ዶሮና እንቁላል በመስረቁ ለ10 ዓመታት ታስሮ የሞት ቅጣት ሲጠባበቅ የነበረው ናይጄሪያዊ ይቅርታ ሊደረግለት እንደሚችል ተገለጸ። የናይጄሪያ ደቡብ ምዕራብ ግዛት ኦሳን ሀገረ ገዢ ይቅርታ ለማድረግ ቃል እንደገቡለት ተገልጿል። እአአ በ2010 ሴጉን ኦሎዎክሬ የ17 ዓመት ወጣት ሳለ በስርቆት የታሰረው በድርጊቱ ተሳትፏል ከተባለው ሞራክዩ ሰንደይ ጋር ነበር። የፖሊስ ኃላፊ ቤት ላይ ጥቃት አድርሰዋል ተብለዋል። ሌላንም ሰው ከእንጨት በተሠራ ሽጉጥ በማስፈራራት ዶሮና እንቁላል ሰርቀዋል።
በ2014 የኦሱን ግዛት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ጂድ ፋሎላ ሁለቱንም ታንቀው እንዲሞቱ ፈርደውባቸዋል። የፖሊስ ኃላፊ ቤት በመዝረፍ ጥፋተኛ ተብለዋል። የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በጣም የከፋ ነው በሚል ከሕዝቡ ቅሬታ ተሰምቷል። ሁለቱም እስረኞች ሌጎስ ወደሚገኘውና ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግለት ኪሪኪሪ ማረሚያ ቤት ተወስደው የሞት ፍርድ እየተጠባበቁ ነበር።
ሀገረ ገዢው አድሞላ አድሌኬ የሰው ሕይወት ዋጋ ስላለው ለ10 ዓመታት የሞት ቅጣት ሲጠባበቅ የነበረው ሴጉን ኦሎዎክሬ ይቅርታ ሊደረግለት ይገባል ብለዋል። “የፍትሕ ሚኒስትር ለዚህ ወጣት የይቅርታ ሂደት እንዲጀምሩ ትዕዛዝ ሰጥቻለሁ። ኦሱን የፍትሕና እኩልነት ግዛት ነው። ፍትሐዊነትንና የሕይወት ዋጋን ማክበር አለብን” ብለዋል።
ሌላኛው በእስር ላይ ያለው ሞራክዩ ሰንደይ እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ እስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይቅርታ ይደረግለታል የተባለው ሴጉን ኦሎዎክሬ ቤተሰቦችና የሠብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለዓመታት ከእስር እንዲለቀቅ ሲጠይቁ ነበር። ብቸኛ ልጃቸው እንዲለቀቅ እያለቀሱ ወላጆቹ ሲጠይቁ በቅርቡ በአንድ ፖድካስት ላይ ተደምጠዋል። በ2025 ይለቀቃል ተብሎም ይጠበቃል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
አዲስ ዘመን ዓርብ ታኅሣሥ 11 ቀን 2017 ዓ.ም