
ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ የምትገኝ ግዙፍ ሀገር ነች። ግዙፍነቷ ከሕዝብ ብዛት እስከ ኢኮኖሚ ጥንካሬ ድረስ ይገለጻል። ከዲፕሎማሲ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እስከ ጠንካራ መከላከያ እና የጸጥታ ተቋማት ግንባታ ድረስ ይዘልቃል። የነጻነት ተጋድሎዋና እና የጥቁር ሕዝቦች አለኝታ መሆኗም ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ያጎላዋል።
ኢትዮጵያ ታሪካዊት ሀገር፤ ሕዝቧም የዚህ ታላቅ ጀብዱ ባለቤት ነው። ይህ ጀግና ሕዝብ የብሄር፤ የሃይማኖት፤ የጾታ እና ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ልዩነቶች ሳይበግሩት ወደ ዓድዋ በአንድነት በመትመም ቅኝ ገዢዎችን አሳፍሮ መልሷል። ለመላው ጥቁር ሕዝቦችም መከታ ሆኗል።
ዛሬም ይህ ኩሩ ሕዝብ ሌላ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛል። ኢትዮጵያ ከድህነት ተላቃ በምጣኔ ሃብት እድገት ለማስመዝገብ የተፈጥሮ ሃብቷን በተለይም የውሃና ኢነርጂ እምቅ አቅሟን ለማልማት ቆርጣ በመነሳት በትልቁ አባይ ወንዝ ላይ በራስ አቅም ግድብ ለመገንባት መጋቢት 24/2003 ዓ/ም ይፋ አደረገች። ይህ ታሪክ ከተጻፈ አስራ አራት ዓመታት አስቆጠረ።
የግድቡ ይፋ መደረግ የዘመናት ቁጭትና ወኔ ሊቋጭ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ ዓድዋ ጦርነት በመላው ሀገሪቱ ከተሞች አደባባይ በመውጣት በታሪክ ለመጀመያ ጊዜ ለልማት በድጋፍ ሰልፍ ከተሞች ተጥለቀለቁ። ሕዝቡ በያለበት አንድም ሰው የቀረ እስከማይመስል ድረስ ግልብጥ ብሎ በመውጣት “በተፈጥሮ ሃብታች መጠቀም ሉዓላዊ መብታችን ነው!” “ያለማንም ድጋፍ እና ብድር ተባብረን ዓባይን እንገድባለን!”፣ “ዓባይን በፍትሃዊነት በጋራ እንጠቀማለን!”፣ “ድሮም ተካፍሎ መብላት ባህላችን ነው!” ሲሉም በአደባባይ በመፈክር፣ በሆታ እና በዜማ ገለፁ።
ዓባይ ሁሉንም በጋራ አንድ አድርጎ በማሰለፉ ከልጅ እስከአዋቂ፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል፣ ሃብታም ድሐ ሳይል፣ ምንም አይነት የፖለቲካ፣ ብሄር፣ ቋንቋ፣ ባህል፣ ሃይማኖት፣ ወዘተ ልዩነት ሳያግደው ለግድቡ ድጋፍ ለማበርከት ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተሰለፈ።
ሠራተኛው ከወር ደሞዙ፣ አርሶ አደሩ ከምርቱ፣ አርብቶ አደሩ ከሚያረባቸው እንሰሳቱ፣ ነጋዴው ከንግዱ፣ ባለሃብቱ ከጥሪቱ፣ ምሁሩ በእውቀቱ፣ የኪነ ጥበብ እና ስነ ጥበብ ባለሙያው በሙያው፣ ተማሪው ከወር ቀለቡ፣ የቀን ሠራተኛ ከዕለታዊ ገቢው፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሰማራበት መስክ ከሚያገኘው ቆጥቦ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በመደገፍ ግንባታውን ጀምሮ ለመጨረስ ተነሳ።
በመላው ሀገሪቱ ያለው ሕዝብ ያለምንም የውጭ ሀገራት ብድርና ዕርዳታ በራሳችን አቅም ግድባችንን መገንባት እንችላለን ሲል ለግድቡ በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በዕውቀት፣ በሙያና በፐብሊክ ዴፕሎማሲ ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። የዓባይ ግድብን ላይ በራስ አቅም መሥራት የልማት ብቻ ሳይሆን የሉዓላዊነትና የማንነት ጉዳይ መሆኑን ሕዝቡ በተጨባጭ ድጋፍ አረጋገጠ።
የሀገር ውስጡን የሕዝብ የድጋፍ ማዕበል ተከትሎ በተለያዩ የውጭ ሀገራት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እና በትውልድ ኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ ልማት በጋራ በመነሳት ታላቁ የህዳሴ ግድብን መገንባት ሀገራዊ ግዴታ ነው ሲል፣ በገንዘቡ፣ በዕውቀቱ እና በፐብሊክ ዴፕሎማሲው መስክ ለሀገሩ አምባሳደር በመሆን ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ። ዲያስፖራው ለሀገሩ ግድብ ውጭ ምንዛሬ ቦንድ በመግዛም ሆነ በስጦታ ሲያበረክት ርቀትም ሆነ ድንበር አልገደበውም።
መላው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚገኙት ለግድቡ ያሳዩት የድጋፍ መነሳሳት ሰፊና ሁሉን አቀፍ በመሆኑ ይህን ድጋፍ ለማስተባበር የሚያስችል ሁሉን አቀፍ የሆነ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ተቋቋመ። በምክር ቤቱ በተቻለ መጠን በሀገር ውስጥ የሚገኙ የሲቪል ማኅበራ እና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች፣ ሙያ ማኅበራት እና ታዋቂ የሀገራችን ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ወዘተ… የተካተቱ ሲሆን የምክር ቤቱንም ተግባር ለማከናወን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት በደንብ ቁጥር 244/ 2003 ዓ/ም ተቋቁሞ ወደ ተግባር ተገባ።
የኅብረተሰቡ ድጋፍ በዓይነትም ሆነ በብዛት ሰፊ ከመሆኑ አንጻር ተሳትፎውን በዘላቂነት ለማስቀጠል እና በትክክል ለታለመለት ግብ እንዲውል ለማስቻል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ በተግባር ላይ በማዋል ለግድቡ በየወሩ ከደሞዝ ላይ እስከ አስር በመቶ እየቆረጡ በመደገፍ እግረ መንገድም የዜጎችን የቁጠባ ባህል ማሳደግ ተቻለ።
ለታላቁ ህዳሴ ግብ በብሄራዊ ደረጃ እና በክልሎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች በሚከናወኑ የንቅናቄ እና ሃብት ማሰባሰቢያ ሁነቶች ከሕዝብ በስጦታ የሚመጡ ልዩ ልዩ ድጋፎችን (የቀንድ ከብት ግመሎች፣ ሌሎች እንሰሳት፣ አዝርዕቶች፣ የቅባት እህሎች፣ ማዕድናት፣ ቁሳቁሶች፣ ወዘተ…) በገንዘብ ተለውጠው በልገሳ እንዲገቡ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። እስካለፈው ጥር ወር ድረስ በቦንድ ግዢ እና በስጦታ ባለፉት ዓመታት በአጠቃላይ ከሀገር ውስጥ 17 ቢሊዮን 994 ሚሊዮን 511ሺ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ዲያስፖራውም ከተለያዩ ዓለማት 1ቢሊዮን 502 ሚሊዮን 390 ሺ ብር በላይ ድጋፍ አድርጓል።
ኅብረተሰቡ በቦንድ ግዢ እና ልገሳ ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የተለያዩ ገቢ ማሰባሰቢያ እና ንቅናቄ መፍጠሪያ ሁነቶች በስፋት የተካሄዱ ሲሆን በተለይም በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ወገኖችን በቀላሉ ማሳተፍ እንዲቻል የ8100 -A የሞባይል አጭር መልዕክት ዕጣ ተዘጋጅቶ ለሶስተኛ ዙር በአየር ላይ በማዋል በአንድ መልዕክት ሶስት ብር በመላክ በአንደኛው እና በሁለተኛው ዙር ወደ 140 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል።
ለ8100 A እና ለተለያዩ ሕዝብ ተሳትፎ እንዲውሉ ከተለያዩ ድርጅቶችና ባለሃብቶች በልገሳ የተሰበሰቡ ከመኖሪያ ቤት እና ከዘመናዊ ተሽከርካሪዎች ጀምሮ በርካታ ዕጣዎችን ለደረሳቸው ዕድለኞች በመሸለም በርካቶች በህዳሴ ግድብ ገጸ-በረከት ተንበሽብሸዋል። ዕጣ ያልደረሳቸውም ቢሆኑ በግድቡ ላይ የጣት አሻራቸውን በማሳረፍ የታሪክ ባለቤት ሆነዋል። በአጠቃላይም መላው ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ ከ20 ቢሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ታሪካዊ ኃላፊነቱን ተወጥቷል።
በዓለማችን የተከሰተው የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገራችንም ስጋት በደቀነ ጊዜ ኅብረተሰቡን በማሰባሰብ የሚከናወኑ ሁነቶችን እና መድረኮችን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ከኮቪድ ስጋት ነጻ ሆኖ በጣቱ ሞባይሉን በመጫን በ8100-A ለግድቡ ቤተሰብ በመሆን 1 ብር ድጋፍ የሚያደርግበት አሠራር በሥራ ላይ በማዋል ሶስተኛው ዙር ከተጀመረበት የካቲት 2012 ዓ/ም እስከ ታህሳስ 2017 ድረስ) በዘላቂነት በመቀጠል ከፍተኛ ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል። በዚህም ባለፉት ዓመታት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ እያንዳንዱ ሞባይል ተጠቃሚ በየዕለቱ የሚያስታውሰው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ ተችሏል። ጽህፈት ቤቱ ባከናወናቸው 8100-A እና በልዩ ልዩ ሁነቶች በአጠቃላይ 1 ቢሊዮን 218 ሚሊዮን 997 ሺ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን ከቦንድ ሽያጭ እና ከስጦታ ጋር በድምሩ 20 ቢሊዮን 715 ሚሊዮን 899 ሺ ብር በላይ ከሀገር ውስጥና ከዲያስፖራው ድጋፍ ተሰባስቧል።
ባለፉት ዓመታት የሀገራችን አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች የታላቁ ህዳሴ ግድብን ጠቀሜታ በመረዳት ግድቡ ከተያዘለት የአገልግሎት ዘመን በላይ ተሻጋሪ እንዲሆን ግድቡን በደለል እንዳይሞላ በማለት በመላው ሀገሪቱ የተፋሰስ ልማት (የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ) ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ሕዝብና መንግሥት ለተፋሰስ ልማት ትኩረት እንዲሰጡ ማድረግ ተችለዋል።
ከግብርና ሚኒስቴር በመጣ መረጃ መሰረት አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በማለት በየዓመቱ በአማካኝ 30 ቀናት በተፋሰስ ሥራ ላይ ያዋለው ጉልበት በገንዘብ ሲተመን ከ120 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ግድቡ በሀገሪቱ ዕድገት ላይ ምን ያህል የለውጥ ተነሳሽነት እንደፈጠረ ማሳያ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ታላቁ የህዳሴ ግድብ በሚቃወሙት አካላት የሚነሱ ክሶች ስም ማጥፋቶችና አሉታዊ መረጃዎችን በመመከትና በመድፈቅ ኢትዮጵያውያን፣ በትውልደ ኢትዮጵያውን እና ወዳጆቻችን የሆኑትን በዓለም ዙሪያ በማስተባበር በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጫና በማሳደር የተሠራው ሥራም ለመደበኛ ዲፕሎማሲው ቀላል የማይባል እገዛ አድርጓል።
“አንድ ድምጽ ለግድባችን!” “One Voice for Our Dam!” በሚል በተለያዩ ሀገራት በተለያየ መንገድ ኢትዮጵያውን ለግድባቸው ድጋፋቸውን እንዲገልጹ በማድረግና ፒቲሽን ፊርማ በማሰባሰብ እንዲሁም ለግድቡ የድጋፍ ሰልፍ በማድረግ የምዕራባውያን ሀገራትን ከተሞች በማጨናነቅ ዲያስፖራው የሠራው በውጭ ሀገር ሆኖ ለሀገሩ የመቆም ተግባር በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖር፣ ትውልድን የሚያኮራ ታላቅ ገድል ነው። ለዚህም ነው እስከ የተ.መ.ድ ፀጥታው ምክር ቤት ድረስ ተከሰን በድል የወጣነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያዊ “ዓባይ የኔ ነው!” በሚል በባለቤትነት እየገነባው ያለ የግንባታውን ሂደት ለማየት የሚመኘው ግድብ ነው። በዚህ የተነሳ ቦታው ከመሃል ሀገር እጅግ ርቀት ቢኖረውም ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ እና ምሥራቅ ጫፍ ተነስተው በርካታ ዜጎች በቡድን እና በግል ጭምር ግድቡን ጎብኝተውታል። ዲያስፖራዎችም ባገኙት አጋጣሚ በቡድን ሆነው ግድቡን ጎብኝተዋል።
ከኢትዮጵያውያንም በዘለለ የግድቡ ዜና በመላው ዓለም የተናኘ በመሆኑ ከዓለም ዙሪያ በርካታ ጋዜጠኞች፣ ዲፕሎማቶች እና ከፍተኛ የሉዕካን ቡድኖች እና መሪዎች ግድቡ ድረስ በመሄድ አይተዋል፣ ተደንቀዋል፣ ከመደነቅም በላይ ግድቡ የማይቀለበስ እና ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን የተሰለፉበት፣ ለሀገሪቱ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ተረድተዋል። በዚህም ያለ ምንም ዓለም ዓቀፍ ድጋፍ ኢትዮጵያ በሕዝቦችዋ እና በመንግሥት የተቀናጀ ጥረት ማደግ እንደምትችል ግድቡ ራሱ መስክሯል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የውሃ ሃብቷ ተጠቅማ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ከምትገነባቸው ፕሮጄክቶች ግንባር ቀደም የሆነው ከላይ በተዘረዘሩትና ተነግረው በማያልቁ በርካታ ድጋፎች፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ያስነሳው የይቻላል ስሜት እና የድጋፍ ማዕበል ጭምር ነው። ግድቡ ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የዘመናት ቁጭትና ምኞታቸውን በትውልድ ቅብብሎሽ ያሳኩበት፤ ሲሆን ግድቡን ከጥንት ነገሥታት ጀምሮ ለመገደብ ሲያልሙት የነበረ፤ ግድቡ በአፄ ኃይለ-ስላሴ ቢጠናም፣ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ሙከራ ቢያደርጉም በአቶ መለስ ዜናዊ ግንባታው ተጀምሮ፣ በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመርህ ስምምነት ተፈርሞ፣ በዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የግድቡ ችግሮች ተፈተው ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ ነው። በዚህም የሀገራችን መሪዎች ግድቡን በቅብብሎሽ በመገንባት አሁን ለደረሰበት የፍጻሜ ደረጃ አድርሰውታል። ይህ ትውልድም ከመሪዎቹ ጎን በመሰለፍ ያለምንም ልዩነት ባለው ዓቅም ተረባርቦ ግንባታው በተግባር እውን እንዲሆን በማድረጉ በታሪክ ማህደር በትልቅ ስፍራ ተመዝግቦ ትውልድ በኩራት የሚዘክረው ባለ ታላቅ ገድል የሆነበት ልማት ነው፤፡
ሆኖም ግድቡ ተጠናቆ ለምርቃት በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅትም ቢሆን ግድቡን ዝና ለማውረድ የሚደረጉ ጥረቶች እና የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ርብርብ የሚያሳንሱ መረጃዎች ዛሬም ቢሆን አልጠፉም።
ኢትዮጵያ ፈተና የማያጣት ሀገር ነች። ሆኖም ለፈተና የማትንበረከከው ሀገር የታሰረችበትን ገመድ በጣጥሳ፤ የተከረቸመባትን በር በርግዳ፤ እሾህና አሜካላውን አስወግዳ ጠላቶቿን ማሳፈር ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። የዘመናት ቁጭት የነበረው የዓባይ ውሃ ተገድቦ ለኢትዮጵያም ለምሥራቅ አፍሪካም ብርሃን መሆን ጀምሯል። ጠቅላላ ሥራው ተጠናቆ ሙሉ ብርሃን ለመስጠትም የሚቀረው ሪባን መቁረጥ ብቻ ነው። ዐረቦቹ እንደሚሉት ውሻዎቹም ይጮሃሉ፤ ግመሎቹም ይጓዛሉ።
እስማኤል አረቦ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም