በመንግሥት በኩል ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተከናወኑ ካሉት አበይት ተግባራት መካከል አንዱ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መሆኑ ይታወቃል። ይህ እንቅስቃሴ በሚገባ ታስቦበት በሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲታገዝ ከተደረገ የቆየ ሲሆን ለዚህም ቁጥር 374/2008 “የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ” በሚል የፀደቀው የማቋቋሚያ ደንብ አንዱና ትልቁ ማሳያ ነው።
ምንም እንኳን መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም በተቻለ መጠን የሥራ ዕድል መፍጠርንና ዜጎችን፤ በተለይም ወጣቱን ተጠቃሚ ማድረግ የሚገባው መሆኑ የሚታወቅ ነው። ይህ ሲባል የሥራ ዕድል የመፍጠሩ ጉዳይ ችላ የተባለ ጉዳይ ነው ለማለት ሳይሆን በሚፈለገው ደረጃና ጊዜ እየተከናወነ ነው ወይ? የሚለው አነጋጋሪ ከመሆኑ አኳያ ነው። ይህ አነጋጋሪነቱም ተቀባይነት የሚኖረው “በኢትዮጵያ በየዓመቱ 600ሺ ወጣቶች ሥራ ፈላጊውን ማሕበረሰብ ይቀላቀላሉ” የሚለውን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት ጥናት ሲታሰብ ነው። የእነዚህ ሥራ አጦች ቁጥር ባሉት ላይ ተጨማሪ መሆኑ ሲታሰብ የችግሩ ግዝፈት ግዘፍ ነስቶ መታየት የግድ ነውና ደግሞ ደጋግሞ በጉዳዩ ላይ ማሰብ ይገባል።
በወጣቱ ዘንድ ሁሌም አንገብጋቢ ሆኖ የሚነሳውን የሥራ ፈላጊነት ጥያቄ መንግሥት በተቻለው አቅም ከማስተናገድ ቦዝኖ አያውቅም። ለዚህም የቅድሚያ ቅድሚያ ከተሰጣቸው አገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ይሄው የሥራ ዕድል ፈጠራና የወጣቶች ተጠቃሚነት ጉዳይ መሆኑ ይታወቃል። በ«የኢትዮጵያ ወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ የማቋቋሚያ አዋጅ» መሠረት ሕግ አድርጎ በማፅደቅ ወጣት ሥራ አጦችን ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ በመንግሥት የተመደበውን የ10 ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድን በማስረጃነት በመጥቀስ ምስክር (የክትትል፣ ቁጥጥርና ግምገማ ተግባራትን ችግሮቹ ሳንጨምር) መሆን ይቻላል። ይህንንም ተከትሎ በክልሎች ደረጃም የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፤ እየተደረጉም ነው።
ባለፈው ጥቅምት ወር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ161 ሺህ በላይ አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን ለወጣቶች የሚፈጥር መነሻ እቅድ አዘጋጅቶ ለ”የሥራ ዕድል ፈጠራና የኢንተርፕራይዞች ልማት ምክር ቤት” መድረክ ለውይይት ማቅረቡ እንደ አንድ መልካም እርምጃ ተወስዶ ልምዱም ወደሌሎች ክልሎች ሊስፋፋ፣ ሊለመድና ሊሰራበት የሚገባ ነው። በተለይ ኅብረተሰቡንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ከማሳተፍና የጉዳዩ ባለቤት ከማድረግ አንፃር ይህ የአዲስ አበባ ተሞክሮ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
እዚህ ላይ የሥራ ዕድል ፈጠራና የሥራ አጡ ኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ጉዳይ ሲነሳ ኃላፊነቱን የመንግሥትና የመንግሥት ብቻ አድርጎ መውሰድ አለ። ይህ ፍፁም ስህተት ብቻ ሳይሆን ሊታሰብ የማይገባው ነው። ምነው ቢሉ በነፃ ገበያ ሥርዓት በምትከተል፤ የግል ባለሀብቶች ያለገደብ በሚንቀሳቀሱበት አገር እና የመሳሰሉት መብቶች ለግሉ ዘርፍ በተሰጡበት ሁኔታ የግሉ ዘርፍ ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባዋል፡፡
በዘርፉ ያለው ችግር በቂ የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉ ብቻ አይደለም። በተፈጠረው የሥራ ዕድልም ዜጎች መስራት አለመቻልና የመልቀቅ ሁኔታ እየተስተዋለ መገኘቱ ተጠቃሽ ነው። በቅርቡ ከኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ከተገኘ መረጃ መረዳት እንደተቻለው ኩባንያዎች በከተሞች ያለውን የኑሮ ውድነት ያገናዘበ ደመወዝ ባለመክፈላቸው ምክንያት እና ፍላጎቱም የሌላቸው መሆኑን ተከትሎ በየካቲት 2011 ዓ.ም ከአራት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ በአጠቃላይ 2ሺ 40 ሠራተኞች ሥራቸውን ለቅቀዋል። ይህ እንግዲህ መንግሥት ሥራ የመፍጠር ኃላፊነቱን ብቻ መወጣት አለበት ከሚለው ወጣ ያለና ዝቅተኛው የሠራተኞች ደመወዝ መጠን ስንት መሆን እንዳለበት ማሰብና ወደመወሰን መምጣት ያለበት ጊዜ ላይ መሆኑን አመላክች ነው፡፡
ሌላው መንግሥት ባለፉት ሁለት አስር ዓመታት ሀገሪቱ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ ዕድገት በተጨባጭ ካለው የሥራ ዕድል እውነታ ጋር አለመጣጣሙ በበርካታ በተለይም በወጣቱ ዘንድ ብዥታ መፍጠሩንና ወዳልታሰበ ግጭት መዛወሩን ልብ ማለት ወይም አለመርሳት ተገቢ ይሆናል። አሁንም ይህ ተመልሶ ሌላ ቁጣን ከመቀስቀሱ በፊት መፍትሄን ከወዲሁ መሻት ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከሥራ ዕድሎች በአሻገር በርካታ የሥራ ዓይነቶችን (ባንድ ወቅት ካናዳ በአንድ ሩብ ዓመት ብቻ ከ700 በላይ የሥራ ዓይነቶችን እንደፈጠረችው ዓይነት) መፍጠር፤ ለዚህም ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ከጎኑ ሊሆኑና ሊያግዙት፤ ወጣቱም ሥራ ሳይመርጥ፣ ሳይንቅና ሳያጣጥል የቀረበለትን ለመስራትና በሂደት ተጠቃሚ ለመሆን ዝግጁ መሆን አለበት።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 7/2011