የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን የ80 ዓመት ጉዞ ያስቃኘው ጉባዔ

ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ባለፉት ስምንት አስርት ዓመታት የተለያዩ አደረጃጀቶችንና ሂደቶችን አልፏል:: በዚህም የኢትዮጵያን ቅርሶች በመጠበቅ፣ በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብና ቅርስ ጥገናዎችን በመሥራት ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ ሪፎርሞችን በማካሄድ ወደ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ወደ የበለጠ ቅርስ ማልማት ሥራ እየገባ ነው::

ይህ ቀደም ሲል በተለያዩ ስያሜዎች ሲጠራ የቆየው የዛሬው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት የ80 ዓመታት ጉዞውን የሚዳስስ የቅርስ ምርምር ጉባዔና የዓውደ ርዕይ መርሃ ግብር አካሂዷል:: በመርሃ ግብሩ አንጋፋ፣ ስመጥርና በዘርፉ ልምድ ያካበቱ የተቋሙ፣ ተጋባዥ ተመራማሪዎችና ምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበዋል::

ከጥናታዊ ጽሁፎቹ መካከልም የፓሊዮንቶሎጂ ጥናት በኢትዮጵያ፣ የአርኪኦሎጂ ጥናት በኢትዮጵያ፣ የማይዳሰሱ ቅርሶች በኢትዮጵያ፣ የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች አጠባበቅ በሀገሪቱ ታሪክ ከወጡት አዋጆች አንፃር ሲቃኙ፣ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ከውጭ ሀገር በማስመለስ ሂደት የተከናወኑ ታሪካዊ ክንውኖችና ወቅታዊ ተነሳሽነት፣ የባህላዊ ቅርሶች ጥበቃ ጥናትና ልምድ፣ ተግዳሮቶችና እድሎች እንዲሁም የአርት ታሪክና ጥናታዊ ዘዴዎቹ ከቅርስ ጥበቃ አንፃር የሚሉት ይገኙበታል::

በተጨማሪም የምርምር ዘርፉን ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ምክክር ተካሂዷል:: በጉባዔው ማጠናቀቂያም በቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፎች ዙሪያ ጥያቄዎችና አስተያየት ቀርበው ከመድረኩ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል። ከዚህ ለሁለት ቀናት (ማክሰኞና እሮብ) በተካሄደ ጉባዔ ጎን ለጎንም የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱን ያለፉት 80 ዓመታት ጉዞ የሚያስቃኝ የፎቶ አውደ ርዕይ ቀርቦ በጉባዔው ተሳታፊዎች ተጎብኝቷል።

የዝግጅት ክፍላችን ከሥፍራው ባገኘው መረጃ መሠረት ለተቋሙ የመጀመሪያ የሆነው የዚህ የቅርስ ምርምር ጉባዔ ዋና ዓላማ ኢትዮጵያ የበርካታ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ማስገንዘብና ቅርሶቹን ለማልማትና ለመጠበቅ መከናወን ስለሚገባቸው ተግባራት ሳይንሳዊ ምላሽ መስጠት ነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለፁት፤ መሥሪያ ቤቱ በምርምር ረገድ አቅሙን ማጎልበት እንዲችል ከጥቂት ዓመታት በፊት የሪፎርም ሥራዎች ከመሥራት ጀምሮ በርካታ ምክክርና ውይይቶች ተደርገዋል። በዚህም የቅርስ ምርምር ክፍል በአዲስ መልክ የማደራጀ ሥራ ተሠርቷል።

ቅርስ የመጠበቅ፣ የመንከባከብና የማልማት ሥራ በምርምር ሲታግዝ ውጤታማ እንደሚሆንም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል። የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። አሁንም ይህን ሥራ በምርምር ለማገዝ የሚያስችል አደረጃጀት መፍጠሩ ተግባሩ ውጤታማ እንዲሆን መሠረት እንደሚጥል ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው መሥሪያቤቱ ወደ ምርምር ተቋምነት መሸጋገሩን አስታውቀዋል። በዚህም የኢትዮጵያ ቅርስ ምርምርና እንክብካቤ የ80 ዓመት ጉዞን መሠረት በማድረግ ለሁለት ቀናት የመጀመሪያውን ዓመታዊ የቅርስ ምርምርና አውደርዕይ መዘጋጀቱን ይናገራሉ። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱም በርካታ አደረጃጀቶችና ሂደቶችን እያለፈ አሁን ላይ መድረሱን ጠቅሰው፣ በእነዚህ ዓመታትም የሀገሪቱን ቅርሶች በመጠበቅ፣ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገቡ፣ ቅርሶች ተገቢውን ጥገና በወቅቱ እንዲደረግላቸው በመሥራት ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻለ ተቋም መሆኑን አመልክተዋል።

ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት:: ተቋሙ ባለፉት 80 ዓመታትም በተለያዩ አደረጃጀቶችና ስያሜዎች ሲጠራ ነበር። ባለሥልጣን መሥሪያቤቱ የተመሠረተው በ1936 ዓ.ም ሲሆን፣ በሂደቱም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ሥራ፣ የመሳፍንትና የመኳንንቱን የወግና የክብር አልባሳት በቤተ መፅሕፍት ህንፃ ውስጥ አውደ ርእይ በማቅረብ በቅርስ ጉዳይ ላይ የመጀመሪያውን የግንዛቤ ማስጨበጫ በመስጠት ሠርቷል። በ1945 ዓ.ም በተፈጠረው ግንዛቤና በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ በተፈረመ ስምምነት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተከናወኑ ጥናትና ምርምሮች በርካታ ቅርሶች ተገኝተዋል። በውጤቱም የአርኪዮሎጂ ሙዚየም ተቋቁሟል። በ1958 ዓ.ም ተጠሪነቱ በወቅቱ የጽህፈት ሚኒስቴር በመባል ለሚታወቀው ተቋም ሆኖ የታሪካዊ ቅርሶች አስተዳደር የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።

ከ1967 ዓ.ም አንስቶ ደግሞ ተጠሪነቱ ለባህል፣ ስፖርትና ወጣቶች ሚኒስቴር እንዲሆን ተደርጎ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ መምሪያ በሚል ተደራጅቶም ነበር። በ1987 ዓ.ም በድጋሚ ተጠሪነቱ ለባህልና ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲሆን ተደርጎ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ድርጅት በሚል ስያሜ ተግባርና ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

አደረጃጀቱ በጊዜ ሂደት ውስጥ ሲቀያየር ቆይቷል፣ የአሁኑ የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን በ1992 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 209 በባለሥልጣን ደረጃ ተደራጅቶ ለቀድሞው ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠሪ እንዲሆን ተደርጎም ነበር። እስከ 2014 ዓ.ም ድረስም በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነትና ሥልጣን መሠረት ቅርሶችን በአግባቡ በመለየት፣ በማጥናት፣ በመመዝገብ፣ በማልማትና በመጠበቅ ለትውልድ ለማስተላለፍ ሠርቷል።

በመጨረሻም በአዋጅ 1263/2014 መሠረት ባለሥልጣኑ ሀገራዊ ተልዕኮውን በላቀ ደረጃ እንዲወጣ ያስችለው ዘንድ ተጠሪነቱም ለቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሆን ተደርጎ፣ የኢትየጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የሚለው ስያሜ ተሰጥቶታል።

‹‹ቅርሶቻችን የትናንት ታሪካችን፤ የዛሬ ማንነታችን ፤የነገው ደግሞ ዐሻራችን በመሆናቸው በአግባቡ መዝግቦ መያዝ ያስፈልጋል›› የሚሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሊታወቁ፣ ሊጠኑ፣ ሊለሙና በእንክብካቤ ለትውልድ ሊተላለፉ እንደሚገባ ይገልፃሉ። አዲሱ አደረጃጀትና መዋቅርም ባለሥልጣን መሥሪያቤቱን ወደ ምርምር ተቋም ማሳደግ ያስቻለ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ከትናንት አንስቶ ዛሬ ላይ የተደረሰበትን ውጤት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ይናገራሉ። የመጀመሪያው የቅርስ ምርምር ጉባዔም የዚሁ አካልና ምሳሌ እንደሚሆን አስረድተዋል።

የጉባዔው ዋና ዓላማ በቀጣይ ጊዜያት የምርምር ዘርፉ በበቂ ግብዓት፣ ቴክኖሎጂ፣ በጀትና የሰው ኃይል ተጠናክሮ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማስቻል መሆኑን ያስታወቁት አቶ ኤልያስ ሽኩር፤ በተጨማሪ በአውቶሜሽንና ዲጂታል አሠራር ትግበራ ከዓለም አቀፍ ምርምር ተቋማት ጋር ቅንጅት ለመፍጠር የሚያስችል አቅም ለማደራጀት በማሰብ እንደሆነ ይናገራሉ።

በዚህም ረዘም ያለ የዘርፉ ልምድ ያላቸውና በኢትዮጵያ አንጋፋ የሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማእከላት ያገለገሉ እንዲሁም ወጣት የባለሥልጣን መሥሪያቤቱ ባለሙያዎችና ምሁራን የጥናት ውጤቶቻቸውን በሁለቱ ቀናት መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያቀርቡ መደረጉን ያስረዳሉ። በውጤቱም ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ ዘላቂነት ያላቸው ስልቶችን የሚገኙበት እንደሚሆን ተናግረዋል።

በአንደኛው የቅርስ ምርምር ጉባዔ ላይ ከተገኙት እንግዶች መካከል የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ አንዷናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ምድረ ቀደምት የሆነችው ኢትዮጵያ በርካታ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ነች። እነዚህ ቅርሶች የማንነት መገለጫ የሀገሪቱ መለያ ኩራት ናቸው። በዘመናት ሂደት ውስጥም ከትውልድ ትውልድ እየተላለፉ እዚህ ደርሰዋል።

የአሁኑ ትውልድም ዘመኑ የደረሰበትን የእድገት ደረጃ በሚመጥን መንገድና ሥነ ዘዴ መዝግቦ፣ ተንከባክቦ፣ ጠብቆና አልምቶ የማስተላለፍ ኃላፊነት እንዳለበት ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል። ይህም ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆኑን አሳስበዋል። ይህንን ዓላማ ለማሳካትም መንግሥት ለቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሀገሪቱ ካላት የቅርስ ሀብት አንፃር ከዘርፉ እየተገኘ ያለው ገቢ ዝቅተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል:: በመሆኑም ያሏት ቅርሶችና የመስህብ ሀብቶች እንዲጠበቁ ብቻ ሳይሆን ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያስገኙ የሚያግዙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ይናገራሉ። ይህ የምርምር ጉባዔም ይህንኑ መነሻ በማድረግ መዘጋጀቱን ገልጸዋል::

ሚኒስትሯ እንዳስታወቁት፤ ቅርሶች የቱሪዝም መዳረሻ ሆነው የመጎብኘት እድል አላቸው :: ኢትዮጵያ ካላት የቅርስ ሀብት አንፃር ለምተው የተሪዝም መዳረሻ የሆኑት እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው። መንግሥት ይህንንን እውነታ ለመቀየር በማሰብ በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 የመንግሥት አስፈፃሚ አካላትን በድጋሚ ሲያደራጅ ቱሪዝም ከአምስቱ ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ ሆኖ በሚኒስቴር ደረጃ እንዲደራጅ፣ ቅርስም የዘርፉ ዋነኛ አቅም እንደሆነ በማሰብ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ተጠሪነት ለቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሆን ተደርጓል::

ቅርሶች እንዲጠበቁ ብቻ ሳይሆን እንዲለሙና አገልግሎት ላይ እንዲውሉ በማስፈለጉ በርካታ የቅርስ መስህቦች ልማትና እንክብካቤ እየተካሄደ መሆኑን የሚናገሩት ሚኒስትሯ፤ ከእነዚህ ውስጥ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የዋናው ቤተመንግሥት፣ የአባጅፋር ቤተመንግሥት እንዲሁም ሌሎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ይህም መንግሥት ለቅርሶች ልማትና እንክብካቤ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ጠቅሰው፤ ይህንን ተከትሎ ክልሎች በተመሳሳይ መልኩ ለቅርሶች የሰጡት ትኩረትና ተግባራዊ ርምጃ አበረታች መሆኑን ያነሳሉ።

‹‹የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከ1936 ዓ.ም ጀምሮ በተለያየ አደረጃጀት ለ80 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል›› የሚሉት ሚኒስትሯ፤ በውጤቱም 11 ቋሚ ቅርሶችንን እና አምስት የማይዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በዩኔስኮ ማስመዝገብ መቻሉን አስታውቀዋል። በዚህ ዓመት ብቻ ሁለት ቋሚ ቅርሶች (የባሌ ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ እና የጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድርን) እንዲሁም አንድ የማይዳሰስ ቅርስ (የሀረር ሸዋል ኢድን) ማስመዝገቡን እንደ ስኬት አንስተዋል።

እንደ አምባሳደር ናንሲሴ ጫሊ ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከፊቱ ያሉትን ተግባርና ኃላፊነቶች ለማከናወን በርካታ ሥራዎች ይጠብቁታል:: በተለይ የሀገሪቱን የመስህብና ቅርስ አቅም በሚመጥን መልኩ ተግባራቱን ማከናወን ይኖርበታል። በቅርስ ረገድ በርካታ ጥናቶችና ሳይንሳዊ ምርምሮች ሊካያካሂድ ይገባል። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ይህንን ተግባርና ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተገቢውን ድጋፍና ትብብር ያደርጋል።

ከዚህ ቀደም የነበረውን የባለሥልጣን መሥሪያቤቱን አቅም ካዳከሙት ተግዳሮቶች መካከል የተጠናከረ የቅርስ ምርምር አቅም አለመኖር መሆኑን የሚያነሱት አምባሳደሯ፤ ከምዝገባ ጀምሮ እስከ ልማት ድረስ የሚደረግ የቅርስ ሥራ ያለምርምር እና ጥናት የሚሳካ አለመሆኑን ይገልፃሉ። በዚህ ምክንያት መንግሥት የቅርስ ምርምር ሥራው እንዲጠናከር አደረጃጀቱ በመሪ ሥራ አስፈፃሚ እንዲደራጅ እና በበቂ የሰው ሃይል እንዲዋቀር መደረጉን ያነሳሉ። ቱሪዝም ሚኒስቴርም አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን ይናገራሉ።

‹‹ይህ ጉባዔም የዚሁ የአደረጃጀት ለውጥ ውጤት ነው›› ያሉት ሚኒስትሯ፤ የቅርስ ምርምር ፈርጀ ብዙና ሁሉንም የእውቀት መስኮች የሚዳስስ እንደሆነም ተናግረዋል:: ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በመስኩ የልህቀት ማእከል በመሆን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤታማ ለመሆን ራዕይ ይዞ ወደ ተግባር መግባት እንደሚገባው አስገንዝበዋል። ይህንን ለማሳካትም አደረጃጀቱን በተሟላ የሰው ሃይል የማሟላት ተግባሩን ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው ተናግረዋል። በምርምር የተሻለ ልምድ ካላቸው የሀገር ወስጥና የውጪ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር እንደሚኖርበትም ገልፀዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ግንቦት 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You