የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከሚያስገነባቸው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መካከል አንዱ የጃንሜዳ ጂምናዚየም ነው። ይህ ጅምናዚየም በጃንሜዳ መከናወኑም፣ ጃንሜዳ፣ የከተማዋን ነዋሪዎች በስፖርታዊ እንቅስቃሴ ከሚያሳትፉ ቦታዎች ዋነኛው እንደመሆኑ ግንባታው ተጨማሪ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ ስለታመነበት ነበር። ነገር ግን በዚህ ወቅት ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተቋርጦ ባለበት ቆሟል። «ግንባታው በምን ምክንያት ተቋረጠ?» በሚለው ላይም አዲስ ዘመን ጋዜጣ የሚመለከታቸውን አካላት አናግሮ በዛሬው እትሙ እንደሚከተለው አሰናድቷል።
አቶ ማቲዎስ ኦልቀባ፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክተር ተወካይ ናቸው። ሰኔ 10 ቀን 2005 ዓ.ም ቢሮው ለጂምናዚየሙ ግንባታው ውለታ ሲገባ በ540 ቀናት (ታህሳስ 9 ቀን 2007 ዓ.ም) ይጠናቀቃል በሚል ነበር። ይሁን እንጂ ከግንባታው መጓተት ባለፈ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ስራው ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት እለት ድረስ ግንባታው በጅምር ቀርቷል፡፡ ለግንባታው መቋረጥ ምክንያት የሚሆነውም የመዋቅር ስራው ሙሉ ለሙሉ ከተጠናቀቀ በኋላ ጣሪያ ለማልበስ የማይቻል በመሆኑ ነው። ግንባታው በዚህ መልክ ከመቋረጡ አስቀድሞ የጂምናዚየሙ ዲዛይን በተዘጋጀው መልኩ ለመገንባት መሰረቱ ስለማይችል ባለ አንድ ፎቅ መሆኑ እንዲቀር መደረጉንም ተወካዩ ያስታውሳሉ።
እንደ አቶ ማቲዎስ ማብራሪያ፤ ዲዛይኑ እንዲስተካከል ከተደረገ በኃላ በድጋሚ ወደ ግንባታ የተገባ ቢሆንም፤ ጣሪያውን የሚይዙት ምሰሶዎች ላይ ሌላ ችግር መኖሩን ተቋራጩ አስታወቀ። ለሁለተኛ ጊዜም ዮሃንስ አባይ የተባለው አማካሪ ድርጅት ዲዛይኑን ማስተካከል እንዳለበት በተቋራጩ ጥያቄ በመቅረቡ፣ የማጣራት ስራው ለሶስተኛ አካል ሊሰጥ ችሏል። በማጣራቱ ላይ የተሳተፈው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ችግሩ መኖሩን በደብዳቤ በማረጋገጡና አማካሪውም በማመኑ በድጋሚ ማሻሻያ ለማድረግ ተስማማ። በዚሁ መሰረት አማካሪው ድርጅት ማሻሻያ ያደረገበት ዲዛይንም 10 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ወጪ የሚጠይቅ ነበር።
የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክቶሬትም የገንዘቡን መጠን ለፋይናንስ ቢያሳውቅም ፍቃደኛ አልነበረም። የመንግስት ግንባታን በበላይነት የሚከታተለው የአዲስ አበባ ኮንስትራክሽን ቢሮም ይህ ሊሆን እንደማይችል አቋም አሳየ። የስራ ተቋራጩም በበኩሉ በተሻሻለው ዲዛይን የቀረበው ጥሬ ዕቃ ውድ በመሆኑ በዚህን ያህል ዋጋ ግንባታውን ሊያከናውን እንደማይችል አሳወቀ። በእነዚህ ምክንያቶችም የኮንስትራክሽን ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ውሉ ተቋርጦ በጃንሜዳ የተጀመረው ጂምናዚየም ግንባታ ላለፉት ስድስት ዓመታት ከሚጠበቅበት የጥራትና የአፈጻጸም ደረጃ በታች ሆኖ የቆየው ሥራ ባለበት ሊቆም ተወስኖበታል።
ግንባታው እዚህ ደረጃ ከመድረሱ አስቀድሞ ዲዛይኑ ችግር እንዳለበት ተቋራጩ እንዲሁም ተቆጣጣሪ መሃንዲሶች በደብዳቤ ሲያሳውቁ እንደነበር ተወካዩ ያስታውሳሉ። በዚሁ ምክንያትም ባለ አንድ ፎቅ መሆኑ ቀርቷል፡፡ በዚህም ቢሮው ከመስማማት በቀር አማካሪውን ተጠያቂ የማድረግ ስራ አላከናወነም ነበር። አሁን ግን ዲዛይኑ ችግር እንዳለበት አማካሪው በማመኑ ለደረሰው ኪሳራ ኃላፊነቱን ይወስዳል። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ላደረገው ማጣራትም 200ሺ ብር ከአማካሪው እንዲከፈለው የሚያደርግ ውሳኔም ተላልፎበታል።
ከዚህ ባሻገር ከላይ ሆኖ ስራውን የሚቆጣጠረው መንግስታዊው አካል ጣልቃ ገብቶ ችግር መኖሩን፤ በዚሁ ምክንያትም መዘግየት መፈጠሩን ለቢሮው አለማሳወቁም በክፍተትነት እንደሚታይ ተወካዩ ይገልጻሉ። ቢሮው ለደረሰበት የገንዘብ፣ የጊዜ እና ሌሎችም ኪሳራዎች አማካሪውን በህግ ተጠያቂ ለማድረግ የኮንስትራክሽን ቢሮው የኮንስትራክሽን ህጉን ማጣቀስ ስለሚገባው በእነርሱ በኩል የሚከናወን ይሆናል።
ስለ ግንባታው ግንባታውን በበላይነት የሚቆጣጠረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽን ቢሮ በባለሙያዎች (መሃንዲሶች) የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በቢሮው የሳይት ሱፐርቫይዘር ታደለ ደንደና፤ ሁለተኛ የዲዛይን ማሻሻያ በተደረገበት ወቅት (2008 ዓ.ም) ወደ ስራ እንደገባ ይገልጻል። በወቅቱ ተቋራጩ ችግር መኖሩን ቢያሳውቅም አማካሪው ሊቀበል ባለመቻሉ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንዲያጣራ መደረጉን ያስታውሳል። በዲዛይኑ ላይ ችግር መኖሩ ከተረጋገጠ በኃላም ተቋራጩ ውሉ እንዲቋረጥ በ2009 ዓ.ም በጠየቀው መሰረት በ2010 ዓ.ም ግንባታው እንደቆመ ያረጋግጣል።
በቢሮው የውለታ አስተዳደር ባለሙያ መቆያ አለማየሁ በበኩሉ፤ በከተማዋ ያሉ የመንግስት ግንባታዎችን በበላይነት የሚቆጣጠረው ኮንስትራክሽን ቢሮው ቢሆንም፤ ከአቅሙ በላይ የሆኑ ስራዎችን ግን ለሌሎች አማካሪዎች እንደሚሰጥ ያስረዳል። በዚህ መሰረትም የጃንሜዳ ጂምናዚየም ግንባታ በበርካታ ፕሮጀክቶች ላይ እየተሳተፈ ላለው ዮሃንስ አባይ ለተባለ አማካሪ ድርጅት በጨረታ ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ ወደ ስራው ከተገባ በኋላ ግን የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋል፤ ተቋራጩም ውሉ ይቋረጥልኝ ሲል ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ግንባታው 54 በመቶ ላይ እያለ ሊቋረጥ እንደቻለም ባለሙያው ያስረዳል።
ዲዛይን በባህሪው ሙሉ ሊባል የማይችልና በየጊዜው ሊሻሻል የሚችል ሲሆን፤ በመጀመሪያ ያጋጠመውም ትንንሽ ማሻሻያ ሊባሉ ከሚችሉት የሚመደብ ነበር። ከዚያ በኋላ ያለውና ፕሮጀክቱንም ያስቆመው ትልቁ ምክንያትም የቆሙት ምሰሶዎች ጣሪያውን መሸከም ስላልቻሉ ነው። ተቋራጩ በአማካሪው ችግር ፕሮጀክቱ ላይ አንድ ነገር ቢደርስ ተጠያቂ ስለሚሆን፣ ባለቤትንም ካሳ መጠየቅ ስለሚችል፤ እንዲሁም ከአማካሪው ጋር አለመግባባት ውስጥ በመግባቱ በስምምነት ውሉ እንዲቋረጥ ባለቤትን በመጠየቅ መቋረጡንም ባለሙያው ይገልጻል።
እስካሁን ለደረሰው ብክነትም በዋናነት ተጠያቂ የሚሆነው አማካሪው ቢሆንም፤ ለተጓተተው ጊዜ ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተጋሪ ይሆናሉ። በዚህ መሰረትም ኮንስትራክሽን ቢሮው አማካሪው መቀጣት ይኖርበታል ከሚል ውሳኔ ላይ ደርሶ ለባለቤቱ ደብዳቤ ጽፏል። ከገንዘብና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የደረሰበትን ተከታትሎ የሚያስቀጣውም ባለቤት መሆኑን ይጠቁማል።
ውስብስብ ችግሮች ካሉባቸው ፕሮጀክቶች መካከል ከራስ ኃይሉ ስፖርት ማዕከል ቀጥሎ የጃንሜዳ ጂምናዚየም መሆኑን የሚጠቅሰው ደግሞ፤ የስፖርት ፕሮጀክቶች ተባባሪ መሃንዲስ ፍቃዱ አለሙ ነው። ቢሮው ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቱ ይቋረጥ በሚል ሃሳቡን ቢያሳውቅም ባለቤት ግን ባለው ይቀጥል የሚል ምላሽ መስጠቱንም ይጠቁማል።
በዚህ ሃሳብ የማይስማሙት ተወካዩ አቶ ማቲዎስ በበኩላቸው፤ ቢሮው ውል የማቋረጥ ኃላፊነት እንደሌለውና ይህ ስራ የሚመለከተውም ኮንስትራክሽን ቢሮውን መሆኑን ነው የሚጠቅሱት። ግንባታውን የመከታተል ስራ የኮንስትራክሽን ቢሮ እንደመሆኑ ውሉን አቋርጦ ለቢሮው ማሳወቅ ይችል እንደነበርና ውሉ ይቋረጥ በሚል በቅድሚያ ደብዳቤ የጻፈውም ቢሆን ተቋራጩ መሆኑን ይገልጻሉ። ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከዲዛይን ጋር በተያያዘ የአማካሪ ድርጅቱ ውል ይቋረጥ የሚል ደብዳቤ ከኮንስትራክሽን ቢሮ ለስፖርት ቢሮ መጻፉን አልሸሸጉም። የቢሮው ምላሽም እስካሁን ለደረሰው ነገር ተጠያቂ ይሁን የሚል እንደነበርና ከዚያ በኋላ ኮንስትራክሽን ቢሮው ተመልሶ ወደ ድርድር መግባቱንም ያስታውሳሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በጂምናዚየሙ መዘግየት፤ የጊዜ፣ የገንዘብና የጥራት ብክነት ደርሶበታል። ተወካዩ ይህንን ሲያብራሩም ጊዜው በጨመረ ቁጥር ገንዘቡም በዚያው ልክ የሚጨምር ይሆናል። በወቅቱ ውል የተገባው በ48 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፤ እስካሁን ለመዋቅር ስራው ብቻ 36 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል። አሁን ላለበት ደረጃ ከ50 በመቶ በላይ መውጣቱም ቢሮውን ተጎጂ ያደርገዋል። ግንባታው በጥራት ሳይሰራ ቢጠናቀቅ ኖሮም የሰውን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ኪሳራ ያደርስ ነበር።
ሆኖም ጃንሜዳ እንደሚታወቀው በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አካላዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ቦታ እንደመሆኑ ጂምናዚየሙ በጉጉት የሚጠበቅ ነበር። ነገር ግን ቦታው ለህብረተሰቡ ግልጋሎት ሳይውል፤ ግንባታውም ሳይጠናቀቅ ዓመታትን ማስቆጠሩ ማህበራዊ ጉዳትና ኪሳራ አስከትሏል። በዚህ ግንባታ ምክንያትም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ ሊደርስ ችሏል።
ኮንስትራክሽን ቢሮ ባለቤትን ወክሎ የሚሰራ እንደመሆኑ ፕሮጀክቱ በተያዘለት ጊዜ ተገንብቶ ባለመጠናቀቁ፤ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እንዲሁም ከሃገራዊ ገጽታ አንጻር ችግር ማስከተሉን የፕሮጀክት አስተባባሪው ያመላክታል። እንደ ኮንስትራክሽን ቢሮም ለከተማዋ የተሻለ ገጽታ በማላበስ ረገድ የተሰጠውን ኃላፊነት በተወሰነ መልኩ ይቀንሳል። አማካሪው ላደረሰው ኪሳራም በህጉ መሰረት እስከ ሁለት ሚሊዮን ብር እንዲቀጣ ተወስኖበት ለባለቤት ተላልፏል። ከዚህ በኃላም መሰል ጥፋት እንዳይደርስ አማካሪዎች ምን ሰርተዋል የሚለውን በቴክኖሎጂ አስደግፎ ለመስራትና ተቋራጩ ደረጃ አንድ እንዲሆን መወሰኑንም ያክላል።
ግንባታውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ኮንስትራክሽን ቢሮ ለከተማው ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሂደቱን በማሳመን ውሉን ካቋረጠ በኃላም ቀሪ ስራዎች ተለቅመው ወደ ስራ እንዲገባ ተወስኗል። በዚህም መሰረት የማዘውተሪያ ስፍራዎች ዳይሬክቶሬት ፋይናንስን የጠየቀ ሲሆን፤ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ተጠንቶና ውስን ጨረታ ተደርጎ ወደ ስራ ይግባ በሚል መፍቀዱን ተወካዩ አቶ ማቲዎስ ያስረዳሉ። ይህንንም ለኮንስትራክሽን ቢሮ በማሳወቅ ቀሪ ስራዎችን ለቅመው እንዲያመጡ ተጠቁሟል። በመሃል የባለሙያዎች መቀያየር ስለነበር መዘግየት ቢኖርም በቅርቡ ይጨርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የውለታ አስተዳደር ባለሙያው በበኩሉ፣ አሁን ባለበት ሁኔታ ቀሪ ስራዎችን በመያዝ እንደ አዲስ ጨረታ የተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻል። ጨረታው የወጣውም ጣሪያውን በራሱ ዲዛይን አድርጎ መስራት የሚችል ነው፤ ይህም ከዚህ ቀደም ያጋጠመውን ጨምሮ በርካታ ጉዳዮችን ለማስቀረት ይችላል። በዚህም መሰረት በአዲስ ውለታ በቅርብ ጊዜ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ስራውም በ6 ወራት ይጠናቀቃል የሚል እቅድ ተይዟል።
ቢሮው አሁንም የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል፤ ከዚህ በኋላም በእቅድ የያዛቸው ግንባታዎች አሉ። በመሆኑም ተመሳሳይ የዲዛይንና ሌሎች ችግሮች እንዳይገጥሙት እንደ ባለቤት ምን ለመስራት አቅዷል በሚለው ላይም ተወካዩ እንዳሉት፤ ቁጥጥሩን ከስራው ጎን ለጎን እንዲሄድ ይደረጋል፤ ቢሮውን በባለሙያ በማጠናከር ላይ ይሰራል። ቢሮው ጥናት አድርጎ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ማሰቡም የተሻለ ስራ ለመስራት ያስችላል፡፡