ታክሲ ጠባቂዋን ወጣት…

ንጋት ላይ ነው። ቀኑ ቀለል ያለ ብዙም የማይቀዘቅዝ ጠዋት ነበር። አስራ ሁለት ሰአት ላይ ሁለት ህፃናት ልጆቿ እንደተኙ ጉንጫቸውን ስማ ወደ ሥራ ለመሄድ ተጣድፋ ወጣች። ባለቤቷ ለሥራ ጉዳይ አምሽቶ እቤት ስለገባ እንቅልፍ ጥሎት ነበር። ለወትሮው ተነሰቶ የሚሸኛት ባሏ ድካሙን ስታይ አሳዘናት ፤ በተኙበት ጉንጮቻቸውን ስማ ወጣች። ታክሲ መጠበቂያው ጭር ብሎ ነበር። ቡዙም ሰው አይታይም። እንደ ቆመች ደቂቃዎች አለፉ አንድም ታክሲ ዝር አላለም። የሰአቱ መርፈድ ብሎም የታክሲው አለመምጣት እያቁነጠነጣት ቆማለች። ግማሽ ሰአት ገደማ እንደቆመች ነበር አንድ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪ ፊቷ መጥታ የቆመችው።

ክፉ ገጠመኝ

ታክሲ አጥታ በቆመችባቸው ደቂቃዎች የኋሊት ብዙ ዓመታትን ነጉዳ እያሰላሰለች ነበር። በልጅነቷ ብቸኛ ልጅ በመሆኗ የተነሳ እንዴት ቀብጣ እንዳደገች ታስታውሳለች። ለእናት ለአባቷ እንድና ብርቅዬ ልጅ በመሆኗ ከሰፈር ጓደኞቿ በተለየ ሁኔታ ነበር ያደገችው። የዚህች ብርቅ ልጅ ወላጆች የሀብት ደረጃቸው ከፍ ያለ ባይሆንም ለአንድ ልጃቸው ትምህርት ግን ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።

ልጅትም ስታሳፍራቸው በጥሩ ውጤት ዩኒቨርሲቲ ገብታ በጤና ትምህርት ተመርቃ የጤና መኮንን ሆናለች። አንድ ነሽና ብዥልን ያሏት ቤተሰቦቿን ለማስደሰት ስትልም እንደተመረቀች አግብታ በሃያ ሰባት ዓመቷ የሁለት ልጆች እናት ሆናለች።

ወላጆቿ ከዓይናቸው እንድትርቅ ባለመፈለጋቸው የተነሳ የራሳቸው መኖሪያ ጊቢ ውስጥ ቤት ሠርተው እንድትኖር አድርገዋታል። እሷም ልጆቿን ያለስጋት የሚያሳድጉላት ወላጆች ስላሏት ፈጣሪን እያመሰገነች ልጅም እናትም ሆና አብረው ይኖሩ ጀመር።

በተመሳሳይ የሙያ ዘርፍ ላይ የተሠማሩት ባልና ሚሰቶች እየተደጋገፉ ኑሯቸውን የተሻለ ለማድረግ ይጥራሉ። ወጣቶቹ ባልና ሚስቶች በሚያስቀና ፍቅርና መከባበር መኖራቸው በመሆኑ ወላጆቿ እፎይ እንዲሉ አድርጓቸዋል።

ልጃችን መልካም ሕይወት ውስጥ ገባች እያሉ የኑሮ ውጣ ውረድ እንዳይከብድባት መንገድ እየጠረጉ አብረው ይኖራሉ። ያን እለት ባለቤቷ የምሽት ተረኛ ስለነበር ሲሠራ አምሽቶ እንቅልፍ ጥሎታል። እናትና አባቷም ሌሊት ኪዳን ለማድረስ ወደ ቤተከርሰቲያን እንደወጡ አልተመለሱም።

ህፃናቱ ልጆቿና ባለቤቷ በሚያስቀና እንቅልፍ ውስጥ ስለነበሩ ልትቀሰቅሳቸው አልፈለገችም ነበር። ለዚህም ነው ማንንም ሳትሰናበት በእንቅልፍ ልባቸው ስማ በችኮላ ወደ ታክሲ ተራ የሮጠችው። በእለቱ ንጋት ላይ ስለሆነ ይሁን በሌላ ምክንያት መንገዱ ላይ ብዙም ሰው አይታይም ነበር።

መንገድ ዳር ቆማ ለግማሽ ሰዓታት ያክል ታክሲ ከጠበቀች በኋላ አንድ በውስጧ ሰዎችን የያዘች ባጃጅ ፊቷ ቆመች። እሷ በምትሄድበት አቅጣጫ የባጃጅ ትራንስፖርት ባለመኖሩ የተነሳ ግራ ተጋብታ አየት አድርጋ አንገቷን መለሰች።

ከዛ በኋላ ፊቷ የቆመው ባጃጅ ሳይንቀሳቀስ ውስጥ ያለው አንዱ ተሳፋሪ ትሄጃለሽ ብሎ በመጠየቅ አሳፍረው ውስጥ ለውስጥ በኮብል ስቶን መንገድ ላይ ይወስዷታል። ሁኔታው አላምር ያላት ወይዘሮ ልትወርድ ብትፈልግም በሁለት ሰዎች መካከል ስላስቀመጧት ሳይሳካለት ቀረ። ድምፅ አሰምታ ርዳታ ለማግኘትም ብትሞክር ማንም ሰምቷት የመጣ ሰው አላገኘችም ነበር።

ሌቦቹና ምስኪኗ ሴት

ባጃጁ ፊቷ መጥቶ እንደቆመና አንዱ ተሳፋሪ ወርዶ እንድትገባ ጋብዟት ጉዞ ሲጀመሩ ነው ሹፌሩና ሌሎች ሁለት ሰዎች መኖራቸውን የተመለከተችው። መካከላቸው ካስቀመጣት በኋላ ወደ ኮሮኮንች መንገድ እስኪገቡ ድረስ አንድም ቃል አልተነፈሱም ነበር። ሥራ ለመድረስ የቸኮለችው ወጣት ልቧ መድረሻዋን እያሰበ ቢሆንም የሰዎቹ ሁኔታ ግን ምቾት አልሰጣትም ነበር።

ባጃጅ ውስጥ የነበሩት በረከት ብርሃኑ፣ ዮናስ ካሳ፣ ዳግም ውብሸት የተባሉ ሶስት ወጣቶች ነበሩ። መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 12 ሰአት ከ30 ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ሰላም ፍሬ ጤና ጣቢያ አካባቢ ነበር ደርጊቱን የፈፀሙት። ወጣቶቹ በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እያሉ ነበር ወይዘሮ እጸገነት አንተነህ የተባለች ግለሰብ መንገድ ዳር ቆማ የተመለከቷት። ይህች ሴት በማለዳ ከቤቷ ወጥታ ታክሲ በመጠበቅ ላይ ነበረች። በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ውስጥ ያሉት ወጣቶች ታክሲ በመጠበቅ ላይ የነበረችውን ሴት ትሄጃለሽ ብለው በመጠየቅ አሳፍረው ውስጥ ለውስጥ በኮብል ስቶን መንገድ ላይ ይወስዷታል።

በዝምታ ጉራንጉርና ጭር ያለ ቦታ እየመረጡ የሚሄደው የባጃጅ ሹፌር እንዲያቆም በሃይለ ቃል ብትናገረውም ጆሮ ሳይሰጣት ጭር ያለ ቦታ በመፈለግ በፍጥነት ይነዳ ጀመር። ምንም እንኳን ድምፅ ለማውጣት ብትሞከርም ከባጃጁ ሞተር በላይ ድምጿ ወጥቶ ሊሰማላት አልቻለም ነበር። በትግልና በጩኸት ራሷን ብታደክምም ምንም ለወጥ ሳታመጣ ቀረች።

ከዛ ቀጥሎም ከላይ በተጠቀሰው ቦታ ሲደርሱ በአካባቢው ሰው አለመኖሩን ካረጋገጡ በኋላ በወቅቱ የያዘችውን ንብረት ለመውሰድ እንዲያመቻቸው አንዱ ሌባ አንገቷን በእጁ አንቆ ሲይዛት ስትንፈራገጥ፣ ሌላው ተከሳሽ እግሯን በመያዝ ጄ ፋይፍ ሳምሰንግ ሞባይል ግምቱ 7 ሺ ብር፣ ጥቁር ተንጠልጣይ ቦርሳ፣ ሁለት ጃኬት እና ሁለት ሱሪ ግምታቸው 2 ሺ 450 ብር፣ የብር የአንገት ሀብልና የጣት ቀለበት ግምቱ 400 ብር፣ የሆኑ ንብረቶቿን ከወሰዱባት በኋላ ከባጃጁ ውስጥ አውርደው መንገድ ላይ ጥለዋት ይሰወራሉ።

በእለቱ ለሰው የምታደርሰው ልብስ በፌስታል ይዛ የነበረ ሲሆን የራሷንና ለሰው የምታቀብለውን እቃ ዘርፈው እንደ አልባሌ እቃ ከባጀጁ አውጥተው አሽቀንጥረው ጥለዋት ተፈተለኩ። የሁለት ህፃናት ልጆች እናት፤ የእናት የአባቷ ብርቅ ልጅ፤ የባለበቷ አፍላ ፈቅር የሆነችው ይህች ሴት ያልተገባ ብልፅግና በፈለጉ ሰዎች ተዘርፋ፤ በመታነቋና በመወርወሯ ምክንያት እስከወዲያኛው አሸለበች።

ሌቦቹ የወሰዱትን ንብረትንም ሸጠው ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋል እና ግለሰቧም በእጅ አንገቷን በመታነቋ እና በራሷ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ በዚሁ እለት እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ ፖሊስ ፍለጋውን አጧጡፎ ቀጠለ።

የፖሊስ ምርመራ

ወይዘሮ እፀገነት በወደቀችበት መንገድ በኩል ሲያልፍ የነበረ አንድ ሰው ለፖሊስ ባደረገው ጥቆማ መሠረት የፀጥታ ሃይሎች በአካባቢው ተገኙ። መሬት ላይ ወደተዘረረችው ሴት ቀርበው ሲመለከቱ ሕይወቷ ማለፉን አረጋገጡ። ያን ጊዜ አስክሬኑ ተነሰቶ ለምርመራ ወደ ሆስፒታል ከተላከ በኋላ በወደቀችበት አካባቢ ፍለጋ ሲካሄድ ባዶ የገንዘብ ቦርሳ አገኙ። ቦርሳው ውስጥ መታወቂያዋ በመገኘቱ የአደጋ ጊዜ ተጠሪዋ ለሆነው ባለቤቷ ተደወለለት።

ለወትሮዋ ሥራ ስትገባ የምትደውለው ሚስቱ ሳትደውል መቆየቷ ብቻ ሳይሆን ስልኳ ያለመስራቱ ነገር የከነከነው ባል ድንገተኛው የስልክ ጥሪ ሲደርሰው አስደንጋጭ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ እንደነበር ፖሊሶቹ ይናገራሉ።

ምርመራው ሲጠናቀቀ አስክሬን ለቤተሰብ አስረክቦ የክትትል ሥራውን የጀመረው ፖሊስ በቀላሉ ስልኩ የተሸጠበትን ቦታ በማግኘቱ ተጠርጣሪዎችን ሊያገኛቸው ቻለ። ሌቦቹ እንደ ልማዳቸው ዘርፈው የጣሏቸው ሰዎች ሕይወታቸው ላይ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ በመቆየቱ አለመያዛቸውን በእምነት ክህደት ቃላቸው ገልፀዋል። እሷንም ለመግደለ ሳይሆን ለመስረቅ ብቻ አስበው እንዳደረጉት ተናገሩ።

ፖሊስ የእምነት ከህደት ቃሉን፤ የቴክኒክና የታክቲክ ምርመራ፤ የፎረንሲክ ምርመራዎችን አንድ ላይ በማጠናቀር ለፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ አቀረበ።

የዐቃቤ ሕግ የክስ ዝርዝር

የዐቃቤ ሕግም ማስረጃውን ተቀብሎ ክስ መሠረተ። የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው 1ኛ በረከት ብርሃኑ፣ 2ኛ ዮናስ ካሳ፣ 3ኛ ዳግም ውብሸት የተባሉ ሶስት ተከሳሾች ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሳቸው ለማግኘት በማሰብ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 12፡30 ሰዓት ሲሆን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ሰላም ፍሬ ጤና ጣቢያ አካባቢ ተከሳሾች በባለሶስት እግር ተሽከርካሪ በመጓዝ ላይ እያሉ ወ/ሮ እጸገነት አንተነህ የተባለች ግለሰብ መንገድ ዳር ቆማ ታክሲ በመጠበቅ ላይ እያለች ትሄጃለሽ ብለው በመጠየቅ አሳፍረው ውስጥ ለውስጥ በኮብል ስቶን መንገድ ላይ ይወስዷታል።

ቀጥሎም ከላይ በተጠቀሰው ቦታ ሲደርሱ በአካባቢው ሰው አለመኖሩን ካረጋገጡ በኋላ በወቅቱ የያዘችውን ንብረት ለመውሰድ እንዲያመቻቸው 3ኛ ተከሳሽ አንገቷን በእጁ አንቆ ሲይዛት ስትንፈራገጥ፣ 2ኛ ተከሳሽ እግሯን በመያዝ ጄ ፋይፍ ሳምሰንግ ሞባይል ግምቱ 7 ሺ ብር፣ ጥቁር ተንጠልጣይ ቦርሳ፣ ሁለት ጃኬት እና ሁለት ሱሪ ግምታቸው 2 ሺ 450 ብር፣ የብር የአንገት ሀብልና የጣት ቀለበት ግምቱ 400 ብር፣ የሆኑ ንብረቶቿን ከወሰዱባት በኋላ ከባጃጁ ውስጥ አውርደው መንገድ ላይ ጥለዋት ይሰወራሉ።

የወሰዱትን ንብረትንም ሸጠው ገንዘቡን ለግል ጥቅማቸው በማዋል እና ግለሰቧም በእጅ አንገቷን በመታነቋ እና በራሷ ላይ በደረሰባት ጉዳት ምክንያት ሕይወቷ በዚሁ እለት እንዲያልፍ ያደረጉ በመሆኑ በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ/ እና 671/2/ መሠረት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ሰው ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በፈፀሙት ከባድ ውንብድና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ክርክር ሲደረግ ቆይቷል።

 

ውሳኔ

በክርክሩ ሂደትም የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ከተሰማ በኋላ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቶ ሁሉም ተከሳሾች የመከላከያ ምስክር አቅርበው ያሰሙ ቢሆንም በዐቃቤ ሕግ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ባለመቻላቸው ምክንያት ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ላይ የጥፋተኛነት ፍርድ በመስጠት ከዚህ ቀደም ወንጀለኞቹ በ 14 ዓመት ተቀጥተው የነበረ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ ጠይቆበት በድጋሜ በተሻሻለ ውሳኔ መሠረት 1ኛ እና 3ኛ ተከሳሾች በ20 ዓመት፣ 2ኛ ተከሳሽ ደግሞ በ16 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ግንቦት 10 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You