ባለፉት አስር ዓመታት ገደማ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች በርካታ ግዙፍ ስቴድየሞች ግንባታ ቢጀመርም ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑ የሉም። በከፊል ተጠናቀው አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ያደረጉ ጥቂት ስቴድየሞችም ቢሆኑ አንዳቸውም ለዓለም አቀፍ ውድድሮች ብቁ መሆን አልቻሉም። ይህም የሆነው ለግንባታ የሚበጀተው ገንዘብ አንዳንዱ በሙስና ተመዝብሮና ግንባታውም ደረጃውን ጠብቆ መሰራት ስላልቻለ መሆኑ በተደጋጋሚ ተነግሯል። በጅምር የቀሩና የተሻለ ይዞታ ላይ የሚገኙ ስቴድየሞች የካፍና ፊፋ ውድድሮችን ዝቅተኛ መስፈርት ማለፍ ባለመቻላቸው የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን በገለልተኛ ሜዳ እየተሰደደ ጨዋታዎችን ለማድረግ ተገዷል። በዚህም ኢትዮጵያ በርከት ያለ የውጪ ምንዛሪ ማውጣት ግድ ብሏታል።
እየተገነቡ ከሚገኙ ስቴድየሞች መካከል አንዱ የሆነው የአቃቂ ቃሊቲ ዞናል ስቴድየም ለረጅም ዓመታት መጠናቀቅ ካልቻሉት አንዱ ነው። የዚህ ስቴድየም ግንባታ መጠናቀቅ እንደሌሎቹ ሁሉ የዘወትር ጥያቄ ሲሆን በሌሎች ስቴድየሞች የታዩት ችግሮች እንዳይደገሙ የዚህን ስቴድየም ግንባታን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታዎች ቢሮ ለአዲስ ዘመን ገልጿል። ቢሮው በርካታ ችግሮች ቢኖሩበትም በኢትዮጵያ ያለውን የስቴድየሞች ግንባታና የጥራት ደረጃ መጓደልን ለማስቀረት የአቃቂ ቃሊቲን ዞናል ስቴድየም በተገቢው መስፈርት መሰረት በመስራት እስከ መጪው ግንቦት መጨረሻ ድረስ ለማጠናቀቅ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁማል። ለዚህም በከተማ አስተዳደሩ አስተባባሪነት ስራውን ለማጠናቀቅ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ቢሮው አስታውቋል። የስቴድየሙ ግንባታ ደረጃውን ጠብቆ በፍጥነት መጠናቀቅና ቀደም ሲል የነበሩትን የግንባታ አማካሪዎችና ባለሙያዎች እንደቀየረም ቢሮው ጠቁማል። ከዚህ በተጨማሪ ስቴድየሙ ቀደም ሲል የካፍና ፊፋን ደረጃ ስለማያሟላ የዲዛይን ማሻሻያዎች የተደረገለት ሲሆን፣ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ማስተናገድ በሚችልበት ደረጃ እየተገነባ እንደሚገኝ ታውቋል።
ስቴድየሙ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በውስጡ አራት የመልበሻ ክፍሎች፣ ትናንሽ ስብሰባ አደራሾች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መብራቶች፣ የተመልካች መቀመጫ ወንበሮች እንደሚገጠምለት የተጠቆመ ሲሆን፣ የመጫወቻ ሜዳው በተፈጥሮ ሳር የሚሸፈን ይሆናል። ለአትሌቲክስ የሚያገለግል የመሮጫ መም (ትራክ) ይዘረጋለታል። የሚዘረጋው መም የ100ሜትር መንደርደርያና አትሌቶች ውድድራቸውን ሲያጠናቅቁ ተንደርድረው የሚቆምበትን ያካትታል። ስቴድየሙ በዙሪያው የመለማመጃ ሜዳ፣ 25ሺ ካሬ የመኪና ማቆሚያና ሌሎች አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ነገሮች ያካተተ እንደሚሆንም ተገልጿል።
የስቴድየሙ ግንባታ በ2008 መጨረሻ እንደተጀመረና በ540 ቀናት (በ18 ወራት) ለማጠናቀቅ ታስቦ ወደ ስራ መገባቱን የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታዎች ቢሮ የአቃቂ ቃሊቲ ስቴድየም ኮንትራት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ተፈራ ይገልጻሉ። በወቅቱ ስራው እንዳይጀመር በርካታ እንቅፋቶች እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ቢኒያም፣ የይዞታ ማስከበርና በዚያም ምክንያት ስቴድየሙ ሊገነባበት ከታቀደው ቦሌ ክፍለ ከተማ ወደ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ እንዲዞር ምክንያት እንደነበረ አስረድተዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ግንባታው ለአንድ ዓመት ቆሞ እንደነበር አስታውሰው፣ ወደ ስራ ከተገባ በኋላ የግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ ሌላ እንቅፋት መሆኑን ገልፀዋል። በዚህም ኮንትራክተሩ የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግለት በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርቦ በወቅቱ ምላሽ ባለማግኘቱ ግንባታው ሊዘገይ ችሏል። ይሁን እንጂ የዋጋ ማሻሻያ ጥናቱ አልቆ የከተማ አስተዳደሩም ምላሽ ተሰጥቶት ስራው በ2013 ድጋሚ ሊጀመር እንደተቻለ ተናግረዋል።
እንደ አቶ ቢኒያም ገለፃ፣ ለግንባታው የተመደበው በጀት 514 ሚሊዮን 392ሺ 809 ብር ቢሆንም የ211 ሚሊዮን ስራ ተሰርቶ ድጋሚ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ አስፈልጓል። በዚህም ለቀሪው ግንባታ 476 ሚሊዮን ብር ተጨምሮ በፊት ከተሰራው ማሻሻያ ጋር 791 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞ ስራው እንዲቀጥል ተደርጓል። ያም ሆኖ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የሚፈጀው ገንዘብ ይሄ ብቻ እንዳልሆነ የገለፁት አቶ ቢኒያም፣ አሁን ባለው የግንባታ መሳሪያ የዋጋ ጥናት እየተደረገ በመሆኑ የቀሩ ስራዎች ሲጠናቀቁ በአጠቃላይ በግምት ወደ 1ቢሊዮንና ከዚያ በላይ ወጪ ሊጠይቅ እንደሚችል አብራርተዋል።
ስቴድየሙ 25ሺ ተመልካች የመያዝ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየተገነባ ሲሆን፣ ግንባታው ሲጀመር በነበረው ዲዛይን መሰረት ተመልካች የመያዝ አቅሙ ከዚህ በታች ነበር። የስቴድየሙ ግንባታ ላይ የዲዛይን ማሻሻያ በመደረጉና ተጨማሪ ስራዎች በመካተታቸው የግንባታው አፈፃፀም ወደኋላ እንደጎተተ የገለፁት አቶ ቢኒያም፣ አሁን ላይ ግንባታው 76 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል። የስቴድየሙ የጣሪያ ስራ በአሁኑ ወቅት እየተሰራ ሲሆን የጣሪያን ስራ ቀደም ሲል በፋይበር ግላስ ለመስራት ነበር የታቀደው። ይሁን እንጂ ፋይበር ግላስ ለኢንተርናሽናል ስቴድየም ተመራጭ ባለመሆኑ ወደ ፖሊካጎኒክ እንደተቀየረ ታውቋል። የስቴድየሙ ግንባታ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ከተጠናቀቀ በኋላ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በባለቤትነት እንደሚያስተዳድረውም ታውቋል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ጥር 4 ቀን 2015 ዓ.ም