“ከተኖረው ያልተኖረው”

ከባሕር በሚልቀው ሰፊ መናፈሻ ውስጥ ብቻዋን ተቀምጣ “በፍቅር እስከመቃብር” ትረካ ትቆዝማለች። የፈካ አሊያም የተጎሳቆለ የሕይወት ገጽ ባየሁ ቁጥር ማንነታዊና ምንነታዊ ይዘቱን እበረብር ዘንድ አመሌ ነውና ምን ሆና ይሆን? የሚል ጥያቄ ሆዴን ቢቆርጠኝ ይሁንታዋን ሳልጠብቅ ከጎኗ ወንበር ስቤ ተቀመጥኩና ‹‹ሃዲስ አለማየሁና ወጋየሁ ንጋቱ ተጋግዘው የሸለሙሽን የትዝታ ፈረስንማ እኔም አብሬሽ መቆናጠጥ አለብኝ›› አልኳት መግቢያ እንዲሆነኝ ጨዋታ ቢጤ በማስቀደም። “ይህን መጽሐፍ አብዝቶ ነበር የሚወደው፤ ያለንበትንም ስፍራ እንዲሁ” አለች እንባ ያረገዙ ዓይኖቿ ቦዘው። ‹‹ወጋየሁ ንጋቱ ነው? ወይስ ሃዲስ አለማየሁ?›› አልኳት ያልገባኝ በመምሰል፡፡ የነገሯን ጫፍ ለማግኘት በምናቤ እየኳተንኩ። በስንት ልመና እሽታዋን ስትሰጠኝ ምስሏንና ትንፋሿን ለማስቀረት ካሜራዬንና መቅረጸ ድምጼን እንደአልሞ ተኳሽ ወደርኩና የሚጣፍጥ ነገር ግን የማያጠግብ እንጎቻ ወጓን እሰለቅጥ ገባሁ።

በወርሃ ጥር 1981ዓ.ም ከአባቷ አቶ መኮንን መሰለና ከእናቷ ወይዘሮ እናኑ መኮንን አዲስ አበባ የተወለደችው ዮዲት ዕድገቷ “የካቲት አስራ ሁለት” ሆስፒታል አካበቢ ነው፡፡ ይህ ሰፈር ለእሷ በብዙ መልክ ይገለጻል፡፡ ስምና ሰብዕናዋ ነው፡፡ የልጅነት ፍቅሯ በሃሜትና ነቀፌታ ሲፈተን መስዋእትነትን ትከፍል ዘንድ መልካም ሞራል አስታጥቋታል። ዮዲት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስተኛ በር ትይዩ ‹‹ሊጋባ›› ቢሮ ከተሰኘው መንደር የ‹‹ የኔታ››ን የቄስ ትምህርት ፉት ብላለች፡፡ ትምህርቱ ለአስኳላው እርሾ ቢሆናት አጼ ናኦድ፣ በላይ ዘለቀንና ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤቶችን ጎብኘች፡፡ የቀለም ቆይታዋን ተሻግራም ከአላባ ቴክኒክና ሙያ በጸሐፊነት ሙያ ለመመረቅ በቃች።

‹‹የአዲስ አበባን ምድር አስለቅቆ አላባ የሚያደርስ ምን ሰበብ አገኘሽ?›› አልኳት መልሷን ለመከተብ የወረቀቱን ደረት በብዕር እያረስኩ። ግንባሯ ላይ የተነሰነሰውን ጸጉሯን ወደኋላ እየላገች እንደ አምባሰል ዜማ ሆድ በሚበረብር ድምጸት ትዝታ የተጫነውን ሃሳቧን አቀበለችኝ።

እናቷ እናኑ ኑሮን ለማሸነፍ ከሚተዳደሩበት መሸታ ቤት ከሚመጡ የስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሃል ዛሬ ሦስት ልጆችን ካፈራችለት አቶ አበበ ሞላ ጋር በፍቅር ተጣመሩ።የእዛኔ እሷ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፡፡ በጊዜው ፍቅራቸውን ሊገልጡት ሲሹ ዘመድ ባዳው ፊት ነሳቸው። እነሱ ግን “የሰው ዓይን በላን” ብለው ተስፋ ሳይቆርጡ በጽናት ቀጠሉ፡፡ ጥንዶቹ የበርካቶችን ጎታች አመለካከት ወደኋላ ትተው የታሪክ መምህር ሆኖ ወደተመደበበት አላባ ተጓዙ።

አክዬም ‹‹ከቤተሰብ ፍቃድ ወጥተሽ እንድትጠፊ ያስገደደሽ ምክንያት ምን ይሆን?›› ስል ጥያቄ ሰነዘርኩላት። እርሷም “እንዴት አካል ጉዳተኛ ታገቢያለሽ? ብለው ነዋ! አለችኝ፡፡ በጊዜው ለጋብቻው እንደ ወግ ባሕሉ የሚጠበቀውን ሥርዓት አልከወኑም፡፡ የኋላ ኋላ ልጆች ሲመጡና የወላጆቿን የኑሮ ቀዳዳ መድፈን ሲጀምሩ ግን የተሳሳተ አመለካከታቸውን ማረቅ ችለዋል፡፡ ዮዲት ዳሩ ምን ይሆናል” ስትል ቀጠለች፡፡ ወዲያው ዓይኖቿ በዕንባ ተሞልተው ማልቀስ ጀመረች፡፡ በሁኔታዋ ክፉኛ መረበሼ ጥያቄዬን ለማቆም ያስገድደኝ ያዘ፡፡ “አትፍራ ግድ የለም፤ ይልቁንስ ተከተለኝ” አለችና መናፈሻው ውስጥ ወደአቆመቻት መኪናዋ መራችኝ። ሚጢጢ መኪናዋን ኮልኩላ እንደአገው ፈረስ ስታሰግራት “አንካሳ ወፍ ቀደመችሽ፤ ቶሎ በይ” የምትላት ይመስል ነበር።

“ለመጀመሪያ ጊዜ የጋበዘኝ

“ቤትሽ ከመንገድ ዳር መውጫ መውረጃዬ፣

ድምጽሽን ስሰማ ወደቀ ዱላዬ።”

የሚለውን ያዝማሪው ወረቀትን ዘፈን ነበር” አለች ግንፍሌ ድልድይ አይዳ ሕንጻ ስንደርስ መኪናዋን አቁማ እየወረደች። ግራ በመጋባት የሚቃብዘው ዓይኔ እግሬን ተከትሎ ከአንድ ጠባብ ቢሮ ሲዘልቅ ግን ጉድ ያልኩትን ትንግርት ተመለከትኩ። ፈጥኜ የክፍሉን ዙሪያ ገባ ቃኘሁት፡፡ እንደክራንች፣ ዊልቸር የመሳሰሉ የተለያዩ የአካል ድጋፍ መሣሪያዎች፣ የመማሪያ ቁሳቁሶችና ለዓይነስውራን የሚሆኑ እንደብሬል ኳስ፣ ካርታ፣ ዶሚኖስ፣ ቼዝና ሌሎችም ሸልፉን ሞልተውታል፡፡ ከቅኝቴ መለስ ብዬ ‹‹በማን ብርታት ሊቋቋም በቃ?›› ስል ጠየኳት፡፡

“ከገቢ አንጻር እዚህ ግባ የማይባል ትርፍ ቢሆንም ባለቤቴ አበበ ሞላ በሕይወት እያለ በሁሉም መስክ የአካል ጉዳተኞችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉና ጥገኝነትን የሚቀንሱ ውስን ቴክኖሎጂዎችን ያስመጣ ነበር፡፡ በጊዜው ከሽያጭ ባለፈ ለበርካቶች ድጋፍ አድርጓል። ሥራውን እኔ ባስቀጥለውም በፈለግነው ልክ ግን መራመድ አልቻለም”

ምን እንቅፋት ገጠማችሁ? አልኳት በማስከተል። ለመልሱ አልዘገየችም፡፡“የአካል ድጋፍ መሣሪያዎችና የመማሪያ ቁሳቁሶች የቅንጦት እቃ አይደሉምና እንደ መኪናው ሁሉ ከቀረጥ ነጻ ቢደረጉ ለብዙዎች ተደራሽ ማድረግ ይቻላል፤ ለምሳሌ ለዓይነስውራን የትምህርት ተቋማት የብሬል መጽሐፍት ሲገዙላቸው የተማሪዎቹን በጀታቸውንና መብታቸውን የማክበር ግዴታቸው እንደሆነ ሳይሆን በአብዛኛው እንደጽድቅ ቆጥረው ነውና ምስጋና ጠባቂዎች ናቸው። ግንዛቤ እንዲጨብጡ ሃሳቡን ስናካፍላቸው ደግሞ ለራሳችን ገበያ ስንል የሚመስላቸው ጥቂቶች አይደሉም”

ተማሪዎችን ተዟዙሬ ሳናግር መረዳት እንደቻልኩት የውጭ ምንዛሪ ባሻቀበ ቁጥር የዕቃዎችም ዋጋ ሰማይ ይነካልና ‹‹የተገልጋዮችን አቅም በምን ስሌት ከግምት ውስጥ ታስገባላችሁ?›› ስል ጥያቄ ሰነዘርኩላት። ብሩህ ተስፋ ገጿን እያፈካው በሀገር ውስጥ ምርቶች ለመተካት የተጀመሩ ጥረቶች እንዳሉና ለወደፊትም በስፋት ለማምረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትስስር መፍጠራቸውን ገለጸችልኝ። በመጨረሻም ‹‹የቴክኖሎጂ ውጤቶች የኑሮ ዘይቤያችንን ያቀላሉና አካል ጉዳተኞች ከተኖረው ይልቅ ያልተኖረው ሊናፍቃቸው ስለሚገባ በለውጥ ሂደት ዘመኑን ሊዋጁ ይገባል›› ስትል ምክረ ሃሳብ ለገሰችኝ፡፡ እኔም ስለቆይታችን አመስግኜ በስንብት ተለያየን፡፡

በሃብታሙ ባንታየሁ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You