አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ዕድሜያቸው ከአንድ ምዕተ ዓመት አይዘልም። ኢትዮጵያ ግን የረጅም (ሦስት ሺህ) ዘመን ታሪክ ያላት፤ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ በንጉሠ- ነገሥታት እና ንግሥተ-ነገሥታት የተመራች ሀገር ናት። የዘውዳዊው የአገዛዝ ሥርዓት በ1967 ከተገባደደ በኋላም ኢትዮጵያ በተለያዩ የመንግሥት አይነቶች ተዳድራለች።
የኢትዮጵያ ሕዝብም በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓት ሥር እየተዳደረ በከፍታም፣ በዝቅታም አልፏል፣ ነፃነቱን ጠብቆ፣ ዳር ድንበሩን አስከብሮ ለዛሬ ደርሷል። ከራሱ አልፎ የጥቁር ሕዝብ የነፃነት ምልክት ለመሆን በቅቷል። ነገር ግን ሕዝቡ አገሩን ሊወር የመጣ ጠላትን ለመመከት ከከፈለው መስዋዕትነት በላይ በተለያዩ ዘመናት አገሪቱን ሲያስተዳድሩ በነበሩ መንግሥታት የደረሰበት ግፍና መከራ ህልቆ መሳፍርት የለውም።
በተለያዩ የአገዛዝ ዘመን ሲደርስበት ከነበረው የጭቆና ቀንበር ለመላቀቅም መራራ መስዋዕትነት ከፍሏል። ይሁን እንጂ ሕዝቡ መተኪያ የሌለውን ውድ ሕይወቱን ገብሮ፣ ደሙን አፍሶ ያመጣውን ለውጥ ተንከባክቦ ዳር ሳያደርሰው በጮሌዎች ይነጠቃል። መስዋዕትነት ከፍሎ ያመጣው ለውጥ ሐዲዱን እንዳይስት ማሠሪያ ሥርዓትና ተቋም ሲያበጅለት አይስተዋልም።
በዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ከአጋም እንደተጠጋ ቁልቋል ዕድሜ ልኩን ሲያለቅስ ኖሯል። በተለያየ ጊዜ ለውጥ እንዲመጣ፣ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን፣ እኩልነትና ፍትሐዊነት እንዲነግስ መስዋዕትነት ቢከፍልም በመጣው ላውጥ ሳይጠቀምበት ደመ ከልብ ሆኖ ቀርቷል።
ቀደም ያለውን ትተን ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ጀምሮ በአገሪቱ የመጡ ፖለቲካዊ ለውጦችን ብንመለከት፤ የካቲት ወር 1966 ዓ.ም የዘውድ አገዛዙን ሥርዓት በመቃወም በአርሶ አደሩ፣ በተማሪው፣ በአስተማሪው፣ በመንግሥት ሠራተኛው፣ በወዛደሩ፣ በነጋዴው እና በመለዮ ለባሹ ወ.ዘ.ተ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ጊዜ ሳይወስድበት በ6 ወራት ውስጥ ግቡን መታ::
ሆኖም ሕዝባዊ አመጹን የሚመራው የተደራጀ ፓርቲ ባለመኖሩ በር የተከፈተለት መለዮ ለባሹ ኃይል፤ ከጦር ኃይሎች ፣ ከክቡር ዘበኛ እና ከፖሊስ የተውጣጡ አስተባባሪ ኮሚቴ መሥርቶ “ኢትዮጵያ ትቅደም፣ አቆርቋዧ ይውደም” በሚል መርሕ ስር ሰፊ ሊባል የሚችል የሕዝብ ድጋፍ አገኝ። ሕዝቡም ለዘመናት የታገለለትን የእኩልነት፣ የፍትሐዊነት፣ የዲሞክራሲ፣ የልማት፣ ወ.ዘ.ተ ጥያቄዎቹን የሚመልሱለት ተቋም ሳይመሠርትና ሥርዓት ሳያበጅ እጁ ላይ መስዋዕት የከፈለበት ለውጥ በመለዮ ለባሹ ተመነተፈ።
ሕዝቡ የከፈለውን መስዋዕትነት ለግል የሥልጣን ጥሙ ማርኪያ ያደረገው ወታደራዊ ኮሚቴም ንጉሡን ከሥልጣን አውርዶ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር “ደርግ” የሚል ስም በመያዝ ኢትዮጵያን ከመስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ጀምሮ ማስተዳደር ጀመረ:: ቀስ በቀስም ደርግ የሥልጣን ወንበሩን በማመቻቸት የአገሪቷ መንግሥት ለመሆን ቻለ::
የደርግ መንግሥት በሥልጣን በቆየበት 17 ዓመት ውስጥ በሚከተለው ሶሻሊዝም ወይም ኅብረተሰባዊነት ርዕዮተ ዓለም የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ እድገትና ልማት ከድጡ ወደ ማጡ የገባበትና ሕዝቡም በአምባገነናዊና ፈላጭ ቆራጭ አስተዳደር ሥርዓት ነጻነቱ ተገፎ፣ ኃይማኖቱ ተዋርዶ፣ ባሕል ወጉ ጠፍቶ 17 ዓመታት የጨለማ ጊዜን ገፍቷል።
አያሌ ወጣቶችና ምሑራን በቀይ ሽብር ተረሽነዋል፣ በአብዮታዊ ውትድርና እረግፈዋል። በጥቅሉ ግርማዊ ቀዳማዊ ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ተወግደው የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ አገሪቷ ሰላም እርቋት በቀይና ነጭ ሽብር ታመሰች። የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቱ ነገሰ።
የሴራና የመጠላለፍ ፖለቲካ መርዝ ተጸንሶ፣ ተወልዶ፣ አደገ። ይህ የፖለቲካ ባሕል በአገሪቱ እየተንሰራፋ መጥቶ ዳፋው ለዛሬው ትውልድ ተርፎታል። የደርግ ሥርዓት እጅግ አምባገነናዊ ከመሆኑ የተነሳ እናት “ልጄን የዛሬን ማሩልኝ፣ ዳግመኛ ወንድ ልጅ አልወልድም!” እስከ ማለት የደረሰችበት ጊዜ ነበር።
በደርግ ዘመን ይደርስ የነበረውን ግፍና መከራ ለመታገል ብሎም ከቀይና ነጭ ሽብር ሰይፍ ለማምለጥ በዚያን ዘመን አያሌ የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በየአቅጣጫው በረሃ ገቡ። የትጥቅ ትግሉንም ተቀላቀሉ። በወቅቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ወደ ትጥቅ ትግል ከገቡት መካከል በትግራይ ክልል በደደቢት በረሃ የተጠነሰሰው “የሕወሓት” ቡድን አንዱ ነው።
ይህ ቡድን ከ17 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ መናገሻ የሆነችውን አዲስ አበባን ተቆጣጠረ። ሕወሓት ቀስ በቀስም እንደድመት ጸጉሩን አለስልሶ መላ አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ “ለኢትዮጵያ ነፃነትና ዲሞክራሲ” ስል ብዙ መስዋዕትነት ስለከፈልሁ በአገሪቱ ለሚመሠረተው መንግሥታዊ ሥርዓትና መተዳደሪያ ሕግ “እኔ አውቅላችኋለሁ” አለ።
በወቅቱም የመጣውን ለውጥ ተቀብሎ የሚመራ ሌላ የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲና ተገዳዳሪ ኃይል ባለመኖሩ ሕወሓት በስሩ ተላላኪዎችን አሰልፎ አገሪቱን በራሱ አቅጣጫና ራዕይ እንድታመራ አደረጋት። በዚህም ሕወሓት ኢትዮጵያን በዘር፣ በቋንቋ እና በኃይማኖት ከፋፍሎ የሕዝቡን አንድነት በመሸርሸር እንዳሻው ለመግዛት ያመቸው ዘንድ ከደደቢት በረሃ ይዞት የመጣውን ሕገ ደንቡን የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አደረገው::
በዚህ የከፋፍለህ ግዛ የአስተዳደር ሥርዓትም የኢትዮጵያ ሕዝብ አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓትን በአንድነት ይታገል ከነበረበት ከፍታው ወርዶ፤ በታሪኩ አድርጎት በማያውቀው ልክ በዘር፣ በኃይማኖት፣ በቋንቋ፣ ወ.ዘ.ተ ተቡድኑ ለተለያዩ ግጭቶች ተዳረገ ።
ታዲያ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም በአገሪቱ የመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ለኢትዮጵያ እና ሕዝቧ ምን ይዞለት መጣ? ከተባለ ዳግም ሕዝቡ የከፈለው መስዋዕትነት በአንድ ቡድን የበላይነት ተጠልፎ ላለፉት 27 ዓመታት የጨለማ ሕይወት እንዲገፋ ተገዷል። ላለፉት 27 ዓመታት በሕወሓት መራሹ የአስተዳደር ሥርዓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የደረሰውን ግፍና መከራ መናገር ለቀባሪ እንደማርዳት ነው።
ዲሞክራሲ፣ ፍትሕ፣ ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል የማይታሰብበት፣ ዜጋው በፈለገው የሃገሩ ግዛት የመኖር ለዘመናት ተጠብቆ የቆየው መብቱ የተነፈገበት፤ በአንጻሩ ሙስና (ሌብነት)፣ ስደት፣ ዘረኝነት የተንሰራፋበት ነበር።
ሕዝቡ ዋጋ ከፍሎ ያመጣውን ለውጥ በማይናወጥ የዲሞክራሲ መሠረት ላይ ማስቀመጥ ቢሳነውም ሁሌም ለውጥ ለማምጣት የማይበገረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሓት መራሹ የአስተዳደር ሥርዓት መቋጫ እንዲያገኝ ሁሉን አቀፍ ትግል አድርጓል። በተለይ ወጣቱ ደረቱን ለስናይፐር ጥይት ማብረጃ አድርጎ በከፈለው መራራ የሕይወት መስዋዕትነት እና በለውጥ ኃይል ቁርጠኛ አቋም መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም ሕወሓት መራሹ የአስተዳደር ሥርዓት ላይመለስ ተገርስሶ ወድቋል።
ሥርዓቱን ያስወገደው ለውጥ አሁን ላይ አምስት ዓመታቱን እያስቆጠረ ነው። በነዚህ ዓመታት ውስጥም የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱትን ጨምሮ የተለያዩ ተግዳሮቶች አጋጥመውታል። እነዚህ ከውስጥም ከውጪም ያጋጠሙት ፈተናዎች ሀገርና ሕዝብን ያስከፈሉት ዋጋም ከፍያሉ፤ ጠባሳዎቹም ገና በአግባቡ ያላገገሙ ናቸው።
ትናንት ሆነ ዛሬ ላይ እንደ ሀገርና ሕዝብ እየከፈልነው ያለው ዋጋ በዋናነት ሀገሪቱን ወደተሻለ የዲሞክራሲ ሥርዓት ያሸጋግራታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ለውጥ ውጤታማ ለማድረግ ነው። ይህ ለውጥ እንደቀደሙት ለውጦች ፍሬ አልባ እንዳይሆን ከሁሉም በላይ ሥርዓቱን በአግባቡ ለመገንባት የሚያስችሉ ተቋማት ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስን ጠይቋል ፡፡
በተለይም የፍትሕ፣ የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማትን ገለልተኝ እና ዘመኑን የሚመጥኑ ማድረግ፤ ለውጡን ፍሬያማ ከማድረግ ባለፈ ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ ወሳኝ እንደሆኑ ታምኖባቸው ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተቋማቱ ላይ የሪፎርም ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ ይገኛሉ ።
የተቋማቱ የሪፎርም ሥራዎች ከሁሉም በላይ የአመለካከት ለውጥ የሚፈልጉ ከመሆናቸው አንጻር፤ በአንድ ምሽት ተጠናቀው ፍሬያቸውን ማየት ባይቻልም፤ የሪፎርም ጅማሪያቸውን በጠንካራ መሠረት ላይ ማዋቀር ከተቻለ አሁን ላይ ሆኖ ስለለውጡ ተስፈኛ መሆን እንደሚቻል ይታመናል። ከዚህ የተነሳም የሪፎርም ሥራዎች በጠንካራ መሠረት ላይ ከማዋቀር ጀምሮ፤ ሥራዎቹ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ተገቢ ነው። ሕዝቡም የለውጡ ባለቤት ከመሆኑ አንጻር ሪፎርሙን ከመንግሥት ጎን ሆኖ ከመደገፍ ባለፈ የእለት ተእለት ሂደቱን በኃላፊነት መንፈስ መከታተል ይጠበቅበታል። ይህንን በቁርጠኝነት ማድረግ ሲቻል ነው፣ ለውጡ በስኬት መንገድ ላይ ስለመሆኑ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ።
ሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም