪሳቸው ውስጥ አድርገው መንጎራድ ጀመሩ::

ሌላው ደግሞ በመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ውስጥ ከተሳተፉ የጦሩ አባላት መካከል አንዳንዶቹ መፈንቅለ መንግሥቱ እንደሚሳካ ቀድመው እርግጠኛ በመሆን ‹‹እዚህ አድማ ውስጥ እኔንም አካፍሉኝ እንጂ ጎበዝ! በ1953ቱ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ወቅት ሳይነግሩኝ ቀሩ:: ዛሬም ልትተውኝ ነው እንዴ? …›› ብለው የተናገሩ የጦር መሪዎች እንዳሉ ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው የተፃፉ ታሪኮች ያሳያሉ::

የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ‹‹ታማኝ ናቸው›› ያሏቸውን የጦሩን አባላት ሰብስበው ሲነጋገሩ ንግግራቸው ጭቅጭቅ የበዛበት ነበር:: የመንግሥቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ተወግዶ በምትኩ በጀኔራል መኮንኖች የሚመራ አዲስ መንግሥት የማቋቋም እቅዳቸውን ተናገሩ:: በብዙ ጉዳዮች ላይ መግባባትና መተማመን እያጡ በሄዱ ቁጥር ጊዜ እየመሸባቸው መሆኑን መገንዘብ አቃታቸው::

የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ በሊቀ መንበሩ ሽኝት ላይ ሳይገኙ የቀሩ የጦር አዛዦች ሁኔታ ስላላማራቸው አዛዦቹን የሚከታተል ቡድን አደራጅተው ስለነበር እያንዳንዱን ድርጊት ይከታተሉ ነበር:: ጉዳዩ የመፈንቅለ መንግሥት አድማ መሆኑን ሲያረጋግጡም ነገሩን የሊቀ መንበሩ ቀኝ እጅ ለነበሩት ለሻለቃ መንግሥቱ ገመቹና ለሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን አሳወቋቸው::

ኮሎኔል አዲስ ተድላ እና ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ በሽምግልና ወደ መከላከያ ሚኒስቴር ቢላኩም የመፈንቅለ መንግሥቱ ሴራ ጠንሳሾች ግን ‹‹ያለቀለት ነገር ስለሆነ ሽምግልናና ድርድር አያስፈልግም›› ብለው መነታረካቸውን ቀጠሉ:: ለመንግሥት ታማኝ በነበረው ጦርም ተከበቡ:: በሁኔታው ተስፋ የቆረጡት አንዳንድ የጦር አዛዦችም ራሳቸውን አጠፉ::

የመፈንቅለ መንግሥቱ ጠንሳሾችና መሪዎች በፈፀሙት የእቅድና የአፈፃፀም ስህተት ለአራት ዓመታት ያህል ታቅዶበት ሲውጠነጠን የነበረው መፈንቅለ መንግሥትም ሳይሳካ ቀረ::

ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ በተወደሰው ርምጃ ኢትዮጵያም በርካታና ‹‹በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ ነበሩ›› የተባሉ የጦር መሪዎቿን አጣች:: ደርግም የደመ ነፍስ ጉዞውን ቀጠለ:: ሊቀ መንበር ሌተናንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ከግንቦት 1981 ቢተርፉም ከግንቦት 1983 ግን ሳይተርፉ ቀሩ::

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You