የትራምፕ አስተዳደር የዩክሬን ልዩ መልዕክተኛ በሩሲያ ጉብኝት ሊያደርጉ ነው

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን እና የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ኪት ኬሎግ በሚቀጥለው ወር ኪቭን ከጎበኙ በኋላ ወደ ሞስኮ ለመጓዝ ማቀዳቸውን ብሉምበርግ ጉዳዩን የሚያውቅ ምንጭ በመጥቀስ ዘግቧል። ምንም እንኳን እቅዱ በውሳኔ ደረጃ ባይጎለብትም ኬሎግ ወደ ሩሲያ የሚያቀኑ ከሆነ የተለየ ፖሊሲ ማስተግበር ላይ ከማተኮር ይልቅ በሞስኮ በኩል የሚነሱ ሃሳቦችን መረጃ በማሰባሰብ ላይ ሊያተኩሩ እንደሚችል ተገልጿል::

ልዩ መልዕክተኛው ወደ ምስራቅ አውሮፓ ከመጓዛቸው በፊት ወደ ለንደን ፣ ፓሪስ እና ሮም በማቅናት በአካባቢው ሁኔታ ዙርያ ከከፍተኛ አመራሮች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል:: በመጀመሪያው የትራምፕ የሥልጣን ዘመን በብሔራዊ ደህንነት ሚናዎች ላይ ያገለገሉት ጡረተኛው ጄኔራል፤ በሞስኮ እና በኪየቭ መካከል የሰላም ስምምነትን ለማደራደር በመሞከር የወደፊቱ አስተዳደር ቁልፍ ሰው ሆኖው ባለፈው ወር ተሹመዋል::

በብሉምበርግ ዘገባ መሠረት ኬሎግ እና ሌላው የቀድሞ የትራምፕ አማካሪ ፍሬድ ፍሊትዝ ሩሲያ ለተቆጣጠረቻቸው ቦታዎች እውቅና ሳይሰጥ አሁን ባለበት ሁኔታ ግጭቱ እንዲቆም የድርድር ሃሳብ ለፕሬዚዳንቱ ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል:: ከዚህ ባለፈም ሁለቱ በዩክሬን ሩሲያ ጦርነት ዙርያ በቅርበት እየሠሩ የሚገኙ አካላት ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም የዩክሬንን የኔቶ አባልነት ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ማዘግየት እንደሚገባ ምክራቸውን መለገሳቸው ተሰምቷል::

በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ጦርነቱን በ24 ሰአት አስቆማለሁ ሲሉ የተደመጡት ትራምፕ ለዩክሬን የሚደረግ ወታደራዊ ድጋፍን በመያዣነት በማቅረብ ኪየቭ ወደ ድርድሩ እንድትቀርብ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችል የዲፕሎማሲ ተንታኞች ያነሳሉ::

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዩክሬን እና የሩሲያ ልዩ መልዕክተኛ ኪት ኬሎግ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ደም አፋሳሹን ጦርነት ሊያስቆሙ እንደሚችሉ፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን እና የዩክሬኑ አቻቸውን ዘለንስኪን በበዓለ ሲመታቸው ላይ እንዲታደሙ ግብዣ ሊያቀርቡ እንደሚችሉም ተናግረዋል:: ትራምፕ እራሳቸው ጦርነቱን በማስቆም ዙርያ ከዘለንስኪ እና ፑቲን ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል::

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፑቲን ተመራጩ ፕሬዚዳንት የዩክሬንን ግጭት በማስቆም ላይ የሰጡት መግለጫ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን በመጥቀስ ትራምፕን ለማነጋገርም ሆነ አስቀድመው ስልክ ለመደወል እንደማይከብዳቸው ተናግረዋል። ነገር ግን ዩክሬን በዘላቂነት የኔቶ አባል እንደማትሆን ማረጋገጫ ማግኘት እና ሩሲያ አሁን የተቆጣጠረቻቸውን ክልሎች እውቅና እንዲሰጥ ክሪምሊን ያስቀመጠውን ቅድመ ሁኔታ አሁንም አልቀየረም:: ፕሬዚዳንት ፑቲን እና የዩክሬኑ አቻቸው በትራምፕ በዓለ ሲመት ላይ እንዲታደሙ ሊጋበዙ እንደሚችሉም ተነግሯል ሲል አል ዐይን ዘግቧል::

አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You