ለጦርነት የበረታነውን ያህል ለሰላም እንበርታ!

ስለኢትዮጵያ በጋራ ለጋራ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ ከትላንት የተመዘዘ፣ ዛሬም የቀጠለ ለነገም ዋስትና የሚሆን ከብዙኃነት ለብዙኃነት ዓይነት ዘውግ ያለው ሃሳብ መሆኑ ሲያስማማን ከጥቅምና ከመሰል የጋርዮሽ መስተጋብሮች አኳያ ሲታይም እጅግ ዋጋ ያለው፣ በላጭና አዋጭ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ለነበሩብንና ለሚኖሩብን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች አስታራቂ ምላሽ በመስጠት ስለሰላም አቻ የለሾች ናቸው፡፡

ስለኢትዮጵያ በጋራ ለጋራ በትልቁ የሚነሳ ሰፊና ገናና መልዕክት ያለው ሃሳብ ነው። በተለይ አሁን ላለንበት የፖለቲካ ሽኩቻ፣ በተለይ በዘርና በጎጥ ለተቧደነው ትውልድ፣ በተለይ ኢትዮጵያዊነት ለጠፋበት አእምሮ፣ ጦርነትን እንደዋነኛ የመፍትሔ አማራጭ ለወሰደው ፖለቲከኛ፣ በሀሰት ትርክት የጥላቻ መርዝ እየረጩ ላሉ መልስ የሚሰጥ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት እጅግ በጣም በሚል አጋዥ ቃል ካልተገለጠ በቂ ሊሆን የማይችል የብዙኃነት ስም ነው፡፡ የዛሬን አያድርገውና በዓለም አደባባይ ስም ባሰጡን የነፃነትና የሰላም፣ የፍትህና የሰብዓዊነት ስሞች ተጠርተናል፡፡ እኚህ ስሞች እንዴት መጡ ብሎ የጠየቀ ለጋራ በጋራ በተማጠ ሃሳብና ትስስር እንደመጡ መረዳት ይችላል፡፡ አሁናዊ ዘር ተኮር እሳቤዎች፣ የሰላምና መሰል ጥያቄዎች እንዴት ተወለዱ ላለም በጋራ ለጋራ ትስስራችንን በማላለት የፈጠርናቸው እንደሆኑ ለመረዳት አይቸግረውም፡፡

በጋርዮሽ ውስጥ ስላለው ጸጋና በረከት፣ አንድነትና ሉዓላዊነት፣ ክብርና ከፍታ ከእኛ በተሻለ የሚያውቅ የለም፡፡ ታሪክ የከተቡ ዳናዎቻችን በዚህ ቀለም ተውበው ኢትዮጵያዊነትን የፈጠሩ ስለመሆናቸው ተጠራጣሪ ባይኖርም አሁን ላይ ስለወየቡበት ምክንያት ግን መልስ የሌለን መሆናችን በራሱ ትልቅ ጥያቄ ሆኖ የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ በጋራ ለጋራ ጽንሰ ሃሳብም ይሄን ድብዛዜ በማድመቅ ወደመጣንበት ጥንተ ጠዋታችን በመመለስ ኢትዮጵያዊነትን የማስቀጠል ንቅናቄ ነው፡፡

ሀገር እንደ አንዲት ጉብል ብትዘከር ስሜት ያላት፣ ራዕይና ህልም የነበራት፣ ጥላቻና መለያየት የሚያስጨንቋት፣ ዘረኝነትና ቡዳኔ ክብሯን የሚገልቡባት ብለን ልንገልጻት እንችላለን፡፡ ይሄ ገለጻ ኢትዮጵያ ድሮና ዘንድሮ በሚል መታየት የሚችልም ነው፡፡ ሀገር ስሜት የሌላት የሚመስለን ካለን ስህተተኞች ነን፡፡ ሀገር ስሜት አላት፡፡ ምንም እንኳን በግዑዝ የምትጠራ ብትሆንም የዜጎቿን ስሜት በማስተጋባት በቀዳሚነት የምትጠራም ናት፡፡ ለዛም ነው ሀገራችን ስትነካ የምናነባው፡፡ ለዛም እኮ ነው ለሀገር በተዜሙ ዜማዎች ትካዜ ውስጥ የምንወድቀው፡፡

ነፃነቶቻችን ክብሮቻችን እንደሆኑ አሁናዊ ንትርኮቻችንም ስቃዮቻችን ናቸው። አስታራቂነታችን መጠሪያዎቻችን እንደነበሩ አሁናዊ የእርስ በርስ መገዳደላችንም ውርደቶቻችን ናቸው፡፡ አሸናፊ በሌለው በእኔና በእናንተ ትግል ኢትዮጵያ ከክብሯ ትጎላለች፡፡ ብኩርና በሌለው የወንድማማችነት ግፊያ ሀገራችን ክብረ ንጽህናዋ ያድፋል፡፡ ቀዳሚ በሌለው የእርስበርስ እሽቅድምድም አብሮነታችንን እያወደምን ነው፡፡ በእልህና ባለመደማመጥ ሀገር ጠባቂ መሆናችን ቀርቶ ሀገር ደፋሪዎች እየሆንን ነው፡፡ ይሄ ዓይነቱ አካሄድ እንዲረግብ ስለሀገራችን በጋራ ለጋራ ልንወያይ፣ ልንመካከር ይገባል፡፡ ያጠፋ ተረከዝ እንዲይዝ፣ የተበደለ በካሳ እንዲሽር ቢደረግ መልካም ይሆናል፡፡

ሌላው ሀገር ከእኛ ባነሰ የእርቅና የሉዓላ ዊነት አረዳድ ሀገር ሰርቷል፡፡ ከእኛ ባነሰ ሥልጣኔና ዘመናዊነት ታሪክ ሰርቷል፣ እሴት ገንብቷል፡፡ ከእኛ ባነሰ ሕዝባዊ ትስስር ሥርዓት ሰርቷል፣ በፍቅር የሚመራ ትውልድ አንጿል፡፡ ፊት ተፈጥረን የእኛ ወደ ኋላ ማለት የሚያስቆጭ ቢሆንም ለተሃድሶ ከተነሳን ግን አሁንም ቢሆን ጊዜ እንዳለን ማወቅ ይቻላል፡፡ የሀገሩን ክብረንጽህና ጠብቆ በስሟ ስም አግኝቶ እንዲኖረው እንደዛኛው ትውልድ ልዩነቶቻችንን በእርቅ በመቅጨት በጦርነት ክብሯን ያጣች ሀገራችንን መካስ እንችላለን፡፡

በአክሳሪ ጦርነት ስድስት አስርት ዓመታትን መጓዝ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዓለም አቀፍ የሰላም ስም ላላቸው ሀገራት ከፍተኛ ውርደት ነው፡፡ ይሄ ዘመን ያለፉ አክሳሪና ጥቅም አልባ ጦርነቶችን እየጠቀስን ስለሰላም አስፈላጊነት የምንናገርበት እንጂ አዲስ ጦርነት ከፍተን መከራ የምናይበት አይደለም፡፡ ሌላው ዓለም ንቆና ገፍቶ የተዋቸው የዘረኝነት እሳቤዎች እኛ ሀገር የመዘመናቸው ነገር ያስቆጫል፡፡ በሰባና በሰማኒያ ዘመን ለተመተረ እድሜያችን ፍቅር ሰጥተን ፍቅር ብንቀበል፣ ትውልዱን በሀቅ ምንጣፍ ላይ ብናራምድ ምን እናጣለን፡፡

ሀገር ግን ለሁልጊዜ በዜጎቿ ትከሻ ላይ ናት። እንደ ሰው ከአስራ ስምንት ዓመት በኋላ የራሷ ኃላፊነት ነው የምትባል አይደለችም፡፡ በሕዝቦቿ ምክር እና መርገምት የምትለማና የምትከስር ሆና የምትኖር ናት፡፡ ለዛም ነው በሃሳብ ሀገር ስለመገንባት አብዝተን የምናወራው። ዜጎች ሃሳብ ከሌላቸው ሀገር በምግብ እጦት እንደቀነጨረ ሕፃን ልጅ ናት፡፡ ለሰው ምግብ ለሀገር ደግሞ ሃሳብ እጅግ ወሳኝ ነገሮች ናቸው፡፡ የእርቅና የስምምነት ሃሳብ ስላጣን ነው ስልሳ ዓመታትን በጦርነት የሰነበትነው። የከሸፍንባቸው እነዛ ስልሳ ዓመታት ለእኛ የውድቀት ለታናናሾቻችን ደግሞ የከፍታ ዘመን ሆነው አልፈዋል፡፡

ስለኢትዮጵያ በጋራ ለጋራ ሲባል፤ ከላይ ለዘረዘርኳቸው እንከኖቻችን የመፍትሔ አማራጭ እንዲሆኑ፣ ሰላምን በጦርነት ውስጥ ከመፈለግ ወጥተን በሃሳብ የበላይነት ችግሮቻችንን ድል እንድንነሳ በማሰብ ነው፡፡ አዲስ ነገር የለንም… አሁን ላይ አዲስ ነገሮቻችን አልቀዋል፡፡ ስለሰላምና ዋጋው አውርተናል። ስለጦርነት አስከፊነት ብዙ ዘክረናል፡፡ ስለአንድነትና ወንድማማችነት ብዙ ጽፈናል። ስለኢትዮጵያዊነት እልፍ ጊዜ ለምክክር ተቀምጠናል፡፡ ያቃተን ተግባር ነው፡፡ ለውጥ ያለተግባር ደግሞ ከንቱ ነው፡፡

ዓለም ብዙ ድንቅ አስተምህሮቶች አሏት። ከዛ ውስጥ አንዱ ለውጥ ከተግባር ጋር የተቃቀፉበት አስተምህሮ ነው፡፡ የጦርነት አስከፊነትን እያወቅን ሰላምን ጦርነት ውስጥ ከፈለግን፣ የወንድማማችነትን አስፈላጊነት እየተረዳን ስለዘረኝነት ከደከምን ራሳችንን በብርቱ መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ እየሆኑብን ላሉ ማናቸውም ነገሮች ተጠያቂ ራሳችን ነን፡፡ ለጦርነት የበረታነውን ያህል ለሰላም መበርታት አለብን፡፡

ልማድ ክፉ እንደሆነ ዓለም ሌላም አስተምህሮ አላት፡፡ ከሰይጣን የበረታ አንድ እውነት በምድር ላይ ቢኖር ክፉ አመል ነው። ሰይጣንን በስመአብ ብለን እናባርረዋለን ክፉ አመል ግን በቀላል እንዳይተወን ሆኖ የተጣበቀን ነው፡፡ የሀገራችን የጦርነት አባዜም ከዚህ ክፉ ልማድ ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ የሚበልጠውን መከተል ያስፈልጋል፡፡ ሀገር የሁላችንም ቀዳሚ ጉዳያችን ናት፡፡ በሰላም ካልሆነ በጦርነት ልናስከብራት አንችልም፡፡ ልምዶቻችን ዋጋ እያስከፈሉን ከሆነ ቆም ብሎ በማሰብ የሰላም አማራጮችን ማጤን ያስፈልጋል፡፡ 60 ዓመት ተዋግተን ትርፍ ካላመጣን የጦርነት ጥቅሙ ምንድነው? ስንል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ከግጭት ወደ ሃሳብ ፍጭት የሚደረግ አዲስ የሰላም አቅጣጫ የዚህ ጽሑፍ አበይት ጉዳይ ሆኖ የሚነሳ ነው፡፡ የመጣንበትን ባለመድገምም አዲስ የእርቅ ጎዳና በመቅደድ ልማዶቻችንን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ ሀገር የጋራ ርስታችን ናት፡፡ በጋራ ርስት ላይ ደግሞ የብቻ ሃሳብ፣ የብቻ እቅድ የለም። የጋራ ርስት የጋራ ሃሳብ፣ የጋራ ባሕል፣ የጋራ ሥርዓት የተባው እውነት ነው፡፡ አጉል ትርክት ለመፍጠር ካልሆነ በዚህ አብሮነት መሀል የሚነሳ ማንኛውም ነገር ትርጉም አይሰጥም፡፡

አሁን ያለው ሀገራዊ ሁኔታ ስለኢትዮጵያ ዝም ባለማለት፣ ስለሰላሟ አስታራቂ ሃሳቦችን በማንሳት የበኩላችንን እንድንወጣ የሚያስገድድ ነው፡፡ በያገባኝም መንፈስ ከዳር ቆመን የምንመለከተው ሳይሆን በየሙያችን ሰላም ሰባኪ፣ አንድነትን ዘካሪ በሆኑ በጎ ንግግሮች እንደአስታራቂ በመሆን የበኩላችንን የምንወጣበት ጊዜ ነው፡፡ ጊዜያቸውን ያልጠበቁ ዝምታዎች ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ ጊዜው የራሳችንን ጠጠር የምናስቀምጥበት እንጂ በምንቸገረኝ ዝም የምንልበት አይደለም፡፡

በጋራ ለጋራ በሚል ሃሳብ መነሳቴ በብዙ ምክንያት ቢሆንም እንደዋነኛ የሚነሳው ግን ጥልን በፍቅር መሻር ላይ ነው፡፡ ጥልን በፍቅር የሚሽር ትውልድ ምንሽሩ ኢትዮጵያዊነት ነው። ጦርነትን በሰላም የሻረ ፖለቲከኛ አላማው ሀገርና ሕዝብ ነው፡፡ ከግል ፍላጎት መንጭተው የሚፈሱ ወንዞች የሆነ ጊዜ ውቅያኖስ ሆነው ሀገር ማስመጣቸው አይቀርም፡፡ ሀገር ከመስመጧ በፊት በጋራ ለጋራ መኖርን እንለማመድ፡፡ ከአንድ ወገን በተነሳ ማዕበል ታሪክ ከተበላሸና ሀገር ከሰመጠች በኋላ ለሰላም የምንቀመጠውን ነባር ልምምድ ትተን ከማዕበሉ በፊት የሚነሱ ገባር ወንዞችን በሰላማዊ ማድረቅ ላይ እናተኩር።

በድህነትና በኋላ ቀርነት እየተጠራን በጦርነት ወደባሰ አዘቅት መውረድ እጅግ አሳፋሪ ነው። ሰማይ እንኳን በደመና ይሻራል፡፡ በጋ እንኳን በክረምት ይረታል፡፡ ጸደይ በመኸር፣ በልግ በሆነ ወቅት ያበቃል፡፡ የእኛ ከጦርነት መውጪያ ዘመን መች ነው ? በደም አጊጠን ደመኛ መባል ውበቱ ምኑ ነው? በወንድም ሞት ጀግኖ ኒሻን ማጥለቅ ምኑ ነው ዝማኔው ? በጋራ ለጋራ ደከምን እንጂ መቼ ለብቻ ኖረን? ከብዙኃነት ለብዙኃነት የወገነ፣ ነጣጣይ ትርክቶችን በመሻር የእርቅና የስምምነት አማራጮችን የሚከፍት የትውልዱ የተሃድሶ አቅጣጫ እስከመሆን የሚደርስ የመከባበር መንፈስ ነው፡፡

ከእርስ በርስ በተወጣጣ ባሕልና ወግ የዳበሩ፣ በምንም እንዳይላሉ የጠበቁ፣ በደምና የተሳሰሩ የትስስር ገመዶች ቋጠሯቸውን ሰውረው ኢትዮጵያዊነትን እንዲያስቀጥሉ እንዲህ ያሉ የሰላም ቃሎች ዋጋቸው የት የሌለ ነው፡፡ አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ የሚፈለገውን ሕዝባዊ ሰላም ከማምጣትና የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት ረገድ ቢታዩም አዋጪ የሚሆኑ ናቸው፡፡ አብረን በቅለን በኢትዮጵያዊነት ተነስተን ሰውና ባለታሪክ የሆነበት ያ ማለዳ፣ ያ ረፋድ የከሰዓትና አመሻሽ በኩር ሳቄ ናፍቆቴ ነው፡፡

በጋራ መንጭተው ለጋራ የቆሙ በመልካም እሴት የሚጠሩ፣ ከሕዝብ ተመዘው ሕዝብን እያገለገሉ ያሉ የኢትዮጵያዊነት ጽንሰ ሃሳብ አቀንቃኝ እውነታዎች አሉን፡፡ በሥርዓት ተገርተው ነውረኝነትን የሻሩ፣ እኛነትን ያስቀጠሉ ለአብሮነት የወገኑ የወንድማማችነት አክሊሎች ያስፈልጉናል፡፡ ሞት የሌለበት፣ ዘረኝነት የመከነበት ስለአብሮነት ቃልኪዳን የምንገባበት ከሁላችን ለሁላችን የሚሆን አስተሳሰብ፤ ጦርነትን በነበር ትተን በምክክር የጸናች ሰላማዊ ሀገር የምናዋልድበት የሰላም ምኩራብ ያስፈልገናል፡፡
ቴልጌልቴልፌልሶር (የኩሽ አሸክታብ)
አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም

Recommended For You