ብራዚል ከሩሲያ፣ ቻይና፣ ካናዳ እና አሜሪካ ቀጥላ አምስተኛዋ ትልቅ ሀገር ነች። ስፋቷም ከጠቅላላው የደቡብ አሜሪካ አህጉር ግማሽ ያህሉን ይይዛል። የፖርቹጋላዊው የፔድሮ ካብራል ጉዞ የብራዚልን አፈር የረገጠው የመጀመሪያው ሰው እንዲሆን አድርጎታል። ፖርቹጋላውያን ወደ ሕንድ የሚወስዱትን አዳዲስ መንገዶችን እየፈለጉ የነበር ቢሆንም የፈለጉትን ያህል የከበረ ማዕድን ማግኘት አልቻሉም ነበር። ነገር ግን በጉዟቸው አንድ የማይታወቅ መሬት አግኝተዋል። እሱምን “የቅዱስ መስቀል ምድር” ብለው ይጠሩታል።
ፖርቹጋሎች የወርቅ እና የከበሩ ድንጋዮች ክምርን አልመው ነበር። ሆኖም ፍለጋቸው አልተሳካም። በጣም ዋጋ ያለው እንደ ፖርቹጋሎች ሰፋሪዎች በአዲሱ ቅኝ ግዛት ውስጥ ደማቅ ቀይ ቀለም የተገኘበት የፓውብራሲል ዛፍ ነበር። ይህ ቀይ ዛፍም ስያሜው ብራዚል ስለነበር አገሩ በስሙ ተሰይሟል – ብራዚል።
የብራዚል ሁለቱ የተፈጥሮ ክልሎች (በደን የተሸፈነው የአማዞን ወንዝ ሜዳ ፣ ገባር ወንዞቹ እና የብራዚል ፕላቶ) በእጅጉ ይለያያሉ። አማዞን በጣም ትልቅ ከመሆኑ የተነሳ ሙሉ በሙሉ ከጠፈር ላይ ብቻ ሊታይ ይችላል። ይህ አረንጓዴ ወሰን የሌለው የማይበገር ስፋት ነው ። አንዳንድ ጊዜ በዚህ አረንጓዴ ጥቅጥቅ ያለ ሰፊ ሰማያዊ ነጠብጣቦች ይታያሉ። ይህ ሰፊ ምድርም በወንዞቹ ሪባን አንድ ላይ ይጣመራል።. ከዚህች የዓለም ሳንባ ከተባለችው ሀገረ ብራዚል፤ በቅርቡ በሞት ከተለየን ከእግር ኳስ ንጉሱ ፔሌ ሀገር የተነሱና መዳረሻቸውንም ደቡብ አፍሪካ ያደረጉትን የሁለት ብራዚላውያን ሴቶችን ታሪክ ላካፍላችሁ ስለወደድኩ ነው ስለብራዚል ያነሳሳሁት።
እፅ ማዘዋወር መተዳደሪያቸው ያደረጉ ብራዚላውያን
ብራዚላውያን ጓደኛሞች ናቸው። ኤልዳ ሪጂና ሳንቶስና ሚስ ናዲራ ጋብርኤላ። ከልጅነታቸው ጀምሮ የድሆች መንደር ውስጥ በማደጋቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት የተገኘውን ሥራ በሙሉ ለመሥራት ይታትሩ ነበር። መላላክ፤ አነስተኛ ንግዱንም አለ የተባለውን ሥራ በሙሉ በመሥራት የዕለት ምግባቸውን ዳቦ መግዛት ችለውም ነበር። የልጅነት ጊዜያቸውን አንዴ ትምህርት ቤት ሲሄዱ፤ ረሀብና ችግር ሲፈራረቅባቸው ደግሞ ሲቀሩ ፊደል ከመለየትና የተወሰኑ የሂሳብ ቀመሮች ከማወቅ የዘለለ እውቀት የሚያስገኝ የትምህርት ደረጃ ላይ አልደረሱም ነበር።
ለአቅመ ሄዋን እንደደረሱ ብዙም ያልገፉበትን ትምህርት ወደ ጎን በመተው ከእነሱ ሰፈር ወደ ሀብታሞቹ ሰፈር አደንዛዥ እፆችን በማዘዋወር ሥራ ላይ ተጠመዱ ። አንድ ሁለት እያሉ የተሠማሩበት ሥራ ከድህነት አላቆ ከፍ ወዳለ የሀብት ማማ የሚያደርስ መሆኑን ከሚያሠሯቸው ሰዎች ኑሮ ተመልክተው ተረድተዋል።
እነሱም እራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ከችግር ለማላቀቅ ምርጫቸው ያደረጉት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲያዩት ያደጉትን ሥራ ነበር። ከሰፈር ሰፈር አደንዛዥ እፅ በማዘዋወር የተጀመረው ሥራ በብራዚል ውስጥ የሚገኙ ክፍለ ሀገራትን በሙሉ አዳርሷል። ብራዚል ውስጥ የተለያዩ ቦታዎች ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን የጀመሩትን ሥራ በዓለም ደረጃ ለማዳረስ አሰቡ ። እቅዳቸውን እውን ለማድረግም መዳረሻቸውን በማስፋት ከትውልድ ቀያቸው በመነሳት የተለያዩ ሀገራትን መርገጥ ጀመሩ።
ከሀገረ ብራዚል የተነሱት እፅ አዘዋዋሪዎች
በ214 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ያላት የዓለማችን አምስተኛዋ ባለብዙ ሕዝብ ሀገር ብራዚል በእግር ኳስ የመታወቋንም ያህል ወንጀል በብዛት ከሚፈፀምባቸው ሀገሮች አንዷ እንደሆነች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የኢኮኖሚ የበላይነት የያዙት ሀብታም ብራዚላውያን የሀብት ማማ ላይ ቢቀመጡም ድሆቹ ግን በሴተኛ አዳሪነት፤ በአነስተኛ ሥራዎችና በአደንዛዥ እፅ ዝውውር ስማቸው ይነሳል።
ታዲያ ድህነት እግር ከወርች ያሠራቸው፤ ከድሆቹ ወገን የሆኑት ጓደኛሞች እንደ ልማዳቸው ከትውልድ ቀያቸው ተነስተው የአፍሪካ ኩራት በሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል አደንዛዥ እፅ የተሞሉ ሻንጣዎቻቸውን እንደያዙ ለመሄድ ሲነሱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከፍትሕ ሚኒስቴር ድረገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ኤልዳ ሪጂና ሳንቶስና ሚስ ናዲራ ጋብርኤላ የተባሉ ብራዚላዊ ዜግነት ያላቸው ሁለት ሴቶች እፆችን ለማዘዋወር የፀና ፍቃድ ሳይኖራት መነሻቸውን ብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ አድርገው ቀጣይ ጉዞዋቸውን ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስ በርግ ከተማ ለማድረግ በኢትዮጵያ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ለትራንዚት ባረፉበት ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል።
በቅድሚያ ኤልዳ ሪጂና ሳንቶስ የተባለችው ብራዚላዊ ዜግነት ያላት ተከሳሽ እፆችን ለማዘዋወር የፀና ፍቃድ ሳይኖራት መነሻዋን ብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ አድርጋ ቀጣይ ጉዞዋን ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ ለማድረግ መስከረም 26 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ30 ሲሆን በኢትዮጵያ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ለትራንዚት ባረፈችበት ጊዜ በፌደራል ፖሊሶች አደገኛ ዕጽዋት ቁጥጥር እና ክትትል ሠራተኞች የያዘችው ሻንጣ ሲፈተሽ በውስጡ 1ሺ 76 ጥቅል ፍሬ ሲመዘን 23 ሺ 73 ግራም የሆነውን ኮኬይን እፅ ደብቃ ለማሳለፍ ስትል ተይዛለች፡፡
ሌላዋ ሚስ ናዲራ ጋብርኤላ የተባለችው ብራዚላዊ ዜግነት ያላት ተከሳሽ ልዩ ፈቃድ ሳይኖራት ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውን ኮኬይን እፅ በሻንጣዋ ውስጥ ደብቃ ለማዘዋወር በማሰብ መነሻዋን ብራዚል ሀገር ሳኦፖሎ ከተማ አድርጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ለትራንዚት ባረፈችበት ወቅት ነሐሴ 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት አካባቢ ብዛቱ 533 ፍሬ ጥቅል ኮኬይን መያዟ በፍተሻ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመችው አደገኛ ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል በቁጥጥር ስር ውላለች።
የአንዷ ጥፋትና ቅጣት ያላስተማራት ሌላኛዋም በድፍረት የሀገሪቱን አየር አቋርጠው ያልተገባ ወንጀል ለመሥራት መሞከራቸው የሀገሪቱን ሕግ የጣሰ መሆኑን ፖሊሶች ይናገራሉ።
የፖሊስ ምርመራ
የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ በኢትዮጵያ ሕግ ከተመለከቱ ወንጀሎች ውስጥ ማንኛውንም ወንጀል ቢያደርግ የሀገሪቱ ሕግ ተግባራዊ ተደርጎበት በሀገራችን ሕግ መሠረት የሚቀጣ ሲሆን የኢትዮጵያ ግዛት የብሱን፣ አየሩንና የውሃ አካላቱን የሚያጠቃልል መሆኑን ፖሊሶች ሕግን ጠቅሰው አስረድተዋል። ይህን ሕግ ተጠቃሽ ያደረጉት የአየር መንገዱ የደህንነት አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ለተጨማሪ ምርመራ ወደ ጣቢያ ከተወሰዱ በኋላ የዓይን ምስክር የሰነድና በኤግዝቢትነት የተያዙ ዕፆችን ማስረጃዎችን በማያያዝ ፖሊስ ለዐቃቤ ሕግ ያቀርባል።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ኤልዳ ሪጂና ሳንቶስ የተባለችው ብራዚላዊ ዜግነት ያላት ተከሳሽ ዕፆችን ለማዘዋወር የፀና ፍቃድ ሳይኖራት መነሻዋን ብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ አድርጋ ቀጣይ ጉዞዋን ደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ ያደረገችው ሙከራ የከሸፈባት ተከሳሽም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት ቀርባ ክሱ ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ስትል የእምነት ክህደት ቃሏን ሰጥታለች።
ዐቃቤ ሕግ ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልገው ተከሳሿ ባመነችው መሠረት የጥፋተኝነት ፍርድ እንዲሰጥ ጠይቋል። ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር በዝርዝር ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሠረት የጥፋተኝነት ፍርድ ሰጥቷል፡፡
በሌላ የችሎት ውሎ ከ 14 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን የኮኬይን እፅ ይዛ የተገኘችው ናዲራ ጋብርኤላ ደግሞ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ 14ሺ 412 ግራም የሚመዝን የኮኬይን ዕፅ በተደረገ ፍተሻ በሻንጣዋ ውስጥ የተገኘባት ብራዚላዊት ናት።
የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ሚስ ናዲራ ጋብርኤላ የተባለችው ብራዚላዊ ዜግነት ያላት ተከሳሽ ልዩ ፈቃድ ሳይኖራት ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወርና በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውን ኮኬይን እፅ በሻንጣዋ ውስጥ ደብቃ ለማዘዋወር በማሰብ መነሻዋን ብራዚል ሀገር ሳኦፖሎ ከተማ አድርጋ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመጓዝ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ለትራንዚት ባረፈችበት በፈፀመችው አደገኛ ዕፅ ማዘዋወር ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶ ውሳኔ አሰጥቷል፡፡
ውሳኔ
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ 23ሺ 73 ግራም የሆነውን የኮኬይን እፅ ደብቃ ለማሳለፍ ስትል በተደረገ ፍተሻ በተያዘችው ኤልዳ ሪጂና ሳንቶስ የተባለች ብራዚላዊት ዜጋ ላይ ክስ አቅርቦባት በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ አደረገ፡፡
ሌላዋ ጥፋተኛንም በተመሳሳይ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎት የቀረበችው ተከሳሽም ክሱ በችሎት ተነቦላት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ያለች ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግም ማስረጃ ማቅረብ ሳያስፈልገው ባመነችው መሠረት የጥፋተኝነት ፍርድ ይሰጥልኝ ሲል ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር በዝርዝር ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሠረት የጥፋተኝነት ፍርድ በመስጠት በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል፡፡
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29 ቀን 2015 ዓ.ም