የመምህርነት ሙያ በመማር ማስተማር አውድ ውስጥ ትውልድን አገር ተረካቢና ገንቢ ዜጋ አድርጎ የመቅረጽ ከባድ ኃላፊነት ያለበት ነው፡፡ ይህ ተግባር ከውጤት መድረስ የሚችለው ደግሞ መምህራን ሙያቸውን አፍቅረው ሲሰሩና በሚሰሩት ሥራም ስኬት ማስመዝገብ ሲችሉ፤ ይሄን የማድረግ ውስጣዊ ዕምነት ሲፈጥሩ ነው፡፡ይሄን እውን ከማድረግ አኳያም ባለፉት ጊዜያት ለየትምህርት ደረጃው የመምህራን ምልመላና የሥልጠና ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡
ሆኖም ለትምህርት ጥራቱ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት መምህራን ላይ በአቅምም ሆነ በሥነምግባር የሚታዩ ክፍተቶች ስለመኖራቸው ይገለጻል፡፡ መንግሥትም ይህን ችግር በመገንዘብ የመምህራንን የሙያ ብቃት መመዘን ጀምሯል፡፡ ለአብነት፣ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን ላይ በተደረገ የሙያ ብቃት ምዘና 82 በመቶ የሚሆኑት መምህራን ምዘናውን መውደቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ለዛሬም በአሁኑ ወቅት እየተዘጋጀ ላለው ፍኖተ ካርታ አጋዥ የሆነው ጥናት በጉዳዩ ላይ ያወጣቸውን መረጃዎች፤ እንዲሁም ዝግጅቱ ችግሩን ለማቃለል እንዴት ያግዛል የሚል ዳሰሳ አድርገናል፡፡
የመምህራኑ ውጤት
የመጀመሪያው ዙር ማለትም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል 73 በመቶ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሁለተኛ ሳይክል ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል 95 በመቶ፣ የሁለተኛ ደረጃ መምህራን ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል 93 በመቶ ለደረጃው ብቁ የሚያደርግ የትምህርት ዝግጅት እንዳላቸው በ2009 ዓ.ም የወጣው ዓመታዊ የስታትስቲክስ መጽሔት ያመለክታል፡፡ ምንም እንኳ አብዛኞቹ መምህራን ለደረጃው የሚጠበቀውን የትምህርት ዝግጅት ቢያሟሉም፤ ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም በተካሄዱ የሙያ ፍቃድ ምዘና ከወሰዱት 140ሺ 435 የመጀመሪያና 24ሺ 63 ሁለተኛ ደረጃ መምህራን ውስጥ የመቁረጫ ነጥቡን በማሟላት ያለፉት 22 በመቶ መምህራን ብቻ እንደሆኑ ጥናቱ ያመላክታል፡፡
የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ መምህራን የሚኖራቸው ፋይዳ የጎላ በመሆኑም ካሉት ችግሮች በመነሳት ከዩኒቨርሲቲዎች መስፋፋት ጎን ለጎን መምህራን ምልመላ የአቅም ግንባታ ሥራ በሰፊው ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን ቁጥር በፍጥነት እያደገ መጥቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመላክቱትም በ2005 ዓ.ም 23ሺ 905 የነበረው መጠን በ2009 ዓ.ም ወደ 32ሺ 734 አድጓል፡፡ ከብቃት አንፃር ሲታይ ግን ብዙ ችግሮች ይስተዋሉበታል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ለደረጃው ብቁ የሰው ኃይል በብዛት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ከዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ መምህራን ተመልምለው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉ በመማር ማስተማሩ ላይ አሉታዊ ጫና አሳድሯል፡፡ ለዩኒቨርሲቲ መምህርነት የሚመለመሉት በከፍተኛ ማዕረግ ከተመረቁት ማለትም 3ነጥብ 25 እና ከዛ በላይ ውጤት ካስመዘገቡት ውስጥ ሲሆን፤ ፈተና በመስጠት እንዲለዩ ይደረጋል፡፡ ሆኖም የፈተናው ውጤት የከፍተኛ ትምህርት ስርዓቱ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማል፡፡
ምክንያቱም ለፈተና ከተቀመጡት 8ሺህ 392 ዕጩዎች ውስጥ በተመረቁበት የትምህርት ዓይነት መሠረታዊ ሳይንሱን ተፈትነው ግማሽ በመቶና ከዛ በላይ ያመጡት 27 ነጥብ 79 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ በተለይ በሒሳብ 1ነጥብ3፣ ኢኮኖሚክስ 2ነጥብ 65፣ እንግሊዝኛ 3ነጥብ 48፣ ታሪክ 3 ነጥብ 77፣ ፊዚክስ 4ነጥብ 61፣ አካውንቲንግ 8ነጥብ 37 እና ኬሚስትሪ 9ነጥብ 2 በማስመዝገብ እጅግ አነስተኛ አፈፃፀም ያለባቸው የትምህርት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ጂኦግራፊ 20ነጥብ 78፣ የእንስሳት ሳይንስ 26ነጥብ 58 እና ዕፅዋት ሳይንስ 45ነጥብ 66 አነስተኛ አፈፃፀም ታይቶባቸዋል፡፡ ሌሎቹ ባዮሎጂ 64 ነጥብ 68፣ የተፈጥሮ ሃብት አስተዳደር 63 ነጥብ 98፣ ግብርና ኢኮኖሚክስ 59 ነጥብ 85 እንዲሁም ማኔጅመንት 56 ነጥብ 98 በመቶ በአንፃራዊነት የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቦባቸዋል፡፡ አጠቃላይ ውጤቱ የሚያሳየውም የከፍተኛ ትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ያለ መሆኑን ነው፡፡
የእነዚህ ተፈታኞች ምዘናውን ካለማለፋቸው ባሻገር፣ ያላቸውን ዕውቀት በክፍል ውስጥ ማካፈል ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የትምህርት ክፍለ ጊዜ የሚያባክኑ መምህራን ከፍተኛ እንደሆኑ ጥናቱ ያሳያል፡፡ መምህራን ሥራቸውን ሳይለቁ ነገር ግን ከመልቀቅ ባልተናነሰ ሁኔታ ጥናት በተደረገባቸው በ222 የገጠርና በ125 የከተማ ናሙና በተወሰደባቸው ትምህርት ቤቶች ውስጥ 12 በመቶዎቹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ያለምንም በቂ ምክንያት ይቀራሉ፡፡ 28 በመቶ ያህሉ ደግሞ በትምህርት ቤት ውስጥ እያሉ ክፍል ውስጥ የማይገቡ ሲሆኑ፤ ሰባት በመቶ ያህሉ ከዚህ በከፋ ሁኔታ በክፍል ውስጥ ያሉ፣ ነገር ግን የማያስተምሩ ናቸው፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በክፍል ተገኝተው በአግባቡ የሚያስተምሩት 51 በመቶዎቹ ብቻ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ለትምህርት የተመደበው ውስን የጊዜ ሀብት ምን ያህል እየባከነ እንደሆነና አገሪቱ ከእያንዳንዱ ተማሪ የምትጠብቀው የዕውቀት፣ የክህሎትና የአስተሳሰብ ልማት በምን ያህል የጉዳት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪ በ2009 ዓ.ም ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት ለመከታተል የ11ኛና የ12ኛ ክፍል ይዘቶችን የያዙ ጥያቄዎች ተዘጋጀተው የመግቢያ ፈተና ከተፈተኑ 21ሺ 91 የሁለተኛ ደረጃ መምህራን መካከል 50 በመቶ በላይ ውጤት ያመጡት 37ነጥብ 72 በመቶው ብቻ ናቸው፡፡
መንግሥት በልዩ ትኩረት ከሚሰራባቸው ሳይንስ ትምህርቶች ውስጥ ለፈተና ከተቀመጡት 1ሺህ 732 የፊዚክስ መምህራን መካከል ከግማሸ በመቶ በላይ ያመጡት 12 መምህራን ብቻ መሆናቸውን ጥናቱ ያመላክታል፡፡ በተመሳሳይ ኬሚስትሪ 4ነጥብ 43 እንዲሁም ሒሳብ ደግሞ 11ነጥብ 86 በመቶ መምህራን ብቻ መሆናቸው ውጤቱ እጅጉን ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህም የሒሳብ፣ የፊዚክስ፣ የኬሚስትሪና የባይሎጂ መምህራን ውጤት ከተማሪዎች ውጤት ጋር የሚዛመድ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ተማሪዎች በእነዚህ የትምህርት ዓይነቶች ያመጡት ውጤትም እንደ መምህራኑ ሁሉ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም ተማሪዎቹ የሚማሩት ብቁ ባልሆኑ መምህራን መሆኑን አመላካች ነው፡፡ በተያያዘም የመምህራን አሰለጣጠን ላይ ያለውን ችግር ማሳያ ይሆናል፡፡
በ2010 ዓ.ም በአፕላይድ ሣይንስ ዲግሪ ከተመረቁት ውስጥ ለሁለተኛ ደረጃ መምህርነት በመመልመል በሙያው ለማሰልጠን ለፈተና ከተቀመጡ 4ሺ 282 ዕጩዎች ውስጥ ማለፍ የቻሉት 1ሺህ 147 ብቻ ናቸው፡፡ ይህም በተመሳሳይ የዩኒቨርሲቲ አሰለጣጠኑ ላይ ምን ያህል ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት ያለው ሥርዓተ ትምህርት የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለሁሉም ከሚል መርህ የሚነሳ አይደለም፡፡ ይልቁኑም የተወሰኑ ተማሪዎችን ለከፍተኛ ትምህርት የሚያዘጋጅ ከመሆኑም ባሻገር በአካዳሚክ ንድፈ ሃሳብ የታጨቀና በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ የሚሞክር ነው፡፡ ይዘቱም ቢሆን ከሌሎች አገሮች ጋር ሲወዳደር ከባድ እንደሆነ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ይዘቶች ለመምህራኑም ይከብዳሉ፡፡
የችግሩ ገጽታ
በአፍሪካ ጎረቤት አገራት እንኳ ለትምህርት ዕድሜያቸው የደረሱ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ በተሻለ ሁኔታ ይልካሉ፡፡ በኬንያ 76 በመቶና ማላዊ 82 በመቶ የዓለም መመዘኛ መስፈርት ደግሞ 80 በመቶ ሲሆን፤ ከዚህ ሁሉ በተቃራኒው ግማሽ በመቶ ያልሞላ ተሳትፎ ያለው በኢትዮጵያ ነው፡፡ የነገ አገር ተረካቢ ትውልድ የሚቀረጽበት ቅድመ መደበኛ ደረጃ ላይ በተለይ እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡ 28 ሚሊየን ተማሪዎች አሉ ቢባልም አሁንም ቢሆን ከትምሀርት ገበታ ውጪ ያሉ ዜጎች አሉ፡፡ አርብቶ አደሩና አርብቶ አደሯ ለከብቶቻቸው ግጦሽ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ትምህርት የማያገኙ ልጆቻቸው ብዙ ናቸው፡፡ እንደ ዕድሜ እኩዮቻቸው ሁሉ ትምህርት ቤት በመግቢያ ዕድሜያቸው የከብት ጭራ ሲከተሉ የሚውሉም አልጠፉም፡፡ ከዚህ ውጪም ለፍልሰትና ከአቅማቸው በላይ በሆኑ ሥራዎች ሲሰማሩ ይታያል፡፡
ዕድሜያቸው ለትምህርት ከደረሱት 100 በአገሪቱ የሚገኙ ህፃናት ውስጥ 55 ወደ ትምህርት ቤት እንደማይሄዱ ተረጋግጧል፡፡ ወደ ትምህርት ገበታ የሚያቀኑት 45 ተማሪዎች ውስጥም በተገቢው ሁኔታ ዕውቀት የሚቀስሙት ውስኖች ናቸው፡፡ በዚህም ብዙዎች ውለው ለመመለስ መገደዳቸውን የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ይናገራሉ፡፡ የተማሪዎች ውጤትም ዝቅተኛ ነው፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ በተጠናው ጥናት መሠረት አራተኛ ክፍል ከሆኑ ተማሪዎች መካከል ማንበብ የሚችሉት 44 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ በተመሳሳይ በእንግሊዘኛም ትምህርት የሚጠበቅባቸውን ያክል ችሎታ ያላቸው 27 በመቶ አልዘለሉም፡፡ በአጠቃላይ በደረጃቸው የሚጠበቅባቸውን ዕውቀት ያላቸው 36 በመቶ ተማሪዎች እንደሆኑ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ከፍ ባሉት የክፍል ደረጃዎች ላይ ደግሞ ከይዘት ባሻገር ሥርዓተ ትምህርቱን በትምህርት ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ በመደገፍ የተማሪዎችን የመማር ውጤት ለማሻሻል እንዲቻል ብዙ ሃብት ፈሶበት ትምህርቱ በፕላዝማ ቴሌቭዥን ይሰጣል፡፡ ይሁን እንጂ አፈፃፀሙ ሲታይ የሚተላለፍበት ቋንቋ መክበድና ገለፃውም በጣም ፈጣን ከመሆኑ ባሻገር የመምህሩንና የተማሪውን የሁለትዮሽ በመስተጋብር የማይፈቅድ፣ መምህራን በፕላዝማ ቴሌቭዥኑ ሙሉ በሙሉ ዕምነት በመጣል የራስን ዝግጅት አለማድረግ፣ በቴክኖሎጂው ተጠቅሞ ሰፊ ዕውቀት ለተማሪው አለመስጠት ችግሮች እንዳሉ በጥናቱ ተዳሷል፡፡
የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ መሆን ጎን ለጎን በሥራ ላይ ያሉት መምህራን በአገር ደረጃ ተመዝነው ብቃትና ዕውቀታቸው በጣሙን ዝቅተኛ ነው፡፡ ምልመላ፣ ስልጠና፣ ስምሪትና ክትትላቸውም ለደረጃ የማይመጥኑ መምህራን እንዳሉ የሙያ ብቃት ምዘናው እንደሚያሳይ ዶክተር ጥላዬ ይጠቁማሉ፡፡ ለሁለተኛ ዲግሪ ወይንም ማስተርስ ትምህርት የሚገቡ መምህራንም 11ኛ እንዲሁም 12ኛ ክፍል የሚያስተምሩትን የትምህርት ዓይነት የተውጣጣ ፈተና ወስደው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ያለፉት በቁጥር አነስተኛ ናቸው፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያ በፊዚክስ ትምህርት 12 ብቻ እንዳለፉም በመግለጽ ችግሩ ያለበትን ደረጃ ያስረዳሉ፡፡
ቀጣይ አቅጣጫ
የትምህርት ዘርፍ የአገሪቱ የጀርባ አጥንት የሆነውን ግብርና ወደ ኢንደስትሪ ማሸጋገር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህንንም ዕውን ሊያርግ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፡፡ ነገር ግን በቀጣይ በዘርፉ ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን ትርጉም ባለው ደረጃ ለማቃለል ሥርዓተ ትምህርት መቀየር ወሳኝ እንደሆነ ነው ሚኒስትሩ እንደ መፍትሔ የሚናገሩት፡፡ በዚህም በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ላይ ከተደራሽነቱ ባሻገር በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት በመለየቱ ይህን ለመቀየር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ይሰራል፡፡
በተለይም ዘርፉ ለኢንደስትሪ መጋቢ ቢሆንም ከኢንደስትሪ ፍላጎት ጋር ያልተሳሰረ፣ ቅንጅት የጎደለው ብሎም የአሰልጣኞች ብቃት አጠያያቂ ደረጃ የደረሰና ቴክኖሎጂ የሚያሸጋግሩ ባለሙያዎች የሌሉት በመሆኑ ይህን ሊፈታ በሚችል መልኩ ይተኮርበታል፡፡ ነገ አገር የሚረከቡና የሚገነቡ ትውልዶች የሚቀረጹበት መንገድም ሊሻሻል ይገባል፡፡ በእያንዳንዱ ሂደትም ኅብረተሰቡ የራሱን ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡ መንግሥትም መምህራንን ሊያሰለጥን፣ ጥራት ያለው ትምህርት ሊያዘጋጅ፣ እንዲሁም መምህራንን በየጊዜው በሙያቸው ሊያበቃቸውና ምቹ ሁኔታ ሊፈጥርላቸው ማቀዱን ሚኒስትሩ ያመላክታሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 24/2011
በፍዮሪ ተወልደ