ጠቅላይ ሚኒስትር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከትናንት በስቲያ በአዋሽ አርባ ውጊያ ትምህርት ቤት ተገኝተው በአየር ኃይል እና በሜካናይዝድ ቅንጅት የተካሄደውን የጥምር ጦር ወታደራዊ ትርዒት ተመልክተዋል። በአዋሽ አርባ ውጊያ ቴክኒክ ትምህርት ቤት በመቀጠልም በቢሾፍቱ የሚገኘውን የአየር ኃይል ዋና መምሪያ በመገኘት በዝግጁነት ላይ የሚደረገውን ማሻሻያ ጎብኝተዋል። ምልከታ እና ጉብኝታቸውን መነሻ በማድረግም “ጠንካራ ኃይል፣ የማይደፈር ኃይል፣ በቀላሉ የማይቆረጠም ኃይል ሲኖር ጠላት ውጊያን ደግሞ እንዲያስብ እና እንዲያስቀር ያስገድዳል፤” ያሉ ሲሆን፤ ይሄን ያስደመጡበት ንግግራቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ጄነራል አበባው ታደሰ፣ ኮምሽነር ጄነራል ደመላሽ፣ የአየር ኃይል አዛዥ፣ መድፈኛ አዛዥ የተከበረችሁ ጄነራሎች፣ የጦር ሰራዊት አባላት በዚህ በሚያምር መስክ ለሀገር ኩራት የሆኑ እና ኢትዮጵያ አንድነቷን ጠብቃ በክብር እንድትኖር ጋሻ መከታ ለመሆን የሚችለውን ኃይል ለማየት በመታደሌ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ልገልፅላችሁ እወዳለሁ።
በኢትዮጵያ የጀመርነው ሪፎርም ከዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ቀጥሎ አበክረን ስንሰራበት የነበረው የኢትዮጵያን ኮርቺቭ ፓወር የማድረግ አቅም ያለው ኃይል ግንባታ ነው። በዚህ ግንባታ ውስጥ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የደህንነት ተቋማት፣ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መንገድ እስካሁን በኢትዮጵያ ታሪክ ተገንብቶ በማይታወቅ ልክ እነዚህን የማድረግ አቅም፣ ውጊያ የማስቀረት አቅም ፣ ውጊያ ሲጀመር በአጭር የመቅጨት አቅም ያላቸውን ኃይሎች ላለፉት ሁለት ሶስት ዓመታት በከፍተኛ ትኩረት ስንሰራ ቆይተናል።
ይሄ ኮርቺቭ ፓወር /ኃይል ግንባታ የሚያስፈልግበት ዋነኛው ዓላማ፡- አንደኛው ውጊያ ለማስቀረት ነው። ጠንካራ ኃይል፣ የማይደፈር ኃይል፣ በቀላሉ የማይቆረጠም ኃይል ሲኖር ጠላት ውጊያን ደግሞ እንዲያስብ እና እንዲያስቀር ያስገድዳል፤ ዲተር የማድረግ ኃይል አለው። ሁለተኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ላለፉት በርከት ላሉ አስርት ዓመታት የነበረን የውጊያ ስርዓት ይሄን ወደ ዘመናዊ የውጊያ ስልት ለመቀየር ያለው ዋነኛው መንገድ የአየር ኃይል እና የከባድ መሳሪያ አቅምን ማጠናከር ብቻ ሳይሆን መቀናጀት ነው። አየር ኃይል እና መድፈኞች፣ ታንከኞች፣ መድፈኞች፣ ሚሳኤል ምድብተኞች፣ ውጊያን ይጀምራሉ፣ ውጊያን ያጧጡፋሉ፤ አስፈላጊ ሲሆን ትጥቅ ኤልት ፎርስ እስፔሻል ፎርስ ውጊያን ይጨርሳል። የሰው መስዋትነት ቀንሰን በመሳሪያ ኃይል በቴክኖሎጂ ኃይል ውጊያን ጀምረን እንድንጨርስ መስዋትነት እንድንቀንስ ያስቀመጥነውን ግብ የሚያሳካው ትልቁ ስራችን እና ውጤቱ በሁሉም ዘርፍ ያሉ የከባድ መሳሪያ አቅሞቻችን ከአየር ኃይል ጋር ተቀናጅተው እየተናበቡ ለውጊያ ዝግጁ መሆናቸው ነው።
የተከበረው የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር እና በውስጡ የምትገኙ የጦር መኮንኖች እና የሠራዊት አባላት ኢትዮጵያ ፀንታ እንድትቆም የናንተ መጠንከር፣ የናንተ ብቁ መሆን ሁልጊዜም ለባንዲራ እና ለመለዮ የማይዛነፍ አቋም ያለው ኃይል መሆን የምናስበውን ልማት እንዲፋጠን ያደርጋልⵆ ሁላችሁም እንደምታውቁት ያደግንበት ቤት ስለሆነ ኢትዮጵያ አሁን ባላት ልክ የአየር ኃይል፣ የካባድ መሳሪያ የመዋጋት አቅም፣ ክላሽ የመጠገን አቅም በሠራዊት ቁጥር እና በጦር መኮንኖቻችን በወረቀት ላይ ሳይሆን በውጊያ የተፈተነ ብቃት ኖሮን አያውቅም፤ ከፍተኛ ኃይል ተገንብቷል።
ይህ ኃይል ለኢትዮጵያ የልማት ምንጭ እና ድልድይ ሆኖ እንዲያገለግል፡- አንደኛ በዚህ ስፍራ ያየነው የጦር ልምምድ ማሳያ ቦታ በሚቀጥለው ጊዜ ስንገናኝ እጅግ ተውቦ በርከት ያሉ ሲቪሊያንስ መጥተው የሚያዩበት ሰፈር እንዲሆን፤ ይሄንን ቦታ የምንሰለጥንበት ወጣ ብለን የምንዝናናበት፣ ኃላፊዎች ከከተማ እየመጡ ከናንተ ጋር የሚገናኙበት ውብ ስፍራ ማድረግ ስለምንችል፤ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤቱን እጅግ ዘመናዊ አድርጎ በአፍሪካ ውብ ስፍራ ማድረግ ችሏል። የአየር ኃይሉንም እንደዛው በጣም በተዋበ መንገድ መቀየር ተችሏል፤ ይሄንን ስፍራ ቀይረን መከላከያ የብልፅግና ምልክት፣ የዕድገት ምልክት፣ የቴክኖሎጂ ምልክት እንዲሆን ማድረግ ይኖርብናል።
ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው የፖለቲካ ሸቀጥ፣ የፖለቲካ ገበያ፣ ዘረኝነት፣ በእምነት በአካባቢ መከፋፈል ላይ ያጠነጠነ ነው። ከኢትዮጵያዊነት አንድ ደረጃ ዝቅ ስትል ውርደት፣ ዝቅ ስትል መፍረስ፣ ዝቅ ስትል መበተን መሆኑን በተግባር ያየን ስለሆንን፤ ከከፍታቹ ዝቅ ሳትሉ አንድ መሆናችሁን በተግባርም እያጠናከራችሁ ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ፣ ማልማት፣ መጠበቅ እና ለልጆቻችን ማሸጋገር ህይወት ዘመን ተልዕኳችሁ መሆኑን ተገንዝባችሁ፤ የውስጥ አንድነት እንድታረጋግጡ አበክራችሁም እንድትሰሩ አደራ ልላችሁ እፈልጋለሁ።
አሁን ባለው ዘመን የሶሻል ሚድያው ዋናው ስራው በሰፈር፣ በእምነት፣ በዘር ብቻ ሳይሆን በትንንሽ ወረዳዎች የመከፋፈል አባዜ ነው። ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያን ያሳንሳል። ትልቅ ሀገር ነው ያለን ፣ ሊለማ የሚችል ሀገር ነው ያለን፣ ሰፊ ህዝብ ነው ያለን አንድ መሆን ከቻልን ሌሎችን መሳብ የምንችል እንሆናለን፤ ስንለያይ ስንበተን ግን ለጠላት ለጥቃት የምንጋለጥ ስለምንሆን በዚህ ልክ ጠንካራ መሆን ዘመናዊ ትጥቅ መታጠቅ ብቻ ሳይሆን የውስጥ አንድነት እና ወንድማማችነትን ማጠናከር ከሁላችሁም የሚጠበቅ የዕለት ተዕለት ተግባር እንደሆነ ከአደራ ጭምር ላሳስባችሁ እፈልጋለሁ።
በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት ኢትዮጵያን የድህነት ታሪኳን ቀይረን አንድ መሆኗን ለእኛም ለዓለምም አሳይተን የምናሻግራት ዕንቁ ምድር እንጂ የምትበተን በጎጠኞች፣ በፅንፈኞች፣ በአሸባሪ ኃይሎች፣ የምትለያይ ሀገር አለመሆኗን በተደጋጋሚ ተናግረን በተግባርም ማሳየት እንደቻልነው ሁሉ፤ በሚቀጥሉት ዘመናት በልማት ጠንክረን በሰላም ጠንክረን ውጊያ በሚያስቀር አቅም ጠንክረን የኢትዮጵያን አንድነት ጠብቀን ሰላማችን እና ልማታችንን አረጋግጠን ልጆቻችን የበለፀጉ የለሙ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ሀገራቸውን የሚወዱ በሀገራቸው የሚሰሩ የማይሰደዱ እንዲሆኑ ለኛ ትውልድ የተጣለ ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝበን በጋራ እንድንሰራ አደራ እያልኩ፤ ዛሬ ባየሁት ብቃት፣ ዛሬ ባየሁት ልምምድ፣ ዛሬ ባየሁት ትርኢት እጅግ የኮራሁ መሆኔንና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይሄን የማየት ዕድል ሲኖረው በናንተ በልጆቹ ደግሞ ኩራቱን የሚያረጋግጥ እንደሚሆን ያለኝን ሙሉ ዕምነት እየገለፅኩ፤ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን በርቱ የኢትዮጵያ ልማት እና ሰላም እንዲሁም አንድነት በእኛ አንድነት እና ጥንካሬ የሚረጋገጥ ይሆናል፤ ይሄን በጋራ ለማየት እንዲያበቃን እመኛለሁ። አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 16 ቀን 2015