ሰሞኑን ወደ ጦር ኃይሎች ለመሄድ ፒያሳ ሸዋ ዳቦ አጠገብ ከተደረደሩ ታክሲዎች አንዱ ውስጥ ገብቼ ጉዞ ተጀመረ፡፡ ታክሲው ቁልቁል ወደ ሱማሌ ተራ ጥቂት እንደተጓዘ በስተቀኝ በኩል ካለው የፈራረሰ የአሜሪካ ግቢ የሚወጣው ሽታ በታክሲው ውስጥ የነበርነውን ሁሉ አፍንጫችንን እንድንይዝ አስገደደን፡፡
ይህ አካባቢ ከሦስት ዓመታት በፊት ለልማት በሚል ምክንያት ተነስቶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ያለምንም ልማት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆኖ የቆየ ቦታ ነው፡፡ አካባቢው ከአትክልት ተራ በመርካቶ ጫፍ ዞሮ እስከ ተክለሃይማኖት አደባባይ ከዚያም በሱማሌ ተራ እስከ አትክልት ተራ ያለውን ሰፊ ቦታ የሚያካልል ነው፡፡
ይህ ስፍራ ለልማት ሲነሳ በርካታ ቅሬታዎችና የህዝብ ሮሮ የተስተናገደበት እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ለልማት አካባቢው ሲነሳ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑም ባሻገር በርካታ ነዋሪዎች ቤት ሳይሰጣቸው ቤታቸው እንዲፈርስ በመደረጉ የላስቲክ ቤት ሠርተው ለመጠለል ተገድደውም ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር አንዳንድ ነዋሪዎች ተነስተው ከፊሎቹ ባለመነሳታቸው እና ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ መፀዳጃ ቤቶች ፈንድተውና በተለያየ ወቅት በቱቦ የተገናኙ የፍሳሽ ማስወገጃዎች እየተጥለቀለቁ ዜጎች ለከፍተኛ የጤና ችግር የተዳረጉበት ወቅት እንደነበር እናስተውላለን፡፡ በተለይ ህፃናትና አረጋውያንን በቦታው ላይ በዚያ የቆሸሸ ስፍራ ተቀምጠው ማየት አስቸጋሪ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
የአሜሪካ ግቢ ነዋሪዎች ችግር የዚያን ጊዜው ችግር ብቻ አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን በዚህ የፈራረሰ ስፍራ በርካታ ነዋሪዎች ላስቲክ ዘርግተው ይኖራሉ፡፡ አካባቢውን በዚህ መልኩ ውስጡ ገብቶ ያየ አንድ እንግዳ አዲስ አበባ አካባቢ ሳይሆን ፈፅሞ የማይታወቅ የቅጣት ስፍራ ሊመስለው ይችላል፡፡ ይህንን ስፍራ አብዛኛው የአዲስ አበባም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት አሁን ባለበት ደረጃ የሚገነዘቡት አይመስለኝም፡፡
አሁን ስለተነሳሁበት የአካባቢው የፅዳት መጓደል ሁኔታ ከማንሳቴ በፊት ቀደም ሲል በአካባቢው ላይ ስለተፈፀመው ደባ በጥቂቱ ልጨምር፡፡ መንግሥት በርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎችን አንስቶ በጥሩ ሁኔታ መልሶ ማልማቱ የሚካድ አይደለም፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ ከአሜሪካ ግቢ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የልደታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሰፈር ማየት በቂ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአሜሪካ ግቢ የመልሶ ማልማት ሥራ በዚያ አይነት ሁኔታ የአካባቢውን ነዋሪዎች በሚያስከፋ ሁኔታ በተጣደፈና በክረምት መከናወኑ በርካቶች ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር የተዳረጉበት ነው፡፡ በዚህ ብቻም አያበቃም፡፡ በአካባቢው ለበርከታ ዜጎች አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ አነስተኛ ድርጅቶችም በአስቸኳይ እንዲዘጉ በመደረጉ በርካታ ዜጎች ከስራ እንዲፈናቀሉም ምክንያት ነበር፡፡ የዚህ እጣ ፈንታ ከደረሰባቸው ውስጥ ደግሞ የበላይ ተክሉ ኬክ ቤት ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህ ኬክ ቤት ለበርካታ ዓመታት የቆየና አንድ መካከለኛ ህንፃ ላይ የሚከናወን አነስተኛ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ኬክ ቤት ቢሆንም በአነስተኛ ዋጋ ዳቦን ጨምሮ የተለያዩ ጣፋጭ ብስኩቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚው ሲያቀርብ የኖረ ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ከ80 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ሠራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ድርጅት ነበር፡፡ ይህ ኬክ ቤት ግን በወቅቱ በአስቸኳይ እንዲፈርስ በመደረጉ ሠራተኞች ተበትነዋል፡፡ ያም ሆኖ ግን አካባቢው ላለፉት ሦስት ዓመታት ያለምንም ልማት ፈርሶ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆኗል፡፡
በወቅቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን ሲያነጋር የነበረው ደግሞ ይህ ኬክ ቤት የነበረበት ህንፃ ጠንካራና በውበትም ቢሆን አሁን በአካባቢው ሳይፈርሱ ባሉበት እንዲቀጥሉ ከተደረጉ ህንጻዎች ጋር ተመጣጣኝ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ህንጻ ለምን በዚያ ሁኔታ እንዲያ በአስቸኳይ የመፍረስ ዕጣ እንደተፈረደበት የሚያውቁት ባለቤቶቹና ያፈረሱት አካላት ብቻ ናቸው፡፡
እንግዲህ ከላይ እንደገለፅኩት ይህ አካባቢ በዚህ ሁኔታ በክረምት ወቅት በአስቸኳይ እንዲፈርስ ቢደረግም ላለፉት ሦስት ዓመታት የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆኖ እስከዛሬ ዘልቋል፡፡ ሰሞኑን በአካባቢው በታክሲ ስናልፍም ያጋጠመን ሽታም ከዚሁ አካባቢ የሚመነጨው የቆሻሻ ሽታ ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ተክለሃይማኖት አደባባይ ጫፉ ላይ መቆም በቂ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ለጥቂት ደቂቃ የሚቆም ሰው አንድም ለጉንፋን ተዳርጎ አልያም በቆሻሻው ሽታ አፍንጫው ተደፍኖ እንደሚመለስ ለአፍታም አያጠራጥርም፡፡
ከዚህም ባሻገር የዚህን አካባቢ መበላሸት ለመረዳት በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ተሳፍሮ ከጊዮርጊስ አደባባይ ወደ አውቶቡስ ተራ መጓዝ በቂ ነው፡፡ በዚህ መስመር በባቡር ሲጓዙ ከባቡር ላይ ቁልቁል ይህንን የፈራረሰና የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሆነ ስፍራ በቀላሉ ይገነዘባሉ። እውን አዲስ አበባችን በዚህ መልኩ ስትበላሽ ዝም ብሎ ለማየትም አቅም አይኖርም (የመወሰን ሥልጣን የተሰጠው አካል ከሆነ)፡፡ በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ባለሥልጣን አንዳንድ ጊዜ ወደ ህዝቡ ወረድ ብሎ ማየት ቢቻል በርካታ ችግሮች መገንዘብ እንደሚቻል ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ በተለይ በባቡር፣ በአውቶቡስና አንዳንዴም በግላቸው ተሽከርካሪም ቢሆን ወደ መንደሮች ውስጥ ገባ ብሎ ማየት ቢቻል ምን ያህል የአዲስ አበባ የአኗኗር ሁኔታ የተዘበራረቀ እንደሆነ ለመገንዘብ ይጠቅማል፡፡
ይህ የቆሻሻ ችግር ደግሞ አሁን አሁን በሲኒማ ራስ በኩል ግማሽ አስፋልት ድረስ ዘልቆ እየገባ አካባቢውን የቆሻሻ መጣያ አስመስሎታል፡፡ በዚህ አካባቢ በአስፋልት ላይ የሚጣለው ቆሻሻ ከሰዓት በኋላ ተሸከርካሪዎችን እስከመዝጋት በሚያደርስ ሁኔታ መሃል አስፋልት ድረስ ይከመራል፡፡ ከዚያም በኋላ ቆሻሻው ሲነሳ በአግባቡ ተነስቶ አካባቢው ስለማይጸዳ አካባቢው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ መስሎ ይታያል፡፡
በፒያሳ አካባቢ ያለውም የመልሶ ማልማት ሥራ በተመሳሳይ በመዘግየቱ የቆሻሻ መንስኤ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በተለምዶ «ውቤ በረሃ» እየተባለ ይጠራ በነበረው አካባቢ ያለው መንደር መፍረሱን ተከትሎ በአካባቢው ያለው የቆሻሻ ሁኔታ አልፎ አልፎ ከውስጥ ወደ አካባቢው እየገነፈለ አካባቢውን የቆሻሻ መጣያ ሲያስመስል ይስተዋላል፡፡ ይህ አካባቢም ለረጅም ጊዜ ያለግንባታ የቆየ በመሆኑ የችግሩ መንስኤ ነው፡፡
ሌሎች በዚህ መልኩ ለልማት ተብለው የፈረሱና ግንባታ ሳይካሄድባቸው ለረጅም ጊዜ የቆዩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ የቆሻሻ መንስኤ ሲሆኑ ማየት የተለመደ ነው፡፡ በአንድ በኩል ከአካባቢው የሚነሳው ማህበረሰብ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ይዳረጋል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አካባቢው ሳይለማ በቆየ ቁጥር የማህበራዊ ቀውስ መንስኤ ይሆናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ለልማት የሚነሱ አካባቢዎች ለምን በዚህ መልኩ ለረጅም ጊዜ ሳይለሙ እንደሚቆዩ ግልፅ መሆን ያልቻለ ምስጢር ነው፡፡ በርግጥ የሚመለከታቸው አካላት ይህንን የመዘግየት ምክንያት ከካሳ ክፍያና ከተለያዩ ችግሮች ጋር ያገናኙታል፡፡ ምንም አይነት ምክንያት ቢኖር ግን በዚህ መልኩ ለረጅም ጊዜ ያለግንባታ መቆየቱ አሳማኝ ምክንያት ሲቀርብበት አላየሁም፡፡
በእኔ እምነት ግን የአብዛኛው ችግር መንስኤ የሚከናወኑ ሥራዎች የዘመቻ ሥራዎች በመሆናቸው ነው፡፡ በተለይ አንድ ሰሞን «ይህ አካባቢ ሊፈርስ ነው» ሲባል በዘመቻ ነዋሪዎችን ለማስነሳት ርብርብ ይደረጋል፡፡ በዚህ መልኩ የሚካሄደው ውክቢያ ግንባታው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የሚካሄድ እስከሚመስል ድረስ ሁሉም ይሯሯጣል፡፡ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ሁሉም ነገር መልሶ በነበረበት ይቀጥላል፡፡
አሁን አሁን በአዲስ አበባ የሚታየው የቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በመልሶ ማልማት አካባቢዎች ቆሻሻን በተገኘበት ቦታ የመጣል አዝማሚያ በስፋት ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ከተማዋን የቆሻሻ ማጠራቀሚያ እያደረጋት ይገኛል፡፡
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የበርካታ ዓለምአቀፋዊና አህጉራዊ ተቋማት ማዕከልና የበርካታ ዲፕሎማቶች መቀመጫ መሆኗ የሚታወቅ እውነታ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ኃላፊነት የተሰጣት ከተማ ደግሞ በዚህ መልኩ በፅዳት ወደ ኋላ ስትመለስ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይደለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የካቢኔ አባሎቻቸውን ሹመት ይፋ ባደረጉበት ወቅት እንደገለፁት፣ አዲስ አበባ ለሥራ ምቹና ለመዝናናትም ተመራጭ ከተማ እንድትሆን ጠንክሮ መሥራት እንደሚገባ ማሳሰባቸው ይታወሳል፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ ፅዳት ዋነኛው ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡
ሰሞኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በለገሃር አካባቢ ያስጀመሩት የዘመናዊ መንደር ግንባታ አዲስ አበባን ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ ከተያዙ እቅዶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ እንዲህ አይነት አበረታችና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች ባሉበት ሁኔታ በአንፃሩ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚታየው የቆሻሻ በየቦታው መጣልና ከተማዋን የመበከል አዝማሚያ ደግሞ በአጭሩ ሊገታ ይገባል፡፡ ይህ በአግባቡ ካልተሠራ ግን የአዲስ አበባን ገፅታ የሚያበላሽ በመሆኑ ሊታሰብት ይገባል፡፡
አዲስ አበባ ላለፉት አስር ዓመታት ሰፊ ርብርብ የተደረገባት ከተማ ናት፡፡ በተለይ የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግሮች ለመፍታት የተከናወኑ ተግባራት ሰፊ ሀብት የፈሰሰባቸው ናቸው፡፡ በርካቶችም የመኖሪያ ችግሮቻቸው ተቀርፎላቸዋል፡፡ የከተማዋን የመሰረተ ልማት ፍላጎትም ለማሟላት የተሠራው ሥራ ተጠቃሽ ነው፡፡ የመንገድና የባቡር ግንባታውን ማንሳት ይቻላል፡፡ ያም ሆኖ ግን የከተማዋ ችግሮች ዛሬም ቢሆን ገና የበላይነታቸውን ይዘው ይገኛሉ፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት በርካታ የሥራ ዕድሎችንም እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የሴፍቲኔት ፕሮግራም ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ፕሮግራም በአንድ በኩል የከተማዋን የፅዳት ችግር ለመፍታት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህብረተሰቡን የሥራ አጥነት ችግሮች ለማቃለል እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት ሥራ ላይ በማተኮር ጠዋት ጠዋት በየመንደሩ ፅዳት ሲደረግ እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን ይህ ፅዳት ዝም ብሎ አለ ለመባል ብቻ መሆን የለበትም፡፡ የሚፈለገው ውጤት በሚያመጣ መልኩም ተግባዊ ሊደረግ ይገባል፡፡
አዲስ አበባ ዛሬም ቢሆን ገና ለነዋሪዎቿ ምቹ መሆን አልቻለችም፡፡ ህዝቡ ገና የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱ አልተቀረፈም፡፡ በመሰረተ ልማት ረገድም ገና የመንገድና የትራንስፖርት ችግሮች የህዝቦቿ መሰረታዊ ጥያቄ ከመሆን አልዘለሉም፡፡ በተወሰነ ደረጃ እየተሻሻለ መጥቶ የነበረው የከተማዋ ፅዳት ደግሞ ተመልሶ እንዲህ ሲዝረከረክ አዲስ አበባችን አንድ እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ እንዳትሆን ከወዲሁ ጥንቃቄ ማድረግን የሚሻ ነው፡፡ በተለይ በእጃችን ያለውና በቀላሉ ልንወጣው የምችለው የቆሻሻ አያያዝ ሥርዓት ለምን ከቁጥጥራችን ውጪ እንደሚሆን ማጥናትና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ህደዳር 24/2011
ውቤ ከልደታ