ሰላም ልጆች እንደምን ሰነበታችሁ፤ ፈተና እየደረሰ ነው አይደል፤ ጥናት እንዴት ይዟችኋል? ልጆች ትምህርትና ጥናት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ በትምህርት ላይ እስካላችሁ ድረስ የግድ ማጥናት እንደሚያስፈልጋችሁ በደንብ ታውቃላችሁ አይደል? በእርግጥ ሁላችሁም ይሄን ታውቃላችሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ መልሳችሁ አዎ እናውቃለን እንደሆነም እርግጠኛ ነኝ፡፡
ልጆች ፈተና ተፈትናችሁና ከክፍል ወደ ክፍል የማለፋችሁን መልካም ዜና ሰምታችሁ ትምህርት ቤት እስኪዘጋ ድረስ እንደገና ወደ ትምህርትና ጥናት ለመመለስ የግድ በትምህርትና በጥናት የተጨናነቀ አእምሯችሁን ዘና ማድረግ አለባችሁ እሽ! በተለይ ከሰኞ እስከ አርብ ያለው ጊዜ ዘና ለማለት ላይበቃችሁ ይችላል፡ ፡ ምክንያቱም ከትምህርት ቤት መልስ ያለው ጊዜ ጥቂት ስለሆነ ከእማማና አባባ ጋር ሽርሽር ለመሄድም ሆነ ወጣ ብሎ ሻይ እየጠጡ ለመዝናናት አይበቃም፡፡ ሆኖም ልጆች እናንተን ዘና የሚያደርጉ ብዙ አማራጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ስለ ተለያዩ እንስሳት መዝሙር ማድመጥ፤ ከሰው በተረት መልክ መስማት፤ እንዲሁም ጋዜጣና መጽሐፍት ላይ ስለ እንስሳትና ሌሎች አዝናንተው እውቀት የሚያስጨብጡ ጽሑፎችን በማንበብ ዘና ማለትና መደሰት ትችላላችሁ፡፡
ልጆች ለዛሬ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ወደሚገኘውና በአገራችን ብቸኛው ወደ ሆነው የኢትዮጵያ የእንስሳት የተፈጥሮ ቅርስ መዘክር (ሙዚየም) ጎራ ብዬ እንደተለመደው የመዘክሩ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ለማ አስደናቂ አፈጣጠር ስላላት ጥንቸል የነገሩኝን እውቀት እያገኛችሁ ዘና እንድትሉበት ላካፍላችሁ፤
ልጆች ታዲያ ኃላፊዋ ወይዘሮ አልማዝ እንደነገሩኝ ጥንቸል ከአጥቢ የዱር እንስሳት ዓይነት ትመደባለች፡፡ ጥንቸል መድፍ የማይበሳው የሚባል ዓይነት ጠንካራ ቆዳ አላት፡፡ መጠኗ ትንሽ ቢሆንም በዚህ ጠንካራና ቶሎ ሊጎዳ በማይችል ቆዳዋ የአራዊቶች ንጉስ እየተባለ በኃይለኛነቱ በእንስሳት ዘንድ ከሚፈራውና ከሚከበረው ግዙፍ እንስሳ ከአንበሳ እንኳን በድብድበ ብትገጥም በቀላሉ የማትጎዳና የማትሸነፍ ይባልላታል፡፡ ልጆች ጥንቸል 28 ጥርሶች ያሏት ሲሆን፤ ጥርሷ እስከ እለተ ሞቷ ድረስ ማደግ እንደማያቆምም ነግረውናል አስጎበኛችን፡፡
ጆሮዋ ሹክሹክታን ጨምሮ ከሩቅ የትኛውንም ድምጽ የመስማት ችሎታ ያለው ንቁ እንስሳም ነች። ልጆች ጥንቸል ብዙ አስገራሚ ነገሮች ያላት ፍጥረት ስትሆን በሩጫም ከእንስሳት ወገን በጣም ፈጣን ነች፡፡ በተለይ በሩጫ ፈጣን እንድትሆን የረዳት አጭር ቁመቷና በመጠን ትንሽነቷ እንደሆነም ይነገርላታል፡፡ ጥንቸል መራባት የምትጀምረው በተወለደች በሶስትና አራት ወራት ጊዜ ውስጥ መሆኑንም ኃላፊዋ ወይዘሮ አልማዝ አስረድተውናል፡፡
ልጆች ከሚያስገርመው የጥንቸል አፈጣጠር አንዱ ምን መሰላችሁ፤ በማንኛውም ጊዜ የወንድ ዘር ካገኘች መፀነስና መውለድ መቻሏ ነው፡፡ ሆኖም ልጆች ጥንቸል በማንኛውም ጊዜ መፀነስና መውለድ ትቻል እንጂ የተወሰነ የእርግዝና ወቅት የላትም። አይገርምም ልጆች ? ጥንቸል የወንዴ ዘር ፍሬ ካገኘች በ24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ እንቁላሏን ማዘጋጀት ትችላለች፡፡ የወንዴውን ዘር ተቀብላ እስከ ተወሰነ ሰዓት ድረስ በምቾት ማስቀመጡን በሚገባ የምታውቅ አስደናቂና ብልጥ ፍጥረት ናት ፡፡ ልጆች ጥንቸል እንዳልኳችሁ ቋሚ የእርግዝና ወቅት የላትም፡፡ ከፀነሰች በኋላ አርግዛ የምትቆየው ለተለያዩ ቀናት በመሆኑ የእርግዝናዋ ጊዜ ይሄ ነው ብሎ ለመወሰን በፍፁም አይቻልም፡፡ ግን ደግሞ የእንስሳት መዘክሩ ኃላፊ ወይዘሮ አልማዝ ለማ እንደነገሩን ጥንቸል በእርግዝና የምትቆይበት ትልቁ ጊዜ 31 ቀን ነው፡፡ ልጆች አሁንም ቢሆን ስለ ጥኝቸል ማወቅ ያለባችሁ ቋሚ የእርግዝና ወቅት ያላት አለመሆኑን ነው። ያም ሆነ ይህ ጥንቸል ይሄን ያህል ቆይታ በአንድ ጊዜ እስከ 11 ግልገሎች ልትገላገል እንደምትችልም ወይዘሮ አልማዝ አውግተውናል፡፡
ልጆች ጦጣ ብልጥ ፤ ከብልጥም ደግሞ በጣም ብልጥ እንስሳ እንደሆነች ታውቃላችሁ አይደል? እማማና አባባ ወይም የሴትና የወንድ አያቶቻችሁ አለዚያም ፤ ትላልቅ ወንድምና እህቶቻችሁ እንዳንዴም መምህራኖቻችሁ የጦጣን ብልጠት በተረት ነግረዋችኋልና ሁላችሁም ብልጠቷን ታውቃላችሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ ትክክል ነኝ አይደለም? ልጆች የጥንቸል ብልጠቷ በጣም የረቀቀና ከጦጣም በእጅጉ የበለጠ ነው ፡፡ በአቅራቢያዋ ምግብ በማታገኝበት ወቅት ዝም ብላ አትራብም፡፡ በሚገርም ሁኔታ በጠጧን እንደገና በመመገብ የምግብ እጥረትን ታካክሳለች፡፡
ልጆች የጥንቸል ፀጉር ጠንካራ በመሆኑ እንደጠቀማት ሁሉ ይጎዳታልም፡፡ ፀጉሯ ጠንካራ በመሆኑ በገበያ ላይ ስለሚፈለግና ውድ ዋጋ ስለሚሸጥ በዓለማችን በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ጥንቸሎች ለፀጉራቸው ሲባል በሚያሳዝን ሁኔታ በሰዎች እየታደኑ ይገደላሉ። ጥንቸል በኢትዮጵያ ከ2 ሺ140 እስከ 4ሺ 380 ሜትር ባሉ ከፍተኛ ተራራማ ስፍራዎች፤ ለአብነትም በሸዋ፣ ባሌ እና አርሲ አካባቢ ትገኛለች፡፡ የቦረና ሳይንት ወረሂመኖ እና የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርኮች በስፋት ከምትገኝባቸው ጥብቅ ቦታዎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡ ፡ ልጆች ስለ ጥንቸል ወይዘሮ አልማዝ አካፍለውኝ ያካፈልኳችሁን አንብባችሁ ዘና እንዳላችሁ ተስፋ አድርጋለሁ፡፡ የምትችሉ ልጆች ደግሞ ስለ ጥኝቸል የበለጠ ለማወቅ በእረፍት ጊዚያችሁ ወደ መዘክሩ ጎራ ማለትና ጥንቸሏንም በአካል ማየት ትችላላችሁ፡፡ በኔ በኩል በሌላ የእንስሳት ታሪክ እስከምንገኛኝ ደህና ሁኑ!
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም