የዛሬው የወቅታዊ ገጽ እንግዳችን አቶ ፋሪስ መሀመድ ይባላሉ። የሳይበር ደህንነት ባለሙያ ናቸው። ራሳቸውን ቴክኖሎጂስት ብለው የሚጠሩት እንግዳችን አዲስ አበባ ውስጥ በቴክኖሎጂ ዙሪያ የሚሠራ ድርጅርት ከፍተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቆይታ አስተዳደጋቸውን፣ የሥራ ልምዳቸውን፣ የሳይበር ደህንነትን እና ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ጉዳዮችን ዳስሰናል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- አስተዳደግዎ እና የትምህርት ዝግጅትዎ ምን ይመስላል ?
አቶ ፋሪስ፡- ፋሪስ መሀመድ ሙባረክ እባላለሁ። እኔ ያለ አባት ያለ እናት ነው ያደግኩት። ፈረንጆች “ሰልፍ ሜድ ፕሮፌሽናል” ነው የሚሉኝ። እናቴ የተወለድኩ ቀን ከመንታ ወንድሜ ጋር ነው የሞተችው። አባቴ ደግሞ የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ ነው በሞት የተለየኝ። አባቴ ከመሞቱ በፊት ተማር ልጄ እያለ የትምህርት ፍላጎትን በውስጤ ተክሎብኝ ነው የሞተው። ይሄ የአባቴ ምክር እስካሁንም ድረስ የሚነዳኝ ኃይል ነው። ማንበብ እወዳለሁ። በትምህርቴም ጎበዝ ነበርኩኝ።
ከኢትዮጵያ የወጣሁት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው። 11ኛ ክፍል የደረስኩት ግን 7ኛ እና 8ኛን እንዲሁም 9ኛ እና 10ኛ የክፍል ደረጃዎችን በአንድ ዓመት በመማር ነበር። 11ኛ ክፍል ሦስት ቀን እንደተማርኩ ወደ ውጪ እንደምወጣ ተነገረኝ። ወዲያውኑ ከጎሬ ሃይስኩል አዲስ አበባ መጥቼ በሶስት ሳምንት ውስጥ ወደ ቡልጋሪያ ተጓዝኩ።
ከሀገሬ የወጣሁት በ16 ዓመቴ ነው። ኢንዱስትሪያል ኤሌክትሮኒክስ ለመማር ነው ወደ ቡልጋሪያ ያመራሁት። በቡልጋሪያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት ኢንዱስትሪያል ኤሌክትሮኒክስ ትምህርቴን አጠናቅቄያለሁ። ከዚያ የቡልጋሪያ መንግሥት ነጻ የትምህርት ዕድል ሰጥቶኝ ሬዲዮና ቴሌቪዥን አጥንቼያለሁ። በአውሮፓውያኑ 1989 ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ሁሉ ነገር ወደ ጦር ግንባር የሚባልበት ጊዜ ስለነበር ትንሽ ቆይተህ ብትመጣ ይሻላል የሚል ምክር ተሰጥቶኝ ወደ ቡልጋሪያ ተመለስኩ።
ከዚያ ቀጥሎ ለሥራ ጉዳይ ወደ እንግሊዝ ሀገር ተጉዤ ሳልመለስ እዚያው ቀረሁ። እንግሊዞች በውጭ ዲግሪ ሥራ ስለማይሰጡ እንደገና እንደ አዲስ ዲግሪዬን መማር ነበረብኝ። በኤሌክትሮኒክስ እና ዳታ ኮሙኒኬሽን ዲግሪ ያዝኩኝ። ከዚያም በኢንፎርሜሽን ሲስተምስ ኢንጂነሪንግ ማስተርስ ሰርቼ ሥራ ጀመርኩኝ። እንግሊዝ ሀገር 31 ዓመታት ኖሬያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- እንግሊዝ ሀገር በቆዩባቸው 31 ዓመታት የነበርዎ የሥራ ልምድ ምን ይመስላል?
አቶ ፋሪስ፡- 24 ዓመታትን በሥራ ስላሳለፍኩ ብዙ የኢንዱስትሪ ልምድ መቅሰም ችያለሁ። እኔ ቴክኖሎጂስት ነኝ። የሳይበር ደህንነትና የአይሶ ስታንዳርድ ከፍተኛ ባለሙያ ነኝ። እንግሊዝ ሀገር የመጀመሪያ ዲግሪዬን ሰጨርሽ አንድ የአሜሪካ ካምፓኒ ቀጥሮኝ አንድ ዓመት እንደሠራሁ ተዘጋ። በሥራ ጉዳይ እንገናኝ ስለነበር የብሪትሽ ቴሌኮም ኢንጂነሮች ስለሚውቁኝ በሁለት ሳምንት ውስጥ ቀጠሩኝ። ብሪትሽ ቴሌኮም አምስት ዓመታት አገልግያለሁ። ከዛም ፈተና ወስጄ ፈቃድ ካገኘሁ በኋላ የራሴን አማካሪ ድርጅት ፈጠርኩ። ይህ ካምፓኒም አሁንም በለንደን ይገኛል።
ከብሪትሽ ቴሌኮም ወጥቼ የራሴን አማካሪ ድርጅት ማቋቋሜ ትልቅ ዕድል ፈጠረልኝ። በጣም ትልቅ ስም ባላቸው ፕሮጀክቶች ላይ የመሥራት ዕድል ገጠመኝ። የመጀመሪያው ፕሮጀክት ሆላንድ ሀገር የሚገኙ ዳታ ሴንተሮችን ኦዲት ማድረግ ነበር። ከለንደን እያመላለሱኝ ሥራውን አጠናቀቅኩኝ። ቀደም ሲል ቀጥረውኝ በወር ይከፍሉኝ የነበሩት ብሪትሽ ቴሌኮሞች ሁለት ጊዜ እንደ ኮንትራክተር በከፍተኛ ደሞዝ ቀጥረውኝ አብሬያቸው ሠርቻለሁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያርፍበት የሂትሮ አየርመንገድ ተርሚናል ሁለት፣ ፈርሶ እንደ አዲስ ሲሠራ እንደ አማካሪ ተቀጥሬ ለሁለት ዓመት 12 ኢንጂነሮችን ሜንቶር አድርጌ የተለያዩ የኮሙኒኬሽን እቃዎችን በመዘርጋት እና የሴኪዩሪቲ ሲስተሞችን ሴት አፕ በማድረግ ሰርቻለሁ። ቀጥሎም ዩናይትድ ኪንግደምን የመሰረቱትን አየርላንድ፣ ስኮትላንድ፣ ዌልስ እና ብሪታንያን የሚያገኛኝ የ17 ነጥብ አምስት ቢሊየን ፓውንድ ፈጣን ባቡር ፕሮጀክት ላይ እንደ አንድ ኮንትራክተር በመሳተፍ ልምድ አግኝቻለሁ።
በዚያው በእንግሊዝ ሀገር ሦስት ከፍተኛ ሆስፒታሎችን የሳይበር ሴኪዩሪቲ እና ኢንፎርሜሽን አሹራንስ መርቻለሁ። ሥራዬ የነበረው በሆስፒታሎቹ ላይ ምን ያህል የሳይበር ጥቃቶች እንደተሞከሩና እንዴት ማቆም እንደሚቻል የሚገልጽ መረጃን ለቦርድ ሪፖርት ማድረግ ነበር። በዓለማችን በጣም ከፍተኛ የሳይበር ጥቃት ከሚደርሱባቸው ዘርፎች አንዱ ጤና ነው። የሰዎች የማንነት ስርቆት የሚመነጨው ከሆስፒታሎች አካባቢ ነው። ያንን ለመከላከል የጤና ዘርፉ ከፍተኛ የሳይበር ሥራ ይሠራል። ስለዚህ እኔም ለሦስት ዓመታት የሳይበር ሴኪዩሪቲ እና ኢንፎርሜሽን አሹራንስ አማካሪ ሆኜ ብዙ ረድቻቸዋለሁ።
ከአዘርባጃን ወደ ቱርክ የተፈጥሮ ጋዝ ለማመላለስ በተወጠነ ፕሮጀክት ላይም በንድፍ ከተሳተፉት ኢንጂነሮች አንዱ ነኝ። በሌሎችም ፕሮጀክቶች ላይ ተሳትፌያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በሀገርዎ ለመኖር ወስነው የተመለሱት በሙያዎ አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው ?
አቶ ፋሪስ፡- እኔ ሀገሬን በጣም እወዳታለሁ። ከ40 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ስመጣ የተደላደለ ኑሮ ይገጥመኛል ብዬ አልመጣሁም። ስለዚህ ተዘጋጅቼ ነው የመጣሁት። ሀገሬ የዋለችልኝን ውለታ ለመመለስ ብዬ ነው የመጣሁት።
አዲስ ዘመን፡- ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንጻር አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ደረጃ እንዴት ይገመግሙታል ?
አቶ ፋሪስ፡- በኢትዮጵያ መኖር ከጀመርኩ አራት ዓመታት ሆኖኛል። በእነዚህ ጊዜያት ያየኋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ሀገራችን ላለችበት የቴክኖሎጂ ደረጃ ማንንም መቀየም ወይም መውቀስ አንችልም። አሁን የምናያቸው አሜሪካን፣ እንግሊዝን እና ካናዳን የመሳሰሉ ሀገሮችም ከዚህ የባሰ ሁኔታ ውስጥ ነበሩ። ስለዚህ አሁን እኛ ያለንበት ደረጃ የሚለወጥ ነው። ነገር ግን ሰው ላይ መሥራት አለብን። ኢትዮጵያ ውስጥ የሥራ ባሕል ብልሽት አለ። ያንን ማስተካከል ይኖርብናል።
ሌላው የትምህርት ሥርዓታችን ማሽቆልቆል ላሉብን ችግሮች ምክንያት ሆኗል ብዬ ነው የማስበው። እኔ ተማሪዎችን ስጠይቅ የመማር ፍላጎት የላቸውም። ምክንያታቸውን ሲጠየቁ የተማሩት የት ደረሱ የሚል መልስ ይሰጣሉ። እንደዚህ አይነት የአመለካከት ችግር አለ። ሀገራችን ሀብታም ሀገር ናት፤ ነገር ግን ሰው ላይ መሠራት አለበት። የሰዓት አያያዛችንም በጣም የተበላሸ ነው። ቴክኖሎጂና ሰዓት ጓዳኛ የላቸውም፤ ሁለቱም አብሯቸው የሚጓዘውን ነው ይበልጥ መጥቀም የሚችሉት። አንተ ትናንት ማከናወን የነበረብህ ነገር ኖሮ ሳትፈጽመው ብትቀር፣ ጊዜ ጓደኛዬ ነህ ብሎ ወደ ኋላ ተመልሰህ እንድትጠቀምበት አይፈቅድልህም። ቴክኖሎጂም እንዲሁ አብጠርጥሮ የሚያውቀውን እና በቅርብ ርቀት የሚከተለውን ነው የሚጠቅመው።
በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የምመክረውና የምማጸነው ሰዓት በጣም አስፈላጊ ስለሆነ አታጥፉት ተጠቀሙበት የሚለው ነው። የአበሻ ቀጠሮ የሚባለውን ነገር እኔ እንደ ካንሰር በሽታ ነው የማየው። እንዳናድግ ከሚያደርጉን ነገሮች አንዱ ይሄ የአበሻ ቀጠሮ የሚባለው ከጊዜ አጠቃቀም ጋር የተያያዘ አሉታዊ አመለካከት ነው። እሱን ማስወገድ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- በሀገራችን በቂ የሚባል የሳይበር ደህንነት ግንዛቤ አለ ብለው ያምናሉ ?
አቶ ፋሪስ፡- በሳይበር ደህንነት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው አፍሪካ ብዙ ችግሮች አሉ። አፍሪካ ውስጥ ወደ ዘጠና ፐርሰንት የሚጠጉ ቢዝነሶች የሳይበር ዝግጅት የላቸውም። ቢዝነስ በምንሠራበት ጊዜ ለሳይበር ጥቃት የምንጋለጥባቸው መቶ ቀዳዳዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ እንደ ቢዝነስ ሰው መቶውንም ቀዳዳዎች መሸፈን መቻል አለብን። አንዲት ቀዳዳ ከቀረች ለሳይበር ወንጀለኞች በቂ ናት። ከዚህ ተነስተው የሳይበር ተመራማሪዎች እየደመደሙ ያሉት ነገር ምንድን ነው፣ አፍሪካ በቅርብ ጊዜ የሳይበር ወንጀለኞች መራቢያ ትሆናለች የሚል ነው። እንደተባለው አፍሪካ የሳይበር ወንጀለኞች ማዕከል ከሆነች ትልቅ ችግር ውስጥ ነው የምንገባው።
በዓለም ላይ ሁለት አይነት ጦርነት ነው ያለው። አንደኛው በጦር መሳሪያዎች የሚካሄደው ጦርነት ነው። ሌላው የሳይበር ጦርነት ነው። የሳይበር ጦርነቱ በጣም አደገኛና አስጊው ነው። ምክንያቱም ድንበር የለውም። ማንም ሰው ከየትም ሆኖ ወንጀል ለመሥራት ስለሚችል ምርመራ ለማድረግም በጣም ከባድ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ በምናይበት ጊዜ እኔ ከአራት ዓመታት በፊት ስመጣ የነበረውና ዛሬ ያለው የሳይበር ወንጀል በጣም ተራርቋል። ወደ ዲጂታላይዜሽን እያመራን በመጣን ቁጥር የሳይበር ጥቃት እየጨመረ መጥቷል። ቅርብ ጊዜ ለሕግ ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቼ ነበር። ፍርድ ቤት በብዛት ከሚመጡት ፋይሎች አንዱ ይህን ያህል መቶ ሺህ ብር ተሰረቅን የሚል ነው።
ሕብረተሰባችን ያለው የሳይበር ግንዛቤ በጣም ዝቅተኛ ነው። በዚህ ረገድ ሁለት ችግር ነው ያለው። አንደኛ የቢዝነስ መሪዎች ስለሳይበር ግንዛቤ የላቸውም። ብዙዎቹ አሁንም ሰራተኞቻቸውን የሳይበር ግንዛቤ እንዲኖራቸው ሲያደርጉ አይታዩም። በእርግጥ በየጊዜው የሚታዩ መሻሻሎች አሉ። ነገር ግን ከሳይበር ወንጀል መርቀቅና መስፋፋት አንጻር ሰፊ ዝግጅት ያስፈልገናል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ያሉበት ደረጃ እንዴት ያለ ነው ?
አቶ ፋሪስ፡- በጥንቃቄ ረገድ ብዙ ይቀረናል። ሰዎችም ሆነ የግለሰቦች መረጃ አጠባበቅ ላይ ገና ነን። አውሮፓውያን በ2016 ያጸደቁት ጂዲፒአር (ጀነራል ዳታ ፕሮቴክሽን ሬጉሌሽን) የሚባል ሕግ አለ። በዚህ ሕግ መሰረት የአንድ ካምፓኒ ኮምፒዩተር ኔትዎርክ ተሰብሮ የደንበኞቹ መረጃ ከተሰረቀ የሀገሪቱ ኢንፎርሜሽን ኮሚሽን ቢሮ የገቢህን አራት በመቶ ሊቀጣው ይችላል። ታዲያ ዝም ብሎ መጥቶ አይደለም የሚቀጣው ካምፓኒው ምን አይነት ጥንቃቄ ያደርግ እንደነበር ተፈትሾ ማድረግ የነበረበትን ጥንቃቄ ሳያደርግ ከቀረ ብቻ ነው ቅጣቱ የሚተላለፍበት።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አንድ ችግር አንዳንድ ሰዎች እኛ ያላደግን ድሃ ሀገር ነን ማን ነው የሚፈልገን ሲሉ እሰማለሁ። የሳይበር ወንጀለኞች በቅርብ ያለውን ፍሬ ነው የሚፈልጉት። መንግሥት አሁን ጥሩ ርምጃ ወስዷል። የኢትዮጵያ ዳታ ጥበቃ አዋጅ ቅርብ ጊዜ ወጥቷል። አዋጁ እንዴት ሥራ ላይ እንደሚውል የሚገልጸው ዝርዝር መመሪያ የወጣ አልመሰለኝም። ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያው ሲወጣ በተለያየ ሴክተር ውስጥ ያሉ ድርጅቶች ማድረግ ያለባቸው ጥንቃቄ ተጠቅሶ ሥራ ላይ ይውላል ብዬ እጠብቃለሁ። ያ በሚሆንበት ጊዜ አሁን ከምናደርገው ጥንቃቄ የተሻለ ጥንቃቄ ይኖረናል።
አሁን ዓለም ላይ ዳታ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። የባንክ፣ የትምህርት ተቋማትና የወታደራዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ ዳታዎች በሳይበር ወንጀለኞች እጅግ ተፈላጊ ናቸው። ስለዚህ መንግሥት ሁኔታውን ተረድቶ ሕግ አውጥቷል። ስለዚህ ጥሩ መንገድ ይዘናል። ደጋግሜ እንዳልኩት ግን ያደረግነውና እያደረግን ያለነው በቂ አይደለም። የሳይበር ዘርፍ በዓለም ላይ ሦስተኛው ኢኮኖሚ ሆኗል። አንደኛ አሜሪካ ሁለተኛ ቻይና ሶስተኛ ሳይበር ነው። መልቲ ትሪሊየን ኢኮኖሚ ነው የሚንቀሳቀስበት።
አሁን ደግሞ ኤአይ መጥቷል። ኤአይ ጥቅምም ጉዳትም አለው። ለእኛ ብዙ ጥቅም እንዳመጣልን ሁሉ ለሳይበር ወንጀለኞችም ሁኔታዎችን አቅሏል። ከዚህ ቀደም አንድ ካምፓኒ በሳይበር ወንጀለኞች ከመጠቃቱ በፊት ተቋሙ ያለው አጠቃላይ እሴትን የሚያሳይ መረጃ መሰብሰብ ይጠይቅ ነበር። አሁን ይሄን ጊዜ የሚወሰድ ነገር ኤአይ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ነው የሚሠራው። ለሳይበር ወንጀለኞች ብዙ ጥቅም እየሰጠ ነው ማለት ነው። ስለዚህ በየጊዜው ራሳችንን ከቴክኖሎጂው ጋር እያዘመንን መቀጠል ስንችል ነው የሳይብር ስጋትን የምንቀንሰው።
አዲስ ዘመን፡- ተቋማትም ሆኑ ዜጎች ምን አይነት ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው ?
አቶ ፋሪስ፡- የሳይበር ንጽህና እንደ ሰውነት ንጽህና ነው። ሰው ጠዋት ታጥቦ ካልወጣ ንጽህና አይሰማውም። የሳይበር ንጽህናም እንደዚህ በየቀኑ የሚደረግ መሆን አለበት። የምንጠቀምባቸው ስማርት ፎኖች፣ ላፕቶፖች፣ ኮምፒተሮችና የተለያዩ ነገሮች በጥንቃቄ መያዝ አለባቸው።
ለማኅበራዊ ድረገጾች፣ ለተለያዩ ኢሜሎች እና ለባንክ የምንጠቀማቸው የይለፍ ቃሎቻችን በጥንቃቄ መዘጋጀት አለባቸው። በተለይም አንድ የይለፍ ቃል ለተለያዩ ነገሮች መጠቀም ማቆም አለብን። ምክንያቱም የሳይበር ወንጀለኞች አንድ የይለፍ ቃል ካገኙ በግለሰቡ የተለያዩ አካውንቶች ላይ ሙከራ ያደርጋሉ። ብዙ ጊዜ ደግሞ ይሳካላቸዋል። ምክንያቱም ሰዎች በስንፍና አንድ የይለፍ ቃልን ለብዙ ነገር ይጠቀማሉ። ይሄ ልማድ መወገድ አለበት። በተጨማሪም የይለፍ ቃል ስናዘጋጅ የሚስት፣ የባል እና የልጅ ወይም ለእኛ ቅርብ የሆነን ነገር ስም መጠቀም የለብንም።
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ካሉት የሳይበር ወንጀሎች አንዱ ስልክ እየደወሉ ከቴሌ እና ከንግድ ባንክ ነው በማለት መረጃዎችን በመጠየቅ የሚያገኙትን መልስ በመጠቀም ከአካውንት ላይ የገንዘብ ሥርቆት መፈጸም ነው። ዜጎች ከቴሌም ሆነ ከንግድ ባንክ ደውሎ የሚስጥር ቁጥራቸውን የሚጠይቅ አካል እንደሌለ ማወቅ አለባቸው።
ሌላው ሀገራችን ውስጥ እየታየ ያለው የሳይበር ወንጀል አይነት በእንግሊዝኛ ሶሻል ኢንጂነሪንግ የሚባለው ነው። ሶሻል ኢንጂነሪንግ ወንጀለኞች የሰውን ብሬን ወሽ አድርገው ግለሰቡ መጠበቅ ያለበትን መረጃ ፈልቅቀው የሚያወጡበት ዘዴ ነው። ስማርት ስልኮቻችንም ሆኑ ሌሎች የኮሙኒኬሽን እቃዎቻችን በአካል እንዳይሰረቁም ጥንቃቄ ማድረግ መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ለማረጋገጥ ስለሚሠራው ሥራ ምን ይላሉ ?
አቶ ፋሪስ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋማትን የሳይበር ደህንነት ለመጠበቅ ብዙ ሥራ እየሠራ ነው። ነገር ግን በቂ አይደለም። ከላይ እንደገለጽኩት ወንጀለኞች አንድ ቀዳዳ ነው የሚፈልጉት። ስለዚህ ሕብረተሰቡን በሰፊው ማስታጠቅ አለብን። ኢንሳዎችም ባላቸው አቅምና ቴክኖሎጂ ጥሩ ሥራዎችን እየሠሩ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ጉዳይ ላይ ንቃት ስላላቸው ባጣም ግፊት እያደረጉ ያሉ ይመስለኛል። ሆኖም ግን በቂ ሊሆን አይችልም።
በሳይበር ደህንነት በኩል ያለብን ችግር እየተቀረፈ ሊሄድ የሚችለው የግሉ ዘርፍና የመንግሥት የጋራ ትብብር መድረክ ከተመሰረተ ብቻ ነው የሚል እምነት አለኝ። በውጪው ዓለም ብዙ የሳይበር ደህንነት ሥራዎች በግል ድርጅቶች ነው የሚሠሩት። ይህ የሚሆንበት ምክንያት አለው። የግል ድርጅቶች ንግድ ነው የሚሠሩት ስለዚህ ሪሶርስ አላቸው። እንዲሁም ራሳቸውን ለሥራው ሰጥተው ነው የሚሠሩት ብዬ አምናለሁ። በአንጻሩ የመንግሥት ተቋማት ዘንድ የበጀት እጥረት አለ። በተጨማሪም በሚፈለገው አቅም የሚፈገለውን ሥራ መሥራት የሚያስችላቸው ብቃት ያላቸው አይመስለኝም።
ስለዚህ ሁነኛው መፍትሄ በሌሎች ሀገራት እንደሚደረገው የመንግሥትና የግሉን ዘርፍ ጥምረት አስፍቶ መቆጣጠርና መመሪያ መስጠት እንጂ መንግሥት ሥራው ብቻውን መወጣት አይችልም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- በአዲስ አበባ የከፈቱት የቴክኖሎጂ አማካሪ ድርጅት ምንድን ነው የሚሠራው ?
አቶ ፋሪስ፡- በአዲስ አበባ የከፈትኩት ድርጅት ሰኪዩር ቴክኖሎጂ ይባላል። ሦስት ሥራዎችን ነው የሚሠራው። አንደኛ ከሳይበር ደህንነት መሰረታዊ መርሆች ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ደረጃ ድረስ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን። የግልም ሆነ የመንግሥት መሥሪያቤቶች ሠራተኞች ስለሳይበር ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤው እንዲኖራቸው እናደርጋለን። ሀገራችን የምታወጣውን የውጭ ምንዛሬ የሚያስቀር ባንኮችን ጨምሮ ለተለያዩ ተቋማት አመራሮች ከፍተኛ የሳይበር ደህንነት ሥልጠናም እንሰጣለን። እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መብራት ኃይል እና ውሃ ልማት ያሉ ተቋማት ሊኖራቸው የሚገባውን ከፍተኛ የሆነ የሳይበር ባለሙያ እናሰለጥናለን።
ሁለተኛው ሥራችን የማማከር ሥራ ነው። የማማከር ሥራ የምንሠራው አይሶ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ላይ ነው። አይሶ ስታንዳርድን በምሳሌ ብናየው ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረተ ባቡር ኬኒያ ወይም ደቡብ አፍሪካ በተሠራ ሀዲድ ላይ መሄድ ይችላል ወይ የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ ነው። አሁን የውጭ ኢንቨስተሮች በወጪና ገቢ ምርቶች እንዲሠማሩ ተፈቅዶላቸው ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው። እነዚህ ኢንቨስተሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ ለመሥራት በሚመጡበት ጊዜ ሁለት ነገሮችን ነው የሚያዩት። መጀመሪያ ይህች ሀገር የሳይበር ደህንነት አቋሟ ምን ይመስላል የሚለው ነው። ሁለተኛው የጥራት ጉዳይ ነው። አይሶ 9ሺ አንድ የምንለው ጥራት ላይ እንዴት ነው የሚሠሩት የሚለውን ይመለከታሉ። እኛ በዚህ ዙሪያ ሥልጠናዎችን በመስጠትና ትግበራውንም በመሥራት ተቋሞችን ለሰርቲፍኬት እናበቃለን። ሦስተኛው ሥራችን እንደ ማንኛውም የቴክኖሎጂ ድርጅት ፕሮጀክቶችን መምራት ነው። የአይሲቲ ፕሮጀክቶችን እንሠራለን።
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽን ጎዳና ላይ እያደረገች ያለችውን ጉዞ እንዴት ተመለከቱት ?
አቶ ፋሪስ፡- ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን መያዟ እሰይ የሚያሰኝ ነገር ነው። ዲጂታል ኢኮኖሚ ሶስት ምሦሶዎች አሉት። አንደኛው መሰረተ ልማት ነው። መሰረተ ልማት በኮምፒዩተር ኔትዎርክ እና በኃይል አቅርቦት ነው የሚመነዘረው። አሁን በቂ የኮምፒዩተር ኔትዎርክ ስለመኖሩ ብንጠየቅ አፋችንን ሞልተን ለመመለስ እንቸገራለን። በኃይል አቅርቦት ረገድም በስርጭት መሰረተ ልማት ላይ ውስንነቶች አሉ። ለአንድ ዲጂታል ኢኮኖሚ መንቀሳቀስ የቴሌኮም መሰረተ ልማት የመጀመሪያው አስቻይ ሁኔታ ነው።
ሁለተኛው ኢ-ቢዝነስ ነው። አሁን የተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ኢ-ቢዝነስን በጥሩ ደረጃ ጀምረዋል። ይሄ የሚበረታታ ቢሆንም በቂ አይደለም። ሦስተኛው ኢ-ኮሜርስ ነው። ኢ-ኮሜርስ ማለት እያንዳንዱ አምራች ምርቱን ኦን ላይን መሸጥ የሚችልበት ሥርዓት ነው። እነዚህ ሶስቱ ምሶሶዎች ናቸው ዲጂታል ኢኮኖሚን ከግቡ የሚያደርሱት።
ለቴክኖሎጂ ቅርብ መሆኑም አንዱ ቁልፍ አካል ነው፡ እንደ አጠቃላይ የያዝነው መንገድ ደስ የሚያሰኝ ነው። ብዙ ካምፓኒዎች ብዙ ነገር እየሠሩ ነው። ነገር ግን ደግሞ ገና ይቀረናል። ሀገራችን ትልቅ ናት። 130 ሚሊየን ሕዝብ ነው ያለን። ይህን ያህል ቁጥር ላለው ሕዝብ ኢትዮቴሌኮም ወይም ኢንሳ ብቻ በቂ አይሆኑም። የሕብረተሰቡን ጥርቅም እወቀት የሚፈልግ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ማኅበረሰብ ለቴክኖሎጂ ዝግጁ ነን ይባላል፤ ይስማማሉ ?
አቶ ፋሪስ፡- ሕብረተሳባችን ለቴክኖሎጂ ቅርብ አይደለም። ይሄ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ቀላል ምሳሌ ብሰጥህ በቅርቡ መንግሥት ነዳጅ በቴሌ ብር እንዲከፍል አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር። ከቴክኖሎጂው አጠቃቀም ጋር በተያየዘ መዘግየት ለሦስትና አራት ሳምንታት በነዳጅ ማደያዎች ረጃጅም ሰልፍ ይታይ ነበር። ሰዎች መቶ ሺህ ብሮች የሚያወጡ ውድ ስማርት ስልኮችን እየተሸከሙ ጭምር መተግበሪያውን አውርደው በትክክል ለመጠቀም ሲቸገሩ ነበር። ይሄ የሚያሳየው ለቴክኖሎጂ ቅርብ አለመሆናችንን ነው። ከቴክኖሎጂ ርቀን መኖር አንችልም ጊዜው አይፈቅድም። የሰው ልጆች ከቴክኖሎጂ ጋር ፍቺ የለሌለው ጋብቻ አድርገናል።
ዛሬ ባደጉ ሀገራት ብዙ የሰው ልጅ እንቅስቃሴዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ ናቸው። ይሄ ወደ ኢትዮጵያም እየመጣ ነው። ስለዚህ ሕብረተሰባችን ራሱን ለቴክኖሎጂ ክፍት ማድረግ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍላችን ስም ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ!
አቶ ፋሪስ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም