እአአ 2019 ግንቦት ወር ከሚካሄደው የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ሁለት ወር በፊት የአፍሪካ ብሄራዊ ሸንጎ ፓርቲ አባልና የአሁኑ ጉቴንጅ አስተዳዳሪ ዴቪድ ካሁራ ‹‹እኔ እንደማስበው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት በተወሰኑ ቡድኖች ተደርጓል። በጥቃቱም የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች ተሳትፈዋል።›› ብለዋል። ማንኛውም የፖለቲካ ስልጣን ያለው ሰው የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ላይ ቅሬታ የሚያቀርብ ሲሆን ስደተኞቹ ወንጀል እንደሚሰሩና ህግ እንደማያከብሩ ይገለፃል። ይሄም ጉዳይ በሁሉም ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ይታያል። በዚህ አስተሳብ ምክንያት ላለፉት ዓመታት ስደተኞች ተገድለዋል።
እአአ 2008 ላይ ‹‹ዜኖፎቢክ›› በሚል መፈክር በተደረገ ነውጥ ከ60 በላይ ስደተኞች ተገድለዋል። በወቅቱ የነበረው ሰብዓዊ መብት ጥሰት የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናትን በሃሳብ ለሁለት የከፈለ ሲሆን ድርጊቱን የሚቃወሙና የሚተባበሩ ባለስልጣናት እንዲፈጠሩ አድርጓል። ከዚያ በኋላ በአገሪቱ ከውጭ የመጡ ስደተኞች ላይ በመደበኛነት ጥቃት ማድረስ ተጀመረ። በቅርብ ወራት በተደረጉ ህዝባዊ አመፆች በውጭ ስደተኞች ሱቆችና ቤቶች የወደሙ ሲሆን ሶስት ሰዎችም ተገድለዋል።
በደቡብ አፍሪካ እአአ ግንቦት 8 /2019 ላይ አጠቃላይ ምርጫ ይደረጋል። በምርጫው የሚሳተፉት ገዥው ፓርቲ አፍሪካ ብሄራዊ ሸንጎ ፓርቲና ዋነኛ ተቀናቃኙ የዴሞክራሲ ጥምረት ፓርቲ የፀረ ስደተኛ አቋማቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የተጠቀሙትን አይነት ንግግር በደቡብ አፍሪካም ተስተውሏል። ‹‹ስደተኞች ወንጀለኞች ናቸው። በአገሪቱ ያለውን ሀብት ከነዋሪዎቹ ነጥቀው እየወሰዱ ነው።›› የሚሉ ቅስቀሳዎች እየተደመጡ ይገኛሉ።
የአፍሪካ ብሄራዊ ሸንጎ ፓርቲ ለደጋፊዎቹ በህገወጥ ስደተኞች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ ቃል ገብቷል። በተያያዘም የዴሞክራት ብብር ፓርቲም በስደተኞች ጉዳይ ያለውን ችግር እንደሚፈታ ተናግሯል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለደቡብ አፍሪካ ስደተኞች ዋነኛ ችግር ነው የሚለው አጠያያቂ ጉዳይ ሆኗል። በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ሁለት ሚሊዮን ስደተኞች ውስጥ የአደገኛ እፅ አዘዋዋሪዎች፣ የሰዎች ንብረት ጠላፊዎች፣ መኪና ሰራቂዎች፣ ገዳዮች፣ ደፋሪዎች እና ነጣቂዎች ይገኛሉ። በማንኛውም የወንጀል ዝርዝር ውስጥ ስደተኞች የሚገኙ ቢሆንም ደቡብ አፍሪካውያን በመፍራትና በመናደድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀም የለበትም።
በሌላ በኩል ህግ በሚጥሱ ስደተኞች የመኖሪያ ፈቃድ ይኑራቸው አይኑራቸው አይታወቅም። የውጭ አገራት ወንጀለኞች ሆን ብለው ፖለቲካው ላይ ጫና ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ ነው የሚል መረጃ አለ። በተለያዩ ምክንያት ከአገራቸው ተሰደው ደቡብ አፍሪካ የመጡ ስደተኞች ወንጀል ስራ ላይ ተሰማርተው ማየት አስደንጋጭ ጉዳይ ነው። እውነታው ግን አብዛኛው ስደተኛ በወንጀል ስራ ላይ የተሰማራ አለመሆኑ ነው። እአአ 2017 ደቡበ አፍሪካ የፀጥታ ጉዳዮች ጥናት ኢንስትቲዩት ባደረገው ጥናት አብዛኛው በወንጀል ስራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘው ዜጋ ደቡብ አፍሪካውያን እንጂ ስደተኞች አለመሆናቸውን አስቀምጧል። በተጨማሪም ኢንስትቲዩቱ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ላይ አዋጆችን በማውጣት ‹‹ዜኖፎቢክ›› አስተሳሰብ እንዲፈጠር በማድረግ በስደተኞች ላይ ሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲመጣ እየሰሩ እንዳለም በጥናቱ አስቀምጧል።
በአሁኑ ወቅት በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ሰዎች ውስጥ ሰባት ነጥብ አምስት በመቶው የውጭ ዜጎች ናቸው። እንደ አገሪቱ ስታስቲክስ መረጃ ደግሞ እአአ 2011 በተደረገ የህዝብ ቆጠራ አራት ነጥብ ሁለት በመቶ ከውጭ አገራት ከመጡ የተወለዱ ናቸው። በአገሪቱ ስደተኞች በፖሊስ የመያዝ ከፍተኛ እድል አላቸው ምክንያቱም ሆን ተብሎ ስደተኞችን የመያዝ እንቅስቃሴ በመኖሩ ነው። ነገር ግን ስደተኞቹ ወንጀለኛ ስለመሆናቸው የሚቀርብ ማስረጃ የለም። የሌሎችን ችግር በስደተኞች ላይ በመለጠፍ በአገሪቱ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ባልተገኙ መረጃዎች ሊከሰሱ ይችላሉ።
እንደ ማኩራ እና መሰሎቹ እንደሚሉት ስደተኞች የአገሪቱን የጤና መድህን ማግኘት የለባቸውም ብለው ይከራከራሉ። በአገሪቱ በማንኛውም መስክ የተሰማሩ ስደተኞች ግብር ይከፍላሉ። የሚከፍሉት ግብር ደግሞ ለጤና መድህን ዋስትና ሆኖ ሊያገለግላቸው ይገባል። በሥርዓቱ አስፈላጊ ነገሮች ባይሟሉም ስደተኞቹ እየከፈሉ ይገኛሉ። በፕሪቶሪያ የሚገኘው ሆስፒታል ከማንኛውም አገር መጥቶ በአገሪቱ የሚኖረውን ዜጋ በእኩል መንፈስ እያገለገሉ ይገኛሉ። በክልሎች ስር የሚገኙ ሆስፒታሎች በስደተኞች ምክንያት ከመንግስት ድጋፍ አይደረግላቸውም። በሌላ በኩል የተሟላ ዶክመንት ያላቸው ስደተኞች በነፃ የህክምና ሽፋን የማግኘት መብት ቢኖራቸውም በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ሆስፒታሎች እንዲታከሙ አይፈቀድላቸውም። በአገሪቱ የጤና አሰጣጡ ችግር ውስጥ የገባው በአወቃቀር ችግር በተለይ የአስተዳደር ችግርና ለጤና የተመደበውን ገንዘብ ለሌላ ዘርፍ የማዋል ልማዶች በመኖራቸው ነው።
አንዳንድ ስደተኞች ሰርተው ከሚያገኙት ገንዘብ ግብር አይከፍሉም። ይህ ጉዳይ ግን ስደተኞችን የሚመለከት ሳይሆን የአገሪቱን ህግ የሚያስፈፅሙ አካላት ችግር ነው። በማኛውም መንገድ ግብር በስደተኞች እየተከፈለ ባይሆንም በአገሪቱ ኮርፖሬሽንና የንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶች በአግባቡ ግብር እየከፈሉ አለመሆኑ ጋር እኩል አይወዳደርም። በቅርብ በተሰራ ጥናት 98 በመቶ የግብር ቅሸባ የሚደረገው ከፍተኛ ትርፍ ከሚያገኙ ባለሀብቶች ነው። ባለሀብቶቹ 10 በመቶ የአገሪቱን ኮርፖሬት ድርጅቶች የሚያስተዳድሩ ናቸው።
በተመሳሳይ በአገሪቱ የስራ እጥነት ቁጥር እየጨመረ የመጣው በስደተኞች ምክንያት አይደለም። ስደተኞች ብዙ ጊዜ የሚሰሩት አነስተኛ ክፍያ ያለውና በአገሪቱ ዜጎች የማይፈለጉ ስራዎች ሲሆን ይህ የአገሪቱን ኢኮኖሚ የሚገድብ አደለም። ስደተኞች በሚከፈላቸው ዝቅተኛ ደመወዝ አማረው አያውቁም። የሚገኙበት አስከፊ ሁኔታ የሚሰሩበትን የማይመች የስራ እንቅስቃሴና ዝቅተኛ ደመወዝ ሳይወዱ በግድ እንዲቀበሉት አድርጓቸዋል። የተመቻቸ የስራ ሁኔታ በሁሉም ዘርፎች መፍጠር የአገሪቱ ግዴታ ነው። በዚህ ሁኔታ ትልቁን ነገር ሲታይ ስር የሰደደ ድህነት፣ ደካማ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ያላደገ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እና የቤት እጥረትና ከፍተኛ የሆነ የወንጀለኞች ቁጥር መበራከት ባለበት በደቡብ አፍሪካ ስደተኞች ትልቅ ችግር አለመሆናቸው ይታያል።
ነገር ግን ዋናው ጉዳይ መሆን ያለበት ባለፉት 25 ዓመታት ህዝቡን ሲያስጨንቁ የነበሩትን ጉዳዮች ለመፍታት የአገሪቱ የፖለቲካ ባስልጣናት ምንም አይነት ስራ አለማከናወናቸው ነው። በምርጫ ወቅቶችም ቃል ሲገቡ የነበሩ ስራዎች እስካሁን አልተሰሩም። በደቡብ አፍሪካ የዜኖፎቢክ አስተሳሰቦችን ለመቀነስ ከመስራት ይልቅ ጭራሽ የሚያባብሱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል። ይህም የፖለቲካ መልክ ይዞ የሚሰራ ነገር ነው። በአገሪቱ ለተፈጠሩ ማኛውም መጥፎ ስራዎች ስደተኞችን ተጠያቂ ማድረግ አሁንም የአገሪቱ ፖለቲከኞች ለምርጫ ቅስቀሳ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በዚህ ቅስቀሳም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጠሩ ሲሆን በሚደረጉ የቅስቀሳ መልዕክቶች ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ስደተኞች እየተጎዱ ይገኛሉ። አሁን መሬት ላይ ያለው ሁኔታ ዶክመንት የሌላቸው ስደተኞች ግብር እንደማይከፍሉና ያለ ፈቃድ ንግድ እየሰሩ እንደሚገኙ ነው። በዚህም ብዙ ሱቅ ያላቸው ስደተኞች በየዓመቱ እየተገደሉ ነው። ወደ እአአ 2008 ብንመለስ ዜኖፎቢክ ላይ የተመሰረተ ነውጥ ከተካሄደ በኋላ የወቅቱ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ በተፈጠረው ሁኔታ በወቅቱ የነበረውን ፖሊሲ ተችተው ነበር። አሁን፤ ከአስራ አንድ አመት በኋላ ሁኔታው ያቆመ አይመስልም።
እአአ 2014 በነበረው ጥቃት በብዛት ሰለባ የሆኑት የኢትዮጵያ፣ ሶማሌ፣ ናይጄሪያ፣ ሞዛምቢክ፣ ዝምባቡዌ እና የማላዊ ዜጎች ሲሆኑ ከተገደሉት መካከልም ሶስቱ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። በጥቃቱ ምክንያት ኬንያ፣ ማላዊ እና ዙምባቡዌ ወዲያውኑ ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ ለማስወጣት የሞከሩ ሲሆን፤ በተለይ ዙምባቡዌ እና ቦትስዋና ዜጎቻቸው በሰላም እስኪወጡ ድረስ ከጥቃቱ ለመከላከል ልዩ የጦር ኃይል ወደ ስፍራው መላካቸው ይታወሳል። ሞዛምቢክ በበኩሏ ዜጎቿና የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሌሎች ጥቁር አፍሪካውያንን ለመታደግ ድንበሯን የከፈተች ሲሆን፤ ጥቃቱ ወዳለበት ስፍራ ድረስ በመሄድ ዜጎቿን ለመታደግ ትራስፖርትና ሌሎች አስፈላጊው የሆኑትን ሁሉ አቅርባለች።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011
መርድ ክፍሉ