አገሪቱ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግ መስራት ከጀመረች ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለፈው መንግሥት ግብርናው በአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ውስጥ ያለው ሚና እየቀነሰ እንዲመጣ ኢንዱስትሪው የግብርናውን ሃላፊነት እንዲወስድ ለማድረግ ተሞክሯል። ለእዚህም በግብርና ትራንስፎርሜሽን ላይ የሚሰራ ተቋም በማቋቋም ጭምር ነው የተሰራው። ይሁንና ነገሮች በታሰበው ልክ ብዙ ርቀት አልተጓዙም፤ ግብርና መሸጋገር / ትራንስፎርም ማድረግ/ ሳይችል ቀርቷል።
ከአገራዊ ለውጡ ወዲህ ግን ግብርናውን ትራንስፎርም ለማድረግ በስፋት መስራት ተጀምሯል። በዚህም ለሜካናይዜሽን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር የታመነበት የኩታ ገጠም እርሻ እየተስፋፋ ነው፤ ባለፈው ዓመት የኩታ ገጠም እርሻን ከስድስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማድረስ ተችሏል፤ በዘንድሮው የመኸር ወቅት ደግሞ ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በኩታ ገጠም ለመሸፈን ታቅዷል። የኩታ ገጠም እርሻ መስፋፋት ለሜካናይዜሽን ስራ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ትራክተር፣ ኮምባይነር እና የመሳሰሉት የሜካናይዜሽን ማሽነሪዎች በግዥና በኪራይ ወደ አርሶ አደሩ መንደር እየገቡ ናቸው። በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ብዙ ርቀት መጓዝ እየተቻለ ነው።
ግብርናውን ለማዘመን ሲፈለግ የፋይናንስ አቅርቦት ሌላው ጉዳይ ይሆናል። ለግብርናው ዘርፍ በመንግሥት በኩል በበጀትም በድጎማም የፋይናንስ አቅርቦት እየተደረገ ነው። መንግሥት ለአፈር ማዳበሪያ ባለፈው ዓመት 15 ቢሊዮን ዘንድሮ 21 ቢሊዮን ብር ለአፈር ማዳበሪያ በድጎማ መስጠቱን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። በፋይናንስ አቅርቦት በኩል እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባንኮች እንዳልሰሩ ይታወቃል። የአገሪቱ ባንኮች ከሚያዙበት ሀብት አብዛኛው እጅ ባለቤት አርሶ አደሩ ሆኖ ሳለ ሀብቱን የሚጠቀሙበት ግን በከተማ ህንጻ የሚገነቡ ባለሀብቶች ናቸው እየተባሉ ባንኮቹ ተተችተውም ነበር።
በ2014 በጀት ሀምሌ ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ለግብርናው ዘርፍ በሚደረግ የፋይናንስ አቅርቦት ላይ እንዳብራሩት፤ እስከ አቅርብ ጊዜ ድረስ ለአርሶ አደሩ ብድር የሚያቀርብ የፋይናንስ ተቋም አልነበረም። ውስን ሀብት ያላቸው የብድርና ቁጠባ ተቋማት ግን ይህን ያደርጉ ነበር። በ2014 በጀት ዓመት እነዚህ ተቋማት ለሶስት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ብድር አቅርበዋል። በአንጻሩ በትሪሊዮን ብሮችን የሚያንቀሳቅሱት የሀገሪቱ ባንኮች ለ350 ሺ አርሶ አደሮች እንኳን አይደርስም ያቀረቡት ብድር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ነገሮች እየተለወጡ መጥተዋል። በዚህ በባንኮች ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ አቅርቦት አለማድረግ ላይ ይሰማ የነበረው የሁሉም አካላት ድምጽ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን የ2015 በጀት ዓመት የስድስት ወር ሪፖርት ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የፋይናንስ ዘርፉ ለግብርናው ዘርፍ 92 ቢሊዮን ብር አበድሯል፤ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ 29 በመቶ ጭማሪ አለው ሲሉ የገለጹትም የፋይናንስ ዘርፉ ለግብርናው ዘርፍ ብድር እያቀረበ ስለመሆኑ አንድ ማረጋገጫ ነው። አርሶ አደርና ባንክ መገናኘት የጀመሩበት ሁኔታ ስለመኖሩ የኦሮሚያ ህብረት ስራ ባንክ ተሞክሮዎችም ያመለክታሉ። ባንኩ ሙያዊ እገዛን ማዕከል ባደረገ መልኩ ለአርሶ አደሩ የፋይናንስ አማራጮችን በማቅረብ ግብርናውን በማገዝ ላይ እንደሆነም በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ የደንበኞች ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለታ አለሙ ይገልጻሉ።
አቶ ለታ እንደገለጹት፤ ባንኩ የተመሰረተው በአርሶ አደሮች በመሆኑ ጥቅምና አገልግሎቱም እየሰፋ ሄዷል። ባንኩ ከመደበኛ የባንክ አገልግሎት ውጭ አርሶ አደሩ በግብርና ሥራው ላይ የሚያጋጥመውን የእውቀት ክፍተት በመሙላት ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችለውን የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ወይንም በቀጥታ አርሶ አደሩን የሚደግፍ ክፍል በማደራጀት በግብርናው ዘርፍ የተለያዩ ተልእኮዎች በመወጣት ተደራሽ እየሆነ ይገኛል። የባንኩ አንዱ አገልግሎት በማህበር ለተደራጁ አርሶአደሮች ብድርና ሥልጠና መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አግሪካልቸራል ባንኪንግ በሚለው ውስጥ የሚሰጥ አገልግሎት ነው። በዚህ አገልግሎት ዶሮ ለሚያረቡ፣ ከብት ለሚያደልቡና ተያያዥ በሆኑ የግብርና ዘርፍ ውስጥ ለሚሰማሩ የብድር አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው። በተጨማሪም አርሶ አደሮቹ ባንኩ ባመቻቸው በባለሙያዎች የታገዘ ሙያዊ ድጋፍ ያገኛሉ።
ባንኩ ይህን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣትም በግብርናው ዘርፍ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተመረቁ ባለሙያዎችን ቀጥሮ እያሰራ ነው። ባለሙያዎቹ አርሶ አደሮቹ በተሰማሩበት ዘርፍ ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ለአብነትም በእንስሳት እርባታ ላይ የተሰማሩ አርሶ አደሮች የእንስሳቶቻቸውን ጤና ከመጠበቅ ጀምሮ ማድረግ ያለባቸውን ጥንቃቄ ምክር በመሥጠት ጭምር ነው በአቅም ግንባታ የሚያግዟቸው። ሶስተኛው ተልእኮ ወይንም በባንኩ የተቋቋመው ክፍል የምክር አገልግሎት የአቅም ግንባታ የሚሰጥ ነው። ለዚሁ ሥራ ባንኩ የቀጠራቸው የግብርና ባለሙያዎች በባንኩ ቅርጫፎች ተመድበው የሙያ እገዛ እንዲሰጡ ነው የተደረገው።
ባንኩ በዚህ አደረጃጀት አርሶአደሩን በማገዝ በግብርናው ውስጥ ከፍ ያለ ሚና እየተወጣ እንደሆነ መሆኑን አቶ ለታ ጠቁመዋል። በአብዛኛው ባንኩ እየተጠቀመበት ያለው ዘዴ፤ አርሶአደሩ የመሥሪያ ቦታ አመቻችቶ ወደ ባንኩ ሲቀርብ ይዞ የቀረበው የሥራ ዘርፍ እንደሚታይ ጠቅሰው፣ ለአብነት የወተት ላም ማርባት ከሆነ ፍላጎቱ ግለሰቡ ግዥውን ከሚፈጽምበት አካል ውል ይዞ እንዲቀርብ እንደሚደረግ፣ በውሉ መሰረትም ባንኩ ለሻጩ ክፍያ እንደሚፈጽም ገልጸዋል። ለእርሻ ሥራ የሚያስፈልጉ እንደ ትራክተር ያሉ መሣሪያዎች ለመግዛት የሚፈልጉ አርሶአደሮች ዋጋ የሚገልጽ ሰነድ ከተለያዩ የግዥ ቦታዎች (ፕሮፎርማ) ሰብስበው እንዲያቀርቡ በማድረግ በተመሳሳይ የግዥ ሂደቱን ያከናውናል ይላሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የባንኩ ተግባር እዚህ ላይ አያበቃም። ክትትል በማድረግ ብድሩን ያስመልሳል። ባንኩ በዚህ መልኩ እስካሁን እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውጤታማ እየሆነ ነው።
ባንኩ አርሶ አደሩን ለማገዝ በሚል በከፈተው የግብርና ዘርፍ ክፍል ብቻ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ብድር ተሰጥቷል። ባንኩ በአጠቃላይ ለአርሶ አደሩ የሰጠው ብድር ግን ወደ ስምንት ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር ይደርሳል። አርሶ አደሩ የመበደር፣ ብድሩንም በወቅቱ የመመለስ ባህል እያሳደገ መሆኑን ባንኩ ከሰራቸው ሥራዎች መገንዘብ ችሏል። ባንኩ ‹‹ኢኮ ፍሬንድ›› የሚባል የአገልግሎት አሰጣጥም በባንኩ ቅርጫፎች መስጠት መጀመሩንም አቶ ለታ ነግረውናል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ይህ አገልግሎት በአነስተኛ ከተሞች ውስጥ ነው የሚሰጠው። ለጊዜው በ50 ቅርጫፎች ነው የተጀመረው። በኤሌክትሪክ ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር እንዳያጋጥም በፀሐይ ኃይል እንዲሰራ ይደረጋል። አገልግሎቱ ከባንክ አገልግሎት የተለየ አሰራር አይደለም። አርሶአደሩን በተለያየ አማራጭ ተደራሽ ለማድረግ የተዘረጋ አሰራር ነው።
ሌላው ባንኩ ‹‹ፍርቱ›› ብሎ በሰየመው አገልግሎት ደግሞ የአጭር ጊዜ የብድር ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ሲሆን፣ አገልግሎቱም በእጅ ተንቀሳቃሽ ስልክ በመጠቀም የሚፈጸም ነው። ባንኩ ይህን አገልግሎት የጀመረው አርሶአደሩ ለግብርና ሥራው ግብዓት የሚሆኑ እንደ ማዳበሪያ፣ ምርጥዘርና ሌሎችንም ግብዓቶች ለማሟላት ግለሰብ ዘንድ ብድር ጥየቃ የሚሄድባቸው አጋጣሚዎችንና መሬቱንም እስከማከራየት የሚደርስበትን ሁኔታ ለማስቀረት የተመቻቸ የብድር አገልግሎት ነው። ባንኩ ይህን አገልግሎት ሲሰጥም ከግብዓት አቅራቢዎች ጋር የጠበቀ ግንኙነት በማድረግ ነው። ይህ አይነቱ አገልግሎት ለባንኩ በአነስተኛ ብድር ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይቀርብለት እንደነበር አስታውሰው፣ ጥያቄውንም በዚህ ዘዴ መፍታቱን ነው አቶ ለታ የነገሩን።
አርሶ አደሩ በዘር ወቅት የሚያስፈልገውን የተለያየ ግብዓት ለማሟላት በቀላሉ በተንቀሳቃሽ ስልኩ ሲጠቀም እግረ መንገዱንም እንደ አገር የተያዘውን የዲጂታል ግብርና ለመተግበር የሚያስችለው እንደሆነም ባንኩ እየተገበረ ካለው ቴክኖሎጂ መገንዘብ ይቻላል። ባንኩ ግን ለጊዜው እያደረገ ስላለው ጥረት አቶ ለታ እንደገለጹልን የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት መሪዎችን በማሰልጠንና የሚጠቀሙበትን የስልክ ቀፎ በማቅረብ የአርሶ አደሮቹን የብድር ጥያቄ እንዲያቀርቡላቸውና የሚያስፈልጓቸውንም ሰነዶች ተቀብለው እንዲያስተናግዷቸው በማድረግ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያለውን ክፍተትም ለመቅረፍ ጥረት አድርጓል። በአሰራር ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር በባንኩ ውስጥ በተቋቋመው የግብርና ዘርፍ ውስጥ ባሉ ባለሙያዎችም ይታገዛል።
ባንኩ የግብርና ዘርፍ ክፍል ለማቋቋምና ባለሙያዎችንም ለመቅጠር መነሻ የሆነውንም ምክንያት አቶ ለታ ሲያብራሩ፣ ከ57 በመቶ በላይ የሚሆኑት የባንኩ ባለድርሻ አካላት አርሶ አደሮችና የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት ናቸው። ባንኩ ሲመሰረትም አርሶአደሩን ማዕከል ያደረገ ነው። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የተለያዩ ዘዴዎችን በመቀየስ አርሶ አደሩ ያጋጥመው የነበረውን የፋይናንስ ችግር እየፈታ ይገኛል።
ባንኩ በዚህ መንገድ ትኩረት ሰጥቶ አርሶአደሩን እየደገፈ ከሆነ ድጋፉ በአርሶ አደሩ የኑሮ ለውጥ ላይ እያስገኘ ያለውን ውጤት ባንኩ በጥናት የለየበት አሰራር ይኖር እንደሆንም አቶ ለታን ጠይቀናቸው በምላሻቸው፤ ባንኩ አርሶ አደሩ ዘንድ መቶ በመቶ ተደራሽ ሆኗል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። የአርሶ አደሩ የፋይናንስ፣ የክህሎትና ተያያዥ የድጋፍ ጥያቄዎች ሰፊ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ብዙ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። ባንኩም ከፍላጎት ጋር የተጣጣመ ሥራ ለመሥራት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ከመደበኛ የባንክ አሰራር በተጨማሪ በባንኩ በኩል እየተከፈቱ ያሉ የሥራ ክፍሎች የባንኩ ጥረት ማሳያ ተደርገው ይወሰዳሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ባንኩ የአርሶአደሩን ፋይናንስ ችግር ለመፍታት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በዘርፉ ወደፊት መከናወን ባለባቸው ተግባራት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ የባንኩ እንቅስቃሴ ትክክለኛ ሲሉ ገልጸውታል። እርሳቸው እንዳሉት፤ ሲውዘርላንድ፣ አውሮፓ ውስጥ ገበሬው ፋይናንስ እንዲያገኝ አርሶ አደሮች የራሳቸውን ባንክ እንዲያቋቁሙ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋል። በኢትዮጵያም ጅምሩ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ተጨማሪ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ቢቋቋሙ የእድገት ለውጦች ይመዘገባሉ። የባንኩ ባለድርሻዎች አርሶ አደሮች ከሆኑ፣ የሚመርጧቸው ተወካዮቻቸው ገበሬውን ማዕከል ያደረገ የኢንቨስትመንት አቅጣጫዎች ይዘው የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ይፈጠራል ይላሉ።
ኢትዮጵያ አብዛኛውን የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው ዘርፎች በገበሬው ምርቶች መሆናቸውን ገልጸዋል። ከዘርፉ የሚገኘው ውጤት ከፍተኛ ሆኖ ገበሬው ተጠቃሚ ነው ወይ? ሲባል ግን ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ። ለእንዲህ ያሉ ጥያቄዎች እንደ ኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ ያለ ባንክ መፍትሄ መስጠቱ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ይጠቁማሉ። እንዲህ አይነት ጅምሮች ባለመጠናከራቸው እንጂ ከዚህ ቀደምም ተሞክሮ እንደነበር የጠቆሙት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ገበሬውን መሠረት ያደረገ አሁን ልማት ባንክ ተብሎ የሚጠራው አግሮኢንዱስትሪያል ባንክ ተብሎ የተቋቋመ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ባንኩ እንደ ትራክተር ያሉ ለእርሻ ሥራ የሚውሉ መሣሪዎችን በብድር እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ በአፋር ክልል ደግሞ የጥጥ እርሻዎች ሰፊ ልማት መከናወኑን ለአብነት ገልጸዋል። ጅምሩ ተጠናክሮ ባለመቀጠሉ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ አመልክተዋል። እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገለጻ፤ አሁንም ቢሆን በኦሮሚያ ህብረት ሥራ ባንክ የተጀመረው ለአርሶ አደሩ ፋይናንስ ማቅረብ ስራ ተጠናክሮ መስፋፋት ይኖርበታል። ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥትም በመስፋፋት ላይ የሚገኙት የግል ባንኮች ለግብርናው ዘርፍ ሳይሆን፣ ለግንባታ ሥራ ነው ትኩረት እየሰጡ ያሉት።
ባንኮቹ ትኩረታቸውን በግብርናው ላይ በማድረግ ባለድርሻ አካላቸውን ገበሬውን ቢያደርጉ ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ነው ያስረዱት። ግብርና በአጭር ጊዜ ኢንቨስትመንትን የሚመልስ ሥራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ባንኮቹንም፣ገበሬውንም ሆነ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። ግብርናውንም ለማዘመን ትልቅ እድል ይፈጠራል ሲሉ ያብራራሉ። ‹‹በኢትዮጵያ ከተሞች እያደጉ፣ ተቋማት እየሰፉ፣ የህዝብ ቁጥርም እየጨመረ ነው። ለዚህ ሁሉ ምግብ ለማዳረስ አሁን በሥራ ላይ ባለው የግብርና ዘዴና አስተዳደር መቀጠል አይቻልም። ›› የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፣ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋትም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ግብርናው መዘመን አለበት ይላሉ።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኩታገጠም እና በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ግብርናውን ወደፊት ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ በዚህ ላይ የበለጠ የተጠናከረ ሥራ እንደሚጠበቅም ነው ያስገነዘቡት። ለግብርናው ዘርፍ የፋይናንስ ድጋፍ ይጠናከር ሲባል ግን አርሶአደሩ ገበሬ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ እንዳልሆነም ጠቅሰው፣ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ እንዲሸጋገር ማድረግም ይገባል ብለዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም