በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ በሚያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 2023 በስፖርቱ ዓለም በርካታ ውድድሮችና ሁነቶችን ለማከናወን መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል። ዓመቱን ሙሉ ውድድር የሚካሄድበት አትሌቲክስ ደግሞ በዓለም አትሌቲክስ የወርቅ ደረጃ በተሰጠው የዚመን ማራቶን ሲጀመር፤ አህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ደግሞ ከቀጣዩ ወር አንስቶ ቀጥሎ የሚከናወኑ ይሆናል። በአትሌቲክስ ስፖርት ታዋቂ የሆነችው ኢትዮጵያም በዓመቱ የዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፎ ታደርጋለች በሚል ይጠበቃል።
የዓለም አትሌቲክስ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ከተጋፈጡ ስፖርቶች መካከል አንዱ ሲሆን፤ በርካታ ውድድሮችን ለማራዘምና ለመሰረዝ አስገዳጅ የሆነበትን ጊዜ አሳልፏል። በዚህም ምክንያት ስፖርቱን የሚመራው የዓለም አትሌቲክስ፤ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው ዓመት 2022 ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል። በጊዜ ሰሌዳው መሰረት ውድድሮችን ወደ ቀድሞ ቅርጻቸው ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት በአዲሱ ዓመትም እንደሚቀጥል ያብራሩት ደግሞ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ናቸው። በዓመቱ ከሶስት በላይ ታላላቅ ውድድሮች እንደሚከናወኑ የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፤ ያለፉት ሁለት ዓመታት ስፖርቱን በአዲስ መልክ የመንደፍ ያህል እንደነበረና አሁንም ጠንካራ ስራ እንደሚጠብቃቸውም ትራክ ኤንድ ፊልድ ኒውስ ለተባለው ድረገጽ ገልጸዋል።
በዓለም አትሌቲክስ በተያዘው መርሃ ግብር መሰረት መጪው የየካቲት ወር የዓለም ሀገር አቋራጭ ውድድር በአውስትራሊያ ለ44ኛ ጊዜ ይካሄዳል። ይህ ውድድር ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በግልና በቡድን ስኬታማ ከሆኑባቸው መካከል አንዱ ሲሆን፤ ጀግናው ቀነኒሳ በቀለ ደግሞ 6 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በግሉ በመሰብሰብ በውድድሩ ታሪክ ውጤታማ አትሌት ነው። ከሁለት ወር በኋላ በሚካሄደው ውድድር ላይም ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች የሚመረጡበት የጃንሜዳ ሀገር አቋራጭ ውድድር በመጪው እሁድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2015 ዓ.ም ይከናወናል።
በዓመቱ በተለይ ከሚጠበቁ ታላላቅ ስፖርታዊ ውድድሮች መካከል አንዱ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ነው። ከኦሊምፒክ እና ከዓለም እግር ኳስ ዋንጫ በመቀጠል ልዩ ትኩረት የሚሰጠውና በርካታ ሀገራት የሚሳተፉበት ይህ ቻምፒዮና ለመጀመሪያ ጊዜ በተከታታይ ዓመት (2022 እና 2023) ይደረጋል። ኦሊምፒክ ከመካሄዱ አንድ ዓመት አስቀድሞ እንዲሁም በተከታዩ ዓመት የሚደረገው ይህ ውድድር በዓለም አቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ 19 ምክንያት የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለአንድ ዓመት መራዘሙን ተከትሎ በተፈጠረ የመርሃ ግብር መደራረብ ቻምፒዮናው በወራት ልዩነት እንዲካሄድ አድርጎታል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ ሀገራት የሩጫ፣ የውርወራ እና የዝላይ ተወዳዳሪዎቻቸውን የሚያፎካክሩበት ይህ ውድድር ከወራት በፊት በአሜሪካዋ ኦሪጎን መከናወኑ የሚታወስ ነው።
እአአ በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ የሚደረግ በመሆኑም ቻምፒዮናው በዋዜማው በሃንጋሪዋ ከተማ ቡዳፔስት የሚከናወን ይሆናል። 200 የሚሆኑ ሀገራት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ኢትዮጵያ ሰፊ ተሳትፎ ሲኖራት፤ ከመድረኩ 29 የወርቅ፣ 30 የብር እና 26 የነሃስ በድምሩ 85 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በሰንጠረዡ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በኦሪጎን በተካሄደው ቻምፒዮና ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛ ሆና ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው። በመሆኑም በዚህ ውድድር ላይም በድጋሚ የሀገራቸውን ስም ለማስጠራት ሯጮቿን የምታሳትፍ ይሆናል።
ሌላኛው የዓመቱ ተጠባቂ ዓለም አቀፍ ውድድር ደግሞ የጎዳና ላይ ሩጫዎች ቻምፒዮና ነው። የግማሽ ማራቶን፣ 5ኪሎ ሜትር እና የአንድ ማይል ሩጫን የሚያጠቃልል ሲሆን፤ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝባዊ ሩጫንም እንደሚያካትት የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያሳያል። ውድድሩም በተረኛዋ የውድድሩ አዘጋጅ የላቲቪያ ዋና ከተማ ሪጋ ይደረጋል። እአአ በ2020 ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በግልና በቡድን አመርቂ ውጤት ያስመዘገቡበት ይህ ውድድር፤ በአዲሱ ዓመትም ድል የሚመዘገብበት ይሆናል በሚል ይጠበቃል።
ከቀናት በኋላ በሚገባው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የዓለም አትሌቲክስ ከሚመራቸው ውድድሮች ባሻገር፤ ዳይመንድ ሊግ፣ አህጉር አቀፍ የቱር ውድድሮች፣ የቤት ውስጥ ቱር እንዲሁም በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሚከናወኑ የማራቶንና ሌሎች የጎዳና ላይ ውድድሮች የሚቀጥልም ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20 ቀን 2015 ዓም