ሰላም ቀዳሚ መገኛዋ ቀና ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ሰላማዊ ተግባቦት ነው። ከሰላማዊ ተግባቦት ውጪ የተሟላ ሰላምን ሊያመጣ የሚችል ነገር ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆንም አይቻልም። ምክንያቱም ሰላማዊ ተግባቦት ሰላምን ማዕከል በማድረግ አገርና ህዝብን አስቀድሞ ፖለቲካዊ መሻትን ያስከተለ ነው። ሰላማዊ ተግባቦት ሁሉም ሰው የተለየ እና ልዩ ልዩ ሀሳብና ፍላጎት እንዳለው በመረዳት ያን ብዙ አይነት ሃሳብ ወደ ጠቃሚ አንድ ሀሳብ መቀየር ነው። ሰላማዊ ተግባቦት የራስን ፍላጎት ወደጎን ብሎ የብዙሀኑን ፍላጎት ማስቀደም ነው። ይሄ ሁሉ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ሰላም ሊመጣ አይችልም። ሆኖም በዘመናት ሂደት ውስጥ ለሚያጋጥሙን ሰላምን የሚያደፈርሱ ሁነቶች የሰላም መገኛዎችን ዘግቶ የመጓዛችን ውጤቶች ናቸው።
ምክንያቱም የሰላም መንገድን ዘግቶ፣ ቀና እሳቤዎችን አርቆ፣ ከሰላማዊ ተግባቦት ተነጥሎ ሰላም ለማምጣት መሞከር አይቻልም። ይሁን እንጂ ሰላም ሊሰጡንና ሊያግባቡን የሚችሉ ብዙ የጋራ ትውፊቶቻችንን ችላ ብለን በሚለያዩን ጥቂት ነገሮች ላይ ጊዜ ስናጠፋ ከርመናል። ይሄ አካሄድ ደግሞ የምንፈልጋትን አገር አልፈጠረልንም። በመሆኑም የምንፈልጋትን አገር እውን ለማድረግ በምናደርገው ጉዞ ይሄን የኖረ አቅጣጫችንን መቀየር፤ ባልሄድንባቸው መንገዶች መሄድ፣ ባልተመለከትነው አቅጣጫ መመልከት ይኖርብናል።
ብዙዎች የሰላምን መገኛ መንገድ ሳያውቁ ሰላም ለማምጣት ብዙ ለፍተዋል። ሆኖም ሰላም አንድ ቦታ ነው ያለው፤ እርሱን በመነጋገር ውስጥ ነው። መነጋገር ስንል መግባባት ያለበትን መነጋገር ነው። ዓለም ሁሌም በመነጋገር ውስጥ ናት፤ ሁሉም መነጋገሮች ግን ሰላም ሲያመጡላት አይታይም። ይሄ የሆነው ደግሞ በራስ ወዳድነትና የአንድ ወገንን የበላይነት በማሳየት ነው። የአንድ ወገን የበላይነት በሚንጸባረቅበት ሁኔታ ላይ ሰላም የለም። ሰላም የእኩል ሀሳብ፣ የእኩል ተግባር ነጸብራቅ ነው። አገራችን ለምን ሰላም ራቃት ብለን ስንጠይቅ ይሄን እውነት ነው የምናገኘው። እኛ አገር ሁሉም ነገር በእኩልነት ላይ ሲንፃባረቅ አይታይም። ፖለቲካችንን ብናየው የእኔነት እና የራስ ወዳድነት እድፍ ያቆሸሸው ነው። ይሄ ግለኝነት ደግሞ መጨረሻው ጦርነት ነው። እንደ አገር ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ይሄንን መንገድ መቀየር ይኖርብናል።
አንድ አይነት ታሪክ አገር አይገነባም፤ ትውልድ አያሻግርም። ከኖርበት የጦርነት ልማድ ወጥተን መነጋገርን መሰረት ያደረገ አዲስ አብዮት ያስፈልገናል። ከነበርንበት የቂመኝነት አካሂድ ወጥተን እርቅን ያስቀደመ አዲስ የይቅርታ አስተሳሰብ መላበስ ያስፈልገናል። አገራችን አሁን የሰላም አብዮት ነው የሚያስፈልጋት። የአንድነት፣ የመቻቻል አብዮት ነው የሚያስፈልጋት። ይሄን አዲስና ለዘመኑ የሚመጥን አካሄድ ነው መለማመድ ያለብን። ለመነጋገር ከተሰናዳን ከጦርነት የሚሻሉ ብዙ ነገሮች አሉን። ቀድማ የነበረችው አገራችን ዛሬ ላይ በብዙ ነገር ላይ ወደኋላ ቀርታለች። በዚህ ላይ ጦርነትና አለመግባባት ሲጨመርበት ደግሞ ችግሩን ያገዝፈዋል።
በየትኛውም መስፈርት እንየው ለአገራችን ጦርነት ሳይሆን ሰላም ነው የሚያስፈልጋት። ለህዝባችን መለያየት ሳይሆን አንድነት ነው የሚያስፈልገው። የተጀመረው ሰላም እንዲቀጥል፣ ቀጥሎም አስተማማኝ እንዲሆን ከትላንቱ የተለየ አዲስ ማንነት ያስፈልገናል። በዚህ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ፖለቲካ፣ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ካልሆነ አዲስና ሰላማዊ አገር መፍጠር አይቻለንም። እውነተኛ ሰላም ተነጋግሮ በመግባባት ውስጥ ነው የሚገኘው። ሰው ተነጋግሮ መግባባት ካልቻለ አገር ሊለውጥ የሚችል እውቀትም ሞራልም እንደሌለው ነው የማምነው። ጥበብ ማለት..እውቀት ማለት በብዙሀነት ውስጥ አንድ አገርና አንድ ህዝብ መፍጠር ነው። ምርጥ ፖለቲከኛ ምርጥ ተናጋሪ ሳይሆን ምርጥ አሳቢ ነው። ምርጥ ሀሳቦቻችን ናቸው ምርጥ አገር የሚፈጥሩልን። ምርጥ ሃሳቦቻችን ናቸው በብዙ ተቃርኖ፣ በብዙ የፖለቲካ ልዩነት ውስጥ ለአገር የሚበጅ እውነት የሚሰጡን። ምርጥ ሀሳቦቻችን ናቸው ከኋላቀርነትና ከአዝጋሚ ጉዞ የሚያወጡን። ተነጋግሮ መግባባት ያልቻልነው ለአገር የሚበጅ፣ አገርን ያስቀደመ፣ ከእኔነት የወጣ ምርጥ ሀሳብ ስለሌለን ነው።
ምርጥ ሀሳብ ሁልጊዜም ማረፊያው አገርና ህዝብ ነው። በቀሪ ጊዜያችን በምርጥ ሀሳብ ምርጥ አገር መፍጠር አለብን። በምርጥ ሀሳብ ምርጥ አገር ካልፈጠርን በብላሽ ሀሳብ ብላሽ አገር ፈጥረን ተበላሽተን ነው የምንቀረው። ይሄ ደግሞ ለማናችንም አይበጅም፤ በእርቅና በቀና ተግባቦት ወደ ሰላም መሄዱ ነው ለሁላችንም እኩል ዋጋ ያለው።
አገራችን ሀሳብ አላጣችም፤ እንደ ህዝብ ቁጥሯ፣ እንደ ወጣቷ ብዛቷ ለአገር የሚሆን ብዙ ሀሳብ አለን። ችግር የሆነብን የሀሳብ ልዩነቶቻችንን ወደአንድነት ማምጣቱ ላይ ነው። ችግር የሆነብን ልዩ ልዩ ሀሳቦቻችንን እንዴት በሰላማዊ መንገድ ለሰላማዊ ነገር መጠቀም እንዳለብን አለማወቃችን ነው። በአግባቡ መጠቀም ከቻልን የተለያዩ ሀሳቦች በአንድ አገር ላይ ልማትም፣ ብልጽግናም ናቸው። በአግባቡ መጠቀም ካልቻልን ደግሞ ነውጥና ጦርነትን ነው የሚያስከትሉብን። አሁን የሚጠቅመን የሀሳብ ብዙሀነታችንን በሰላማዊ መንገድ ለልማት መጠቀም ነው። ያለፉ የጦርነት ታሪኮቻችን የሀሳብ ብዙሀነትን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ካለማወቅ የመጣ ነው። አንድ ሰው አንድ ሀሳብ ሲኖረው፣ አንድ ፖለቲከኛ ከሌላው ፖለቲከኛ አዲስ ሀሳብ ሲኖረው በራሳቸው መንገድ ሁሉም ለኢትዮጵያ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ማወቅ አለብን። የትኛውም የሀሳብ ልዩነት ወደጦርነት ከማምራቱ በፊት ጠቃሚ ነው።
የሀሳብ ልዩነቶቻችን ኢትዮጵያን እንዲጠቅሙ እንጂ እንዲጎዱ መፍቀድ የለብንም። የፖለቲካ ልዩነታችን አገር እንዲቀይሩ ህዝብ እንዲያሻግሩ እንጂ ለጦርነትና ለጉስቁልና እንዲዳርጉን መፍቀድ የለብንም። እኛ አገር ፖለቲካውም ሆነ ፖለቲከኞቻችን ኢቲክሱ ከሚፈቅደው ውጪ ነው እየፈነጩ ያሉት። ይሄ ብላሽ አካሄድ ነው የሀሳብ ልዩነትን በአግባቡ እንዳንጠቀም እክል እየፈጠረብን ያለው። አገርና ህዝብን ያስቀደመ ፖለቲካና ፖለቲከኛ በሀሳብ ልዩነት አገር ይሰራል እንጂ ጦርነት አይፈጥርም። ከእኛ በፊት ኢትዮጵያ መቅደም አለባት። ከእኛ በፊት ህዝብ መቅደም አለበት። ከስልጣናችን በፊት፣ ከግል ጉዳያችን በፊት ትውልድ ይቅደም። ከአገር በፊት የግል ጉዳያችንን ማስቀደማችን ነው ዛሬ ላይ ለጦርነት እያዳረገን ያለው። ኢትዮጵያን እስካላስቀደምን ድረስ የምንፈልገውን ሰላም ማምጣት አንችልም። ኢትዮጵያን እስካላስቀደምን ድረስ አሁንም ቢሆን ተነጋግሮ ሰላም ማምጣት ይቸግረናል።
አገር በአንድ አይነት ሀሳብ አትገነባም። ለአገር ግንባታ አሁን ላይ እዚም እዛም የሚሰማ ልዩ ልዩ ሀሳብ ያስፈልገናል። ልዩ ልዩ ሀሳቦቻችን ብልሀትን፣ ስኬትን፣ ተስፋን፣ እውቀትን፣ ልምድን ያነገቡ ናቸው። በሰላማዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ የሃሳብ ማዕድ ዘርግተን እንወያይባቸው። ከዚህ በዘለለ የአንተ ሀሳብ ከእኔ ሃሳብ አይገጥምም ብለን ወደመለያየት መግባት አይኖርብንም። ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ናት ማለታችንም ለዚህ ነው። የተለያዩ መልኮች፣ የተለያዩ ባህሎች፣ የተለያዩ ወግና ስርዐቶች ያቆነጇት፤ በብዝሃነት የቆነጀ ማንነቷም ለከፍታዋ አቅም የሚሆናት ነው።
ታዲያ ይሄን አቅም የሚሆን የብዝሃነት ውበት ገፍቶና ማስተናገድ ሳይቻል ቀርቶ ይቺ አገር እንዴት ሆና በአንድ አይነት ሀሳብ ብቻ ትቀጥላለች? ምክንያቱም ኢትዮጵያ ብዙ ናት፤ ብዙ ሀሳብ፣ ብዙ እይታ ያስፈልጋታል። የሀሳብ ልዩነቶቻችን ወደጦርነት እንዳይወስዱን ተነጋግሮ መግባባትን መልመድ አለብን። ተቻችሎ በጋራ መቆምን ባህል ማድረግ አለብን። የመጣው ሰላም በሁላችንም ልብ ላይ ተስፋን ለኩሷል። ሳቅ አድርጎልናል። እንደሳቅን እንድንቀጥል ሰላማችን እክል ሳይገጥመው መዝለቅ አለበት። ይሄ እንዲሆን ደግሞ ሰላም በሚያመጡ ነገሮች ላይ ብቻ እናተኩር።
ጦርነት በቃን፤ ይሄ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ድምጽ ነው። በወንድማማች መካከል ፍቅር እንጂ መለያየት ዋጋ የለውም። ሲገሉንና ስንገልባቸው የነበሩ ሾተሎቻችን ወደ ሰገባቸው ይመለሱ። ሲያደሙንና ሲያጎሳቁሉን የነበሩ ጎራዴዎቻችን ወደ አፎታቸው ይመለሱ። ፍቅር ነው የሚያስፈልገን፤ ወንድማማችነት ነው የቀረን። ብዙ ነገሮችን ሞክረናል..አሁን የሚቀረን ሰላምና እርቅ ነው። አሁን የሚቀረን ተነጋግሮ መግባባት፣ ተግባብቶ ሰላማዊ አገር መፍጠር ነው። ጦርነት የፈጠሩ ሀሳቦቻችንን ሰላም እንዲፈጥሩ እናድርጋቸው። መለያየትን የፈጠሩ ሀሳቦቻችንን አንድነትና ወንድማማችነትን እንዲያጸኑ እናሰገድዳቸው።
ኢትዮጵያ ቤታችንም፣ የማር ቀፏችን ናት፤ ማር እንድትይዝ አርቀን የሰቀልናት ቀፏችን። ግን ማር አበባ በሌለበት ምንድነው? ማር ንብ በሌለበት ምንድ ነው? አገራችን ማር እንድትይዝ ማር ሊሰጧት የሚችሉ ነገሮች ያስፈልጓታል። ከዚህ ውስጥ አንዱና ዋነኛው ሰላም ነው። አበባ በሌለበት ማር እንደሌለ ሁሉ ሰላም በሌለበትም አገር ምንም ናት። አገራችን ማር እንድትይዝ፣ ህዝባችን ከማሩ እንዲበላ ማር የሚሰራ ሰላም ያስፈልገናል። ይሄ ባልሆነበት ሁኔታ ላይ ድካማችን ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው። አንድን ነገር ስንፈልግ ያ ነገር የሚያስፈልገውን ግብዐት አሟልተን ነው መሆን ያለበት። አሁን ላይ አገራችን ከሰላም ውጪ ምንም አያስፈልጋትም። የአገራችን ሰላም ደግሞ ከሰማይ የሚወርድ ሳይሆን በእኛ በልጆቿ የሚፈጠር ነው። በመግባባት፣ በውይይት የሚመጣ ነው። ፖለቲካውን በማስተካከል፣ የሀሳብ ልዩነቶችን ወደተግባቦት በመቀየር የሚመጣ ነው።
ዓለም እንደ ሰላም የክብር አክሊል የላትም። ሁሌም ጸጋዎች፣ ሁሉም ክብሮች ከሰላም ቀጥለው የሚመጡ ናቸው። ብዙ ነገር እያለን ምንም እንደሌለው የሆንነው ከሁሉም ትልቁ ሰላም ስለጎደለን ነው። ይሄን ጉድለት በሰላም ካልሆነ በምንም አንሞላም። በሰላም መንገድ ከተጓዝን ብቻ ነው የኢትዮጵያን ችግሮች መፍታት የምንችለው። በምክክር መኖር ስንችል ብቻ ነው ለኢትዮጵያ የምንበጀው። እንደ አገር በሰላማዊ ሃሳብ የቆመች ሰላማዊ አገር ታስፈልገናለች። እናም ሁላችንም የሰላም ድልድይ እንሁን፤ ማንም ወጥቶ የሚገባበት ድልድይ። በሰላም ሀሳብ የተገነባ ድልድይ። ከዚህ ወደእዛ መሻገሪያ ድልድይ ያስፈልገናል። የጥል ግድግዳዎችን አፍርሰን፣ የመለያየት ግንቦችን ደርምሰን አዲስ ምስራቅ ማየት አለብን። አዲስ ፀሐይ፣ አዲስ ጀምበር መሞቅ አለብን። ለዚህም ወደ ጦርነት የሚወሰዱ መንገዶችን እየዘጋን የእርቅና የምክክር መንገዶችን መክፈት አለብን። የመለያየት መንገዶችን እየዘጋን የአንድነትና የወንድማማች መንገዶችን መስራት አለብን። የተስፋዋ ኢትዮጵያ በዚህ እውነት ውስጥ ብቻ ነው የምትፈጠረው።
አገር ሰው ከሌለባት ምንም ናት። ሰው አገር ከሌለው ምንም ነው። አገርና ሰው፣ ሰውና አገር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጾች ናቸው። ሰው በአገር..አገር በሰው ነው የሚከበሩት። አገር በሰላም ካልሆነ በምንም አትቆምም። ሰው በሰላም ካልሆነ በምንም አያምርም። ሰላም ስናጣ፣ አንድነት ሲርቀን የአገራችንን መሰረት እየነቀነቅን ነው። ተነጋግሮ መግባባት ሲያቅተን፣ ተቻችሎ መኖር ሲከዳን የአገራችንን መሰረት እየገፋን ነው። በእኛ ሰላም ማጣት ከእኛ ውጪ የሚጎዳ ማንም የለም። ሰላም ባጣንባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ ሁሉንም አይነት መከራ አይተናል። አሁን ስለሰላም የምንጮህበት ጊዜ ነው፤ አሁን የመጣው ሰላም እንዲቀጥል የምንታገልበት ጊዜ ነው።
ኢትዮጵያን እንስራ። ግዙፍም ብዙም ሆና ያነሰችውን፣ እልፍ ሆና የጎደለችውን አገራችንን እንታደግ። ሰው ሳታጣ ሰው ያጣችውን፣ ሀሳብ ሳታጣ ሀሳብ ያጣችውን አገራችንን እንማግር። ታሪክ ሞልቷት ታሪክ ያጣችውን አገራችንን እናድስ። በሰላሙ ዋዜማ ጥላቻ የሞላቸው አሮጌ አቆማዳዎቻችን በአዲስ መተካት አለባቸው። የፖለቲካ እድፍ ያቆሸሻቸው ትርክቶች በምክንያታዊ አሳቦች መሞላት አለባቸው።
ከእንግዲህ ጭንቅላቶቻችን የመፍትሄ ሀሳብ እንጂ የጦርነት ሀሳብ ማምጣቸው ይበቃል። ከእንግዲህ ልቦቻችን የይቅርታና የፍቅር ቦታ እንጂ የመለያየት ቦታ መሆናቸው ያበቃል። ከእንግዲህ ጀርባዎቻችን በጥላቻ መጉበጥ የለባቸውም። ከእንግዲህ ፖለቲከኞቻችን የእርቅ ሀሳብ እንጂ በመለያየት ሀሳብ ጊዜ ማጥፋት የለባቸውም። ከእንግዲህ በሚያግባቡንና በሚያስተቃቅፉን የጋራ ጉዳዮቻችን ላይ እንምከር። ከእንግዲህ ኢትዮጵያን ከፍ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ እንሳተፍ። በሰላማዊ ተግባቦት እጦት ዝቅ ያለችውን አገራችንን ከፍ ማድረግ ይጠበቅብናል። በአገራዊ ምክክር አዲስና ነባር ችግሮቻችንን እየቀረፍን ሰንኮፏን የጣለች ኢትዮጵያን እንውለድ። ለዛሬው አበቃሁ፤ ሰላም!
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥር 3 /2015