እአአ በ2007 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በደቡብ አፍሪካዋ ጆሃንስበርግ ባደረጉት ጉባኤ በአንድ ጉዳይ ላይ ከውሳኔ ደረሱ። ይኸውም በአገር ውስጥ ሊጎች ለሚጫወቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች ተጨማሪ እድል ለመስጠት አገራቸውን የሚወክሉበትና የሊጋቸውንም ጥንካሬ ለተቀረው ዓለም የሚያንጸባርቁበትን ውድድር ማሰናዳት ነበር። በቀጣዩ ዓመትም የአፍሪካ ዋንጫ ይካሄድ ስለነበር እአአ በ2009 ይህ ሃሳብ ወደ ተግባር ተቀይሮ በኮትዲቯር አዘጋጅነት በስኬት የመጀመሪያው የአፍሪካ ቻምፒዮን ሺፕ (ቻን) ተካሄደ። በዚህ ውድድር ላይም ዴሞክራቲክ ኮንጎ ጋናን በመርታት ከ35 ዓመታት ድርቅ በኋላ የመጀመሪያውን ዋንጫ በእግር ኳስ ስፖርት ማግኘት ችላለች።
የኮንፌዴሬሽኑ ሃሳብ በእርግጥም ፍሬያማ መሆኑ የተረጋገጠው በዚህ ሁኔታ ነበር። በርካታ ተጫዋቾቿ በአውሮፓ እና ሌሎች አህጉራት ሊጎች ለሚጫወቱት እንዲሁም በድህነት ምክንያት ዜግነታቸውን ቀይረው ባእድ አገራትን ለሚወክሉባት የአፍሪካ እግር ኳስ ተጫዋቾች አማራጭ ለመሆን ችሏል። ላላደጉት የአፍሪካ አገራት ሊጎችም ትልቅ ዕድልን ያበረከተው ይህ ውድድር በተጫዋቾቹና በውድድሩ ጥራት የሊጎቹ ቁመና እንዲፈተሽ አስችሏል። ምልከታ ያጡ ነገር ግን በስፖርቱ ትልቅ ደረጃ መድረስ የሚችሉ ወጣት የእግር ኳስ ተጫዋቾችም የውድድር እድል ከማግኘት ባለፈ በዚህ ውድድር አማካይነት ከተቀረው ዓለም ጋር መገናኘት ችለዋል።
የሞሮኮ ብሄራዊ ቡድን አባልና የላሊጋው ክለብ ሪያል ቫላዶሊድ ተጫዋች የሆነው ጃዋድ ኤል ያኒክ አሁን ለደረሰበት ስፍራ መሰረት የሆነው እአአ በ2018 አገሩ ዋንጫውን ባነሳችበት ውድድር ላይ የላቀ ብቃቱን ማስመስከሩ ነው። የቶትንሃሙ ተጫዋች ይቬስ ቢሱማ፣ የዌስትሃም ዩናይትዱ ናየፍ አጉዌርድ፣ የቀድሞው የኦሎምፒያኮስ ተጫዋቹ ሂላል ሱዳኒ፣ ለቡልጋሪያው ክለብ የሚጫወተው ናይጄሪያዊው ሼሁ አብዱላሂ፣ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ተጫዋቾች ከብዙ በጥቂቱ ለማሳያ ያህል ተነሱ እንጂ ይህ ውድድር ለበርካቶች ህልም መሰላል ሆኗቸዋል።
ኡጋንዳዊው የእግር ኳስ አሰልጣኝ ጆኒ ማክንስትሪ ይህንኑ ሃሳብ የሚጋራ ሲሆን፤ በዓለም ላይ ከሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮች ሁሉ ቻን ትክክለኛው የተጫዋቾች መታያ መሆኑን ይጠቁማል። ከተለያዩ ዓለማት የተጫዋች መልማዮችን የሚጋብዝ ውድድር በመሆኑ ጠቀሜታው እጅግ ከፍተኛ መሆኑንም ያብራራል። ከተጫዋቾች ባለፈም ሊጎች የቴሌቪዥን ምልከታ ግብዣ የሚያገኙበት መድረክ ስለመሆኑ እንዲሁም በአፍሪካ ዋንጫ እና ሌሎች ውድድሮች የተሳታፊነት ዕድል ለማያገኙ ብሄራዊ ቡድኖች ትልቅ የውድድር መድረክም ነው። ይህ የአሰልጣኙ እይታ ብቻም ሳይሆን ለውጪ አገራት የእግር ኳስ ክለቦች የሚጫወቱ የእግር ኳስ ተጫዋቾች የሌሏቸውና በአህጉር አቀፍ ደረጃ እግር ኳሳቸው ያላደጉ አገራትም ከትልልቅ ቡድኖች ጋር ተፎካካሪ የሚሆኑበትን ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑም በተግባር የታየ ነው።
ዓለም አቀፉን እግር ኳስ በሚመራው ፊፋ ዕውቅና የተሰጠው ውድድሩ በፊፋ ካላንደር መሰረት እንዲመራ በመደረጉ እዲሁም በሌሎች ምክንያቶችም እአአ በ2011 ሁለተኛው የቻን ውድድር በሱዳን ከተካሄደ በኋላ ቀጣዩ ውድድር ሶስት ዓመታትን ዘግይቶ ነበር የተደረገው። በቶታል ስፖንሰር አድራጊነት በሚመራው በዚህ ውድድር ላይ ዴሞክራቲክ ኮንጎ እአአ በ2009 እና 2016 ዋንጫውን ያነሳች ሲሆን፤ ሞሮኮ ደግሞ በተከታታይ እአአ በ2018 እና 2020 አሸናፊ በመሆን ከፍተኛውን የስኬት ታሪክ ይጋራሉ። ሊቢያ እና ቱኒዚያ ደግሞ የተቀሩትን ዋንጫዎች ማሳካት የቻሉ አገራት ሆነዋል።
በርካታ ውድድሮች በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዳይካሄዱ መሰናክል የሆነባቸው ዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ይህንን ውድድርም ለአንድ ዓመት እንዲራዘም አድርጎታል። በመሆኑም የቻን ውድድር ለሰባተኛ ጊዜ ዘንድሮ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያ አስተናጋጅነት መካሄድ ከጀመረ ዛሬ ሶስተኛ ቀኑን ይዟል። ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ 18 ቡድኖች የሚሳተፉበት ቢሆንም ቻምፒዮናዋ ሞሮኮ ከአዘጋጇ አገር ጋር ባላት ፖለቲካዊ ተቃርኖ ምክንያት ራሷን ከውድድሩ አግልላ ጨዋታው በ17 ቡድኖች መካከል መካሄዱን ቀጥሏል። ከተሳታፊ አገራቱ መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ብሄራዊ ቡድኗ ለሶስተኛ ጊዜ በመድረኩ ተካፋይ ለመሆን በቅቷል። ባለፉት ሁለት ተሳትፎዎች ተጠቃሽ የሆነ ውጤት ባይመዘገብም በዚህ ዓመት ግን ካለፉት ጊዜያት የተሻለ ተወዳዳሪ ለመሆን መታቀዱ የሚታወቅ ነው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥር 7 ቀን 2015 ዓ.ም