የገና ጨዋታ ስፖርት ነው አይደለም? የሚሉ ክርክሮች በብዙዎች ዘንድ ይነሳል። መልሱ አጭር ነው፣ የገና ጨዋታ ስፖርት ነው። ስፖርት ለመባልም አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ በኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን እውቅና ተሰጥቶት ውድድሮች ይካሄድበታል። የኢትዮጵያ ባህል ስፖርቶች ፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ባህል ማዕከል ጋር በሀገሪቱ 2 መቶ 93 በህላዊ ስፖርቶች ላይ ጥናት አካሂዶ ነበር። ለአስራ አንዱ በተካሄደላቸው ጥናት ሕግና ደንብ ወጥቶላቸዋል። ከነዚህ ውስጥ የገና ጨዋታ አንዱ ነው።
በ2006 ተከልሶ በተዘጋጀው የባህልና ስፖርት ሰነድ መሠረት የገና ጨዋታ ወደ 7 የሚደርሱ ሕግና ደንቦች ተዘጋጂቶለታል። አቶ ዓለም እዳብራሩት የተዘጋጀው ሕግና ደንብ የገና ጨዋታ ባህላዊ ይዘቱን ሳይለቅ በሕግና ደንብ እዲመራ የሚያደርግ ነው።
የገና ጨዋታ በዓለም ላይ በብዙዎች እንደሚወደደው የእግር ኳስ ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ የሚስብ አዝናኝ ጨዋታ ነው። ታዲያ በገና ጨዋታ ደንብ መሠረት የመጫወቻ ሜዳው ምን መሆን እንዳለበት፤ የተጫዋቾች ብዛት፤ የዳኞች ብዛትና ኀላፊነት፤ ውጤት አሰጣጥና ሌሎች አስፈላጊ ደንቦች የተካተቱለት ነው።
ፍጥነትን፤ አካላዊ ጥንካሬንና ትንፋሽን የሚጠይቀው የገና ጨዋታ ሳቢና ተወዳጅ እዲሆን ልክ እንደ እግር ኳስ ጨዋታ ደንቦቹ ይመሳሳላሉ። በመጀመሪያ ለገና ጨዋታ ሁለት ተጋጣሚ ቡድኖች ያስፈልጋሉ፤ ለጨዋታ የሚስፈልገው ሜዳም በደንብ ለጨዋታ ዝግጁ ይሆናል።ልክ እንደ እግር ኳስ ሜዳ የጎል ጠባቂ፤ የተከላካይ የአጥቂ፤ የማዕዘን መምቻ በኖራ ይሰመራል። የሜዳ ስፋቱ ደግሞ ርዝመቱ 90 ሜትር ጎኑ 50 ሜትር የሆነ ሜዳ ያስፈልጋል።
በዚህ ሜዳ ውስጥ ለመጫወት ሁለቱ ተጋጣሚ ቡድኖች 15 ተጫዋቾችን ያቀርባሉ፤ አስሩ ሜዳ ውስጥ ገብተው የሚጫወቱ ሲሆን አምስቱ በተቀያሪ ወንበር ይቀመጣሉ። ጨዋታውን የሚመራ የመሃል ዳኛ፤ ዳኛውን የሚያግዙ መስመር ዳኞች እዲሁም ተቀያሪ ተጫዋቾችን የሚቀይሩ ዳኞችም የገና ጨዋታ ተሳታፊዎች ናቸው።
የገና ጨዋታን ለመጫወት ሩር እየተባለች የምትጠራ ድቡልቡል መጫወቻ ያስፈልጋል። ክብደቷ እስከ 5 መቶ ግራም የሚመዝን ከእንጨት፤ ከጠፍር አሁን አሁን ደግሞ ከፕላስቲክ ይዘጋጃል። ድቡልቡል መጫወቻ ወይም ሩሩን ለመምታትና ወደ ተቃራኒ ቡድን ግብ ለማስገባት ልክ እደ ማንኪያ ቅርፅ ያለው ከ1ሜትር የማይበልጥ ቁመት ያለው የገና ዱላ ያስፈልጋል። የገና ዱላው ለሁሉም ተጨዋቾች በእኩል ቁመት የተዘጋጀ ሆኖ ይታደላል።
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ልዩነት አለመኖሩን ዳኛው የማረጋገጥ ኀላፊነት አለበት። ጨዋታው ሲጀመር ሁሉም ተጫዋቾች ተነፋነፍ የሚባለውን ባህለዊ ልብሳቸውን ለብሰው ቦታ ቦታቸውን ይይዛሉ አጥቂው ከአጥቂ፤ ተከላካይ እዲሁ በቦታው፣ በረኛውም በተጠንቀቅ በቦታው ይሰየማል።
ጨዋታውን የሚያስጀምሩት ዳኛ ሶስት “ጊዜ እዚህ እሩር እዛ ገና ” ካለ በኋላ ጨዋታው ይጀመራል። በጨዋታው ሕግ መሰረት ሩሯን በእግርና በእጅ መንካት ነጥብ የስቀንሳል። ለ30 ደቂቃ በመጀመሪያው ምዕራፍ ይጫወታሉ ለ10 ደቂቃ እረፍት ከወሰዱ በኋላ የጨዋታ ሜዳ ተቀያይረው ሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታቸውን ያካሂዳሉ።ጨዋታው ለዋንጫ ወይም ለደረጃ ከሆነ ቡድኖቹ ካልተሸናነፉ ተጨማሪ ደቂቃ እዲጫወቱ ይደረጋል። በዚህም ካልተሸናነፉ የቅጣት ምት እየተሰጣቸው እስኪ ሸናነፉ ድረስ ይጫወታሉ።
የገና ጨዋታ በሀገራችን ባህላዊና ሀይማኖታዊ ይዘት ያለው፣ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ጨዋታ እንደሆነ መዛግብት ያስረዳሉ። መምህር ካህሳይ ገ/እግዚአብሔር የተባሉ የታሪክ ተመራማሪና ደራሲ፤ ስለ ገና ጨዋታ ታሪካዊ አጀማመር ሁለት ትውፊቶች ተደጋግመው እንደሚነገሩ ይገልፃሉ። ጌታ ሲወለድ እረኞች ከመላዕክት ጋር አብረው እንደዘመሩና በወቅቱም የገና ጨዋታ መጫወት እንደጀመሩ አንደኛውን ትውፊት በመጥቀስ ያስረዳሉ።
ሁለተኛው ትውፊት ደግሞ ከሰብዓ ሰገሎች ጋር የሚገናኝ ነው። ንጉስ ሄሮድስ የሚባለው የዘመኑ ንጉሥ አዲስ የሚወለደው ህፃን የበለጠ ዝናና ክብር እንደሚያገኝ የሰማው ትንቢት ስላስደነገጠው በዚያን ጊዜ የተወለዱ ወንድ ህፃናት በሙሉ እንዲገደሉ ትዕዛዝ ሰጥቶ እያሳደደ ያስገድል እንደነበር ይወሳል። ሄሮድስ ታዲያ ጌታ ሊወለድ መሆኑ ተነግሮት ስለነበር የት እንደሚወለድና ስለ አጠቃላይ ሁኔታው በቅርበት ለማወቅ በመፈለጉ አንድ ሰላይ የሰብዓ ሰገሎች ዓይነት ልብስ አስለብሶ፣ ከእነሱ ጋር እንዲቀላቀል ይልካል። ሰላዩ ከሰብዓ ሰገሎች ጋር ተቀላቅሎ ጌታ ወደሚወለድበት ሥፍራ ሲጓዙ፣ ይመራቸው የነበረው ኮከብ ድንገት ቀጥ ይላል። ይኼኔ ተጠራርተው መሃላቸውን ሲፈትሹ፣ ሰላዩን እንዳገኙት ይኸው ትውፊት ያስረዳል። ከዚያም ሰብዓ ሰገሎቹ ሰላዩን ይገድሉና ራሱን ቆርጠው እንደ አሁኑ የገና “እሩር” እየተቀባበሉ ተጫወቱበት ይላል – ሁለተኛው ትውፊት። ከዚያም በመነሳት የገና ጨዋታ ተፈጠረ ይላሉ፤ የታሪክ ተመራማሪው።
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ከትውልድ ትውልድ እየተቀባበለው፣ እስከ አሁን የቀጠለው የገና ጨዋታ፤ በየዓመቱ በታህሣሥ ወር በተለይ በኢትዮጵያ የገጠሩ ክፍል እረኞች በድምቀት ይጫወቱታል። በአብዛኛው ጨዋታው ወሩ እንደገባ የሚጀመር ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ከታህሳስ ወር አጋማሽ ጀምሮ እንደሚጧጧፍ ይታወቃል።
የገና ጨዋታ አሁን በዘመናዊ መልኩ በከተሞች ከምናየው ይለያል። በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በገባው ዘመናዊ የገና ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ዱላውን (ገናውን) ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም። በጥንታዊው ወይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚደረገው የገና ጨዋታ ላይ ግን እንደተፈለገው በማንሳት፣ ሩሯን (ጥንጓን) አክርሮ መለጋት ይቻላል።
ሌላው ደግሞ በዘመናዊው የገና ጨዋታ ስፖርት፣ ሩሯ የምትገባበት (የምትለማበት) ሥፍራ እንደ እግር ኳስ የግብ ሥፍራ ያለው ነው። በጥንታዊው ጨዋታ ግን የገና ጨዋታው የሚካሄድበት ሜዳ ወይም የእርሻ ማሣ፣ ሁለቱም ጫፎች የግብ ወይም የመልሚያ ቦታዎች ናቸው። ከሜዳው ወይም ከማሳው ስፋት የተነሳም ተጫዋቾቹ እንደ ልባቸው እየሮጡ ይጫወታሉ። ጨዋታው በውጤት አሊያም በሽንፈት እየታጀበ ይቀጥላል።
መልካም የገና በዓል!
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም