የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት የተለያዩ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታወቀ። አዲስ የወታደራዊና ፖሊስ ሃይል አዛዥ እንዲመረጥ፤አዲስ የብሄራዊ ደህንነትና ፅጥታ ሀይል እንዲደራጅ፤ የፀረ ሙስና ትግል በመደራጀት በተለይ የቀድሞ አመራሮችን ላይ ህጋዊ ምርመራን እንዲጀመር መወሰኑ ታውቋል።
ከዚህ በተጓዳኝ፤በመገናኛ ብዙሃን ላይ የተጣለው ገደብ እንዲነሳ፤ቅድመ ምርምራዎች እንዲቀሩ፤ በፖሊስና በደህንነት መዋቅር ውስጥ ሆነው ተቃውሞውን በመደገፋቸው ለእስር የተዳረጉ ከእስር እንዲፈቱ፤ በአሜሪካና በስዊዘርላንድ የሱዳን አምባሳደር ከስራቸው እንዲነሱ መወሰኑንም ተመላክቷል።
የቢቢሲ ዘገባ እንዳመላከተው፤ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ቃል አቀባይ ጄኔራል ሻምስ አድ ዲን ሻንቶ፤ በሰጡት መግለጫም፤በህዝባዊ አመፅ ከስልጣን የተወገደው የአልበሽር አስተዳደር አባላት የነበሩና በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ባለስልጣናት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ የህዝቡንና የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ የተጠየቀውን ሁሉ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ስለመሆኑ አሳውቀዋል።
ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ዜጎችና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማውሳትም «እኛ ጠቅላይ ሚኒስትር መርጠን ይፋ አናደርገም፤ እናንተው ትመርጣላችሁ ሲሉ ተደምጠዋል።
ሱዳናውያን ድምጻቸውን በሰላማዊ መንገድ እስካሰሙ ድረስ ወታደራዊ ሃይሉ ጉልበቱን በመጠቀም ሊበትናቸው ፍላጎት እንደሌለው ጠቁመው፤ይሁንና አላስፈላጊ ተቃውሞ በተለይ መንገድ መዝጋቶችና መሳሪያዎችን ይዞ አደባባይ የሚወጡ ካሉ ትዕግስት እንደማይኖረው አስታውቀዋል።
ለወራት የቆየው የሱዳን ተቃውሞ እ.ኤ.አ ከ 1989 ጀምሮ ሱዳንን ለሰላሳ ዓመታት ሲመሩ የነበሩትን ኦማር አል በሽርን ባለፈው ሐሙስ ከስልጣን እንዲሰናበቱ ማድረግ ቢችልም ገለልተኛ መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ተቃውሞው ቀጥሏል።
መፈንቅለ መንግስቱን የመሩት የመከላከያ ሚኒስትር ከጊዚያዊ ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበርነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ሌፍተናንት ጀነራል አብድልፋታህ አብድራሀማን የሱዳን ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቢት ሊቀመንበር ሆነው ቃለመሀላ በመፈጸም አገሪቱን በበላይነት መያዛቸው ይታወሳል።
አልበሽር በአሁን ወቅት የት እንዳሉ በይፋ የማይታወቅ ሲሆን፤የመፈንቅለ መንግስቱ መሪ አዋድ ሞሐመድ አህመድ ኢብን በአንፃሩ ፐሬዚዳንቱ በጥብቅ ቁጥጥር ስር ስለመሆናቸውና ተላልፈው እንደማይሰጡ ማስታወቃቸውን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011
በታምራት ተስፋዬ