በሀገራችንም በተለይ በአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተስፋፋ መጥቷል፤ የዚህ አገልግሎት ሀገራዊ ፋይዳም እንዲሁ እያደገ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ይህን ልምድ ለክልሎች የማካፈል ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።
አገልግሎቱ የቆየውን የኢትዮጵያውያን የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባሕል ዳግም እንዲያንሰራራ እያደረገም ይገኛል። በችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች በአገልግሎቱ እየተገነቡ ያሉ መኖሪያ ቤቶች፣ የሚሰጡ የምገባ አገልግሎቶች ፣ የበዓላት ወቅት ማዕድ የማጋራት ተግባሮች የሚያመለክቱትም ይህንኑ ነው፡፡
በዚህ አገልግሎት ወጣቶች፣ ባለሀብቶች፣ ባለሙያዎች ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ። ዜጎች በፈቃደኝነት ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን እውቀታቸውን ለወገናቸው በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ እንዲያበረክቱ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል። ይህን ተከትሎም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባሕል እንዲጎለብት እንዲጠናከር እየረዳ ይገኛል። መርሃ ግብሩ መንግሥት የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመቅረፍ እንዲሁም ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ እያከናወነ ያለውን ተግባር ከጎኑ ሆኖ በመደገፍ እያገለገለ ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ እያደገ የመጣው ይህ አገልግሎት በዚህ የበጋ ወቅትም ቀጥሎ በመዲናዋ አንድ ሚሊየን በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት 784 ሺህ 844 ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጎ ፈቃድ ፕሮግራም በርካታ በጎ ፈቃደኞች በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።
“በጎ ፈቃደኝነት፤ ለማህበረሰብ ለውጥ!” በሚል መሪ ሃሳብ ይፋ የሆነው ይህ የበጋ በጎ ፈቃድ ፕሮግራም ከጥቅምት ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ይሆናል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን መረጃ እንዳመላከተው፤ የበጋ በጎ ፈቃድ ፕሮግራም በ12 ዋና ዋና ፕሮግራሞች እና በ13 መርሃ ግብሮች ይከናወናል። በእነዚህ መርሀ ግብሮች ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት ለመስጠት ታቅዷል። በአገልግሎቱም አንድ ሚሊየን በጎ ፈቃደኞች ሲሳተፉ፤ ስድስት ነጥብ አምስት ቢሊየን ብር የመንግሥት ወጪን ይታደጋል።
የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በሚመራው በዚህ አገልግሎት የከተማዋ ነዋሪ ማሬ ሙሉጌታ ላለፉት አምስት ዓመታት ተሳትፎ አድርጋለች፤ በቀጣይም በበጎ ፈቃድ በሚሰሩ ሥራዎች ጊዜዋንና ጉልበቷን ሳትቆጥብ ባላት እውቀት ማህበረሰቡንና ሀገሯን ለማገልገል ዝግጁ ናት።
ደም በመለገስ ሌሎች ወጣቶችንም በማስተባበር እንዲለግሱ በማድረግ፣ የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በትራፊክ ማስተናበር ሥራዎች በመሳተፍ እና በማስተባበር ሥራ እንዲሁም በጎነት በሆስፒታል በሚል አቅመ ደካሞችን ተዘዋውሮ የመርዳት ሥራዎች ትሰራለች። በበዓላት ወቅትም ለህብረተሰቡ ማዕድ ማጋራት ላይ ከባለሀብቱ ጋር ከብሎክ ጀምሮ ማህበረሰቡን በማነቃቃት እንዲሳተፉ በማድረግ ላይ የበኩሉን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንደምትሰራ ወጣት ማሬ ገልፃለች።
በተለይ በበጎ ፈቃደኝነት በሚገባ ተሳትፎ ያደረገችው ከሶስት ዓመት ወዲህ መሆኑን ጠቅሳ፣ አገልግሎቱ ጊዜን፣ ጉልበትን ሳይቆጥቡ በመስጠት ሰዎችን በፈቃደኝነት በመርዳት የሚከናወን ተግባር ነው ብላለች። ሰዎች ባላቸው እውቀትም ይሁን ጊዜያቸውን በማካፈል አስተባብሮ ከመሥራት እንደሚነሳ ትገልፃለች።
ወጣት ማሬ እንደምትለው፤ መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እና የማስተባበር ሥራዎችን መሥራት ዜጎች ብቻ የሚረዱበት አይደለም፤ በጎ ፈቃደኞች ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በመጠቀም በበጎነት በማገልገላቸው የተነሳ ሀገርም ትጠቀማለች፡፡ የገንዘብ ወጪን በማስቀረት፣ ገንዘቡ ለሌላ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት እንዲውል የሚያስችል በመሆኑ በተዘዋዋሪ ሀገርን መርዳት ነው ብላለች። በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ዜጎች የሚሰጡት አገልግሎት፣ እንደ መንገድ መሠረተ ልማትና ትምህርት ቤት ያሉትን በመገንባት መንግሥት ለእነዚህ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ሊያወጣ የሚችለውን ሀብት እንደ ኮሪደር ልማት ላሉት እንዲያውል በማስቻል ሀገርን የሚያግዝ ሥራ የሚሰራበት መሆኑን ጠቁማለች።
በጎ ፈቃደኛ ወይዘሮ ፀጋ አጪሶ ላለፉት 11 ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፈዋል፤ በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት በይበልጥ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅት በተለይ የትራፊከ እንቅስቃሴን በማስተናበር ሥራዎች ወቅት ስለበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ግንዛቤ ያልነበራቸው ሰዎች ያጋጥሙ እንደነበር በመጥቀስ፣ ይህም በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ የተካሄደው ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ሰፊ ክፍተት እንዳለበት መረዳታቸውን ጠቁመዋል።
የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስ፣ ልብሳቸውንና ገላቸውን በማጠብ፣ አልባሳትንና መጻሕፍትን በማሰባሰብ ለችግረኞች በመስጠት እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ ሥራዎች እስከ አዳማ፣ ሳውላ እና ሀዋሳ ከተሞች ድረስ ማህበረሰቡን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማገዝ እና ልምድ ለማካፈል መንቀሳቀሷን አስታውሰዋል።
እንደ ወይዘሮ ፀጋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ መሳተፍ ለሰው ቅን መሆንንና የግል ተነሳሽነትን የሚጠይቅ ነው። በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ወቅት የሚያመሰግኑና የሚመርቁ በመኖራቸው ከደመወዝ በላይ ርካታን ይሰጣል። በተለይ አዛውንቶችን ሁልጊዜ መደገፍ እና ለነሱ መልካም ነገር ማድረግ የሚሰጡት ምርቃት ትልቅ ደስታን የሚፈጥርና አቅም ቢኖር የበለጠ ለመደገፍ የሚያነሳሳ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
የአዲስ አበባ የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ካሳ እንዳስታወቁት፤ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን እየቀረፈች ዓለም አቀፍ የስበት ማዕከል መሆን በጀመረችው አዲስ አበባ ከተማ ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ የተሰሩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች ፍሬያማ መሆን ችለዋል።
በ2016 ዓ.ም በክረምት በጎ ፈቃድ 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን ከሦስት ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች በድግግሞሽ ተሳትፈውበታል። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን በጎ ፈቃደኛ የህብረተሰብ ክፍሎችን በድግግሞሽ ለማሳተፍ ታቅዶ ከሁለት ሚሊየን በላይ ተሳትፎ አድርገዋል። በዚህም በከተማ አቀፍ 20 ሚሊየን እቅድ ታቅዶ ከ26 ሚሊየን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። በበጋውም የመንከባከብ ሥራውን የሚከናወን ነው።
በአካባቢ ፅዳት፣ ማስዋብ ላይ እና ከኮሪደር ልማት ሥራው ጋር ተያይዞ ከተለያዩ ባለድርሻዎች ጋር በመሆኑ ከ100 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል። በዚህም ከሁለት ሺህ 996 ሜትሪክ ቶን በላይ ቆሻሻ ለማንሳት ተችሏል።
በደም ልገሳም ቋንቋን ፆታን ሳይለይ ከ32 ሺህ 600 በላይ ወጣቶች ደም ለግሰዋል። ይህም አንድም እናት በወሊድ መሞት የለባትም በሚለው መርህ አርአያነት ያለው የበጎነት ተግባር ነው። “በጎነት በሆስፒታል” በሚለው መርሃ ግብርም ህሙማንን የመንከባከብ፣ የመጠየቅ ተግባራት ተከናውነዋል።
የትራፊክ በጎ ፈቃደኞች በማስተባበሪያው መሳተ ፋቸውን አስታውሰዋል። በተመሳሳይ “ሙያዬ በሀገሬ” በሚል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሙያን መሠረት ያደረጉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በተለይ የህክምና ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ የስፖርት ባለሙያዎች በሙያቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡበት መድረክ ተፈጥሯል።
በከተማ ግብርና፣ በከተማዋ ሰላም በጎ ፈቃደኞች አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በድንበር ተሻጋሪ ሥራዎች ከከተማዋ ወጣ በማለት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ውጤታማ ሥራ ተሰርቷል፤ የሕዝብ የእርስ በርስ እሴት በማዳበር ትውውቅ በማጠናከር ፕሮግራሞች ተከናውነዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተከናወነ የሚገኝበትን ሁኔታ ተሞክሮ በማጋራት አርአያነትን የማስፋት ሥራዎች የተሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል። በዚህም በወሰን የለሽ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሁለት ሺህ 220 በላይ በጎ ፈቃደኞችን ማሳተፍ ተችሏል። በእነዚህ ተግባራት አጠቃላይ ክንውን ተሳታፊ የነበሩ አካላት እና ባለሀብቶች ጳጉሜን አራት 2016 ዓ.ም በከተማ አስተዳደሩ እና በየደረጃ እውቅና እና ምስጋና መሰጠቱን አስታውሰዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በዘላቂ ልማት ያለውን አስተዋጽኦ ማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት፣ ተሳትፎ ማጠናከር ላይ በአጠቃላይ ከ764 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታውቀዋል። ከእነዚህ አንዱ ማዕድ ማጋራት ሲሆን፣ በዚህም ዘላቂ ችግሮችን ለመፍታት አብነትን ለማሳየት፣ በስፋት እየተከናወነ ነው።
በቤት እድሳት እና ግንባታ በአራት እና ሶስት ወራት 25ሺ 74 ቤቶች ተገንብተዋል። ከዚህ ውስጥ 812 በከፊል ከ17ሺህ 62 በአዲስ መልኩ ከጂ ፕላስ በላይ የተገነቡ ናቸው። በቤተሰብ ደረጃ ከ14 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ይሄም በተለይም በደሳሳ ጎጆዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደረገ ነው።
ከነፃ ህክምና ጋር ተያይዞ ከፍለው መታከም የማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ የጤና ተቋማት የተሳተፉበት ከ89 ሺህ በላይ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል ሲሉም ጠቅሰው፣ ይህም መስፋፋት እንደሚገባው ጠቁመዋል። ቀደም ሲል ከውጭ ባለሙያዎች ወደ ሀገራችን መጥተው ይህንን ተግባራዊ ሲያደርጉ እንደነበር አስታውሰው፣ የሀገራችን ባለሙያዎች የበጎ ፈቃድ የጤና አገልግሎት እንዲሰጡ አቀናጅቶ ማስተባበር ማስፈለጉን ጠቁመዋል። በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በጎልማሶች፣ በአጫጭር ትምህርት ተግባራት ከትምህርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ከ94 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
እንደ አጠቃላይ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው በእውቀት፣ በጉልበት በሙያ የተሰጡ አገልግሎቶች ወደ ገንዘብ ሲቀየሩ ከአምስት ነጥብ አራት ቢሊየን ብር በላይ የመንግሥትን ወጪ የመቀነስ አስተዋጽኦ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። ከእነዚህም መካከል በቤት ግንባታ ከሁለት ነጥብ ሶስት ቢሊየን ብር በላይ አስተዋጽኦ መደረጉን አመላክተዋል። ለእዚህ ውጤት መገኘት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ የጎላ ሚና ነበረው ሲሉም ምስጋና አቅርበዋል።
አቶ ደረጄ እንደሚናገሩት፤ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያው የትኛውም ዜጋ ያለማንም አስገዳጅነት ገንዘቡን፣ እውቀቱን፣ አቅሙን ጊዜውን ለማህበረሰቡ በሚጠቅሙ ተግባራት በራሱ መልካም ፈቃድ ያለ ክፍያ የሚሳተፍበት ነው። ይህን በማድረጉ ሀገርን ከማገዙ ባሻገር የህሊና እርካታ ያገኝበታል። ማስተባበሪያው ለበጎ ፈቃደኞች የአገልግሎት አሰጣጥ የማስተባበር ሁኔታዎችን ያስተባብራል።
የመዲናዋ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቋም መመራት ከጀመረ ባለፉት ስድስት ዓመታት በርካታ ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል። የህብረተሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ግንዛቤ እያደገ መምጣቱ፣ ባለሀብቶች፣ በጎ ፈቃደኞች በስፋት በመሣተፍ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ናቸው። በተለይ በማዕድ ማጋራት፣ በቤት ግንባታና እድሳት፣ እየተሳተፉ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየቀረፉ ናቸው። ተሳትፎውም ጨምሯል ብለዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትና መርሀ ግብሮች በጥራትም በቁጥርም እየበዙ በተለያዩ መስኮች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ ናቸው። በገንዘብ ደረጃም በጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይም የሚውለው ገንዘብ እያደገ ነው። የከተማ ቤት ግንባታዎች እይታ ከመቀየር አኳያም ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆን ተችሏል።
በጥቅሉም የህብረተሰቡን የመረዳዳት፣ የመተጋገዝ ባሕልን ማጠናከር ላይ፤ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በኢኮኖሚያዊ ዘርፉ ላይ ተሰርቷል። የከተማዋን ሰላም በማስፈን የበጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ ከፍተኛ ነበር። በማህበራዊ ሆነ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፉ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስገንዝበዋል። በዚህ የደረሰን የበጎ ፈቃደኞች ተሳትፎ ከፍተኛ በመሆኑ እንደ ተቋም የበጎ ፈቃድ የሚሰጡትን እንደ ድልድይ ሆኖ የማስተባበር፣ ባሕል እንዲሆን፣ እንዲጎለብት፣ እንዲጠናከር፣ ልምምድ እንዲደረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር የታዳጊ ወጣቶች ስብዕና እንዲገነባ፣ በራስ መተማመናቸው እንዲጨምር ያግዛል።
በዚህ ሂደት ክፍያ የሚባለው ለምሳሌ ለአንድ በጎ ፈቃደኛ ከአንድ አካባቢ በራሱ ትራንስፖርት ተንቀሳቅሶ እንደ ምሳ ላሉ ገንዘብ ያወጣል። ለዚያች የተወሰኑ ወጪ መተኪያዎች ሊደረግለት ይችላል። ከዚያ ባለፈ ማስተባበሪያው በጎ ፈቃደኞች ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጉልበታቸውን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲያውሉ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይ እንደ ድልድይ ሆኖ የማገልገል ሥራ እንደሚሠራ ተናግረዋል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉ ግለሰቦችና ተቋማት አሉ፤ በተመሣሣይ ደግሞ በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን የሚፈልጉ አዛውንት እና አረጋውያን በመኖራቸው ድልድይ ሆኖ ማገናኘት እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግራቸው እንዲቀረፍ የማስተባበር ሥራን ይሠራል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ይመር ከበደ በበኩላቸው በጎ ፈቃደኝነት መንግሥት ተደራሽ ያላደረጋቸውን ተግባራት በመከወን በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን እየፈታ መሆኑን ገልጸዋል። በከተማዋ በ2016 በጀት ዓመት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በመስጠትና የበርካታ ነዋሪዎችን ተስፋ ያለመለመ ፕሮግራም በመተግበር ለሀገራችን ከተሞች በምሳሌነት የሚጠቀስ ሥራ ተሰርቷል ሲሉ ጠቅሰዋል።
በበጋ የበጎ ፈቃድ ሥራዎችም ችግኞችን በመንከባከብ፣ በሰላም እሴት ግንባታ፣ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን በመደገፍና ማገዝ ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። በጎ ፈቃደኞች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በተለመደው ቅንነትና ታታሪነት ማህበረሰቡን እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። በበጋው የተያዘው ፕሮግራም ውጤታማ እንዲሆን ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም