
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ማኦ ተሾመ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። ከምክትል ኮሚሽነሩ ጋር ባደረግነው ቆይታ የድሬዳዋ ፖሊስ መምሪያ ስላከናወናቸው የሪፎርም ሥራዎች፣ የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስከበር እያደረጋቸው ስላሉት እንቅስቃሴዎች፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወንጀልን ለመከላከል የተቀየሱ አሠራሮችን እና ሌሎች ጉዳዮችን ዳስሰናል።
አዲስ ዘመን፡- የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የጸጥታ ተቋማት እንዲያልፉበት በተደረገው ሪፎርም ሂደት ውስጥ ከመግባቱ በፊት የነበረው አቋም ምን ይመስል ነበር?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- የጸጥታ ተቋማት ከለውጡ በፊት በተለይ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር አንጻር ይከተሉት የነበረው የአሠራር ዘዴ በማኅበረሰቡ የተወሰኑ ቅሬታዎች ይታይበት ነበር። የለውጡ መንግሥት በጸጥታ ተቋማት ላይ የሪፎርም ስትራቴጂ ቀርጾ በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የጸጥታ ተቋማት በሪፎርም ሂደት ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል።
የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽንም እንዲሁ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በጸጥታ ተቋማት ሪፎርም ውስጥ ቆይቷል። አሁን የመጡ ለውጦችን ከማየታችን በፊት በድሬዳዋ ከተማ ምን አይነት ሁኔታዎች ነበሩ የሚለውን ነገር ብናይ ስለመጣው ለውጥ ግልጽ ምስል ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።
ድሬዳዋ ከተማ ከስድስትና ሰባት ዓመታት በፊት ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ ነበረች። ነዋሪዎቿ በሰላም ወጥተው መግባት የማይችሉበት፤ አጠቃላይ ድሬዳዋ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበት የንግድ እንቅስቃሴ የተዳከመበት፤ ኢንቨስትመንት የቀነሰበት እና ከተማዋ ላይ ውጥረት የነገሰበት ሁኔታ ነው የነበርው።
ይሄ ችግር የተለያዩ ምክንያቶች ነበሩት። በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ አንዱ ነው። ሌላው ምክንያት የነበሩት የጸጥታ ተቋማት የጸጥታ ችግሮችን የሚፈቱበትና የሚመሩበት አሠራር ኃይል የተቀላቀለበትና ማኅበረሰቡን የሚያስቆጣ ስለነበረ ችግሩን ከመቆጣጠር ይልቅ እየተባባሰ እንዲሄድ በማድረግ ሕጻናትና ወጣቶች ሰለባ እንዲሆኑ ያደረገ ነበር። ስለዚህ ቅድሚያ ትኩረት መሰጠት ያለበት ተቋሙን ለመፈተሽና በአዲስ መልክ ለማደራጀት ነው የሚል አቋም ተወስዷል።
ቀጥሎ ከዚህ ቀደም ተቋሙን ይመሩ የነበሩ አመራሮች በመንግሥት ውሳኔ እንዲነሱ ተወስኖ አዲስ የማኔጅመንት ቡድን እንዲዋቀር ተደርጓል። አዲሱ የማኔጅመንት ቲም አጠቃላይ የከተማውን ሁኔታ በአግባቡ ከፈተሸ በኋላ በተለይ ሰራዊቱ የተደራጀበት አግባብ፣ ያለው ሕግ የማስከበር አቅም እንዲሁም ከማኅበረሰቡና ከራሱ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ያለው ግንኙነት ችግር ያለበት መሆኑን መረዳት ተችሏል። ስለዚህ በሰራዊቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን እና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ያሉንን ግንኙነቶች ከፈተሽን በኋላ ሪፎርም ልናደርግባቸው የሚገቡ መሰረቶችን ለይተናል። የሪፎርም ሥራ እንዲሠራባቸው የተለዩት ከግንኙነት፣ ከአሠራር፣ ከቴክኖሎጂ መጠቀምና ሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- በሪፎርም ሥራው እንዴት ያሉ ማሻሻያዎች ተደረጉ ?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡-መሰረታዊ ሥራዎች ሊሠሩባቸው የሚገቡ አካባቢዎች ናቸው ያልናቸውን ከለየን በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ ነው የገባነው። ይንን ስናደርግ ግን በቅድሚያ ሰራዊቱ ውስጥ ያሉትን ችግሮች የማጥራት ሥራዎች ተሠርተዋል። የሪፎርም ሥራ እንዲሠራባቸው በተለዩት በእያንዳንዱ ችገሮች ላይ የአደረጃጀትና የአሠራር ችግሮችን አስተካክለናል። የሪፎርም ሥራው ከተሠራ በኋላ በከተማዋ ውስጥ የጸጥታ ሁኔታ ተሻሽሏል። ከዚያም ባሻገር ሕብረተሰቡ ራሱ ጸጥታን ለማረጋገጥና የሕግ የበላይነት እንዲመጣ ለማድረግ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለሆነ ከሕበረተሰቡ ጋር ያለን ግንኙነት ጥሩ እየሆነ በመምጣቱ ራሱ ማኅበረሰቡ በጸጥታ ሥራ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ተሳትፎ እያደረገ መጥቷል። በዚህ ምክንያት ፖሊስም የማኅበረሰቡን ተሳትፎና ተነሳሽነት ይበልጥ ማጠናከር ችሏል።
ከዚህ ቀደም እንደማሳያ ሃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ ፖሊስ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ይገባ ነበር። በተለይ የጥምቀት በዓል ላይ በአንድ ወቅት የተፈጠረው ችግር የብዙ ወጣቶች ሕይወት አልፎ የሃይማኖቶችን መቻቻል ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ያንን ሁኔታ ቀልብሰን የሙስሊሙ ማኅበረሰብ የክርስትናን በዓላት እንደራሱ ተቀብሎ ድጋፍ አያደረገ የሚያከብርበትን እንዲሁም የክርስትና እምነት ተከታዩም የሙስሊም በዓላት ላይ ምዕመናኑ ከመስኪድ ሲመለሱ መንገድ ላይ ውሃና ቴምር የሚሰጥበትን ሁኔታ ፈጥረናል። ከዚህ ቀደም የነበረው ሁኔታ ግን ይሄ አልነበረም። ስለዚህ ማኅበረሰቡን ይበልጥ ወደ ፖሊስ እንዲቀርብ ማድረጋችን እና ለግጭት ተጋላጭ የሆኑትን ወጣቶች በአግባቡ መጠቀማችን አሁን የሚታዩት የሰላምና የጸጥታ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩና ውጤታማ እንድንሆን አድርጎናል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን፡- ወንጀልን በመከላከል ረገድ ከአጎራባች ክልሎች ጋር እንዴት ነው በቅንጅት የምትሠሩት?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- በአጎራባች ክልሎች የሚፈጠሩ ችግሮች እኛንም መንካታቸው አይቀርም። ለምሳሌ በምዕራብ ሐረርጌ የተወሰኑ አካባቢዎች የሸኔ እንቅስቃሴ አለ። የጸጥታ ኃይላችን ተቀናጅቶ በእነዚህ ኃይሎች ላይ ርምጃ ሲወስድ ታጣቂዎቹ ራሳቸውን ለውጠው ድሬዳዋ መጥተው ይቀመጣሉ። በአጎራባች ክልል ላለ ግጭት እኛን እንደ መደበቂያ ሊጠቀሙብን ይችላሉ ማለት ነው። ከእነሱ ጋር ተቀናጅተን ካልሠራን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ነው የሚሆነው። ጠላት ዛሬ እኛ ጋር ይመጣል ይደበቃል። የተወሰነ ጊዜ ተቀምጦ የተረጋጋ ሲመስለው ትጥቁን ከቀበረበት አውጥቶ እየሄደ የሚፈልገውን ነገር ያደርጋል፤ እኛንም ሊያጠቃን ይችላል።
ስለዚህ በማናቸውም ጉዳዮች ላይ የምንተባበርበት አንድ የምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የጸጥታ ምክር ቤት አለ። ድሬዳዋ፣ ሐረሪ፣ ሶማሌ እንዲሁም ምዕራበና ምስራቅ ሐረርጌ የተካተቱበት ነው። ብዙ ጊዜ መድረኩ ላይ ስለማይገኙ ነው እንጂ ማሕቀፉ አፋርንም ይጨምራል። እኛ በቀጥታ ከሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን ጋር እንዋሰናለን። ከኦሮሚያ ምስራቅ ሐረርጌና ምዕራብ ሐረርጌ ያዋስኑናል። ከሐረሪ ጋር በቀጥታ በድንበር ባንዋሰንም በቅርብ ርቀት ላይ መሆናችንን ከግምት አስገብተን በጋራ እንሠራለን።
ራሱን የቻለ የግብረ ኃይሉ የጋራ እቅድ አለን። በዓመት ውስጥ አራት ጊዜ አጠቃላይ በቀጣናው ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ውይይቶችን እናደርጋለን። የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና እንደ ኢሚግሬሽን ያሉ የፌዴራል ተቋማት በመድረኩ ይሳተፋሉ። ስለዚህ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለን ግንኙነት በጣም ጠንካራ ነው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ በፌዴራል ፖሊስ የኮሚሽኖች ጉባኤ ላይ የምስራቅ ኢትየጵያ አጎራባች ክልሎች ጥምረት እንደ ምሳሌ ነው የሚነሳው። ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለየ መልኩ ለጥቃት ተጋላጭ ስለሆንን ቅንጅቱን አጠናክረን ካልሰራን የመጋለጥ ዕድላችን የበለጠ ሆኖ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- አሠራራችሁን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ረገድ የተገበራችሁት የሪፎርም ሥራ ምን አስገኝቷል?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- የኢትዮጵያ ጸጥታ ተቋማት ከለውጡ ወዲህ ነው የቴክኖሎጂን ጠቀሜታ በጉልህ የተረዳነው። እኔ በዚህ ተቋም ውስጥ 25 ዓመታት አገልግያለሁ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ኮምፒዩተር መጠቀም ማለት ወርድ መጻፍ እድርገን ነበር የምንወስደው። ይሄ በራሱ ኮምፒዩተር የተሠራበትን ዓላማ አለመረዳት ነው። በዚህ አይነት ሁኔታ አሁን
ካለው ተለዋዋጭ ዓለም ጋር መራመድ እንደማይቻል ተረድተናል። ከሦስትና አራት ዓመታት በፊት ይሄ ነው የሚባል ኮት የተደረገ አንድም መተግበሪያ የለንም ነበር።
የተቋሙን አጠቃላይ የቴክኖሎጂ ፍላጎት አጥንተን ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኞቹ ናቸው የሚለውን ከለየን በኋላ የበጀት ችግር ስላለብን አካባቢያችን ያለውን ሪሶርስ ለመጠቀም በመወሰን ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር ግንኙነት ፈጠርን። ፍላጎት እንዳለን ነገር ግን በጀት እንደሌለን ነገርናቸው በፈቃደኝነት የቴክኖሎጂ ቲም ከእኛ ጋር እንዲገናኝ አደረጉ። ከዚያ ቅድሚያ ልንሰጣቸው ይገባል ያልናቸውን ቴክኖሎጂዎች ወደ ማበልጸግ ገባን።
ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመሆን በሠራነው ሥራ ዛሬ ስድስት ቴክኖሎጂዎችን እየተጠቀምን እንገኛለን። የትራፊክ አደጋ ዳታ ቤዝ፣ ድሬ እንግዳ የሚባል በሆቴሎች የሚያርፉ እንግዶችን የምንከታተልበት ዳታ ቤዝ፣ ከምሽት ታክሲ አገልግሎት ጋር የተያያዘ ሥራ የምንሠራበት ሲስተም፣ የጦር መሳሪያ መመዝገቢያ ሥርዓት እና ለፖሊስ ጥቆማ ማድረሻ ሲስተም እየተጠቀምን እንገኛለን። ቴክኖሎጂ ዳዴ ላይ እንደመሆናችን ያን ያህል የሚያመጻድቅ አይደለም። ነገር ግን ደግሞ በሀገራችን ከሚገኙ ከሌሎች የፖሊስ ተቋማት የተሻለ የሚባል እንቅስቃሴ እያደረግን ነው። በአጠቃላይ ከተለመደው አሠራር ወጣ ባለ መልኩ ቴክኖሎጂን መጠቀማችን ውጤታማ አድርጎናል።
አዲስ ዘመን፡- ወንጀልን መከላከል የጋራ ሥራ ከመሆኑ አንጻር ከፍርድ ቤቶች እና ከማረሚያ ቤቶች ጋር ያላችሁ ግንኙነት እንዴት ያለ ነው ?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- የፍትህ ተቋማት የጋራ መድረክ አለን። በየሦስት ወሩ እንገናኛለን። የአስተዳደሩ ፍትህና ጸጥታ ቢሮ ሰብሳቢ ነው። የፌዴራል ክፍተኛ ፍርድ ቤትና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶችና ሌሎችም በፍትህ ዘርፉ የሚሳተፉ አካላት በመድረኩ ተሳትፎ ያደርጋሉ።
ይህ መድረክ ከተፈጠረ በኋላ ተጠርጣሪዎችን የማስቀጣት አቅማችን ጨምሯል። ከዚህ ቀደም በተከሳሽና በምስክር አለመቅረብ ምክንያት በየጊዜው የሚንጠባጠቡ ጉዳዮች ነበሩ። አሁን እነዚያን ጉዳዮች የማጽዳት አቅማችን እየጨመረ ነው የመጣው። ቅንጅታችን በመጠናከሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ፍርድ ቤት አቅርበን የማስቀጣት ዕድላችን አድጓል። ስለዚህ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ አንጻር ጥሩ ሥራዎችን እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡- የያዝነው በጀት ዓመት ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ ነው የቀረው። የበጀት ዓመቱ አፈጻጸማችሁ በድሬዳዋ ከተማ የሚፈጸም ወንጀል መቀነሱን ያሳያል ?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- የወንጀል የመቀነስ አዝማሚያ አለ። ወንጀል የሚቀንስበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉት። ፖሊስ የሚያደርጋቸው እንቅሰቃሴዎች አንድ ምክንያት ይሆናሉ። ኢኮኖሚውም ያለበት ሁኔታ በራሱ የወንጀል ድርጊት መቀነስና መጨመር ላይ ራሱን የቻለ አስተዋጽኦ ያደርጋል። የማኅበረሰቡ ንቃት እያደገ መምጣት የሚፈጥረው ነገር አለ።
አንድ መረዳት ያለብን ነገር አንዳንድ የወንጀል ሁኔታዎች በባኅሪያቸው ከፖሊስ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። ለምሳሌ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች አሉ። እነዚህ ጥቃቶች በግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ነው ሊቀንሱ የሚችሉት። እንዲህ ያሉ ቀላል ወንጀሎች ወደ ፖሊስ የሚመጡበት ሁኔታ ስላለ የተፈጸመውን የወንጀል መጠን ከፍ ያደርጉታል። እንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሰዎቹ ተስማምተዋል በሚል የሚደበቁ ወንጀሎችም አሉ። አንዳንድ ወንጀሎች በየጥጋጥጉ በእርቅ ሊደመደሙ ይችላሉ። ነገር ግን የትኛውም አይነት ወንጀል ወደ ፖሊስ መምጣት አለበት። ቢታረቁም ፖሊስ እንዲያውቃቸው ሆኖ ቢመዘገቡ የሚያዘው መረጃ ለቀጣይ ሥራችን ግብአት ይሆነናል።
በዓለም አቀፍ መለኪያ ዐበይት የሚባሉ አስር ወንጀሎች አሉ። እነዚህ አስር ወንጀሎች ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጽዕኗቸው በጣም ከፍ ያለ ነው። ይበልጥ ትኩረት የምናደርገው በእነሱ ላይ ነው። ለምሳሌ በድሬዳዋ ከተማ የግድያ ወንጀል እየጨመረ ከመጣ በቀጥታ ከማኅበረሰቡ እንቅስቃሴ ጋር ይያያዛል። ሰው በማታ እየወጣ ግድያ የሚፈጸምበት ከሆነ የወንጀል ፍርሃት ስለሚፈጠር ማኅበረሰቡ በምሽት ከቤት መውጣት ያቆሟል። የሰዎች እንቅስቃሴ መገደብ ደግሞ ኢኮኖሚው እንዲቀዛቀዝ ያደርጋል። ስለዚህ እኛ በዋነኝነት በማኅበረሰባችን እንቅስቀሴ ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩት እንደ ግድያ፣ ዘረፋ፣ ቅሚያና ስርቆት ያሉት አስር የወንጀል አይነቶች ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገን እንሠራለን። ይሄ ዓለም አቀፍ አሠራር ነው። እኛ ብቻ አይደለንም እነዚህ ወንጀሎች ላይ አተኩረን የምንሠራው። ኤፍቢአይም ቢሆን 10ሩ ወንጀሎች ላይ ነው ትኩረት አድርጎ የሚሠራው። ወንጀሎቹ የሚለዩበትም የራሳቸው ሥርዓት አላቸው።
አዲስ ዘመን፡- አምስተኛ ዓመቱን ያከበረው የድሬዳዋ የሌሊት የታክሲ ሹፌሮች ማኅበር የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ረገድ እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- በተለይ ከወጣቶች አንጻር ከዚህ ቀደም በየሰፈሩ ጎራ ለይተው ድንጋይ ሲወራወሩ የነበሩ ወጣቶች ዋነኛ የጸጥታ ሥራው የጀርባ አጥንት ሆነው ሌሊት “ሌሊቱ የኛ ነው” በሚል መርህ የከተማዋን የየዕለት እንቅስሴ ከፖሊስ ባልተናነሰ አንዳንድ ጊዜም በተሻለ መንገድ እየጠበቁ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። ድሬዳዋ ከተማ 24 ሰዓት ሥራ ውስጥ ያለች ከተማ እንድትሆን ማድረግ ችለዋል። እንደሚታወቀው በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች እነዚህ የባጃጅ አሽከርካሪዎች የጸጥታ ስጋት ተደርገው ነው የሚወሰዱት። እኛ ጋር ግን እነሱ በመኖራቸው ማኅበረሰቡ መረጋጋት ይሰማዋል። የፈለገበት ቦታ በፈለገበት ሰዓት መሄድ ይችላል።
የባጃጅ አሽከርካሪዎቹን የምናሰማራበት ራሱን የቻለ ሥርዓት አለን። በቀጥታ ወንጀልን ከመከላከል በተጨማሪ ሁሉም ሞባይላቸው ላይ በተጫነላቸው ጥቆማ የሚሰጡበት መተግበሪያ አማካኝነት በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የሚያዩትን ነገር በምስል፣ በድምጽና በጽሁፍ ወደ እኛ ይልካሉ። የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪ ማኅበሩ አባላት የሆኑት ወጣቶቹ በከተማችን ጸጥታና ሰላም ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
መደበኛ ሥራቸውን ይሠራሉ፤ ከሥራቸው ጎን ለጎን ደግሞ እያንዳንዷ የድሬዳዋ ጥግ ላይ የሚፈጸመውን ነገር ፊት ለፊት ተጋፍጠው ይከላከላሉ። በቅርብ ጊዜ የተፈጠረ አንድ ምሳሌ ልጥቀስልህ። አንድ የጸጥታ አካል መሳሪያውን ከካምፕ አውጥቶ ደብቆ ለማምለጥ ባጃጅ ላይ ይሳፈራል። የባጃጅ አሽከርካሪው የተሸፈነውን እቃ ሲመለከት ይሄ ነገር መሳሪያ ሊሆን ይችላል ብሎ ተጠራጥሮ ወስዶ ፖሊስ ጣቢያ ላይ አዙሮ ለፖሊስ አስረክቦታል። ይሄ የመንግሥትን ንብረት መከላከል ብቻ ሳይሆን በመሳሪያው ወንጀል እንዳይፈጸምበት ወይም ጸረ ሰላም ኃይሎች እጅ እንዳይደርስ ማድረግ ነው። ዜጎች የማይሳተፉበት የጸጥታ ሥራ ውጤታማ ሊሆን አይችልም።
በአጠቃላይ ለድሬዳዋ ሰላም የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወቱ ነው። የሚያዩትን ማናቸውንም ነገር በፈጠርነው ሥርዓት እያሳወቁን ከተማችንን አሁን ወዳለችበት ሁኔታ ማድረስ ችለናል።
አዲስ ዘመን፡- የፖሊስ ኮሚሽኑ ሥትራቴጂክ ዕቅድ የቀጣይ ዓመታት የድሬዳዋ ከተማን የጸጥታ ሁኔታ በተመለከተ ምን ግብ አስቀምጧል?
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- ከላይ ሳልጠቅስ የቀረሁት በሪፎርም ካሳካናቸው ጉዳዮች አንዱ ተቋሙ በሥትራቴጂክ ዕቅድ እንዲመራ ማድረጋችን ነው። ሥትራቴጂክ ዕቅዱ እስከ 2022 ዓ.ም ድረስ ያለውን የተቋማችንን አጠቃላይ ግቦች አካትቶ የያዘ ነው። ራዕያችን በ2022 በላቀ ሙያዊ አገልግሎት ቀዳሚ የፖሊስ ተቋም መሆን ነው። ፖሊስ ሁልጊዚ ብቁ ከሆነ አስተማማኝ ጸጥታን ማረጋገጥ ይችላል ተብሎ ይታመናል። ብቃት በውስጡ ብዙ ጉዳዮች አሉት። እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ያስቀመጥናቸው ሥትራቴጂዎች አሉ። እነዚያን ስትራቴጂዎች ለማሳካት ደግሞ ምን አይነት ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንዲሁም ዕድሎችና ስጋቶች አንዳሉ የመለየት ሥራ ሠርተናል።
ያለንበትን የጂኦፖለቲካ ሁኔታ እንደ አንድ ስጋት ነው የምንመለከተው። ለምሳሌ በጣም ተገማች ያልሆኑ ተለዋዋጭ የፖለቲካና የአካባቢ ችግሮች አሉ። አንዱን ነገር ብንጠቅስ ኢትዮጵያ የምትጠቀመው የጅቡቲን ወደብ ነው። ጅቡቲ ላይ የሚፈጠር ችግር ሁሉ በቀጥታ እኛን ያገኘናል። ገቢና ወጪ እንቅስቃሴዎች የሚደረጉት በድሬዳዋ ከተማ ስለሆነ የድሬዳዋ ከተማ የጸጥታ ችግር የአጠቃላይ ኢትዮጵያ የጸጥታ ችግር ነው ሊሆን የሚችለው። የሶማሊያን አካባቢ ብትወስድ የሽብር እንቅስቃሴ ያለበት አሁንም ያልተረጋጋ ነው። ሶማሌ እና ሐረሪ ክልሎችን ማቋረጥ ከቻሉ ሽብርተኞች በቀላሉ እኛ አካባቢ መገኘት ይችላሉ።
በተለያዩ መስፈርቶች ከተመለከትን ድሬዳዋ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው ትልቅ ከተማ ናት። የሚዲያ ትኩረት የምታገኝና ቱሪስቶች የሚንቀሳቀሱባት ከተማ በመሆኗ በርካታ ሆቴሎች ይገኛሉ። ስለዚህ ሽብርተኞች እዚህች ከተማ ላይ አንድ ጥቃት ቢፈጽሙ ከፍተኛ የሚዲያ ሽፋን ያገኛሉ። እነዚህን ነገሮች እንደ ስጋት ነው የምንወስዳቸው።
በአንጻሩ ዕድሎች ደግሞ አሉ። መንግሥት በፀጥታ ተቋማት ላይ የጀመራቸው ሪፎርሞች አሉ። እነዚህን ሪፎርሞች እኛ እንደ ዕድል ነው የምንቆጥራቸው። ሪፎርሙ ትናንት የነበሩብንን ተቋማዊ ችግሮች እንድንፈታ ዕድል ይሰጠናል። በአጠቃላይ አሉ በምንላቸው ጥንካሬዎችና ድክመቶች እንዲሁም ዕድሎችና ስጋቶች ላይ ትንተና አድርገንባቸዋል።
ከእነዚህ ነገሮች አንጻር በቀጣይ የድሬዳዋ ከተማ እጣፈንታ በጸጥታው ኃይል ላይ ያለ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ነው የደረስነው። ምክንያቱም ሰላም ከሌለ ልማትና ኢንቨስትመንትም ሆነ ምንም አይነት ሌላ ሥራ ሊኖር አይችልም። ስለዚህ ምንድን ነው ማድረግ ያለብን? ሰራዊታችንን እንዴት ነው መገንባት ያለብን? ከማኅበረሰቡ ጋር እንዴት ነው መገናኘት ያለብን? የሎጀስቲክ አቅማችን እንዴት ነው መሆን ያለበት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችን የት ደረጃ ላይ ይገኝ የሚሉትን ጥያቄዎች አንስተን በሰባት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ሥትራቴጂዎች አስቀምጠናል። በእነዚህ ሥትራቴጂዎች ውስጥ በጣም ብዙ ግቦች አሉ። ነገር ግን ጠቅለል አድርጌ ጥያቄህን ስመልስልህ፤ የዛሬ 10 ዓመት የሚኖረውን የድሬዳዋን ሁኔታ ተምብየን የራሳችንን ሴናሪዮዎች ሰርተን የፖሊስ አቅም እዚህ ደረጃ መድረስ አለበት ብለን እየሠራን ነው ያለነው።
ለምሳሌ አንዱን ብጠቅስልህ ፖሊስ በእያንዳንዱ የድሬዳዋ ጥግ ከማኅበረሰቡ የድረሱልኝ ጥሪ በደረሰው በ10 ደቂቃ ውስጥ ቦታው ላይ መድረስ አለበት የሚል ግብ አስቀምጠናል። የትም ሀገር ፖሊስ ከሚመዘንባቸው ጉዳዮች አንዱ ዜጎች ፖሊስን ጠርቶ በምን ያህል ደቂቃዎች ውስጥ ያገኘዋል የሚለው ነው። አሁን ማንኛውም ሰው ወደ ፖሊስ ጥሪ ሲያደርግ በፍጥነት ምላሽ የሚያገኝበት የጥሪ ሥርዓት ሥራ ላይ አውለናል።
አሁን ትልቅ ፈተና እየሆነብን ያለው የአባላት ሥነምግባር ነው። ከማኅበረሰባችን አምጥተን ነው ስልጠና የምንሰጣቸው ነገር ግን የሥነ ምግባር ችግር ፈተና እየሆነብን ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ፖሊስ ከሚፈተንባቸው ትልልቅ ችግሮች አንዱና ዋነኛው የአባላት ሥነምግባር ነው። የአባላት የሥነምግባር ችግር ሕብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር ያለው ግንኙነት እንዲሻክር ያደርጋል። እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ከግምት አስገብተን የነገዋን ድሬዳዋ ሊመጥን የሚችል የፖሊስ ተቋም እየገነባን ነው።
ድሬዳዋ ያላትን አንጻራዊ ሰላም ተከትሎ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። የከተማዋን መስፋፋት፣ የሚመጣውን የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲሁም የንግድና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴዎችን አይተን ተቋማችንን የማጠናከር ሥራ እየሠራን ነው የምንገኘው። ይሄ ማለት ነገ ለሚመጡ ማናቸውም ሁኔታዎች ምላሽ መስጠት የሚችል ተቋም እየፈጠርን ነው የምንገኘው።
አዲስ ዘመን፡- ላቀርብንልዎ ጥያቄ ጊዜ ወስደው የተብራራ ምላሽ ስለሰጡን በዝግጅት ክፍላችን ስም እናመሰግናለን።
ም/ል ኮሚሽነር ማኦ፡- እኔም አመሰግናለሁ!
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 21 ቀን 2017 ዓ.ም