የግብፅ ህዝብ አምጦ የወለደው የካይሮው የጣህሪር አደባባይ ህዝባዊ አብዮት ለዓመታት በፕሬዚዳንትነት የቆዩትን ሆስኒ ሙባረክን በማንሳት መሃመድ ሙርሲን ቢተካም እርሳቸውንም መልሶ ለማውረድ ብዙ ዓመታትን አልጠበቀም፤ አልታገሰም።
በፕሬዚዳንቱ ላይ እምነት በሌላቸው ግብፃውያን ተቃውሞ እኤአ 2013 መንበረ ስልጣናቸውን የተነጠቁትን መሃመድ ሙርሲን ተከትሎ ወደ መሪነት ስልጣኑ የመጡት የቀድሞው የአገሪቱ ወታደራዊ አዛዥ ጄኔራልና የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ግን ለፈርኦኖቹ ሳይስሟማቿው የቀሩ አይመስልም።
በአገሪቱ ታሪክ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ወደ ስልጣን ሲመጡ ተከታይ እንጂ ቀዳሚ የሌላቸው አል ሲሲ፤ ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫም ያለምንም ተቃዋሚ 98 በመቶ በሆነ ድምፅ በማሸነፍ ለተጨማሪ ዓመታት አገሪቱን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ድምፅ ተቀዳጅተዋል።
የህዝቡን ድምፅ ምስክር በማድረግ አል ሲሲ የአብዛኛው ግብፃዊ ፍላጎት ስለመሆናቸው በርካታ ወገኖች ጥርጥር ባይኖራቸውም ፕሬዚዳንቱን በተለይ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወቅሳቸውም አልጠፉም። በተለይም ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የፐሬዚዳንቱን አስተዳደር በዜጎች፤ በተፎካካሪ ፓርቲ አባላትና ጋዜጠኞች ላይ መንግስታዊ ጫና ይደርስባቸዋል፤ ባስ ሲልም ለእስር ይዳረጋሉ ሲሉ ይተቿቸዋል።
ሰውየው በአገር ውስጥ ጉዳይ በተለይ በሰብዓዊ መብት ጥሰትም ትችት የሚያቀርብባቸው ቢሆንም፤ በቀጠናዊ በተለይም በዓለም ዓቀፉ የዲፕሎማሲ ኡደት ተፅእኖ ፈጣሪ ሰለመሆናቸው በርካታ ወገኖች በአንድ ድምፅ ይስማሙበታል። ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት የበርካታ አሜሪካውያን በግብፅ እስር ቤቶች መኖር የነጩ ቤተ መንግስት አስተዳደር ለካይሮ አቻው ያለው ፍቅር ሙሉ እንዳይሆን ቢገዳደረውም በአገራቱ መሪዎች መካከል ያለው ግንኙነት ግን ከአንገት በላይ አለመሆኑ ይታመናል።
የአገራቱ ሁለንተናዊ አጋርነትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ የመጣ ሲሆን፤ ኢጂብት እስትሬት የተሰኘው የአሜሪካን ቻምበር ኦፍ ኮሜርስን ዋቢ በማድረግ እንዳስነብበው፤ በአሁኑ ወቅት ከእስራኤል በመከተል ግብፅ ሁለተኛዋ የዋሽንግተን የውጭ ድጋፍ ተጠቃሚ ናት። እኤአ በ2019የአሜሪካ ኮንግረስ ለግብጽ 1ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ እንዲሰጥ መወሰኑም አጋርነታቸው ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ይቀርባል።
ምንም እንኳን አልሲሲ ከቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ባይኖራቸውም ከወቅቱ ፐሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ግን ወዳጅ ስለመሆናቸው ይታመናል። አብዱል ፈታህ አልሲሲ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ሁለተኛውን የዋሽንግተን ጉብኘታቸውን ከቀናት በፊት አከናውነዋል።
የአሁኑ ጉዟቸውን ተከትሎም እንደ ኒውዮርክ ታይምሱ ማርክ ላንደር አይነት ፀሃፍት አልሲሲ አገሪቱን በማስተዳዳር ሚናቸውን እስከ2034 ለማስቀጠልና ለዚህ ፍላጎታቸው እውነትም የአገሪቱን ህገ መንግስት ለማሻሻል ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ።
ከነጩ ቤተ መንግስት የወጡ መረጃዎች ግን ከዚህ በተቃርኖ ፐሬዚዳንቶቹ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ ስለሚስተዋለው የፖለቲካ ሽኩቻና ዝብርቅርቅ ጉዳይ በተለይም ስለ ኢራን ስለመምከራቸው አመላክተዋል።
ሁለቱ መሪዎች በነጩ ቤተ መንግስት የነበራቸው ቆይታ ውጤታማ እንደነበር ያስታወቁ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ሁለቱ አገራት ግንኙነት በአሁኑ ወቅት በላቀ ከፍታ ላይ ሰለመሆኑ መስክረዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በበኩላቸው አልሲሲን «ታላቅ ፕሬዚዳንት» ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል።
ይህን የትራምፕ ውዳሴና የሁለቱን አገራት ወዳጅነት የተመለከቱ መገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ፀሃፍትም በግንኙነታቸው ላይ የተለያዩ ዘገባና እሳቤዎችን አንፀባርቀዋል። አንዳንዶቹም በተለይ የአገራቱ የልዩነትና የአንድነት ትስስሮች ላይ ልዩ ትኩረትን ሰጥተው ታይተዋል።
ከሁሉም በላይ በመካከለኛው ምስራቅ የሚስተዋለው ቀውስ በሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ ስለሚያሳድረው ጫና በስፋት ያተተው የሚድል ኢስት ኢጂብት ዘገባ፤ የልዩነት አቋሟቸው በግንኙነታቸው ላይ ስለሚያሳድረው ጫና አብራርቷል።
እንደ ዘገባው፤ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳይ የተለያዩ ፖሊሲዎችን የሚያራምዱ ናቸው። የሁለቱ አገራት ልዩነት አቋም መግለጫ ሆነው ከሚጠቀሱት መካከልም የጎላን ተራራ ዋነኛው ነው። ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሶሪያ የሚገኘው የጎላን ተራራ የእስራኤል መሬት ስለመሆኑ እውቅና ሲቸሩ፤ ይህ ግን ለግብፅ የሚዋጥ አይደለምና የዋሽንግተንን ተግባር ትቃወመዋለች።
ሌሎች የልዩነታቸው ማሳያዎች ፍልስጤም እና በነዳጅ ሃብቷ የበለፀገችውና በሜድትራንያን ባህር ጫፍ የምትገኘዋ ሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ መሆናቸውን በመጥቅሰ፣ ግብፅ ከሊቢያ ጋር ድንበር ተጋሪ እንደመሆኗ የትሪፖሊን ጉዳይ በተለየ እሳቤ እንደምትመለከተው አትቷል።
ሊቢያ ከ2014 ወዲህ በፖለቲከኞች አቋም መለያየት ማዕከላዊ መንግስት አጥታ ለሁለት በመሰንጠቅ መቀመጫቸውን ትሪፖሊ ባደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ፋይዝ ሲራጅ እና በጄኔራል ከሊፋ ሃፍጣር እንደምትመራ የሚታወስ ሲሆን፤ ግብፅና አሜሪካም በሊቢያ ምድር ከሁለቱ አንጃዎች ጎን በመቆም የየቅል አቋም አላቸው።
ግብፅ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ፈረንሳይ የጄኔራል ከሊፋ ሃፍጣር ደጋፊዎች ናቸው። አሜሪካ በአንፃሩ የትሪፖሊን ሰላም ከሰባት ዓመታት በሁዋላ ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ በሁለቱ ተፋላሚ ሃይሎች መካከል የስልጣን መጋራት እንዲኖር ፍላጎት አላት።
አገራቱ በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካዊ ምህዋር ውስጥ የልዩነት አቋም ቢኖራቸውም የሚያስተሳስሯቸው ጉዳዮች ይበልጡኑ ሚዛን እንደሚደፉ ያሰመረበት ዘገባው፤ የየቅል አቋማቸውም በወዳጅነታቸው ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም ነው ያለው።
ምንም እንኳን አሁን ሁለቱ አገራት በመልካም ግንኙነት ላይ ስለመሆናቸው ምስክር ባያሻውም በየዓመቱ ዳጎስ ያለ የገንዘብ እርዳታ ከአሜሪካ የምትቀበለው ግብጽ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ኤስ ዩ 35 ኤስ 20 ተዋጊ ጀቶችን ከሩሲያ ለመግዛት ተስማምታለች መባሉ ግን አሜሪካን አላስደሰታትም።
በዚህ ረገድ ዘገባውን ያጠናቀረው የአናዶሉ ኤጀንሲ ዘገባም፤ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖንፒዮ ግብፅ ይህን ለማድረግ አንድ እርምጃ የምትራመድ ከሆነ የዋሽንግተን መንግስት ወቀሳን ብቻ ሳይሆን ቁጣን እንደምታሰተናግድና ይኸውም በማዕቀብ የሚፈፀም ስለመሆኑ መናገራቸውን አስነብቧል።
ከዚህ በተጓዳኝ የሮይተርስ ዘገባ ግብፅ የኢራንን የቀጠናው ጫና ፈጣሪነት ማርገብ አላማው ያደረገውና ጆርዳን፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፤ ሳውዲ አረቢያ፤ ባሃሬን፤ ኦማን፤ ኩዌትና ኳታርን ካሰባሰበው ከመካከለኛው ምስራቅ የጋራ ደህንነት ጥምረት ወይንም አረብ ኔቶ ራሷን ለማውጣት መዳዳቷን ማስነበቡ በአገራቱ መካካል ተጨማሪ ትኩሳት ሆኗል።
በዚህ ረገድ አስተያየታቸውን የሚገልፁ የፖለቲካ ሊህቃንም፤ የግብፅ ውሳኔ የትራምፕን ፍላጎት የማዳከም አቅሙ ግዙፍ ስለመሆኑ አስረድተዋል። በተለይ የኒውስ ዊኩ ፀሃፊ ጃሶን ሌሞን፤ ምንም እንኳን የአገራቱ የየቅል ፍላጎት የአረብ ኔቶ ህብረቱን ጠንካራ ባያደርገውም፤ በአረቡ ዓለም በርካታና ጠንካራ ወታደራዊ አቅም እንዳላት የሚታመነው ግብፅ መውጣት ግን ሌሎችም እንዲከተሏት የማድረግ አቅሙ ግዙፍ ስለመሆኑ አትቷል።
ይህ ደግሞ ለአሜሪካው አስተዳደር ከባድ ራስ ምታት መሆኑ እርግጥ ነው። እናም አሁን የአገራቱ ግንኙነት ሁለት መልክ ቢኖረውና የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ የአንዳንድ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ልዩነት በመጨባባጥ መታሰሩ ቢስተዋልም፤ ስለነገው ግን ማንም እርግጠኛ መሆን አይችልም።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 8/2011
በ
ታምራት ተስፋዬ