ጨቅላ ልጇን ለልመና

እናትነት ታላቅ ስጦታ ነው። ይህን ስጦታ አክብሮ መያዝ ለእናቶች በተፈጥሮ የተሰጠ ፀጋ ነው። እናትነት ደመነፍሳዊነት ነው እስኪባል ድረስ የእናትና ልጅ ቁርኝቱ የእናትነት ስሜቱ ይለያል። ሴቶች እናት ተብለው ከተጠሩባት ቀን አንስተው ለልጃቸው የሚሰጡት ፍቅርና እንክብካቤ የተለየ ነው።

የዛሬ ተናጋሪው ዶሴ ባለታሪካችን ከእናትነት ስሜት በተቃራኒው የወለደቻትን ልጅ የኢኮኖሚ ምንጭ አድርጋ የተጠቀመች፤ እናትነት የሚለው ስያሜን የማይገባት ሴት ሆና አግኝተናታል። ሴትየዋ ልጇን ከወለደች በኋላ ባል አያስፈልገኝም ብላ ትዳሯን ያፈረሰች ስለመሆኗ ከአዲስ አበባ ፖሊስ መዝገብ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ብቸኛዋ እናት

ሴቶች በተለያዩ ምክንያቶች ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ ላጤ እናት (Single Mother) ይሆናሉ። ከአጋራቸው ጋር በሞት አሊያም በፍቺ ሲለያዩ፣ በተፈፀመባቸው ጥቃት ሳቢያ የልጅ እናት ለመሆን ሲገደዱ፤ እንዲሁም የጀመሩት ግንኙነት እንዳሰቡት አልሰምር ሲላቸው ልጃቸውን (ልጆቻቸውን) ብቻቸውን የማሳደግ ውሳኔ ላይ ከሚደርሱባቸው ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

ይህቺኛዋ እናት ግን ልጅ ካገኘሁ ባል አያስፈልገኝም ብላ ፈልጋና አቅዳ፤ ልጅ ብቻ እንዲኖራት በማለም ላጤ እናት (Single Mother) ሆናለች። ለዚህም “በሕይወቴ ያሰመርኩት ቀይ መስመር ነበር፤ እርሱን ማለፍ ስለማልችል ላጤ እናት ሆኛለሁ” የሚል ምክንያት ነው ያስቀመጠችው።

 

በሕይወቷ የምታስበውና የምታልመው ስላልሆነ የግድ በትዳር መታሰር የለብኝም የሚል አቋም ላይ እንደደረሰች ትናገራለች። ይሁን እንጂ ላጤ እናት መሆን በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉት ታነሳለች። እያንዳንዷ ሴት በሰውነቷ ላይ እንዲሁም በምትመሠርተው ቤተሰብ ላይ ውሳኔዎችን ትወስናለች፤ ውሳኔዋም እንደምትኖረው ሕይወት የተለያየ ነው የምትለው ይህች ሴት፤ ይሁን እንጂ ሴቶች ፈልገውና አቅደው ላጤ እናት የሚሆኑባቸውን ምክንያቶችንም ትጠቅሳለች።

በማኅበረሰቡ የሴት ልጅ ሕይወት በጊዜ የተገደበ እንደሆነና እስከተወሰነ ዕድሜያቸው ድረስ ማግባትና መውለድ ካልቻሉ ሕይወታቸው እንደተመሰቃቀለ ተደርጎ መወሰዱ ለእንዲህ ዓይነት ውሳኔ ከሚገፏቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ ትናገራለች።

በተወሰነ መልኩ እየታየ ያለው የማኅበረሰብ አመለካከት ለውጥም የራሱ የሆነ ድርሻ አለው። በቀደመው ጊዜ አንዲት ሴት ሳታገባ ብትወልድ ለልጁ ‘ዲቃላ’ የሚል ስያሜ በመስጠት እናትየዋ ትወገዝ ነበር። አሁን ላይ ግን ይህ ልማድ በትንሹም ቢሆን እየቀረ በመሆኑ ሴቶች እንዲህ ዓይነት ውሳኔ እንዲያሳልፉ አደፋፍሯቸዋል።

“ከዚህ ቀደም ሴቶች ሥራ በማይሠሩበትና የኢኮኖሚ ጥገኛ በሆኑበት ጊዜ ልጅ ወልደው ለብቻቸው ማሳደግ የማይታሰብ ነበር” የምትለው ሴት የኢኮኖሚ አቅም ማደግም ሌላኛው የላጤ እናትነት ምክንያት ነው ትላለች።

አንዲት ሴት በሕይወት ያየችው የትዳር ሕይወት እኩልነት የሌለበት፣ ሴቷ ጥገኛ የሆነችበት፣ ጥቃት የሚፈፀምበት፣ የኃይል ሚዛኑ እኩል ያልሆነበት፣ ሁኔታዎች በሙሉ ለሴት የማይመቹ ከነበሩ፤ ይህን ባለመፈለግ ላጤ እናት ልትሆን ትችላለች።

ምንም እንኳን የኢኮኖሚ አቅሟ የጎለበተ ባይሆንም ታዲያ ‹‹ቀይ መስመሬ ታለፈ›› እና ሌሎች ምክንያቶችን የደረደረችው ይህች ሴት በወለደች በሁለት ወሯ ከባሏ ከተለያየች በኋላ ነበር ችግር እግር ከወርች አስሮ ይደቁሳት የገባው። በአራስ ወገቧ ወዲህ ወዲያ ብትልም አልገፋ ያለትን የኑሮ ዳገት መውጫ ልጇን ለማድረግ አቀደች።

ለሥራ ጎንበስ ቀና አልል ያለው ወገቧ፤ ለሥራ አልዘረጋ ያለው እጇ ለምፅዋት ሲሆን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተሰነዘረ። በየደጀ ሰላሙ እየዞረች እጇን ለምፅዋት ከመዘርጋት አልፋ ልጇን ለልመና በማከራየት ገቢ ልታገኝባት እንደምትችል ሰማች።

በቅርበት የምታውቃት አንዲት ሴት ለንግሥ በዓላት ልጇን እየያዘች በመሄድ ልትለምንባትና ግማሹን ልታካፍላት ተስማምተው ሥራ ይጀምራሉ። በሯሷ ለምና ከምታገኘው ገንዘብ በተጨማሪ ልጇን አከራይታ ገንዘብ ማግኘት መቻሏ ያስደሰታት ይህች ሴት ጡት ያልጠገበች ጨቅላ ልጇን ለልመና በማከራየት የገንዘብ ማግኛ አደረገቻት።

አስለሟኟ ሴት

ወይዘሮ አስማረች ባይለየኝ የተባለችው የ6 ወር ሕፃን ልጇን ለልመና ተግባር እንድታሠማራ ስትል አሳልፋ የሰጠች ሲሆን የዚህችን ሴትዮ ልጅ የተቀበለችው በሕፃናት ልጆች የመለመን የቀደመ ልምድ ያላት ሴት ናት። በየጊዜው ሕፃናት ልጆች ያላቸውን ሴቶች እየቀረበች ልጆቻቸው ከፍ እስኪሉ ድረስ የምትለምንባቸው ሲሆን አዲስ የተወለዱ ልጆች ደግሞ የተሻለ ገንዘብ ስለሚገኝባቸው ምርጫዋ ነበር።

ይህች ወይዘሮ እያዩ ቢሻው የተባለችው ግለሰብም ሕፃኗን ይዛ እየለመነች የሚገኘውንም ገንዘብ በጋራ ለመካፈል ተስማምተው መንገድ ላይ ይዛት መዋል ጀመረች። የሕፃኗ ወላጅ እናት ሞልታ ከሰጠቻት ጡጦ በስተቀር ምንም ተጨማሪ ነገር ሳታቀምሳት በልጅቷ ስትለምን የምትውለው ወይዘሮ አንድ ቀን ያላሰበችው ነገር ገጠማት።

ቀኑን ሙሉ ፀሐይ የሚመታት ጨቅላ ሕፃን ገና ጡጦውን ካፏ ስታደርግ እንቅልፍ ስለሚወስዳት ከዚህ በፊት ተቸግራ አታውቅም ነበር። ያን ቀን ግን ልጅቷ ያለማቋረጥ ታለቀስ ነበር። ሆኖም ከቦታው እንዳትነሳ በእለቱ ሰው በብዛት እጁን ለምፅዋት የሰነዘረበት ቀን ነበረና ገንዘቡ አሳሳት። በዚህ በኩል ደግሞ የልጅቷ ማልቀስ የሰዎችን ትኩረት እየሳበ የመፅዋቾችን ቁጥር ሰላበዛላት ደስ ብሏት ተደላደለች።

በእለቱ ሕፃኗን እያስለቀሰች ስትለምን እያለ በመንገድ ላይ የሚያልፍ ግለሰብ ሕፃኗን ድምፅ ሰምቶ በመጠራጠሩ ምክንያት ጡትም እንድታጠባው ይጠይቃታል። ለቅሶው ገቢ እንጂ ሌላ ጦስ ያመጣብኛል ብላ ያላሰበችው ይህች ሴት መንገደኛው ጡት እንድታጠባ ሲጠይቃት ባለመቻሏ ለፖሊስ ተጠቆመ። ፖሊስም ጥቆማውን ተከትሎ ባደረገው ምርመራ መሠረት የሕፃኗ እናትና አስለማኟ ሴት በሰው የመነገድ ድርጊት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

የፖሊስ መርመራ

ፖሊስ አስለማኟ ሴት የልጅቷ እናት አለመሆኗን ሲረዳ ሕፃኗንና ሴትዮዋን ይዞ ወደ እናትየው ጋር እንድታደርሰው ያደርጋል። ሕፃኗ የምትመገበውን ገዝቶ አረጋግቶ ወደ ወላጅ እናትየው ጋር ሲደርስ ከልጅቷ ደኅንነት በፊት ገንዘብን የወደደችው ሴት ቀድማ ብሬስ? የሚል ጥያቄ ነበር ያቀረበችው።

ፖሊስ የተሠራው ወንጀል መኖሩን በመረዳት ሴቶቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ሕፃኗን የተሻለ እንክብካቤ ወደምታገኝበት ተቋም አስገብቶ ምርመራውን ይጀምራል።

የወለደችውን ልጅ ለምን ለዚህ ተግባር እንዳዋለች ሰትጠየቅ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት የሌለው የብቻ የእናትነትን ወሬ እየደጋገመች ትናገር እንደነበር ፖሊስ ያስረዳል። ስለአዕምሮ ደኅንነቷ ተጠራጥሮ ቢያስመረምርም ፍፁም ጤነኛ መሆኗን የሐኪም ምርመራው አመለከተ።

ደጋግማ “ብቸኛ እናት ስለሆነኩ ነው፤ ቀይ መሰመሬን አልፎ ነው፤ ሲቸገረኝ ምን ላርግ” እና የመሳሰሉትን እያነሳች ብታወራም ፖሊስ ለሠራችው ወንጀል ተገቢውን ቅጣት ማግኘት አለባት ሲል መረጃና ማስረጃውን አጠናቀረ።

ወይዘሮ አስማረች ባይለየኝ እና ወይዘሮ እያዩ ቢሻው የተባሉት ግለሰቦች ታኅሣሥ 27 ቀን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው ሾላ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከቀኑ 11፡45 ሰዓት ሲሆን በሰዎች የመነገድ እና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 3/1/እና 4/1/ሀ/ እና የወ/ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ለልመና ልጇን የሰጠችው እናት እና ስትለምንበት የነበረችው ግለሰብ ተይዘው በሰው የመነገድ ድርጊት ወንጀል እንዲከሰሱ ለዐቃቤ ሕግ ማስረጃው ቀረበ።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር

ፖሊስ አጠናቅሮ የላከውን ማስረጃ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በመመልከት በዚህ መልኩ የክስ ዝርዝሩን ያቀርባል። ወይዘሮ አስማረች ባይለየኝ እና ወይዘሮ እያዩ ቢሻው የተባሉት ግለሰቦች ታኅሣሥ 27 ቀን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 08 ልዩ ቦታው ሾላ ገበያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በግምት ከቀኑ 11፡45 ሰዓት ሲሆን በሰዎች የመነገድ እና ሰውን በሕገ ወጥ መነገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 3/1/እና 4/1/ሀ/ እና የወ/ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ ስር

የተመለከተውን በመተላለፍ ለልመና ልጇን የሰጠችው እናት እና ስትለምንባት የነበረችው ግለሰብ ተይዘው በሰው የመነገድ ድርጊት ወንጀል ተከሰሱ።

የክስ ዝርዝሩ እንደሚያስረዳው ሁለቱ ግለሰቦች አብረው በልመና ሥራ ላይ የሚተዳደሩ እና ወይዘሮ አስማረች ባይለየኝ የ6 ወር ሕፃን ልጇን በልመና ተግባር እንድትሰማራ አሳልፋ የሰጠች በመሆኑ ወይዘሮ እያዩ ቢሻው የተባለችው ግለሰብም ሕፃኗን ይዛ እየለመነች የሚገኘውንም ገንዘብ በጋራ ለመካፈል ተስማምተው ስትለምን እያለ በመንገድ ላይ የሚያልፍ ግለሰብ ሕፃኗ ስታለቅስ ሰምቶ በመጠራጠሩ ምክንያት ጡትም እንድታጠባው ሲጠይቃት ባለመቻሏ ለፖሊስ የጠቆመ በመሆኑ በሰው የመነገድ ድርጊት ወንጀል ተከሰዋል፡፡

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን ፈጽመናል ጥፋተኛ ነን ብለው አምነው የተከራከሩ ሲሆን የሰው እና የሰነድ ምስክር መሰማት ሳያስፈልግ ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል፡፡

ውሳኔ

የዐቃቤ ሕግን የክስ አቀራረብ ተመልክቶ ጉዳዩን የተመለከተው ፍርድ ቤት ግራ ቀኙን ሰምቷል። ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ድርጊቱን ፈጽመናል ጥፋተኛ ነን ብለው አምነው የተከራከሩ ሲሆን የሰው እና የሰነድ ምስክር መሰማት ሳያስፈልግ ፍርድ ቤቱ በተከሶሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፏል፡፡

በመጨረሻም የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የካ ምድብ 5ኛ ወንጀል ችሎት የካቲት 28/2016 ዓ.ም በዋለው ችሎት መሠረት ወንጀሉን በቀላል ደረጃ በመመደብ ተከሳሾቹን ያርማል ሌላውንም የማኅበረሰብ ክፍል ያስተምራል ያለውን እያንዳንዳቸውን በ6 አመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና በ5,000 ብር መቀጮ እንዲቀጡ ወስኖባቸዋል፡፡

አስመረት ብሥራት

አዲስ ዘመን ሚያዚያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You