የተሰደደው ‘ሰላዩ ዓሣ ነባሪ’ ከወታደራዊ ሥልጠና አመለጠ

ከአምስት ዓመት በፊት የቤሉጋ ዝርያ ያለው ዓሣ ነባሪ በኖርዌይ የባሕር ዳርቻ ብቅ ማለቱ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። የአገሬው ሰዎች ነጩን ዓሣ ነባሪ ቫልዲሚር ብለው ሰየሙት። መገናኛ ብዙኃን ደግሞ የሩሲያ ሰላይ ነው በሚል መነጋገሪያ አደረጉት። የዓሣ ነባሪው እንቆቅልሽ አሁን ምላሽ ያገኘ ይመስላል።

አንድ ባለሙያ ዓሣ ነባሪው የጦር አባል ነበር ብለዋል። በዚህም ብቻ ሳያበቁ በአርክቲክ ክበብ ከሚገኝ የባሕር ኃይል ያመለጠ ነው ሲሉ አክለዋል። ዶ/ር ኦልጋ ሽፓክ ግን ሰላይ ነው የሚለውን አያሳምነኝም ይላሉ። ቤሉጋ የሠለጠነው የባሕር ኃይሉን እንዲጠብቅ ነው ብለው ያምናሉ። “አስቸጋሪ” በመሆኑ ሥራውን ጥሎ ሸሽቷል ብለዋል።

ዓሣ ነባሪው በጦር ኃይሏ ስለመሠልጠኑ ሩሲያ አላረጋገጠችም። ተሳስታችኋል ብላም አልካደችም። ዶ/ር ሽፓክ እአአ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ሩሲያ ውስጥ አገልግለዋል። በ2022 ወደ ሀገራቸው ዩክሬን እስኪመለሱም ድረስ የባሕር አጥቢዎች ላይ ምርምር ሲያደርጉ ቆይተዋል። “ለእኔ 100 በመቶ እርግጠኛ ነኝ።”

ዶ/ር ሽፓክ ምስክርነታቸውን የሰጡት ሩሲያ ከሚገኙ ጓደኞቻቸው እና ከቀድሞ ባልደረቦቻቸው ጋር ያደረጉት ውይይት ላይ በመመሥረት ነው። ምሥጢራዊው ዓሣ ነባሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ትኩረትን የሳበው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር። በኖርዌይ ሰሜናዊ የባሕር ዳርቻ የሚገኙ ዓሣ አስጋሪዎች ካገኙት ጀምሮ መነጋገሪያ ሆነ።

“ዓሣ ነባሪው በጀልባው ላይ መታከክ ጀመረ” ይላል ከዓሣ አስጋሪዎቹ አንዱ የሆነው ጆር ሄስተን። “ጭንቀት የገባቸው እንስሳት ከሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው በደመ ነፍስ እንደሚያውቁ ሰምቻለሁ። ይህ አንድ ብልጥ ዓሣ ነባሪ ነው ብዬ አስቤ ነበር” ሲል አክሏል። ትዕይንቱ ያልተለመደ ነበር። ቤሉጋ ወደ ደቡብ አካባቢ እምብዛም አይታይም። ለካሜራ መሸከሚያ የሚሆን ቀበቶም ታጥቋል። “የሴንት ፒተርስበርግ መሣሪያ” የሚል ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ተጽፎበታል።

ሄስተን የካሜራ መሸከሚያውን ለማላቀቅ ረድቶታል። ቀጥሎ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ሃመርፌስት ወደብ ቀዘፈ። በዚያም ለወራት ኖረ። ዶ/ር ሽፓክ ለደኅንነታቸው ሲሉ በሩሲያ የሚገኙትን ምንጮቻቸውን መጥቀስ አልፈለጉም። ቤሉጋ ኖርዌይ ውስጥ ሲታይ የሩሲያ የባሕር ውስጥ አጥቢ እንስሳ ማኅበረሰብ የእነርሱ መሆኑን መለየታቸውን እንደነገሯቸው ገልጸዋል።

“በእንስሳት ሐኪሞች እና በአሠልጣኞች በኩል እንደመጣ መልዕክት ደግሞ አንድሩሃ የሚባል ቤሉጋ ጠፍቷል” ብለዋል። እንደ ዶ/ር ሽፓክ ከሆነ አንድሩሃ/ቫልዲሚር ለመጀመሪያ ጊዜ የተያዘው እአአ በ2013 በሩሲያ ሩቅ ምሥራቅ በሚገኘው ኦክሆትስክ ባሕር ነበር።
ከአንድ ዓመት በኋላ ደግሞ በሴንት ፒተርስበርግ ወደ ሚገኘው ዶልፊናሪየም (የዓሣ ነባሪዎች ማቆያ) አርክቲክ ወታደራዊ ተቋም ተዛወረ። አሠልጣኞቹ እና የእንስሳት ሐኪሞቹ የሚገኙትም በዚህ ተቋም ነው። “በእንስሳው በመተማመን በክፍት ውሃ ውስጥ መሥራት ሲጀምሩ እንስሳው ተስፋ ቆርጦ እንዳመለጠ አምናለሁ” ብለዋል።

“ከነበረበት ዶልፊናሪየም እንደሰማሁት ከሆነ ዓሣ ነባሪው ብልህ ነው። በዚህ ምክንያት ለሥልጠናም ተመራጭ ሆኗል። በዚያው ልክ ደግሞ ኃይለኛ በመሆኑ ጀልባውን [መከተል] ትቶ ወደ ፈለገበት በመሄዱ አልተገረሙም” ሲሉ ገልጸዋል።
የሳተላይት ምሥሎችን በመጠቀም መርማንስክ የሚገኘው የቀድሞው የቫልዲሚር/አንድሩሃ መኖሪያ የነበረው የሩሲያው የባሕር ኃይል ጣቢያን ለመመልከት ተሞክሯል። በአካባቢው ውሃ ውስጥ ነጭ ዓሣ ነባሪ የሚመስሉ ነገሮች በግልጽ ይታያሉ። “የቤሉጋ ዓሣ ነባሪዎች የሚገኙት ባሕር ሰርጓጅ እና ሌሎች መርከቦች ከሚገኙበት አቅራቢያ መሆኑ የጥበቃ ሥራ አካል መሆናቸውን ሊነግረን ይችላል” ብለዋል።

ቫልዲሚር/አንድሩሃ በሠራዊቷ የሠለጠኑ ናቸው ስለሚባለው ጉዳይ ሩሲያ በይፋ ተናግራ አታውቅም። የባሕር ውስጥ አጥቢ እንስሳትን ለወታደራዊ አገልግሎት የማሠልጠን ግን ረጅም ታሪክ አላት። “ይህን እንስሳ ለስለላ የምንጠቀምበት ከሆነ “እባክዎ በዚህ ቁጥር ይደውሉ” ከሚል መልዕክት ጋር የሞባይል ስልክ ቁጥር የምናያይዝ ይመስላችኋል?” ሲሉ የሩሲያ ተጠባባቂ ኃይል አባል የሆኑት ኮሎኔል ቪክቶር ባራኔትስ እአአ በ2019 ጠይቀዋል።

በሚያሳዝን ሁኔታ ግን የቫልዲሚር/አንድሩሃ አስገራሚ ታሪክ ፍጻሜው አላማረም። እራሱን መመገብን ከተማረ በኋላ በኖርዌይ የባሕር ዳርቻ ወደ ደቡብ በማቅናት ለበርካታ ዓመታት በዚያ አሳልፏል። በግንቦት 2023 ደግሞ በስዊድን የባሕር ዳርቻ ለመታየት በቃ። መስከረም 1 ቀን 2024 ግን አስከሬኑ በኖርዌይ ደቡብ-ምዕራብ የባሕር ዳርቻ ላይ በሪሳቪካ ከተማ አቅራቢያ ባሕር ላይ ሲንሳፈፍ ተገኝቷል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው። እንስሳትን ለስለላ መጠቀም በብዙ ሀገራት እየተለመደ መምጣቱ ይታወቃል፡፡

አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም

Recommended For You