ቀንና ሌሊት ሰርቶ ቤተሰቡን የሚያስተዳደር ሰው ነው። የሁለት ቤትን ሸክም ተሸክሞ የቤተሰቡን ዕዳ ለማቃለል የሚታትር ጎልማሳ። ለእናት ለአባቱ ደግሞ የልጅነት ልጃቸው ነው። ከእናቱ ጋር አብረው ሲሄዱ፤ እህትና ወንድም እንጂ እናትና ልጅ አይመሰሉም። እናትና አባቱ በልጅነታቸው እርሱን ከወለዱ በኋላ ሁለተኛውን ልጅ የወለዱት አስራ አምስት ዓመታት አሳልፈው ነው።
እርሱም ወንድም በማግኘቱ እነሱም ሁለተኛ ልጅ ስለተሰጣቸው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ኖሯቸውን ቀጥለው ነበር። ይህ የልጅነት ልጅ እንደ እናቱና አባቱ እሱም በጊዜ አግብቶ የሶስት ልጆች አባት ሆነ። ከቤተሰቦቹ ጋር ሰፋ ባለው የቀበሌ ቤት ውስጥ የሚኖሩት ሁለት ቤተሰቦች በደስታና በመተሳሰብ ሕይወት ቀጠለ።
አንድ ክፉ ቀን የልጁ ሚስትና አባት ማልደው ወደ ሥራ ይወጣሉ። እናቱ የልጇን ሚስትና ባለቤቷን ሸኝታ ቅዳሜ ቀን ስለነበር የተኙትን ልጆቿንና የልጅ ልጆቿን ለመንከባከብ ተፍ ተፍ ትል ጀመር። ከቤት ከወጡ ከሰዓታት ቆይታ በኋላ የነበሩበት ታክሲ ተገልብጦ ሚስትና አባቱን በአንድ ቀን ያጣው ተወዳጅ ልጅ በድንጋጤ አእምሮውን ሳተ።
ከሁለት ቀናት የሆስፒታል ቆይታ በኋላ እናት አደጋውን ስትሰማ በደም ግፊት ምክንያት አንድ ጎኗ በድን ሆነ። ቤተሰቡ በአንድ ቀን ከባድ የሕይወት ፈተና ውስጥ ገባ። ያላደገው ታናሽ ወንድሙና የራሱ ሶስት ሕፃናት ተጨምረው ከታማሚ እናቱ ጋር ኑሮን መግፋት ከበደው።
ቀን የመንግሥት ሥራ እየሠራ ማታ የጥበቃ ሥራን በመሥራት ቤተሰቡ ምንም ሳይጎድልበት እንዲኖር ይተጋ ጀመር። እናቱ እንደ ልቧ መንቀሳቀስ ባትችልም በተወሰነ መልኩ ስለተሻላት ሁሉም ሳይከፋቸው እንዲኖሩ የበኩሏን ጥረት ማደረግ ጀመረች። ሌሊትና ቀን የሚሰራው ልጅም ምንም እንኳን ቤተሰቦቹ ቢናፈቁት ቅዳሜና እሁድን ብቻ እነርሱ ጋር ውሎ እያደረ በሌላው ቀን ይለያቸው ነበር። ሥራው ፋታ ስለማይሰጥ ስልክ ለመደወል እንኳን የሚጠቀመው ምሳ ሰዓቱን ብቻ ነበር ።
ቀን ቀንን እየወለደ ሲሄድ ሀዘኑን እየረሳ በጥንካሬ ለመሥራት ራሱን ማጀገን ጀመረ። በጣም ከሚወደው አባቱና ከሚያፈቅራት ባለቤቱ ቢለይም፤ የተቀረው ቤተሰብ የእሱን ድጋፍ ይፈልግ ነበርና ራሱን አጠንክሮ ወደ ሥራውን በማከናወን አቅሙ እስከሚችለው ድረስ ትግሉን ቀጠለ። በየእለቱ እየሰራ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ይህ ልጅ ልጆቹም በሥነ ምግባርና በትምህርት ጎበዝ በመሆን ያስደስቱት ጀመር። ባለው ነገር ደስተኛ በመሆን ሥራውን በሐቀኝነት የሚሰራው የ35 ዓመት ሰው አንዲት ክፉ ቀን ደግማ ባለሳበው አዋለችው።
የዘራፊዎቹ ክፉ በትር
ቅዳሜና እሁድን ቤተሰቡ ጋር አሳልፎ፤ በእናቱ የጤንነት ሁኔታ መሻሻል ተደስቶ ወደ ሥራ ገባ። በሳምንት አንዴ የሚያገኛቸው ቤተሰቦቹ ጋር በመቆየቱ እየተደሰተ የሙሉ ቀን ሥራውን ጨርሶ ለምሽት ሥራው ተዘጋጀ። በጥበቃ ሠራተኞች ማረፊያ ክፍል ውስጥ ተራው እስኪደርስ ጋደም ብሎ ከቆየ በኋላ አንድ ሰዓት ላይ ነቅቶ ብሎ ሥራ ገበታው ላይ ተገኘ።
መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 እስከ 11፡00 ሰዓት ባለው የጥበቃ ጊዜ ሥራውን የሚፈታተን ነገር ገጠመው። በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ኖህ ፕላዛ 4ኛ ፎቅ ጂ.ኤስ.አይ በተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሰራው ይህ ሰው የጥበቃ ሥራውን በሚሰራበት ወቅት ከአንድ በላይ የሆነ የኮቴ ድምፅ የድርጅቱ የዕቃ ማከማቻ ክፍል ውስጥ ሰማ።
የቤተሰብ አስተዳደሪ የሆነው አቶ ጥላሁን ዓለማየሁ ጆሮው ድምፅ ወደሰማበት ክፍል ሮጦ ሲገባ፤ ሁለት ሰዎች ደህና ገንዘብ ያወጣል ያሉትን እቃ እያነሱ ሊወስዱ መሆኑን ተመለከተ። ልክ ሰው እንደ ደረሰባቸወ ያወቁት ዘራፊዎች የእዚህን የቤተሰብ አስተዳደሪ ሰው መምጣት አለወደዱትም ነበር። ሁለቱም በቀስታ እየተራመዱ ወደ ጥበቃ ሠራተኛው ተጠጉ። ይህ ሰው ሊያመልጡ ወደ በሩ የሚጠጉ ስለመሰለው በሩን በመያዝ ለእርዳታ ጓደኛውን ይጣራ ጀመር። ሌቦቹ ግን ከሁለት ጊዜ በላይ ለመጣራት እንኳን እድል ሳይሰጡት ወደእርሱ ተንደርድረው በመሄድ በቢላዋ ሆዱ ላይ በመውጋትና አንገቱን በእጃቸው በማነቅ ጉዳት እንዲደርስበት አደረጉ።
ያ የብዙ ሰው ነፍስን በእጁ የያዘ ያህል የቤተሰቡን ሸከም ተሸክሞ የሚኖር ሰው ላይመለስ አሸለበ። የልጆች አባትና የእናቱ ጧሪ የሆነው ይህ ሰው ለቤተሰቡ ምንም ሳይተው እስከ ወዲያኛው አንቀላፋ። ተጠርጣሪዎቹ ጉዳት እንዲደርስበት ካደረጉ በኋላ በ2ኛ ክስ የተጠቀሰውን ንብረት በመያዝ ወደ ውጭ ወጣ። አንደኛው ሌባ የድርጅቱ የጥበቃ ሠራተኛ ነበር። የድርጅቱ ጥበቃ መሆኑን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለማምለጥ ሲሞክር፤ ቀድሞ ከእሱ ጋር ተረኛ የነበረውን የጓደኛውን ድምፅ በመስማቱ ወደ ድምፁ ሲሮጥ ከነበረ ጥበቃ ጋር ተገናኙ። ያኔ በቦታው ዘረፋና ጥቃት መፈፀሙን የተረዳው ሰው፤ በጊዜው የድርጅቱን ግቢ ሲጠብቁ የነበሩ ግለሰቦችን በመጥራት ሌቦቹ እንዲያዙ አደረገ።
የጥበቃ ሠራተኞቹ ሌቦቹን በፖሊስ ካስያዙ በኋላ ጓደኛቸውን ለመፈለግ ወደ ውስጥ ሲገቡ ሟችም በስለት መሳሪያ ሆዱ ላይ በመወጋቱ ጉዳት ደርሶበት ይመለከታሉ። ሆዱ ላይ ከመወጋቱም በተጨማሪ በሰው እጅ አንገቱን በመታነቁ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ መሆኑን ፖሊሶች ለመመልከት ቻሉ። አስክሬኑም ለፎረንስክ መርመራ ወደ ሆስፒታል ከተላከ በኋላ ፖሊስ መርመራውን ጀመረ።
የፖሊስ ምርመራ
ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ካዋለ በኋላ የተለያዩ ምርመራዎችን አደረገ። ድርጅቱ የነበረውን የጥበቃ ካሜራ በመመልከት ወንጀለኞቹ ድርጊቱን ስለመፈፀማቸው አስተማማኝ መረጃ አገኘ። በእለቱ የነበሩትን ጥበቃዎች ቃል፤ የፎረንሲክ ምርመራ፤ የካሜራ ምስልና የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል በመያዝ ተከሳሾቹ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የሰው ግድያ ወንጀል እንዲከሰሱ አደረገ።
በተመሳሳይ በ2ኛ ክሳቸው ላይ ተከሳሾች የማይገባቸውን ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓት፣ ቦታ እና ሁኔታ ሟችን ከገደሉ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ተቀጥሮ ጥበቃ ሆኖ የሚሰራበት ጂ.ኤስ.አይ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ንብረት የሆኑትን መለያቸው ሳምሰንግ ኤ 21 ኤስ ብዛታቸው 35 የሆነና የዋጋ ግምታቸው ደግሞ 670 ሺ 909 ብር ከ24 ሳንቲም የሚያወጡትን 1ኛ ተከሳሽ በጥቁር ቦርሳ ተሸክሞ ሊወጣ ሲል እጅ ከፍንጅ የተያዘ በመሆኑ በፈጸመው በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የከባድ ስርቆት ወንጀል ተከሰሰ። ከ1ኛ ተከሳሽ ባሻገር ሌሎችም ወንጀል ፈፃሚዎች ተከሰሱ፡፡
ይህን ሁሉ ማስረጃ የያዘው ፖሊስ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት መረጃውንና ማስረጃውን አቅርቦ የክስ ሁኔታውን ሲከታተል ቆይቷል፡፡
የዐቃቤ ሕግ ክስ ዝርዝር
በዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ላይ 1ኛ ዳኛቸው አንዱበር፣ 2ኛ ሽፈራው አስፋው የተባሉ ሁለት ተከሳሾች በ2 ክሶች ተከሰዋል፡፡ በ1ኛ ክስ ላይ ተከሳሾች ሰውን ለመግደል አስበው መስከረም 29 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡30 እስከ 11፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 ኖህ ፕላዛ 4ኛ ፎቅ ጂ.ኤስ. አይ በተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ ከሚገኘው የድርጅቱ የዕቃ ማከማቻ ክፍል ውስጥ ሟች ጥላሁን ዓለማየሁን ሁለቱም ተከሳሾች በቢላዋ ሆዱ ላይ በመውጋትና አንገቱን በእጃቸው በማነቅ ጉዳት እንዲደርስበት አድርገዋል፡፡
ጉዳት ካደረሱ በኋላ በ2ኛ ክስ የተጠቀሰውን ንብረት በመያዝ 1ኛ ተከሳሽ የድርጅቱ ጥበቃ መሆኑን እንደምቹ ሁኔታ በመጠቀም ለማምለጥ ሲሞክር በጊዜው የድርጅቱን ግቢ ሲጠብቁ በነበሩ ግለሰቦች አማካኝነት በፖሊስ ተይዟል፡፡ ወንጀለኞቹ ሲያዙ ሟችም በስለት መሳሪያ ሆዱ ላይ በመወጋቱ ጉዳት ስለደረሰበት እና በሌላ ሰው እጅ አንገቱን በመታነቁ ምክንያት ሕይወቱ ያለፈ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት የሰው ግድያ ወንጀል ተከሰዋል፡፡
በተመሳሳይ በ2ኛ ክስ ተከሳሾች የማይገባቸውን ብልጽግና ለእራሳቸው ለማግኘት በማሰብ ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ በተጠቀሰው ቀን፣ ሰዓት፣ ቦታ እና ሁኔታ ሟችን ከገደሉ በኋላ 1ኛ ተከሳሽ ተቀጥሮ ጥበቃ ሆኖ የሚሰራበት ጂ.ኤስ.አይ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ንብረት የሆኑትን መለያቸው ሳምሰንግ ኤ 21 ኤስ ብዛታቸው 35 የሆነና የዋጋ ግምታቸው ደግሞ 670 ሺ 909 ብር ከ24 ሳንቲም የሚያወጡትን 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ በጥቁር ቦርሳ ተሸክመው ሊወጡ ሲሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ በመሆኑ በፈጸሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የከባድ ስርቆት ወንጀል የተከሰሱ በመሆኑ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ክስ አቅርቦባቸው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት ክርክር ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ውሳኔ
በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት የቅጣት ውሳኔ በማሳረፍ 1ኛ ተከሳሽ በ12 ዓመት እና 2ኛ ተከሳሽ በ10 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም